በአሜሪካ መንግሥት ጦር የሚደገፈውና የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች (Syrian Democratic Forces – SDF) በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን ራሱን ‹‹እስላማዊ መንግሥት (Islamic State – ISIS)›› ብሎ የሰየመውን ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ከሶሪያ ምድር ጠራርጎ ለማስወጣት ዘመቻ ጀምሯል። በምስራቃዊው ክፍል የተጀመረው የቡድኑ ዘመቻ አሸባሪው በሶሪያ የነበረውን የመጨረሻ ይዞታ ለማሳጣት በቡድኑ ላይ የተከፈተ ጥቃት ነው ተብሏል።
የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ባሆዝ በተባለችውና ደር አዝ ዞር ግዛት ውስጥ በምትገኘው የምስራቅ ሶሪያ መንደር ላይ ጥቃቱን የጀመረው ቡድኑ የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች ትጥቅ እንዲፈቱና እጃቸውን እንዲሰጡ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ በማለቁ እንደሆነ አስታውቋል።
ቡድኑ በእስላማዊ መንግሥት ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት ለመጀመር ያቀደው ከወራት በፊት ቢሆንም፤ በአካባቢው ያሉ ሰላማዊ ሰዎች ቦታውን ለቅቀው እስከሚወጡና በአካባቢው ወደሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እስከሚገቡ ድረስ ጊዜ ለመስጠት ብሎ ጥቃቱን አዘግይቶት እንደነበር ተነግሯል። የቡድኑ ከፍተኛ የጦር አዛዥ አዳን አፍሪን ለሮይተርስ (Reuters) እንደተናገሩት፤ የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች በአካባቢው የተጠናከረ መከላከል ለማድረግ ቢሞክሩም ቡድናቸው የማጥቃት እንቅስቃሴውን ቀጥሏል።
የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሶሪያ ከኢራቅ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አካባቢ (የኤፍራጠስ ወንዝ ዳርቻ) ላይ በሚገኘው የእስላማዊ መንግሥት ይዞታ ላይ የማጥቃት ዘመቻውን የከፈተው በአሜሪካ ጦር የአየር ጥቃት ታግዞ ሲሆን በጥቃቱም እስላማዊው መንግሥት በምስራቅ ሶሪያ የቀሩትን የመጨረሻ ይዞታዎች ለመልቀቅ እንደሚገደድ ፍንጮች የታዩበት ነው ተብሏል። የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቃል አቀባይ ሙስጠፋ ባሊ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በዘመቻው በርካታ የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች መገደላቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም አንድ የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ተዋጊ መሞቱንና አራት ደግሞ መቁሰላቸውን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
አራት የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች የፈፀሟቸው የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች በሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሳቸውን ሙስጠፋ ባሊ ጨምረው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም፤ ሰላማዊ ዜጎች አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውና ቡድኑ ዘመቻውን በጀመረባቸው ቀናት በአካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ያለመኖራቸውን ማረጋገጡ ቡድኑ ጥቃቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያስችለውም አስታውቀዋል።
ሩስታም ሃሳቅ የተባሉ የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የጦር አዛዥ በበኩላቸው፤ በዘመቻው በርካታ የእስላማዊ መንግሥት ምሽጎች መፈራረሳቸውን ተናግረዋል። ‹‹በርካታ ስፍራዎችን ነፃ ማውጣት ችለናል። ከዓለም አቀፍ ኃይሎች ባገኘነው የአየርና የምድር ጥቃት ድጋፍ ዘመቻውን አጠናክረን ቀጥለናል›› ብለዋል።
ባሆዝ የተባለችው የምስራቃዊ ሶሪያ መንደር የእስላማዊ መንግሥት የመጨረሻ ይዞታ ብትሆንም፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአካባቢው የሚገኙ በመሆኑና ቡድኑ ራቅ ካሉ አካባቢዎች ሆኖ ጥቃት የመሰንዘር ልማድ ስላለው አሁንም ድረስ እንደከባድ የደህንነትና የጸጥታ ስጋት መቆጠሩ አልቀረም።
አንድ የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን ከእስላማዊ መንግሥት ባህርይ አንፃር የቡድኑን ተዋጊዎች ከሶሪያ ጠራርጎ ለማስወጣት የሚከፈተው ዘመቻ ብዙ ሳምንታት ቢያስፈልጉ አስገራሚ ሊሆን እንደማይችል ባለፈው ሳምንት ለአሶሺየትድ ፕሬስ (The Associated Press) ገልጸው ነበር።
የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ባሆዝን ከእስላማዊ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ማስለቀቅና መንጠቅ ከቻለ እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ አስፈሪ ግስጋሴ በማድረግ ሲሶ የሚሆነውን የኢራቅንና የሶሪያን ክፍል ተቆጣጥሮ እስላማዊ መንግሥት መስርቻለሁ ብሎ ላለፉት አምስት ዓመታት የቆየውን ቡድን ግብዓተ መሬት እውን ለማድረግ ወሳኝ ርምጃ ይሆናል።
በአሜሪካ ጦር የሚደገፈው የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች እንዳስታወቀው፤ ባለፉት ወራት ከአራት ሺህ የሚበልጡ የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች እጃቸውን ለቡድኑ ሰጥተዋል። የአረብና የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት እስላማዊው መንግሥት ትልቅ የደህንነትና የጸጥታ ስጋት እንደሚሆን የሰጡትን ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ምክንያት በማድረግ የሶሪያ ጦር በምዕራብና በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የቡድኑ ይዞታዎች ላይ በአየር የታገዘ ድብደባ አካሂዷል። አሜሪካ ለሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የምትሰጠው ድጋፍ ቱርክን ብዙም አያስደስታትም። የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በኩርዶች የሚመራ በመሆኑ፤ ቱርክ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የኩርድ ተዋጊዎች የደህንነት ስጋቶቼ ናቸው ብላ ትቆጥራቸዋለች።
በተለይ ደግሞ ከቱርክ መንግሥት ጋር የሚዋጋው ‹ዋይ.ፒ.ጂ›› (People’s Protection Units – YPG) የሚባለው ቡድን በአሜሪካ መደገፉ ለቱርክ ፈፅሞ አይዋጥላትም። እንዲያውም ባለፈው ዓመት የቱርክ መንግሥት ከዚህ ቡድን ጋር የተፋፋመ ውጊያ በገባበት ወቅት አሜሪካ ለቡድኑ የምታደርገው ድጋፍ ሁለቱን አገራት ፍጥቻ ውስጥ አስገብቷቸው ነበር። በወቅቱም ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ቱርክ በአካባቢው የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመቀነስ ሁኔታውን እንድታለዝብና በአካባቢው የሚደርሰውን የንፁሃን እልቂትና ስቃይ ለመቀነስ የድርሻዋን እንድትወጣ፤ እንዲሁም የአሜሪካና የቱርክ ወታደሮች ወደግጭት ውስጥ እንዲገቡ ከማድረግ እንድትቆጠብ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
‹‹ዋይ.ፒ.ጂ›› በአካባቢው የማደርገው እንቅስቃሴ እስላማዊ መንግሥትን ለመዋጋት ነው ቢልም፤ ቱርክ ግን ቡድኑ በሽብርተኝት ከፈረጀችው የኩርድ ሰራተኞች ፓርቲ (Kurdistan Workers Party – PKK) ጋር ግንኙነት አለው ብላ ስለምታስብ ቡድኑን በጥርጣሬ ትመለከተዋለች። የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ‹‹በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ እንደ ‹‹ዋይ.ፒ.ጂ›› (YPG) ያሉ ታጣቂ ቡድኖች ለቱርክ ሉዓላዊነትና ሰላም መሰናክል በመሆናቸው ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል›› በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ባለፉት ወራት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች በእስላማዊ መንግሥት ቁጥጥር ስር ከነበሩ አካባቢዎች ወጥተው በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ወደሚገኘው አል-ሆል ወደተባለው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ገብተዋል።
የርዳታ ድርጅቶችም ለስደተኞቹ ምግብና የሕክምና ቁሳቁስ ለማቅረብ ኃይላቸውን አሟጥጠው እየተጠቀሙና የአቅርቦት እጥረት እየተከሰተ ስለመሆኑ ማሳወቃቸውም ተገልጿል። በአካባቢው የሚንቀሳቀስ አንድ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅት ተወካይ፤ ወደመጠለያው እየገቡ ያሉ ስደተኞች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ በመምጣቱ የመጠለያ፤ የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳጋጠመ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሕፃናት መርጃ ተቋም (UNICEF) በበኩሉ ከቀናት በፊት ባወጣው መረጃ፤ በአል-ሆል የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ከሦስት ሺህ በላይ ሕፃናት እጅግ በጣም አስከፊ በሆነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።
በጣቢያው ውስጥ ከሚገኙ ሕፃናት መካከል ብዙዎቹ የኢራቅና የሶሪያ ሕፃናት እንደሆኑም ተቋሙ ገልጿል። የተቋሙ የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ጌርት ካፔላሬ በቤይሩት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከጥር ወር ጀምሮ ወደ መጠለያ ጣቢያው ከሚገቡት ሕፃናት መካከል በየቀኑ አንድ ሕፃን እንደሚሞት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011
በአንተነህ ቸሬ