አንዳንዴ ኑሮ ሲከብድ ፣እጅ ሲያጥር ጓዳ ሞሰቡ ይራቆታል። የሚታበስ እርሾ ሲሟጠጥ ይጎርሱት፣ ይቀምሱት ቁራሽ ይጠፋል። ይህኔ ከጎን የሚቆም ‹‹አለሁ ባይ›› ወገን ከታጣ ችግሩ በእጥፍ ይገዝፋል። ተስፋ መቁረጥ ነግሶ ፣ኃዘን ስጋቱ ያይላል።
ይህ አይነቱ አጋጣሚ እኛን በመሰሉ ድሀ ተደጋግሞ ቢስተዋል ብርቃችን ላይሆን ይችላል። መራብ፣ መጠማታችን፣ መቸገር፣ እጅ ማየታችን ለማንም አያስገርም ይሆናል ። አንዴ ‹‹ድሆች›› ይሉት ታርጋ ተለጥፎብናልና ‹‹እናውቃችኋለን›› በሚሉን ዘንድ ይህ አይነቱ የኑሮ ገጽታችን ፈጽሞ አያስገርምም።
አዎ! እነሱ እንደሚሉን እኛ ሁሌም ‹‹ድሆች›› ተብለን እንጠራለን። ዕልፍ ማዕድናት ታቅፈን አልተጠቀምንም፣ ድንግል መሬት ታድለን ከእንጀራና ወጥ አላለፍንም። በበርካታ ወንዞች ተከበን ከውሀጥም አልዳንም። ወቃሾቻችን እውነታውን እያወቁ ጣት ቢጠነቁሉብን፣ ‹‹ረሀብተኞች›› እያሉ መዝገበ ቃላት ቢገልጡብን አያስገርምም።
እኛ የእስከዛሬው ትግላችን በእነሱ ላለመረታት፣ በቅኝ ግዛታቸው ሽቦ ጠብቆ ላለመጠፈር መታገል ነበር። ዓላማችን ነጻነታችንን ሸጠን፣በጥቅም ተደራድረን የእነሱን ትራፊ መልቀም፣ መቀላወጥ አልሆነም። ከምንም በላይ ለዚህ እውነታ መታገላችን ደግሞ በታሰበው የእድገት ጎዳና ሳያራምደን ቆይቷል። እነሱ በዘረጉልን የሽንገላ ሀዲድም በፍጥነት ሳያመላልሰን ኖሯል።
ይህ እውነታ ሃገራችን በማንነቷ የስልጣኔ ገመዷን እንዳታስር፣ ሕዝቦቿ ከረሀብና ችግር እንዳይላቀቁ፣ ከእርዳታና ብድር ልማድ እንዳይወጡ ተብትቦ ይዟል። የእነሱ ረጃጅም እጆች ወገን በወገን ላይ፣ ጦር እንዲመዝ፣ እርስ በራስ እንዲጋጭ፣እንዲፋጭ ምክንያት ሲሆን ኖሯል። ይህ ደግሞ የክፉ አሳቢዎቻችን ወጥመድ መሆኑ ጠፍቶን አያውቅም። ዛሬም ሆነ ጥንት እውነታውን አሳ ምረን እናውቃለን።
ይህ የዘመናት የጥቅም ንጥቂያና ያልተገባ ፍላጎት በእኛ ታሪክ ሲደጋገም ኖሯል። እንዲህ በመሆኑም ሃገራችን እያመረተች እንዳታፍስ፣ እየዘራች እንዳትቅም፣ እየጋገረች እንዳትጎርስ፣ አፏን ሲሸብባት፣ እግሯን ሲሸመቅቃት እንድትዘልቅ ጥብቅ ወጥመዳችን ሆኗል።
ለጥቅም ፈላጊዎቻችን ያለመመቸታችን ታሪክም ሃገራችን በረሀብተኝነትና በድህነት ስያሜ በዓለም አደባባይ ተጽፋ ዕድገቷ ሳይሆን ውድቀቷ፣ ማበቧ ሳይሆን መጠውለጓ እየተወሳ እንዲቀጥል ሰበብ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያውንን አስገራሚ ለውጥ ላለማመን ራሳቸውን በሚሸነግሉና ዓይናቸውን በሚጨፍኑ ጠንቆች ዙሪያችን ተከቧል።
በሃገራችን ዕውን ከሆነው ድንገቴ ለውጥ ማግስት የተከሰተው የህልውና ጦርነትና ያስከተላቸው መልከ ብዙ ችግሮች ዛሬ በኢኮኖሚያችን ላይ ስብራት ማስከተሉ አይቀሬ ሆኗል። ጦርነት ካለ ገበሬው ከእርሻው፣ነጋዴው ከጉዳዩ አይውልም። ተማሪዎች ከዕውቀት ገበታቸው፣ ቤተሰቦች ከመኖሪያ ቀያቸው አይገኙም። ጦርነት ዓለም ያወድማል፣ ቤት ጎጆን ያዘጋል፣ ልጅን ከወላጅ ነጥሎ ሕዝብን ከሃገር ያሰድዳል።
ጦርነት የተመቸ ኑሮን ያቃውሳል። ስደት መፈናቀልን ያበዛል። ንብረት አውድሞ ከጫካ ከሜዳ ይጥላል። ክቡር ሕይወትን ነጥቆ ሙሉ አካልን ያጎድላል ። ከዚህ ማጥ ለተረፉት ደግሞ ቀሪው እስትንፋስ ከባድ መሆኑ አይቀሬ ነው። ትናንት የሚሰጡ ሰፊ እጆች ዛሬ የሌሎች እጅን ይጠብቃሉ ። ቁራሽና ፍርፋሪን ናፍቀው ለልመናም ይዘረጋሉ። ይህኔ በረሀብ በእርዛት፣ የተጎዳ አካል ‹‹አለሁ›› ባይነትን ይናፍቃል። የዕለት ጉርሱን፣ የአካል መሸፈኛ ልብሱን ከመልካሞች እጅ እንዲቸር ይሻል።
የዚህ አይነቱ የኑሮ ቀውስና ጠባሳ የሚያርፈው ደግሞ በጦርነቱ ላለፉት ወገኖች ብቻ አይሆንም። የአርጩሜው፣የለበቁ ጫፍ ለሌሎች ጭምር ይተርፋል። የጦርነቱ ክፉ ፍሬ ረሀብን፣ አስከፊ ችግርን ይወልዳል፣ ይህኔ ተፈናቃዩ ይበረክታል። ከገጠር ወደከተማ፣ ከሃገር ወደ ሃገር የሚኖረው ፍልሰት፣ ሰፍቶ ኑሮ ይቃወሳል። የምግብ ሸቀጦች ጣራ ይነካሉ፣ የቤት ኪራይ ሽቅብ ይንራል፡ ትናንት በአቅሙ ሰርቶ በልኩ የሚያድር ሁሉ ዛሬ ላይ እጅ ያጥረዋል። ኑሮን መቋቋም፣ ሕይወትን በወጉ መግፋት ይሳነዋል።
እንዲህ በሆነ ጊዜ ሕይወት የሚከብደው ለአንድ ወገን ብቻ አይሆንም። ሁሉም በየደረጃው የኑሮ ውድነት፣ በአቅም የመኖር ችግር ይፈትነዋል። ልጆችን በወጉ ማሳደግና ማስተማር፣የዕለት ጉርስን ፣የቤት ወጪንና የዓውደ ዓመት ውሎን ማሳካት ሁሉ በ‹‹ነበር›› ታሪክ ይቀራል። የኑሮውን ጫና መሸከም የሚያቅተው ትከሻ ትናንትን በትውስታ እያሰበ፣ ነገን በማይጨበጥ ተስፋ ሊያሳልፍ ይገደዳል ።
መቼም ቢሆን በአንዳችን የሚደርስ ችግርን ከዳር ሆኖ ማስተዋሉ መፍትሔ ሊሆነን አይችልም። እጅ ሲያጥርና የወገን ጓዳ ሲራቆት ‹‹አለሁ›› ባይነት፣ ሊኖር ግድ ይላል። ይህን እሳቤ ነድፎና ቀምሮ ማዋል ማሳደሩ ብቻ መላና መፍትሔ አይደለም።
ታላቁ ነጥብና እውነታ እኛ የሌሎችን ችግር ማስተዋልና ፣ መፈተሻችን ላይ ነው። የጎደለ፣ የተራቆተ ጓዳቸውን ጎብኝቶ አብሮነትን ማሳየት ማስመስከራችን ይበጃል። አዎ! እኛ ኢትዮጵያውያን የተቸገሩ ወገኖቻችንን በራሳችን ጫማ ለክተን ማየታችን፣ ከሌሎች ሁሉ ይለየናል። እኛ መረዳዳትን ባህላችን ያደረግን ሕዝቦች ነን ። ብዙዎች ጠግበው ማደር ቀርቶ ቀምሰው በማይውሉበት አጋጣሚ በተገኘን ጊዜ የመረዳዳት፣የመተጋገዝ ሕሊናችን ይነቃል። ያለንን የማከፈል፣ የእጃችን ተጋርቶ፣ ተቃምሶ የማደር እሴታችን ይጎላል።
ይህ እውነት ከጥንት እስከዛሬ የኢትዮጵያውን ጠንካራ ድርና ማግ እንደሆነ ዓመታትን ተሻግሯል። ይህ በመተሳሰብ ግማድ የተጣመረ አብሮነት በችግር ጊዜ እየጎላ በመከራ ቀናት እየደመቀ ማንነታችንን አስመስክሯል። ጎረቤት እየተራበ ፣የእኛ ጓዳ መሙላቱ፣ ዓውደዓመት፣ ማክበር መደሰቱ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን እፎይታን አይሰጥም። ያለውን አቃምሶ ማደር፣ ልምዳችን ሆኖ ዘልቋል። ተደጋግሞ እንደሚባለው እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ባህል ከምንታወቅባቸው መለያዎች አንዱ የመረዳዳት ልማዳችን ነው። ሁሌም በመተጋገዝ ውስጥ የበርካቶች ችግር ይፈታል። መተሳሰብ፣ መተጋገዝንን ልምድ ያደረጉ ልበ መልካሞች ሲበራከቱ ዕንባቸው የሚታበስ ወገኖች ሥለነገ ተስፋ ያደርጋሉ። ከብቸኝነት ፣ ባይተዋርነት ስሜት ተላቀውም ‹‹አለኝ›› ባይነትን ያውቃሉ። መረዳዳት የውስጥ ስሜትን ያክማል፣ ብሶትን፣ ብቸኝነትን ይጋራል።
ባሳለፍነው የፋሲካ በዓል መንግሥት በኑሮ ጫና እጃቸው ያጠረ ወገኖችን ያማከለ የገበታ ማጋራት መርሐግብርን ሲተገብር ተስተውሏል። በዚህ ጊዜ ጓዳቸው የታየ ችግረኛ ወገኖቻችን በዓሉን ተደስተው እንዲውሉ ምክንያት ሆኗል። ይህ በጎ ጅማሬ በዘለቄታ ይቀጥል ዘንድ ከመንግሥት ይሁንታ ጎን ለጎን የሌላውም አጋርነት ቢታከል አብሮነቱን ያሳያል። መተሳሰብን ያመላክታል።
የገበታ ማጋራቱ ጅማሬ በበጎ ተምሳሌት የሚጠቀስ ምዕራፍ ነው፡ በዚህ አጋጣሚ የተጎበኙ ወገኖቻችን ዛሬን በልተው ነገን ጦም እንዳያድሩ የመተሳሰብ ባህላችንን ያዳብራል። ትናንትን በዚህ መንገድ ያለፉ በርካቶች ነገን ለሌሎች እንዲያስቡ ለማድረግም የገበታ ማጋራቱ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ቦታ ይሰጠዋል።
በተመሳሳይ በቀጣዩ ሳምንት የሚከበረው የኢድ አልፈጥር በዓልም ከወዲሁ በገበታ ማጋራቱ ተሞክሮ እንደታጀበ ጉዞውን ቀጥሏል። በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የረመዳንን ጾም ምክንያት አድርጎ የሚካሄደው የአፍጥር ሥነሥርዓት ሀብታም ድሀ ሳይል ያለን ተካፍሎ፣አካፍሎ በእኩል በመጋራት ባህል ላይ ያተኮረ ነው። በአብዛኛው የጎዳና ላይ መሰናዶን ትኩረት አድርጎ የሚከናወነው የአፍጥሩ መርሐግብር የእኛ የኢትዮጵያውያንን ነባር የመረዳዳት ባህል አመላካች ያደርጋል።
ይህ ድህነታችንን አሸንፎ የሚደምቀው የአብሮነታችን ህብር በየበዓላቱ ብቻ ሊስተዋል አይገባም። በየትኛውም ጊዜና አጋጣሚ የመልካም ልቦች ችሮታ ሊመሰከር ግድ ይላል። ሁሌም በደግ የሚዘረጉ ሰፊ እጆች ፣በመልካም የሚያስተውሉ ብሩህ ዓይኖች ትኩረታቸው መረዳዳት ላይ ሲያተኩር ኢትዮጵያዊነት ይከብራል። ወገናዊነት ያብባል ።
እኛ ኢትዮጵያውያን መረዳዳት፣ መተሳሰብ የምንግዜም ባህላችን ነው። በዚህ እውነታ ውስጥ ዓለም የሚያውቀው እንግዳ ተቀባይነታችን፣ ከማንነታችን የሚቀዳ ደማቅ ማህተማችን ነው። አዎ! እኛ ኢትዮጵያውያን በመተሳሰብ ባህላችን፣ በመደጋገፍ ልማዳችን፣ በመከባበር አብሮነታችን እጅ ለእጅ ተያይዘን ነጋችንን እንሻገራለን። እንዴትና ለምን? ለሚሉን ደግሞ መልሳችን አንድና የተለመደ ነው ‹‹እኛ ኢትዮጵያውን››ነን የሚል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም