የሚያዝያ ወር ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም አለው። ይህን ስል እንዲያው በደፈናውም አይደለም። እያገባደድነው ባለው ወር ላይ በአገራችን ሰፊውን ቁጥር የሚይዙት የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች ታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት (የፋሲካና የረመዳንን) በደማቅ ሥርዓት አክብረው የሚያልፉበት ስለሆነ ነው። ታዲያ በእነዚህ ክብረ በዓላት ወቅት ከምንጊዜውም በተለየ ፍቅርና መተሳሰብ፣ መተባበርና መተጋገዝ ይሰፍናል። ያለው ለሌለው ሲያካፍል አብሮ የመኖር ትርጉሙ ጣዕም እያገኘና ለትውልድ መልካም ስንቅን የሚያሻግር ድልድይ የመሆን ሥራን ይሠራል።
ብዙዎች «ኢትዮጵያዊነት መከባበርና አብሮ መብላት ማለት ነው። በደስታ፣ በኀዘንና በችግር ጊዜ መረዳዳት ነው» ይላሉ። ነገሩ አባባል ሳይሆን መሬት ወርዶ የምናየው ሃቅ ነው። ይህን ስንል ግን አባባሉን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ እኩይ ተግባራት አይታዩም ለማለት አይደለም። ለምሳሌ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንድነታችንን የሚያናጉ፣ አብሮ የመኖር ጥብቅ ባህላችንን ለማላላት እላይ እታች የሚሉ፣ ከኅብረት ይልቅ መለያየትን የሚሰብኩ ቡድኖች በሚፈጥሩት ቀውስ ምክንያት አያሌ ንፁሃን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል እንዲሁም ለረሃብና የከፋ ችግር ተጋልጠዋል። ይሄ ሁሉ ግፍና መከራን የተቀበሉት ኢትዮጵያውያን ግን ለዘመናት የገነቡት ጠንካራ ባህልና ፅኑ የኢትዮጵያዊነት መሠረት ሞራላቸው እንዳይሰበር እምነታቸው እንዳይሸረሸር አድርጓቸዋል።
የትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ ተሸሽጎ የአማራና የአፋር ክልልን መውረሩን ተከትሎ በተፈጠረ ቀውስ በርካታ ቁሳዊና ሰብአዊ ቀውሶች መከተላቸው አይዘናጋም። በወልዲያ ሕዝብ ላይ ብቻ የደረሰውን ግፍና መከራ እንደ ሰበዝ መዝዘን ለመመልከት ብንሞክር እንኳን ብዙ ብዙ በደሎችን ማንሳት እንችላለን። ይሁን እንጂ እኩይ አላማን ይዞ ሕዝቡን ለማፈናቀልና ለእርዛት ቢዳርግም የማኅበረሰቡን ቁስል እንዲሽር ግን የአንድ ሃይማኖት አባት ቀናነትና የማኅበረሰቡ እርስ በእርስ ተደጋግፎ የመኖር ባህል እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል። በዚያ በመከራ ጊዜ ከራሱ ፍላጎት እየቀነሰና ለተቸገረ እያካፈለ በመረዳዳት ባህሉ የችግር ጊዜውን ለመወጣት ችሏል። የወልዲያን ጉዳይ በምሳሌነት አነሳን እንጂ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሙሉ ተመሳሳይ የመደጋገፍና የመከራን ጊዜ በአንድነት እና በመተባበር ለመሻገር ተሞክሯል። አሁንም ይሄ የመተሳሰቡ ሂደት ከውጭ እስከ አገር ውስጥ ቀጥሏል።
ዛሬ ስለመረዳዳት ባህላችን ለማንሳት የወደድነው ያለምክንያት አይደለም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያውያን አብረው የኖሩበትን ባህል ይበልጥ አጠናክረው መቀጠላቸው ስላስደሰተን ነው። ከላይ ባነሳናቸው ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁትን ወገኖች «ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ» ፣ ‹‹ ለወገን ደራሹ ወገን ነው›› በሚል ከሚደረገው ጥረት ባሻገር በተለያየ ምክንያት አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በተለይ አመት በዓላት በመጡ ቁጥር «የማዕድ ማጋራት» ቀጥሎ እናያለን። ይሄ በእጅጉ የሚበረታታ ነው።
የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የፋሲካ በዓልን ባከበሩበት ባሳለፍነው ሳምንት ለተቸገሩና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ወገኖችን በኅብረት የመደገፍና በጋራ ተደስተው የሚያሳልፉበትን ዕድል የመፍጠር በጎ ተግባርን ሲሠሩ ተመልክተናል። ሌሎች ክርስቲያኖችም እንዲሁ በዓሉን በመረዳዳትና በማካፈል ጭምር አክብረውታል። ይሄ ኢትዮጵያዊነት ነው። ትውልዱ ከቀደሙት አባቶቹ የወረሰውና አብሮ የመኖር የጋራ እሴታችን አካል ጭምር ነው።
ቀደም ባሉት ዘመናት የአገሪቱ ዘውዳዊ ሥርዓት «ግብር ማብላት» በሚል በዓላት በመጡ ቁጥርና በተለያዩ ብሔራዊ ቀናት ማኅበረሰቡን የመርዳትና የመደገፍ ተግባር ያከናውን ነበር። ይህ የተቸገሩትን ከመርዳት ባለፈ መከባበር፣ ማካፈል መልመድ እንዲሁም አብሮ የመኖር ብልሃት አንዱ መገለጫ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። በተለይ ንጉሦች መሰል ተግባር በየጊዜው ሲያከናውኑ ሕዝቡም ይህን ምሳሌ በማድረግ ካለው ድርሻውን ለጎረቤቱ የማጋራት ባህል እንዲያዳብር ያደርግ ነበር። ይሄ መልካም ድርጊትም በተደጋጋሚ ጊዜ የኢትዮጵያውያን መገለጫ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ካሉት በተለየ መንገድ የምንታወቅበት እንዲሆን አስችሏል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ ይህ መሰል ዘመናት የተሻገረውን ባህላችንን ወደፊት የማምጣትና ይበልጥ እንዲዳብር ለማድረግ መንግሥት እየሠራ መሆኑን ተመልክተናል። ለምሳሌ ያህል እናንሳ ብንል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ «ማዕድ እናጋራ» በሚል አቅመ ደካማ ለሆኑና ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን በዓላት በመጡ ቁጥር አብረው ለማሳለፍ የሚያደርጉት ተምሳሌታዊ ሥራ አንዱ ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት የፋሲካ በዓል ጊዜም በአንድነት ፓርክ በተካሄደ የ «እናጋራ» ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ ለተቸገሩ 200 ለሚሆኑ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና አዳጊ ሕፃናት አስፈላጊ መሠረታዊ የምግብ ዓይነቶችን አጋርተዋል። በተመሳሳይ ቀን ለ230 አቅመደካምች የምሳ ግብዣ ያደረጉ ሲሆን «የትንሳኤን በዓል ሁላችንም አቅም የሌላቸውን በመርዳት፣ ያለው ለሌለው በማካፈል መንፈስ ልናከብረው ይገባል» በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸውን አንዘነጋውም። ለክርስትና እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ታላቁ የረመዳን ፆም ምክንያት በማድረግ «የአፍጥር ሥነሥርዓት» በማካሄድ ከተቸገሩት ጋር አብሮ መቆምና መረዳዳት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ለማመላከት ሞክረዋል።
መሪዎች ምሳሌ ሲሆኑ ሕዝብ ይከተላል። በጎነትን የሚሰብክ እና በተግባር የሚያሳይ ማንኛውም አካል ሌሎች እጃቸውን እንዲፈቱና ያላቸውን እንዲያጋሩ ያደርጋል። «መልካምነት መልሶ ይከፍላል» እንደሚሉት አባቶቻችን አቅመ ደካሞችን ማገዝ፣ ካለን ለሌለው ማጋራት ለምንሰጠው ሰው ብቻ ሳይሆን ለራሳችን በእጥፍ የደስታ ምንጭና ውለታ ማቆየት የምንችልበትን ዕድል የሚፈጥር ነው።
መረዳዳት ብሔር የለውም፣ መተባበር እና ችግርን በጋራ መወጣት ሃይማኖትም ሆነ ቀለምን አይመርጥም። ኢትዮጵያዊነትም በዚህ እሴት ላይ እንደተገነባ እናምናለን። ለዚያም ነው ሙስሊሙ የክርስቲያኑ በዓልን ክርስቲያኑ የሙስሊሙ በዓልን በጋራና በፍቅር ተባብሮና ተከባብሮ የሚያከብረው። ይሄ የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ ሳይሆን የዕለት ተዕለት የኢትዮጵያውያን የኑሮ ዘይቤ ጭምር ነው። ጉርብትናው ጥብቅ የሆነው ኢትዮጵያዊ በደስታ፣ በችግር፣ በኀዘንና በመሳሰሉት ጊዜያት በእድር፣ በእቁብና በመዋጮ ይተጋገዛል። ሌላው ዓለም ላይ ይህን መሰል ድርጊት ማግኘት የቋጥኝ ያህል ከባድ ይመስላል።
ከመጣብን ፈተና ይልቅ ችግሩን የምናልፍበት መንገድ ፍፁም ብልሃት የተሞላበት እንደሆነ ግልፅ ነው። ለዚህ ነው ከመጋጨት ይልቅ መተባበር እንደሚያምርብን ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለመናገር የምንወደው። ችግሮቻችንን ለመፍታት «እኛው በእኛው» የምንበቃ ለዚያም ለዘመናት ጠብቀነው የቆየነው ውድና ድንቅ የጋራ እሴቶች ያሉን ሕዝቦች መሆናችንን ማወቅ ይኖርብናል። ለዚህ ነው መልካም እሴቶቻችን እንደ ጥሩ መአዛ እንዲበዙልን ሳንታክት መሥራት የሚኖርብን።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም