በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ማሕበራዊና ወንጀል ላይ ያተኮሩ ዜናዎችን መርጠናል። በ1961 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያገኘናቸው ዜናዎች የአሰበ ተፈሪ (የዛሬዋ ጭሮ) ከተማ ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአዲስአበባ የሚገኘው የባልቻ አባነፍሶ ትምህርት ቤት ማሕበር ለትምህርት ቤቱ ችግረኛ ተማሪዎች የደንብ ልብስና የትምህርት መሣሪያዎች እንዲሁም በምግብ ለመርዳት መረባረባቸው፣ ዛሬ ላይ የከተማው አስተዳደር በሁሉም ትምህርት ቤቶች የደንብ ልብስና ምግብና መሣሪያዎች በማቅረብ የሚሠራውን ሥራ እንድናደንቅ ያደርገናል። በወቅቱ ትርፍ ያሠፈሩ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በፍርድ ቤት ጭምር ቀርበው ሲቀጡ ዛሬ ግን መላቅጡ ጠፍቶ ትርፍ እየጫኑ የትራንስፖርት ታሪፍ እየቆለሉ እንደልብ የሚሆኑትን ሥርዓት የሚያሲዝ መጥፋን ያሳየናል። እንድታነቡት እነሆ ብለናል።
አሰበ ተፈሪዎች ከፖሊስ ጋር ተወያዩ
አሰበ ተፈሪ (ኢ-ዜ-አ-) በአሰበ ተፈሪ ከተማ የሚገኙ ባለሥልጣኖች የአገር ሽማግሌዎች የሆቴል ቤትና የሻይ ቤት ነጋዴዎች ባለፈው ሰኞ በአሰበ ተፈሪ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ቅጥር ጊቢ ባደረጉት ስብሰባ ጨለማን ተገን በማድረግ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚሞክሩትን ወስላቶች ለማጥፋት ከፖሊሶች ጋር ተባብረው ለመሥራት ስምምነት አደረጉ።
ይኸው ውይይት እንዲደረግ ያሳሰቡት የጨርጨር አውራጃ ግዛት ፖሊስ አዛዥ ሌተናል ኰሎኔል ጌጡ ተክሌ ናቸው። ሌተናል ኰሎኔል ጌጡ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ሰሞኑን አልፎ አልፎ በከተማው ውስጥ አንዳንድ የንግድና መኖሪያ ቤቶች በሌቦች ተሰርስረዋል። በተለይ የሻይ ቤቶች የማያውቋቸውን ከ፳ እስከ ፴ ሰዎች ተቀብለው ያሳድራሉ።
ሥራ የጠላ የሌብነት አመል ያለበት ሰው ካረፈበት ሻይ ቤት ከሌሊቱ በፈለገበት ሰዓት መውጣትም ለመግባትም ስለሚችል ያሻውን ይሠራል። የሻይ ቤት ሌቦችንም ሆነ ሌላውን ለመቀበል የመኝታ ዋጋ ስለማይጠይቁ የሥራ ፈቶች መሰባሰቢያ ሆነዋል ብለዋል።
ሌተናል ኰሎኔል ጌጡ ተክሌ በንግግራቸው መጨረሻ ሻይ ቤቶች ካበሉና ካጠጡ በኋላ ማንኛውንም ሰው ማሳደር የለባቸውም ። ለማደር የሚፈልግም ሰው ፤ ለማደሪያ በተዘጋጀ ሆቴል ቤት እንዲያድር አደራ ጭምር አሳስበዋል። በስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች በጉዳዩ ላይ አሳብ ለአሳብ በሠፊው ከተለዋወጡ በኋላ ፤ከፖሊስ ጋር በመተባበር በሰባት ሠፈሮች ተመድበው የሚያገለግሉ፤ የሠፈር ሹሞች መረጡ።
እነዚህ የተመረጡ የሠፈር ሹሞች በተመረጡበት ለመዝረፍ ሌሊት የሚሰማሩትን ሌቦች እየመዘገቡ ለፖሊስ ለማቅረብ ወስነው የዕለቱ ስብሰባ ተነስቷል።
(መጋቢት 9 ቀን 1961 የወጣው አዲስ ዘመን)
የባልቻ ት.ቤት ማሕበር ለ15 ችግረኛ ልጆች ልብስ ሰጠ
አዲስ አበባ (አ-ዜ-አ-) የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የበጐ አድራጎት ማሕበር በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለሚማሩ ፲፭ ችግረኛ ልጆች ሙሉ የትምህርት ቤቱን የደንብ ልብስ አለበሰ።
ስጦታው የተከናወነው የበጐ አድራጎት ማሕበሩ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ዓመታዊ በዓሉን ባከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።
በመጀመሪያ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ይፍሩ ስለ ት/ቤት የበጐ አድራጎት ማሕበር በመግለጥ ንግግር አደረጉ። እሳቸውም ባደረጉት ንግግር ፤ የበጐ አድራጎት ማሕበሩ የተቋቋመው መጋቢት ፩ ቀን ፲፱፻፷ ዓ/ም በት/ቤት መምህራን ፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች ሕብረት ነው። የተቋቋመበት ዓላማም ድሆች የሆኑ ወጣት ተማሪዎች በምግብ በትምህርት መሣሪያ ዕጦትና ሌሎችም እነዚህን በመሳሰሉ ችግሮች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ማሕበሩ ከተመሠረተ ጀምሮ ለአንዳንድ ችግረኛ ልጆች የምግብ የመማሪያ መሣሪያ እርዳታ ከማድረጉም በላይ፤ በመጀመሪያ ሲቋቋም ለስምንት ችግረኞች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ሙሉ የደንብ ልብስ አልብሷል።ለሚያደርገውም እርዳታ ቅድሚያ የሚሰጠው በጣም ችግረኞች ለሆኑ ተማሪዎች ሲሆን ፤ ገቢ የሚያገኘው ከመምህራን በየወሩና ከት/ቤቱ ተማሪዎች እንደችሎታቸው መጠን በዓመት አንድ ጊዜ በሚያገኘው የገንዘብ እርዳታ ነው።
እንዲሁም ማሕበሩ በየሳምንቱ በትምህርት ቤት ተማሪዎች ተዘጋጅቶ ከሚሸጠው የሻይና ጣፋጭ ምግች ገቢ ከአንዳንድ በጎ አድራጊዎች እርዳታ እንደሚያገኝ የት/ቤቱ ዲሬክተር በንግግራቸው ገልጠዋል። ወደፊትም ችግረኞች ተማሪዎችን ለመርዳት አንዳንድ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ስለት/ቤቱ የበጎ ተግባር ዓላማ በመግለጥ በቂ እርዳታ የሚያገኙበት መንገድ የሚያጠና መሆኑን አቶ ማርቆስ አስረድተዋል።
ከዚህም ሌላ እርዳታ የሚደረግላቸው ችግረኞች ተማሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው ለመርዳት እንዲችሉ ለማድረግ በት/ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ለአትክልት በመሆን ሥፍራ እየሰጠ ሰብሉ ሲደርስ ተሸጦ ለትምህርት መሣሪያ ዕቃ እንዲገዛበት ከመታሰቡም ሌላ እነዚሁ ችግረኞች ተማሪዎች በት/ቤቱ ውስጥ ዕቃ ሸጠው በትርፉ እንዲረዱበት ለማድረግ የታቀደ መሆኑን ዲሬክተሩ በተጨማሪ ገልጠዋል።
(መጋቢት 21 ቀን 1961 የወጣው አዲስ ዘመን)
ትርፍ ያሳፈሩት ተቀጡ
ብርሃን (ኢ-ዜ-አ) የትራንስፖርት ደንብ በመተላለፍ በሕዝብ ማመላለሻና በከባድ የጭነት መኪናዎች ላይ ትርፍ ተሳፋሪዎችን ጭነው የተገኙት ሁለት ሹፌሮች እያንዳንዳቸው ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ደብረ ብርሃን የሚገኘው የወራና ወረዳ ፍርድ ቤት ፈረደ።
መሸሻ ባሻ የተባለ ሹፌር የሰሌዳው ቁጥር ፳፪ ሺህ ፩፻፵፪ አዲስ አበባ በሆነ የሕዝብ ማመላለሻ ሎንቺና መኪና ከተፈቀደለት በላይ ፲ ተሳፋሪዎችን በትርፍ ጭኖ ከደብረ ብርሃን ወደ ጅሩ ሲጓዝ በክፍሉ ፖሊስ ትራፊክ ተይዞ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ፶ ብር እንዲቀጣ ተበይኖበታል።
እንዲሁም መብራቴ ተድላ የተባለው አሽከርካሪ ቁጥር ፳ሺህ ፺ አዲስ አበባ በሆነ ከባድ የጭነት መኪና ላይ ፲፩ ሰዎችን ጭኖ በመገኘቱ ፶ ብር መቀጣቱን የተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ግዛት የትራፊክ ክፍል ተቆጣጣሪ የአሥር አለቃ አየለ መሸሻ ገለጠ።
(መጋቢት 23 ቀን 1961 የወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መጋቢት 27 /2014