ማርሻል ፕላን የሚባል አንድ ዝነኛ የልማት እቅድ መኖሩን ከታሪክ እንረዳለን። ይህ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ማግስት የተዘጋጀ እቅድ ነው። በወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት ጆርጅ ማርሻል ሀሳብ አመንጪነት የተዘጋጀ የልማት እቅድ አሜሪካ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ክፉኛ ደቅቀው የነበሩት የምዕራብ አውሮፓ አገራት ኢኮኖሚያቸው አንዲያገግም በሚል 15 ቢሊየን ዶላር (በወቅቱ በጣም ትልቅ ገንዘብ ነበር) መድባ የሰራችበት እቅድ ነው። ለአራት አመታት የተተገበረና ውጤት ማምጣት ያስቻለ የተባለ እቅድ ነው።
በእርግጥ አሜሪካ ያንን ድጋፍ ያደረገችበት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንደነበራት መረጃዎች ያመለክታሉ። ፖለቲካዊ ምክንያቷ ኮሚኒዝም ወደ ምዕራብ አውሮፓ እንዳይስፋፋ ማድረግ ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቷ ደግሞ አውሮፓውያን ለመልሶ ግንባታቸው የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ከአሜሪካ እንዲገዙ ማድረግ፣ ለከርሞ የአሜሪካ ምርቶች አስተማማኝ ገበያ መዘርጋት ነው። አሜሪካ ድጋፉን ለምንም ብላ ታደርገው ለምን አውሮፓን ከወደቀችበት እንድትነሳ እና ዛሬ ያለችበት ሰላም እና ብልጽግና ላይ እንድትደርስ አስችሏታል።
የወቅቱን ታሪክ ያጠኑ ምሁራን እንደሚገልጹት፤ ለአውሮፓ (በተለይም ለጀርመን) መነሳት ዋነኛው መንስዔ የአሜሪካ ድጋፍ ሳይሆን ጀርመናውያን ያላቸውን እምቅ አቅም መጠቀማቸው ነው። አቅሙም እውቀታቸው፣ ልምዳቸው እና ጉልበታቸው ነበር። ጀርመኖች በጦርነቱ ኢንዱስትሪዎቻቸው ወድመዋል፤ አልያም ተነቅለው ተወስደዋል። የቀራቸው ግን የሕዝባቸው እውቀት፣ ልምድና ጉልበት እንዲሁም የሥራ ባህል ነው። እናም የማርሻል ፕላን እቅድ ከ5 በመቶ በላይ ጥቅም እንዳልነበረው እና የጀርመን ታሪካዊ ለውጥ የመጣው በጀርመናውያን ትጋት እንደሆነም ምሁራን ይናገራሉ።
በጀርመን ደርሶ ስለነበረው ውድመት አጥኚዎች በምሳሌ ሲያሳዩ እንዳመለከቱት፤ የድሬስደን ከተማ ሙሉ በሙሉ ፈርሳለች፤ የኮሎኝ ከተማ ሕዝብ ከ750ሺህ ወደ 32ሺህ ወርዶ ነበር። የሀገሪቱ የፋብሪካ ምርቶች በአንድ ሶስተኛ ሲቀንሱ በዚህም የተነሳ መንግስት ለሕዝቡ ምግብ የሚያዳርሰው በራሽን ነበር።
የጀርመን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ዋጋ በማጣቱም ጀርመናውያን ወደ ጥንታዊው ዕቃን በዕቃ የመቀየር ግብይት ተመልሰው ነበር። በወቅቱ ጀርመናውያን በሳምንት ከ9 ሰዓት በላይ ምግብ በመፈለግ ያባክኑ ነበር። በጥቅሉ ጀርመን ወድማለች።
ስለዚህም በፍጥነት ወደ ማምረት እና ወደ ግንባታ ገቡ፤ ሰሩ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ከሁሉም በላይ ግን ጀርመንን ከዚያ ታሪካዊ አሰቃቂ ውድመት እንድታገግም ያገዛት የጀርመናውያን ጠንካራ የሥራ ባህል ነው። ጀርመናውያን ወትሮም ቢሆን ሥራ ወዳድ ሕዝቦች ናቸው። የሥራ ወዳድነት ባህላቸውን ጦርነቱ ጥሎባቸው ያለፈውን ቁስል ለማከም ተጠቀሙበት። ዛሬ ጀርመን የአውሮፓ አህጉር አባወራ ናት።
ወደ እኛ አገር ጉዳይ ስንመጣ አሸባሪው ሕወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ባደረሰው ውድመትና ዘረፋ የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ሲተመን እጅግ ከፍተኛ ነው። ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከአይን እማኞች፣ ከተጎጂዎች ያገኘናቸውን መረጃዎች ይዘን ብዙ መቶ ቢሊየን ብሮች የሚገመት ውድመትና ዘረፋ አንደደረሰ መገመት እንችላለን።
አሁን የደረሱ ጉዳቶችንና ለመልሶ ግንባታው የሚያስፈልግ ሀብትን የሚመለከቱ ጥናቶች ይፋ እየተደረጉ ናቸው። ለአብነትም የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከ100 ቢሊየን ብር በላይ፣ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከ36 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል። በውሃ፣ በኤሌክትሪክ አገልግሎትና ኃይል፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ ወዘተ በቢሊየን ብሮች የሚገመት ውድመት ደርሷል፤ ዘረፋ ተፈጽሟል። በሌሎች ዘርፎችና በቤተሰብ እና በግለሰብ ጥሪትና ሀብት ደረጃ የተፈጸመው ዘረፋና ውደመት በቀላሉ ተቆጥሮ ማለቁንም እንጃ። በጥቅሉ ውድመቱ ከባድ የሚባል ነው።
ይህን እጅግ በበርካታ አመታት ሂደት የተገነባ መሰረተ ልማት እና ሃብት መልሶ የመገንባት ግዴታ ውስጥ ገብተናል። ታዲያ ይህን በርካታ በመቶ ቢሊየን ብሮች የሚቆጠር ውድመት እንዴት አድርገን ነው መልሰን የምንገነባው? ገንዘቡንስ ከየት እናመጣለን? አገሪቱ ጦርነት ውስጥ አንደ መቆየቷ፣ የኑሮ ውድነት ያለባት እንደመሆኗ ይህን ተከትሎ መንግስት ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት ሊኖርበት የሚችል እንደመሆኑ ለመልሶ ግንባታው የሚያስፈልገውን ሀብት በሚፈለገው መልኩ እንዴትና ከማን ማግኘት ይቻላል የሚል ጥያቄ ቢቀርብ ትክክል ነው።
ወደ እርዳታ፣ ብድርና ልገሳ ማመተር ሊኖር ይችላል። የእርዳታ ብድርና ልገሳ ምንጭ ሆነው የኖሩት ምዕራባውያን ኩርፊያ ላይ እንደመሆናቸው ከእዚህ አካባቢ ሊገኝ የሚችል ገንዘብ ስለመኖሩ ያጠራጥራል። ምእራባውያኑ የሚዘውሯቸው አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ቢሆኑ የምዕራባውያኑን ይሁንታ ይፈልጋሉና ነገሮች በእዚህ በኩል እንደ ቀደሙት ጊዜያት ላይሆኑ ይችላሉ።
መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም የሚብስ የሚብሰውን የሚያደርግ እንደመሆኑ ለእዚህ ጉዳይ ትኩረት ይሰጣል፤ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። ወዳጅ አገሮችም ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሕዝብ፣ ባለሀብቶች ዲያስፖራው የሚያደርጉት ሊኖር ይችላል። ሁሉም ጥረቶች ግን ከችግሩ ጥልቀትና ስፋት አኳያ ሲታዩ በጣም ውስን ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።
መፍትሄው አንድም የራሳችን ማርሻል ፕላን ማዘጋጀት ነው። ለዚህም የራሳችን ምሁራን አሁን የእውቀታቸውን የመጨረሻ ደረጃ ተጠቅመው መፍትሔ መፈለግ አለባቸው። ምሁርነት የሚፈለግበት ጊዜ አሁን ነው።
ለዚህም የጀርመንን ምሳሌ እንመልከት። ከጦርነቱ በኋላ ጀርመን ነፍስ የዘራችበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋልተር ዩከን አረቀቀ። ዋልተን የቦን ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ምሩቅ ሲሆን፣ በፍራይበርግ ዩኒቨርሲቲም አስተምሯል። ይህ ሰው እጅጉን ውጤታማ የሆነ ‹‹ኦርዶ ሊበራሊዝም›› የተባለ የኢኮኖሚ ፍልስፍናን በማመንጨት ጀርመናውያን በኢኮኖሚው እንዲመነጠቁ አድርጓል። ኢትዮጵያም አሁን አንድ በልኳ የተሰፋ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያረቅ እና የሚያቀርብ ምሁር ትፈልጋለች።
ከፖሊሲው በተጨማሪ ግን ዋነኛዎቹ ሀብቶቻችን የሕዝብ ጉልበት፣ እውቀትና ልምድ ናቸው። ከላይ እንደጠቀስነው ዘረፋና ውድመቱ ብዙ መቶ ቢሊየን ብሮች ስለመሆኑ ጥናቶች እያመለከቱ ይገኛሉ። ይህን ሃብትና ንብረት በቀላሉ በአጭር ጊዜ መመለስ ሊያዳግት ቢችልም፣ በጋራ ጠንክሮ በቁጭት መስራት ግን ወሳኝ ነው። በዚህ ላይ ሰሞኑን በተደጋጋሚ በባለሥልጣናት ሲነገር እንደሰማነው፤ የፈረሱትን የጤና ተቋማትንም ሆነ የትምህርት ተቋማት ቀድሞ ከነበሩበት በተሻለ ሁኔታ እንደ አዲስ ለመገባት እቅድ እንዳለ ነው። ሀሳቡ መልካም ነው።
አዎን፤ ይህ ሁሉ ሊተገበር የሚችለው የሕዝባችንን ሙሉ አቅም መጠቀም ስንችል ነው። አሁን በእጃችን ያለው አስተማማኝ አቅም የሕዝባችን ጉልበት፣ እውቀትና ልምድ ነው። ያን ማንቀሳቀስ መቻል ያስፈልጋል። ለዘመቻው የተፈጠረውን ንቅናቄ አሁን ለመልሶ ማልማቱም ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ መንግስት ሕዝቡን የማሳመን፣ የማስተባበርና የማደራጀት ሥራ ሊሰራ ይገባል።
ለሕዝቡ ነገሮች ቀላል እንዲሆኑለት ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል። ሊታወቅ የሚገባው ነገር ይህ ሕዝብ በገዛ ገንዘቡ በሺህ የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትን እና መስጊዶችን የገነባ ነው። ስለዚህም በመልሶ ግንባታው ላይ በሚገባ ግንዛቤ እንዲኖረው ከተደረገ ትምህርት ቤቱን ፤ ክሊኒኩን ፤ ድልድዩን ፤ ፖሊስ ጣቢያውን ፤ መንገዱን ወዘተ .. ለመገንባት ጊዜ አይወስድበትም። ዋናው በመልሶ ግንባታው ላይ መረጃዎችን ለሕዝቡ ቶሎ ቶሎ እያደረሱ በግንባታው ሙሉ ተሳትፎ አንዲያደርግ መስራት ያስፈልጋል።
ባለፉት ሰሞኖች እንደታየው ዲያስፖራው በመልሶ ግንባታው ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አለው። ነገር ግን ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው መንግስት በተከታታይ ከዲያስፖራው ጋር መወያየት ይኖርበታል። እያንዳንዱ ዲያስፖራ በግሉ ወይም ተደራጅቶ አንድ ትምህርት ቤት ወይም አንድ ጤና ተቋም እንዲገነባ መንግስት መሬቱን ዲዛይኑን ግብዓቱን እና የቢሮክራሲ ሥራውን ማዘጋጀት አለበት።
ለገዛ አገራችን ከራሳችን በቀር ማንም እንደማይመጣ ማሳመን በጣም ያስፈልጋል። መንግስት ማለት ሕዝብ መሆኑን ማስረዳት ይገባል። ያለን ሁነኛ አቅም የሕዝባችን ጉልበት፣ እውቀትና ልምድ መሆኑን በይፋ መናገር እና ሕዝብን ከእርዳታ ጠባቂነት ማላቀቅ ለነገ የማይባል ሥራ ነው። እናም ይህን ሁሉ አቅማችንን ለመጠቅም የራሳችን ማርሻል ፕላን ያስፈልገናል!
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014