በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት ተስተካካይ የሌለው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አንጋፋ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ እግር ኳስ ስኬታማ መሆኑ ሁሉንም ያስማማል። ፈረሰኞቹ በርካታ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ዓመታት ሻምፒዮን በመሆን ይታወቃሉ።
በአንድ ውድድር ዓመት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ባይሳካላቸው በሌላው የውድድር ዓመት ወደ ሻምፒዮንነት የመመለስ ባህልም አላቸው። በተለይም ፈረሰኞቹ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ1990 ዓ.ም አንስቶ እንደ አዲስ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ተከታታይ የሻምፒዮንነት ድሎችን ማሳካት ችለዋል። የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ከሁለት ዓመት በበለጠ ጊዜ ሳያነሱ የቀሩበት አጋጣሚ የለም።
ይሁን እንጂ ባለፉት ሶስት የውድድር ዓመታት ፈረሰኞቹ ከፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮንነት ባልተለመደ መልኩ ርቀው ቆይተዋል። በነዚህ ዓመታት የተለያዩ የውጪ አሰልጣኞችን ቀጥረውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ከመጡት የክልል ክለቦች የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ መንጠቅ አልቻሉም።
የዘንድሮው የውድድር ዓመት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት ፈረሰኞቹን ለመምራት የመጡት ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲችም ከቡድኑ ጋር ብዙ ርቀት መጓዝ ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ ባለፉት በርካታ ሳምንታት ፈረሰኞቹን እየመሩ እንደሚገኙ ይታወቃል። አሰልጣኝ ዘሪሁን ፈረሰኞቹን መምራት ብቻም ሳይሆን ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ ለመዱት የሻምፒዮንነት ድል እያንደረደሩ እንደሚገኙ ፍንጮች መ ታየት ጀምረዋል።
የውድድር ዓመቱ አጋማሽ ሊደርስ የሁለት ሳምንታት ጨዋታዎች በቀሩበት በዚህ ወቅት ስለሻምፒዮኑ ክለብ ለማውራት ጊዜው ገና ቢሆንም ለሻምፒዮንነት ተገማች ስለሆኑ ክለቦች ካላቸው ወቅታዊ አቋም በመነሳት መናገር ከባድ አይሆንም። ፈረሰኞቹ ባለፉት አስራ ሶስት ሳምንታት ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት ሳይደርስባቸው የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ መቀመጣቸው ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጨዋታዎች እያሳዩ የሚገኙት የተሻለ አቋም ወደ ሻምፒዮንነት ለመመለስ ጥሩ እድል እንዳላቸው ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ።
ፈረሰኞቹ በአስራ ሶስቱ ሳምንታት ጨዋታዎች ስድስቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ሰባቱን በድል ተወጥተዋል። በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ካለ ግብ አቻ ተለያይተው የጀመሩት ፈረሰኞቹ በሶስተኛው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያዩ ሲሆን፣ በቀጣይ ሳምንታትም ከመከላከያ ጋር ካለምንም ግብ አቻ ወጥተዋል። በቀጣይም ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ ለአንድ ተለያይተዋል።
ሰባተኛ ሳምንት ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር ባዶ ለባዶ እንዲሁም ባለፈው ረቡዕ በአስራ ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ ከሃዲያ ሆሳዕና ጋር በተመሳሳይ በአቻ ውጤት የተለያዩባቸው ጨዋታዎች ናቸው። በአንጻሩ ፈረሰኞቹ በሁለተኛው ሳምንት የሸገር ደርቢ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን አራት ለአንድ፣ ሐዋሳ ከተማን ሁለት ለአንድ፣ ወላይታ ዲቻን አንድ ለባዶ፣ጅማ ከተማን አንድ ለባዶ፣ የአምናውን ሻምፒዮን ፋሲል ከነማን አራት ለባዶ፣ ባህርዳር ከተማን ሁለት ለባዶ፣ወልቂጤ ከተማን አራት ለባዶ መርታት ችለዋል።
ፈረሰኞቹ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያገኙባቸው ጨዋታዎች አብዛኞቹ በሊጉ የተሻለ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑ ክለቦች ጋር በተገናኙባቸው ፍልሚያዎች መሆኑን ማስተዋል ይቻላል። ፈረሰኞቹ በነዚህ ጨዋታዎች አስራ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥሩ የተቆጠረባቸው አራት ግብ ብቻ ነው። ይህም ፈረሰኞቹ በውድድር ዓመቱ ግብ አስቆጣሪ ብቻ ሳይሆኑ ግባቸውን የሚያስደፍሩ እንዳልሆኑ ያሳያል።
የፈረሰኞቹ ስብስብ የተሻለ መነቃቃት ባሳየበት ባለፉት ሳምንታት ጨዋታዎች ተጫዋቾች በአቻ ውጤት በሚጠናቀቁ ጨዋታዎች ምን ያህል ቁጭት ውስጥ ሲገቡ እንደነበረ ባለፈው ረቡዕ ከሃዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ውጤት በኋላ ይነበብባቸው የነበረውን ስሜት ማስታወስ ይቻላል። ይህ ተነሳሽነት በቀጣዮቹ ሳምንታት ከፈረሰኞቹ ጋር አብሮ መዝለቅ ከቻለና የተለየ ችግር ቡድኑን ካልገጠመው ወደ ሻምፒዮንነት ለመመለስ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሌላ መልኩ በዚህ የውድድር አመት አምናና ካቻምና ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩት ሻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት አለመቻላቸውና ያልተጠበቁ ሽንፈቶች እየደረሱባቸው መሆናቸው ለፈረሰኞቹ የሻምፒዮንነት ግስጋሴ መንገዶችን እያመቻቸ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። ሌሎቹም ክለቦች ቢሆኑ ይህ ነው የሚባል ወጥ አቋም እያሳዩ አለመሆናቸውን እዚህ ጋር ማከል ተገቢ ይሆናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ 1990 ዓም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ አዲስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ መካፈል አልቻለም ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ የብሔራዊ ሊግ ተወዳዳሪ ነበርና። በቀጣይ ዓመት ግን ሊጉን ሲቀላቀል ቻምፒዮን ሆነ። በቀጣዩ አመትም ደገመ።
በ 1993 መብራት ኃይል ሻምፒዮን በመሆኑ ለሶሰተኛ ጊዜ ዋንጫ ለመውሰድ የነበረው ሕልም ሳይሳካ ቀረ። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም በ 1994ና 1995 በተከታታይ የዋንጫ ባለቤት ሆነ።
ሀዋሳ ከነማ የ1996 ሻምፒዮን መሆኑ አሁንም ሀትሪክ የመሥራት ህልሙ እንዲጨናገፍ አደረገው። 1997ና 1998 ለሶስተኛ ጊዜ የተከታታይ ድል ባለቤት ሆነ። 1999 በክለቦችና በፌዴሬሽኑ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት ጊዮርጊሶች ራሳቸውን ከውድድሩ ካገለሉ ክለቦች አንዱ በመሆኑ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ሻምፒዮን የመሆን ዓላማው ለሶስተኛ ጊዜ ተጨናገፈ። በ 2000፤ 2001ና 2002 ዋንጫውን በማንሳቱ ግን በስተመጨረሻው ዓላማውን እንዲያሳካ አስችሎታል። ክለቡ እስከ 2002 ከተዘጋጁት 13 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎች ውስጥ ዘጠኙን በመውሰድም ፍፁም የበላይነቱን አሳይቷል::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም