እንደ ማሳያ፦ ሰሞኑን የትንሳኤን በዓል ታክኮ ቅቤ ከ800 እስከ 1000 ብር ተሽጧል። በመርካቶ፣ በሾላና በሌሎች ገበያዎች ያሉ ነጋዴዎች ለምን እንደጨመረ በጋዜጠኞች ሲጠየቁ ከመጣበት ቦታ ስለጨመረ ነው የሚል የተለመደና ተዓማኒነት የሌለው መልስ ይሰጣሉ። ጋዜጠኛውም ከየት ነው የመጣው? በስንት ተረክባችሁት? ብሎ መጠየቅ ሲገባው እንደ ገደል ማሚቶ የተነገረውን መልሶ ያስተጋባል። የሸኖ ለጋ፣ የወለጋ፣ የጎጃም ቅቤ ከሆነ አዲስ አበባ እየተሸጠበት ያለውን ዋጋ መነሻ በማድረግ ከአካባቢው የገበያ ዋጋ ጋር በማመሳከር የመጣበትን ዋጋ በማጋለጥ ስግብግብ ነጋዴዎችን ማሳጣትና ማስነወር ይችላል። ጋዜጠኛው ግን ይህን አላደረገም። ለዚህ ነው ዘገባው የቢዝነስም የኢኮኖሚም የማይሆነው ። ቁንጽልና ሚዛናዊ ስላልሆነ።
የሚገርመውና የሚያሳዝነው ከእነዚህ አካባቢዎች የመጣ ንጹሕ ቅቤ በምኖርበት አካባቢ ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ በሚያስረክቡ ነጋዴዎች በ500 ብር ሒሳብ ነው የተሸጠው። እንግዲህ እነዚህ ነጋዴዎች በትንሹ ከኪሎ 100 ብር ቢያተርፉ የመጣበት ዋጋ 400 ብርና ከዚያ በታች ነው ማለት ነው። የመርካቶና የሾላ ቅቤ ነጋዴዎች ደግሞ ቋሚ አቅራቢዎች ስላሏቸው ከዚህ ባነሰ ዋጋ እንደሚረከቡት መገመት ይቻላል። ታዲያ ለምን ከ800 እስከ 1000 ብር ይሸጣሉ ከተባለ መልሱ ስግብግብነትና አልጠግብ ባይነት ነው። ይህ የሆነው ደግሞ እነሱ እንደሚዋሹትና እንደሚያታልሉት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ተፈጥሮ አይደለም። መጀመሪያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን፤ አሁን ደግሞ የዩክሬንና የራሽያን ጦርነት ተከትሎ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ እንዳለ ሆኖ፤ ዘይትን ጨምሮ በሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪም ከዚህ የሚመነጭ ነው።
ሌላው ገበያውን እያናጋ ያለው ያልተገባ ትንበያ፣ ሟርትና ስጋት ነው። የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታው በዚያ ሰሞን በቅንነት በአንድ ቴሌቪዥን ቀርበው በዓለማችን የስንዴና የምግብ ዘይት ከፍተኛ አምራችና አቅራቢ የሆኑት ራሽያና ዩክሬን ወደ ጦርነት መግባታቸው በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል ባሉ ማግስት፤ ዘይት ወደ 1000 ብር ከመተኮሱ በላይ ወዲያው ከገበያ እንዲጠፋ ተደረገ። ስንዴም እንደዚሁ። እንግዲህ ይታያችሁ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ ከወራት በፊት የገባ የምግብ ዘይት ዋጋ ነው በዛ ደረጃ በአንድ ጀምበር የተተኮሰው። ስለዚህ ትንፍሽ ያላለው ሚዲያ ሰሞኑን ደግሞ በአናቱ ኢንዶኔዥያ የፓልም ዘይት ለውጭ ገበያ እንዳይቀርብ አገደች በማለት የፓልም ዘይት ዋጋን ለሌላ ጭማሪ እያመቻቸው ነው።
ሚዲያውም ሆነ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲህ ካለ የገበያ ትንበያ/ማርኬት ስፔኩሌሽን/መታቀብ አላቸው። እያንዳንዷ መረጃ ከገበያ አንጻር እንደምትተረጎም ልብ ማለት ግድ ይላል። ደላላውና አሻጥረኛ ነጋዴው የሚነዛው የገበያ ሽብር መች አነሰን። ይህ የቢዝነስ ዘገባዎቻችን ልምሻ ሌላው ማሳያ ነው ። ለዚህ ነው ከዚህ ጥንቃቄና ማስተዋል ከጎደለው ግልብ ዘገባ ወጥቶ የሸማች ጋዜጠኝነትን መተግበር ያሻል የምለው።
በተፈጥሮዬ ጨለምተኛ ባልሆንም ዛሬ በሃገራችን እየተስተዋለ ያለው እጅግ አንገብጋቢና አስፈሪ እየሆነ የመጣውን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት በተቀናጀ ርብርብ ካልተገታ ውሎ አድሮ የህልውና፣ የደህንነት፣ የሰላምና የጸጥታ ችግር እንዳይሆን ያሰጋኛል። ያስፈራኛል። የኑሮ ውድነቱ ከማስበውና ከምገምተው በላይ ስር የሰደደና ውስብስብ ሆኖ ይሰማኛል። በመሆኑም በቀላሉና በአጭር ጊዜ የሚስተካከል አይደለም። ከቀረጥ ነጻ መሠረታዊ ሸቀጦችን በማስገባት፣ በሰንበት ገበያና በፍራንኮ ቫሉታ የሚቀረፍ አይደለም። መፍትሔው በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ የተቀናጀና ዘርፈ ብዙ ምላሽና ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ይጠይቃል። በተለይ የገዥው ፓርቲ ብልጽግና ወጥ የሆነ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እጅግ ወሳኝ ነው። ይሄን ለማድረግ ግን የዋጋ ግሽበቱን ዳራና ውስብስብነት በልኩ መረዳት ያስፈልጋል።
ዛሬ የምንገኝበት የኑሮ ውድነት የዋጋ ግሽበት ቢያንስ ላለፉት 50 ዓመታት ሲድህ የመጣ ነው። በሕወሓት/ኢሕአዴግ ደግሞ በተለይ 1997 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ሶምሶማውን ተያያዘው። ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንደ ፈጣን ሯጭ መፈትለክ ጀመረ። 390 ብር የነበር ዘይት ከእጥፍ በላይ ጋሽቦና ተተኩሶ 1000 ብር ገባ። በሌሎች ተመሳሳይ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይም ግሽበቱ ተመሳሳይ ሽምጥ ጋለበ ። ደረጃው ይለያይ እንጂ በደርግም በኢሕአዴግም ኢኮኖሚው መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር ነበረበት ። ድንገት ተነስቶ ባለፉት አራት ዓመታት የተከሰተ ከመሠለን ተሳስተናል ። ለዚህ ነው የዚህን የኑሮ ውድነት ዳራና ውስብስብ ችግሮቹን በማዕቀፍ በጥልቅ መመልከት የግድ የሚለው። ግልብ ዕይታ ለቁንጽልና ግልብ መፍትሔ ይዳርጋል። ይህ አካሄድ እሳት ማጥፋት እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም ። ሕዝብም ሆነ ሸማቹ የተሟላ ግንዛቤ እንዳይኖረው ያደርጋል። መንግሥትም የተሟላ ስዕል እንዳያይ ያደርገዋል።
ብዙኃን መገናኛዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና እንደ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበራትና የዘርፍና የንግድ ምክር ቤት ያሉ ተቋማት እየመጣ ያለውን ቀውስ ቀድመው ተንብየው የማንቂያ ደወሉን ሊነኩ ይገባ ነበር ። የመፍትሔ ፈለገ ካርታ ሊነድፉ ይገባም ነበር ። በተለይ አንጋፋው የአአዩ በጥናትና በምርምር ታግዞ እየመጣ ስላለው ችግር መንግሥትን ደጋግሞ ሊወተውትና የመውጫ የሚያመለክቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና የፖሊሲ ሀሳቦችን ሊያመላክት ይገባ ነበር ። ዩኒቨርሲቲው ግን በሚያሳፍር ሁኔታ ባለፈው ሰሞን እንደተቀረው ሸማች በኑሮ ውድነቱ የተነሳ ለተማሪዎች ምገባ የሚውሉ መሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ አልቀመስ ማለቱን በመግለጽ ሙሾ ሲያወርድ መስማት ያሳፍራል። የመፍትሔው አካል መሆን ሲገባው የችግሩ አካል መሆንን መረጠ።
በነጻ ገበያ ስም ስድ የተለቀቀው የግብይት ሒደቱና ሰንሰለቱ ሸማቹን ለከፋ ምሬትና እሮሮ እየዳረገውና ሕይወቱን እያመሰቃቀለው ነው። ሃገሪቱ ለቀደሙት 20 እና ከዚያ በላይ በነበሩት ዓመታት ትከተለው በነበረ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት፤ ከለውጡ በፊት ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ከለውጡ በኋላ ደግሞ ለአራት ዓመታት የቀጠለው ግጭትና አለመረጋጋት፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የፈጠረው የሎጂስቲክስና የምርት መስተጓጎል ፤ አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው ታሪክም ሆነ ትውልድ በማይረሳው ክህደትና ጭፍጨፋ ሃገሪቱ ተገዳ ወደ ጦርነት መግባቷ ፤ በግብይት ሰንሰለቱና ሒደቱ የሚስተዋለውን አጉራ ዘለልነት ሥርዓት ለማስያዝ በገዢው ፓርቲ ብልጽግና ወጥ የሆነ ፓለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖሩ፤ አንዳንድ አመራሮችም ከሕገ ወጥ ነጋዴዎችና ደላላዎች ጋር የጥቅም ትስስር ፈጥረው መገኘታቸው ችግሩን ከቀን ወደ ቀን እያባባሰውና ወደማይገመትና ማይታወቅ አደገኛ ስፍራ እየወሰደው ይገኛል።
ሆኖም ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የምንገኝበትን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ወጥ በሆነ አግባብ እንዲረዱት ሚዲያው ከግልብ የቢዝነስና የኢኮኖሚክስ ዘገባ ወጥቶ በምርመራ ጋዜጠኝነት የታሸ የሸማች ጋዜጠኝነትን ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል። በነገራችን ላይ የሸማች ጋዜጠኝነት ለሕዝቡ የተተነተኑ፣ የተተረጎሙና የተመረመሩ የገበያ መረጃዎችን ለሸማቹ ወይም ለሕዝቡ የማድረስ የጋዜጠኝነት ዘውግ ነው። ወቅታዊ መረጃዎችን ከስር ከስር እያነፈነፈ ወዲያው ወዲያው በማቅረብ ለሸማቹ የሸመታ ውሳኔ በአዎንታ በግብዓትነት የሚያገለግል የቢዝነስና የኢኮኖሚክስ አይነት ነው። የገበያውን አካሄድ ፤ የሸቀጦችን ዋጋ ፤ ሸማቹ አንድን መሠረታዊ ሸቀጥ ወይም አገልግሎት ቢገበይ የሚያገኘውን ጥቅም ወይም ጉዳት ቁልጭና ፍንትው አድርጎ የማሳየት ጋዜጠኝነት ነው ። አሁን በኢቢሲ ፣ በፋና ፣ በዋልታና በሌሎች ብዙኃን መገናኛዎች እየታዘብነው ያለው ዘገባ ግን አይደለም ለሸማች ጋዜጠኝነት ለቢዝነስና ኢኮኖሚክስና አቅመ ዘገባነት ያልደረሰ ግልብና መናኛ ቁንጽል መረጃ እንጂ ለሸማቹም ሆነ ለመንግሥት ውሳኔ መነሻ ሊሆን የሚችል አይደለም ። በተለይ መንግሥታዊ ብዙኃን መገናኛዎች ለስብሰባ አዳራሽና ለሁነት ዘገባ ከሚሰጡት ትኩረትና ሰፊ ሽፋን ቀነስ አድርገው ለሸማች ጋዜጠኝነት ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ።
እንኳን እንደ ትንሳኤና ዒድ ያሉ ታላላቅ በዓላት መጥተው ይቅርና በአዘቦትና በሰርክም ሁል ጊዜም በጥፍራቸው ቆመው ዋጋ ለመጨመር የጥፍ ስንጥቅ ለመግፈፍ (በዚህ መጠን የሚጋበስ ትርፍ ሳይሆን ሸማቹን በቁሙ መግፈፍ ነው ብል ስለማምን ነው፤ መግፈፍ ያልሁት) ሰበብ አስባብ የሚጠባበቁ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እና ደላሎች አሉ። 100፣ 200፣ 300፣ 400፣ 500፣ …1000 በመቶ ካላተረፉ የነገዱ የማይመስላቸው ስግብግብ ነጋዴዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው ። ሰሞኑን እያስተዋልን ያለው መረን የለቀቀውን ስግብግብነት ነው ። ጨዋና ለወገናቸው የሚራሩ ጥቂት በጣም ጥቂት ነጋዴዎች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ። ይሄን አጉራ ዘለልና ሥርዓት አልባ የግብይት ሥርዓት እየተከታተለ በማጋለጥ ረገድ የሸማች ጋዜጠኝነት በምንም የማይተካ ሚና አለው።
በአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ በተከፈተው ጦርነት፤ የራሽያንና የዩክሬን ጦርነትን፤ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረትን፤ መንግሥት መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ያደርገው የነበረ ድጎማ በመሐል በማንሳቱ፤ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን በመኖሩ ፤ በእንቅርት ላይ እንዲሉ አጉራ ዘለል የግብይት ሥርዓት ፣ ሙስናና ደላላ ተጨምሮ ሸማቹን በኑሮ ውድነትና በዋጋ ግሽበት ጉማሬ እየገረፈው ነው። ለድምጽ አልባ ረሀብ እየዳረገው ነው ። ድሮም ከእጅ ወደ አፍ የነበረው ኑሮው አልቀመስ እያለውና እያማረረው ነው ። ሆኖም ብዙኃን መገናኛዎቹ በልኩና በደርዙ እየዘገቡት አይደለም ። የዘገባዎቻቸው መሪ ዜና ሊሆን ሲገባ መጨረሻ ላይ ለዛውም በጥድፊያና በግልብ እየታለፈ ነው ። የገበያ ዘገባዎቻቸውም ባዶ የቁጥር ኳኳታ እንጂ በቅጡ የተተረጎሙ አይደሉም።
ይሄ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ሀይ ባይ የሚያገኘው መቼ ነው!? እንዳሻቸው ዋጋ የሚቆልሉ ስግብግብ ነጋዴዎችስ መቼ ይሆን በሕጋዊው የገበያ ሥርዓት የሚመሩት !? መንግሥትስ በነጻ ገበያ ስም ስድ የለቀቀውን ገበያ በዋጋ ጣራና የትርፍ ህዳግ ልጓም የሚበጅለት መቼ ነው!? ሁሉንም ገበያ እንዳሻው ቁጭ ብድግ የሚያደርገው ደላላስ መቼ ይሆን ከሻጩም ከሸማቹም ጀርባ የሚወርደው!? ለመሆኑ የትላንቱም የዛሬውም ንግድና ኢንዱስትሪም ሆነ የዛሬው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ምን ሠራ!? ምን እየሠራ ነው!? እነዚህ ጥያቄዎች ለዘመናት ተነስተዋል ። መልሳቸውን የበላ ጅብ አልጮኸም እንጂ ። ከታች እስከ ላይ ያለው አመራርስ የሃገር ህልውና አደጋ ለመሆን ጫፍ የደረሰውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ለመከላከል ወጥ የሆነ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለው ወይ!? በግብይት ሰንሰለቱና ሥርዓቱ የሚስተዋለውን ሥርዓት አልበኝነት አደብ ለማስገዛትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እውነት አመራሩ ቁርጠኝነት አለው!? መንግሥት በሚያወራው ልክ እየሠራ ነው ወይ!? መልሱ አይደለም ነው።
ምክንያቱ ችግሩ እየተባባሰና ገበያውም ሆነ ኢኮኖሚው ከእጁ እየወጣ ነው። ሥርዓት የማያሲዘውን ገበያና ኢኮኖሚ እየመራሁት ነው ማለት ስለማይችል። ሆኖም ብዙኃን መገናኛዎች እነዚህን ክፍተቶችን ለመንግሥት በቅጡ እያሳዩት አለመሆኑ ይበልጥ ያሳስባል። ያሰጋል ። የራሽያና የዩክሬን ጦርነት ፣ ኮቪድ 19 ፣ በሃገሪቱ የተቀሰቀሰው ጦርነት፣ እዚህም እዚያም የሚስተዋለው ግጭት ፣ የጸጥታና የደህንነት ችግሮች ፣ የምርት እጥረት ፣ ወዘተረፈ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የፈጠራቸው ችግሮች አይደሉም ። ጦርነቱም ተገዶ የገባበት ነው ፤ በሶስት ሳምንት የተቀዳጀውን ድል ማስጠበቅ ፣ ማዝለቅና ማጽናት ላይ የነበረበት ክፍተት ለሁለተኛው ጦርነት ቢዳርገውም። ላለፉት ሰባት ዓመታት በተለይ ላለፉት አራት ዓመታት በመላው ሃገሪቱ የተቀሰቀሱ ጭፍጨፋዎች ፣ ብጥብጦች ፣ ቀውሶች ፣ ግጭቶች ፣ መፈናቀሎች ፣ ወዘተረፈ ለቀደሙት 27 ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ ሲቀነቀንና ሲነዛ የኖረው ጥላቻ ፣ ልዩነት ፣ ቂም ፣ በቀል ፣ ዘረኝነትና ሐሰተኛ ትርክት የወለዳቸው መሆኑን ብዙኃን መገናኛዎች አብራርቶና አፍታቶ ለአድማጭና ለተመልካች ማድረስ ላይ ውስንነት አለባቸው ።
ሆኖም አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የዋጋ ግሽበቱንና ተከትሎ የመጣውን አደገኛ የኑሮ ውድነት በአቅሙ ግን ደግሞ ማድረግ የሚገባውን አበክሮ አልሠራም። አጉራ ዘለል የሆነውን የግብይት ሒደት በሕግ፣ በአሠራርና በአደረጃጀት መግራት እየቻለ ከቀውሱ አሳሳቢነት አንጻር አለመንቀሳቀሱን ፤ በግብይት ሰንሰለቱ ከጉልት እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰጉ ደላላዎችን ሥርዓት ለማስያዝ አለመንቀሳቀሱ ፤ ስግብግብ አከፋፋዮችና ነጋዴዎች “ነጻ ገበያው”ን መሠረታዊ ሸቀጦችን በመደበቅና ዋጋቸውን በአድማ በመወሰን ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በመፍጠር ሽባ ሲያደርጉት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በልኩ አለመንቀሳቀሱን ብዙኃን መገናኛዎች በአግባቡ አላሳዩም ።
የንግዱ ማኅበረሰብ ራሱ ያላከበረውን “ነጻ ገበያ” መንግስት “ነጻ ገበያ ነው” እያለ 120 ሚሊዮን ሸማች ሲታገት ባልሰማና ባላየ ማለፉ አሁን ለምንገኝበት ቀውስ ዳርጎናል ። ስለሆነም በግብይት ሒደቱ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው ጉዳይ ስላልሆነ ፈጥኖ መንቀሳቀስ አለበት። የንግዱ ማኅበረሰብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እየጣሰው ያለውን “ነጻ ገበያ” እስኪያከብረው ድረስ ሌላው ይቅርና ከመርካቶ አምጥቶ እጥፍ ስንጥቅና ከዚያ በላይ ካላተረፈ የነገደ ስለማይመስለው በተለይ በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመንና የትርፍ ሕዳግ ሊቀመጥ ይገባል ። ገበያው ላይ ኮሽ ባለ ቁጥር የኪራይ ዋጋ የሚቆልለው የንግድም ሆነ የመኖሪያ ቤት አከራይ እስኪሰክን ድረስ የኪራይ ተመን ተግባራዊ መደረግ አለበት።
ዓለማቀፍ የፋይናንስ ጉምቱው (Guru) አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በዚያ ሰሞን ከ”Arts tv በነገራችን ላይ …!?” በነበራቸው ቆይታ መንግሥት የዋጋ ግሽበቱንና እሱን ተከትሎ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት የውጭ ምንዛሪን እጥረቱን መቅረፍ አለበት ። ይሄን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ይችላል ። የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት የቱንም ያህል ከፍተኛ ቢሆንም ከአራት ቢሊዮን አይበልጥም፤ ይሄን የውጭ ምንዛሪ መንግሥት አቅርቦ እጥረቱን ማቃለል ቢቻል የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን በዘላቂነት መቅረፍ ይቻላል። ግብጽን ገጥሟት የነበረውን ተመሳሳይ ችግር በማያዳግም ሁኔታ መቅረፍ የቻለችው የውጭ ምንዛሪ እጥረቷን በመፍታት ነው ብለዋል ። የሚገርመው አንድም የመንግሥት ብዙኃን መገናኛ ይሄን ሀሳባቸውን አጀንዳ አድርጎ የሞገተ ፣ ያስተቸና ያስሄሰ አለመኖሩ ነው ።
ከዚህ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ቀለበት ሰብሮ ለመውጣት ከፍ ብሎ ለማሳየት እንደሞከርሁት ያልተሄደበትን መንገድ መያያዝ ግድ ይላል ። ከዘመቻና እሳት ከማጥፋት አሠራር ወጥቶ ስትራቴጂካዊ ዕይታን መከተል ያሻል ። ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የበጋ ስንዴ ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ፣ የመስኖ ልማት ፣ ኩታ ገጠም ግብርና ፣ ወዘተረፈ ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ የተወሰዱ እሰይ የሚያስብሉ ስትራቴጂካዊ ዕይታዎች ናቸው። ከዚህ ጎን ለጎን የግብይት ሒደቱን አንቀው የያዙ ማነቆዎች ካልተፈቱ ፤ ደላላው ከግብይት ሒደቱ ካልወጣ ፤ በነጻ ገበያ ስም ምርት የሚደብቁ ፣ ዋጋ በአድማ የሚወስኑ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ ካልተወሰደ ፤ በመንግሥት መዋቅር የተንሰራፋው ብልሹ አሰራርና ሙስና ካልተወገደ ምርት የቱንም ያህል ቢጨምር ከዚህ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ቀለበት ሰብሮ መውጣት አይቻልም። የሸማች ጋዜጠኝነት ይሄን የትኩረትና የእይታ ሚዛናዊነት በማስጠበቅ ረገድ ብዙ ይጠበቅበታል ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም