ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ ካወጣው ዘገባ ጋር ያያዘው ፎቶ ያለተለመደ መሆን ጉዳዩን መነጋገሪያ አድርጎታል። ፎቶው በአንድ የመማሪያ ክፍል ውስጥ እያጨሱ የሚመሩ ተማሪዎችን ምስል የሚያሳይ ነው።
ይህ አስደናቂ ጉዳይም በእግረ መንገድ የገባን ሰውም ቢሆን እንዲያነበው የሚገፋፋ ሲሆን፤ በማህበራዊ ድረገጾች ላይም ከፍተኛ መነጋገሪያነትን የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል። እርግጥ ነው አንድን ነገር በትክክል ለመረዳት ጉዳዩን ከስር መሰረቱ ማወቅ እንዲሁም ነገሩን መላበስ እንደሚገባ ይታመናል። በሩቅ ሆነው ያዩትን ቀርበውና የጉዳዩ ተዋናይ ሆነው ሲመለከቱትም የተሻለ መረዳትና ግልጽነትን ይፈጥራል። ትምህርት የንድፍና የተግባር ጥምር ውጤት የሆነውም ለዚህ ነው። ነገር ግን በንድፍ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ወደ ተግባር መቀየር የግድ ላይሆን ይችላል።
ለምሳሌ ያህል ስለ ሞት ምንነትና ምክንያት በንድፍ የተማሩትን በተግባር ለማወቅ መሞት አይጠበቅም። ስለ ሲጋራ ለማስረዳት እያጨሱ መሆን አለበት የሚል አመለካከትም ተቀባይነት ያለው አይሆንም። ምክንያቱም ሲጋራ ለጤና ጎጂ እና ሱስ የሚያስይዝ ንጥረ ነገር ያለው በመሆኑ፤ እንዳይጠቀሙት የሚመከር ነዋ። በፎቶው ላይ ምስላቸው የሚታዩት ተማሪዎች ግን ስለ ሲጋራ ዓይነቶች ለማወቅ ነው እያጨሱ የሚማሩት። ፎቶው የተገኘው ከቻይና ሲሆን፤ ዩናን በተባለ የእርሻ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችም ናቸው አጫሾቹ።
እዚህ የመማሪያ ክፍል የገባ ሰው እንደተለመደው መጽሐፍትንና ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን መሳሪያዎች ከተማሪዎቹ ጠረዼዛ ሊመለከት ይችላል። ክፍሉ ግን በጭስ ስለሚታፈን የመማሪያ ክፍል ስለመሆኑ አጠራጣሪ ነው። ተማሪዎቹ በእጃቸው ሲጋራቸውን እየሳቡ ነው ትምህርታቸውን የሚከታተሉት።
የሚገርመው ደግሞ ይህንን እንዲያደርጉ ፈቃድ የሰጣቸው የገዛ መምህራቸው መሆኑ ነው። እንዲያውም መምህሩ ስለ ሲጋራ በሚያስተምሩበት የትምህርት ክፍለ ጊዜ፤ ተማሪዎቹ ልዩነታቸውንና የጣዕማቸውን ለያይተው እንዲረዱላቸው በማሰብም ነው ለተማሪዎቻቸው ያቀረቡላቸውም ተብሏል። ነገር ግን ከተማሪዎቻቸው መካከልም የፈለጉት ሲያጨሱ ያልፈለጉት የሚያጨሱትን ይመለከቱ ነበር።
ነገሩ በመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ከሆነም በሁዋላ ዩኒቨርሲቲው፤ ትምህርቱ ለተማሪዎቹ አስፈላጊ መሆኑንና እንደ እነርሱ አባባል «የሲጋራ ቴክኖሎጂ»ን ለሚመለከተው የትምርት ክፍል እንደሚያግዛቸውም ነው የተገለጸው። ይህ ማለት ግን ተማሪዎቹ ሁሌም እያጨሱ ይማራሉ ማለት እንዳልሆነም ተጠቁሟል። አንድ ተማሪ በበኩሉ «እያጨስን ሳይሆን ትምህርቱን በይበልጥ ለመረዳት ያህል ያደረግነው ምዘና ነው» ሲል ነገሩን ደግፎ አስተያየቱን ሰጥቷል።
በርካቶች በበኩላቸው ተማሪዎቹን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት ነው በማለት እየተቃወሙት ይገኛሉ። ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ዓላማው ትምህርቱን ግልጽ ለማድረግ ያህል መሆኑን እንዲሁም ተማሪዎቹ ከማጨሳቸው በፊት ስልጠና ተሰጥቷቸወ ያደረጉት መሆኑንም ነው ያስረዳው። ሌሎች በበኩላቸው «የመዝጊያ ፈተናቸው ምን ሊሆን ይችላል፤ ማን በፍጥነት ያጨሳል የሚል ይሆን?» ሲሉም ተሳልቀውባቸዋል።
አንዳንዶች ደግሞ «እነዚህ ተማሪዎች ማጨስ ቢፈልጉ እንኳን ከዚህ በሁዋላ ወደ ድብቅ ስፍራዎች መሄድ አይጠበቅባቸውም» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ይህ ዓይነቱ ግራ የሚያጋባ ትምህርት ትክክል መሆን አለመሆኑ የየግል አመለካከታችን ቢሆንም፤ ጥቅሙን ለማወቅ ግን እነርሱን መሆን ያስፈልጋል። እነርሱም ስለ ሲጋራ ዓይነቶችና የጣዕም ልዩነቶች ለማወቅ ሲሉ አይደል በአጫሾች «ጫማ» የተገኙት።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
ብርሃን ፈይሳ