መቼም እንደ ዘንድሮ የዋጋ ንረት ሽቅብ በፍጥነት እየተመዘገዘገ የወጣበት ጊዜ አለ ብሎ መናገር አያስደፍርም። ጣሪያ የነካው መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች የዋጋ ንረት በየዕለቱ ጭማሪ እንጂ ቅናሽ ብሎ ነገር አሳይቶ አያውቅም። ለአንድ እቃ ወይም ሸቀጥ የተሰጠው የዋጋ ግምት ጠዋት ከተተመነለት ዋጋ ፤ በሰዓታት ልዩነት በእጥፍ ይጨምራል ወይም ከዚያ በላይ በሆነ ዋጋ ይጨምራል፤ ባስ ካለ ደግሞ ወዲያውኑ ከገበያ ላይ ይጠፋል ወይም አልቋል/የለም/ ወደሚባል ደረጃ ይደርሳል። እንኳን በቀናት መካከል ያለው የዋጋ ተመን ልዩነት ይቅርና በሰዓታት መካከል የሚጨምረው ጭማሪ የትየለሌ ነው።
ይህ የኑሮ ውድነት የአብዛኛውን ህብረተሰብ ኑሮ ፈታኝ እንዲሆን አድርጎታል። የመኖር ህልውናን አደጋ ጥሎታል። የሚገርመው ደግሞ ዕቃው ወይም ሸቀጡ ከመጨመር በስተቀር ቀድሞ ወደነበርበት ዋጋ ሊመለስ ቀርቶ ባለበት እንኳን ሲገታ አለመታየቱ ነው። አንድ ሰሞን ጉድ! ጉድ! ስንልለት የቆየነው የምግብ ዘይት ዋጋ ንረት እንኳን ከተሰቀለበት ጣሪያ የሚያወርደው ሳይገኝ የበላይነቱ እንደተቆናጠጠ ይገኛል። በአንድ ጊዜ ከአንድ ሺ ብር በላይ ረግጦ ወደነበረበት የሚመልሰው አጥቶ ሽቅብ እየገሰገሰ ነው። ሌሎችም ምርቶች በተመሳሳይ ዋጋቸው ወደላይ እየተመመ ይገኛል። ህብረተሰቡ የዋጋ ንረቱን የመቋቋም አቅሙ ተፈትኖ ኑሮ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉት አይነት ሆኖበት ላለመውደቅና እጅ ላለመስጠት እየተንገዳገደ ፈታኝ ኑሮን መግፋት የግድ ሆኖበታል።
ለዋጋ ንረቱ እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ የኢኮኖሚ የዋጋ ግሽበት፣ የምርት እጥረት መኖር፣ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የሕገወጥ ደላሎች መበራከት፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት እና በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ነጋዴዎች በአምራቾች በምርቶቻቸው ላይ ዋጋ መጨመርን የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው። በተመሳሳይም የሕግ ጥስቱና ሥርዓት አልበኝነት እየተስፋፋ መምጣቱ ነጋዴው ከውጭ የሚያስገባቸውን መሠረታዊ የምግብና ሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ ሳይቀር የተጋነነ ጭማሪ ማድረጉ ይጠቀሳል። ያም ሆነ ይህ የዋጋ ንረቱ የህብረተሰቡን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገው፤ በእጅጉ እያከበደው ይገኛል።
መንግሥት በኩል የዋጋ ንረቱ ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛሉ። የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለህብረተሰብ እንዲያደርሱ በማድረግ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት እየወሰደ ያለው እርምጃ ቀላል አይደለም። ይህም ሆኖ ግን እስካሁን ባለው ሂደት የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት ቀርቶ ባለበት እንዲቆይ እንኳን ለማድረግ በእጅጉ ፈታኝ ሆኗል። የተቀመጠውን የመፍትሔ አቅጣጫ አጥጋቢ ምላሽ አላስገኘም።
ዞሮ ዞሮ ዋንኛው ጥያቄ ታዲያ ሊሆን የሚችለው ለምን መፍትሔ ታጣለት የሚለው ነው። ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም፤ እንደኔ ግን በመንግሥት በኩል የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት እየወሰደው ያለው እርምጃ ወይም አማራጭ መፍትሔ እንዳለ ሆኖ በፍጥነት ማረጋጋት ያልቻለበት ምክንያት ውስጥ ዋንኛው የሕግ ጥስቶች መበራከትና የሕጉ ጥብቅ አለመሆን ወይም መላለት አይነተኛ ምክንያቶች ናቸው ባይ ነኝ።
ለዋጋ ንረቱ ከላይ ተጠያቂ ያደረግናቸው አካላት እንዳሉ ሆኖ ፤ ነገሩ እዚህ ለመድረሱ እነርሱ የተጫወቱት ሚና ብቻ ነው የሚል እምነት የለኝም። ይህንን ለሕገወጥ ነጋዴዎች እና ለደላሎች ብቻ የምንተወው ጉዳይ አይደለም። በዚህ በዙሪያው በርካታ ተዋናይ የሆኑ አካላት መኖራቸው ሊታወቅ ይገባል። ይልቁን ከጀርባቸው ሆነ ደብቅ እጆቻቸውን የሚሰዱ፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገግሰገው የሚገኙ ሌቦች ዋንኛ ተዋናዮች መሆናቸውን በደንብ ሊሰመርበትና ሊፈተሽ የሚገባው ነገር ነው።
ለዚህም ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን ባሳለፈነው ሳምንት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በሕገ-ወጥ ንግድ ተሰማርተው በተገኙ ከ33 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቆ ነበር። ታዲያ ቢሮ እንደዚህ አይነቶች ሕገወጥ ነጋዴዎች አደብ ለማስያዝ እርምጃ ወሰድኩ ቢልም በሌላ በኩል ከሕገ ወጦች ጋር እየተመሳጠሩ የሚሰሩ ኃላፊዎችና ሠራተኞች መኖራቸው ነገሩን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ያደርገዋል። ከሰሞኑ የተሰማው ጉዳይ ይህንን የሚያጠናክር ነው።
ለአብነትም ብንጠቅስ በቦሌ ክፍለ ከተማ የንግድ ቢሮ ኃላፊ ሕገወጥ ተብሎ የታሸገ ንግድ ቤት ለማስከፈት የመቶ ሺ ብር ጉቦ ሲቀበሉ መያዙን የሚያሳይ መረጃ መገኘቱን ሰምተናል። ይህ ደግሞ በሥልጣን ተመክቶ ያሻውን ቢያደርግ ጠያቄ እንደሌለው አመላካች ነው። ሆኖም እንደዚህ አይነቱ ተግባር እጅግ አሳፋሪ ነው። ታዲያ ለማን ይነገራል ማለት ይህንን አይደለም ትላላችሁ?። ሕግ አስፈጻሚው አካል የሕዝብ አደራ ወደ ጎን በመተው ኃላፊነቱን ተጠቅሞ የራሱ ጥቅም ለማጋበዝ ሲል ከሕግ ውጭ የሆነ አካሄድ ይከተላል። ያሻውን ያደርጋል፤ የፈለገው ይፈጽማል። ይህንን በምሳሌነት አነሳን እንጂ በሚዲያ ያልተነገሩና በተጨባጭ መረጃ ያልተገኘባቸው ሕገ ወጥ ሥራዎች መበራከታቸውን ነው ከህብረተሰቡ ጋር ካለ እውነታ መረዳት የሚቻለው።
ይህንን አይነት ተግባራት ሕግን በሚያስተገብሩ የመንግሥት አካላት ዘንድ ሕግ ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መሄዱን ማሳያ ነው። ያለምንም ውጣ ውረድና ውስበስብ ችግር በአግባቡ አገልግሎት በመስጠት የሚቻልበት የአገልግሎት አሰጣጥ አሠራር የራሱን አጀንዳ ለማስፈጸም እንዲያመቻቸው አድርጎ በማወሳሰብ ከተገልጋዩ ያልተገባ ጥቅም የሚፈልጉ ባለስልጣናትም ሆነ ባለሙያዎች እየተበራከቱ መሆን እያየን እየሰማን ነው።
ይህ ደግም የኑሮ ውድነቱ ማናር ብቻ ሳይሆን ወደባሰ ማጥ ውስጥ የሚከት ድርጊት ነው። ይህ አካሄድ የሚቀጥል ከሆነ መንግሥትን ሆነ ሕዝብን ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ነው። ስለዚህ ባለሥልጣንም ሆነ ባለሙያ የተቀመጠበት ወንበር ሕዝብ ለማገልገል መሆኑን አውቆ ለሕግ ተገዥ መሆን ሕግን መሠረት ያደረገ አሠራር በመከተል ይገባል። ዛሬ የላላ የመሰለው ሕግ ልጓም ሲጠብቅ ተደብቆ የሚቀር ነገር አይኖርም። እራስን ከሌብነትና ብልሹ አሠራር በመቆጠብ በሕጉ መሠረት በመሥራት ለሕዝብ ወገንተኛ ለመሆን ይገባል፤ ከህሊና ፍርድ ለማምለጥ መንገድ ነው።
የሕግ ወጦችና ሥርዓት አልበኞች መስፋፋት ተጠያቂነት የጎደለው አሠራርና የሕጉን መላላት በሚገባ የሚያሳይ ነው። ሕግ ለማስከበር ደግሞ የሕግ አስከባሪው ሕግ እንዲከበር ግዴታውን የሚወጣበት ፣ ሕግ አስከባሪው የድርሻ አውቆ የሚተገበርበት ነው። የራሱ ጉዳይ ተብሎ የሚታው ነገር አይደለም እንደገናም እከክልኝ ለከክልህ በሚለው አይነት የሚሠራ ሳይሆን ለሁሉም በእኩል የሚቀመጥ ነው።
አጠቃላይ አገር የምትመራው በሕግ ነው። ለዚህ ደግሞ የሕግ አስከባሪ የሆነ አስከባሪ በእጅጉ ያስፈልጋል። ሕገ ወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት እንዳይሰፋፋ ሕግ አስከባሪው የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። ሕግ አክባሪውም ሕግን በማክበር መብትና ግዴታውን ማስከበር ይጠበቅበታል። የኑሮ ውድነቱ በማረጋጋት በኩል ሆነ አገር ወደ ሰከነ ሰላም ለማምጣት ዋንኛው ጉዳይ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ የበኩሉን የየድርሻውን መውጣት ይኖርበታል ባይ ነኝ። አበቃሁ ቸር እንሰንብት።
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም