ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ጋር ንባብን የተመለከተ ጉዞ ወደ ጎንደር ተደርጎ ነበር። በዚህ የሥራ አጋጣሚ ታዲያ ከቤተመጻሕፍት ጋር በተገናኘ በጎንደርና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችን እንቅስቃሴ ለመቃኘት ወዲያ ወዲህ ማለታችን አልቀረም። ታድያ በጉዞው መካከል ነው፤ ከባለታሪኳና ከጥንታዊቷ ከተማ እንፍራንዝ የደረስነው።
እንፍራንዝ ከጎንደር ወደ ባህርዳር በሚወስደው መንገድ ላይ ትገኛለች፤ ወይም ከጣና ሐይቅ ሰሜን ምስራቅ። ቀጭን መንገዷ ተሳቢ የሆኑ ዕቃ የጫኑ ግዙፍ መኪናዎችን ያሻግራል። እልፍ እልፍ ብለው የተቀመጡ «ኑ ቡና ጠጡ» የሚሉ ባለሙያዎች ደራሹን ሁሉ ያስተናግዳሉ። እንፍራንዝ ቅንጡ ህንጻዎችና ግንባታዎች አይታዩባትም፤ በዚህም ምክንያት በዝምታ ውስጥም ሆና ግን የሞቀች ከተማ ናት። አላፊ አግዳሚዋ ብዙ ነው።
ነዋሪዎቿ ይናገራሉ፤ ታሪክ ያላትና የቀደመች ከተማ ስለመሆኗ ለጠየቃቸው ይመሰክራሉ። በእርግጥም ባለታሪክ ናት። በርካታ የውጭ ዜጎች ይኖሩባት የነበረች ከተማም ነበረች። ለዚህ መንገድ የከፈተው አንድም የነገሥታት መቀመጫ መሆኗ ነው። እንፍራንዝ ከጎንደር ቀድማ ዋና ከተማ በመሆን አገልግላለች። ኢትዮጵያን ከ1556 ዓ.ም እስከ 1589 ዓ.ም ድረስ የመሯት የአፄ ሰርፀ ድንግልም ጉዛራ ቤተ መንግሥትም የሚገኘው በዚህችው ትንሽ ግን በታሪክ ትልቅ ከተማ እንፍራንዝ ነው።
ታድያ በነገሥታቱ ዘመን ከተለያዩ የዓለም አገራት ነጋዴዎች ወደ እንፍራንዝ ያቀናሉ። ያለምክንያት አይደለም፤ እንፈራንዝ የወይን ማሳ ነበራት፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የወይን ምርት ይገኝ የነበረው ከዚህችው ከተማ ነበር። ከዛም ውጪ የጥርኝ ሽቶም የሚመረተው እዚሁ ነው። እናም ከተለያዩ ዓለም አገራት ወደ እንፍራንዝ የሚያቀኑ ነጋዴዎች እነዚህን ምርቶች ይገበያያሉ፤ አልፎም ምርቶቹ ወደ ህንድ ገበያም ይላኩ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል።
ደግሞም የአብሮነት ከተማ ናት፤ እንፍራንዝ። የተለያዩ ሃይማኖቶች በአንድነት ይኖሩባታል። እስልምና እና ክርስትና። ከዚህ በተጓዳኝ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛም ናት። እንዲህ ነው፤ በቀደመው ዘመን የሆነውን ስንመለከት እንፍራንዝን ተመራጭ ያደረጋትና ሰርፀ ድንግልም ዓይናቸው ስፍራዋ ላይ ሊያርፍ የቻለው ከጠላት ለመከላከል ምቹ ቦታ ሆና በመገኘቷ ነበር።
ይህ ሁኔታ ደግሞ ለሌላ ታሪክ ያቀብለናል። እንፍራንዝ እንደ አጼ ሰርፀ ድንግል ሁሉ በደርግ ዘመነ መንግሥትም ለወታደራዊ ስትራቴጂ ምቹ ቦታ ነች ተብላ ተመርጣ ነበር። እናም በመንግሥቱ ትዕዛዝ በአራቱም ማዕዘን ወታደራዊ ካምፕ ነበር። የደርግ ሠራዊት ደግሞ ኅብረ ብሔር ነበርና የከተማዋም ነዋሪ ከዛ ኅብረ ብሔር የተወለደ ነው። እንግዲህ ለዚህ ነው እንፍራንዝ በሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በፍቅርና በሰላም የሚኖሩባት ትልቅ ከተማ ናት የምትባለው።
እንዲህ ያለ ዝና ካላት ከተማ እንዳልኳችሁ በሥራ አጋጣሚ ተገኝተናል። የደረስንበት ጊዜ አየሩ ሞቃታማ ነበር፤ በሙቀት ተቀበለችን። በከተማዋ ከሚገኝ አንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአፍታ አረፍ አልን። ይሄኔ ስለከተማዋ አኩሪ ትናንትና እና አሳሳቢ ስለሆነው ዛሬዋ ተነሳ።
ስለጥንት ገናናነትና ታሪኳ፤ ስለተከበረችበት ባህልና የሕዝቧ ስርዓት፤ ስለተመዘገበባት የበርካታ ሊቃውንት አሻራም ተነሳ። ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በስፍራው ከተገኙ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። «እንፍራንዝ ከሚያሳዝኑኝ ከተሞች መካከል አንዷ ናት።» አለ። እንደምን ቢሉት፤ አሁን አሁን ላይ በታሪኳ ሳይሆን በጫት እየታወቀች በመምጣቷ መሆኑን ገለጸ። ከጎንደር ቀድሞ የነገሥታት መቀመጫ የነበረችው እንፍራንዝ፤ ከአጼ ሚናስ ዘመን ጀምሮ ገናና እንደነበረችም ሄኖክ ይጠቅሳል።
ቀጥሎም አለ፤ እንፍራንዝ ሲጠሯት እንፍራዝ አንዳንዴም እምፍራዝ ይሏታል። ታድያ ግን ከዚህ የተለየ ስያሜ ነበራት፤ እንፍራንዝ «ጉባኤ» ተብላም ትጠራ ነበር። ሃሳብ መለዋወጫ፣ መነጋገሪያና መመካከሪያ ስፍራ በመሆን ታገለግል ነበርና ይህን ስያሜ አግኝታለች። ያም ብቻ አይደለም ብዝሃነት ያለባትና የመቻቻል ከተማም ተብላ ትታወቃለች። «እንፍራንዝ ሃሳብ ሲሰደድ የሚመጣባት ስፍራ ነበረች።» ይላል ሄኖክ። ዘረዓ ያዕቆብ አክሱማዊ በሃሳቡ ምክንያት ተሰድዶ የተቀመጠው እዚህች ከተማ ውስጥ ነው። እናም ከነሃሳቡ ያስተናገደችው እንፍራንዝ ናት። እዚህ ላይ ገታ እናድርግና ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ ላይ ስለ ዘርዓ ያዕቆብ ወደ እንፍራንዝ መግባት የሰፈረውን እንደወረደ እናቅርበው።
እንዲህ ይላል፣ «በ1625 ዓ.ም ሱስንዮስ ሞቶ ልጁ ፋሲለደስ ነገሰ። እርሱም በመጀመሪያ ፈረንጆቹን ወደደ። ግብፃውያንንም አላባረራቸውም በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ሁሉ ሰላም ሆነ። የዚያን ጊዜ ከዋሻየ ወጥቼ መጀመሪያ ወደ አማራ አገሮች ሄድኩ። ኋላም ወደ በጌምድር ተመለስኩ፤ ለሁሉም በፈረንጆች ጠላትነት በሱስንዮስ ዘመን ከተባረሩት መነኮሳት አንዱ መሰልኳቸው። ስለዚህም ወደዱኝና ምግብና ልብስም ሰጡኝ።
በዚህ ሁኔታ ከአገር ወደ አገር ስመላለስ የካህናቶቿን ክፋት አውቃለሁና ወደ አክሱም መመለስን አልወደድኩም። ሰው የሚሄድበት ከእግዚአብሔር እንደሚታዘዝ አሰብኩ። ጌታ ሆይ የምሄድበትን መንገድና የምኖርበትን ነገር ምራኝ አልኩት። ወደ ጎጃም ምድር ተሻግሬም ለመኖር አሰብኩ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ወደ አላሰብኩት መራኝ። አንድ ቀን ወደ እንፍራንዝ አገር ወደ አንድ ጌታ ሰው የእግዚአብሔር ሀብት ነውና ሀብቱ ወደ ተባለ ደረስኩ ፤በዚያውም አንድ ቀን አደርኩ።
በማግስቱም አክሱም ወዳሉት ዘመዶቼ ደብዳቤ እንድልክ ከእርሱ ቀለምና ወረቀት ለመንኩት። ይህ ሰውም «አንተ ጸሐፊ ነህ ወይ?» አለኝ «አዎ ጸሐፊ ነኝ» አልኩት «ከኔ ጋር ጥቂት ቀን ተቀምጠህ የዳዊት መዝሙርን ጻፍልኝና ዋጋህን እሰጥሀለሁ» ብሎ ተናገረኝ «እሺ» አልኩት። የድካሜንም ፍሬ የምመገብበትን መንገድ ስላሳየኝ እግዚአብሔርን በልቤ አመሰገንኩት።
…በጥቂት ጊዜም ቀለምና ብራና አዘጋጅቼ አንድ 16 የዳዊት መዝሙር ፃፍኩ። ጽሕፈቴም ያማረች ናትና ጌታዮ ሀብቱና ሁሉም አይተዋት ተደነቁ። ጌታዬ ሀብቱም ደሞዜን አንድ መልካም ልብስ ሰጠኝ፤ ደግሞም ወልደ ሚካኤል የተባለ የጌታየ ሀብቱ ልጅ ላባቴ እንደጻፍከው ለእኔም ፃፍልኝ አለኝና ጻፍኩለት። አንድ በሬና ሁለት ፍየሎችም ሰጠኝ። ከዚህ በኋላ ብዙዎች ወደ እኔ ዘንድ መጥተው ዳዊትና ሌሎች መጽሐፍትን፣ ደብዳቤዎችን አጻፉ።…»
በነገራችን ላይ ሀብቱ የተባለው ሰው የወልደ ሕይወት አባት ነው። እንፍራንዝን የወልደ ሕይወት አገርም ይሏታል። በዚህ መሰረት ወልደ ሕይወት ከዘርዓ ያዕቆብ እግር ስር ቁጭ ብሎ የተማረ ደቀ መዝሙሩ እንደሆነ እናውቃለን።
ታድያ ይህ ሁሉ ታሪክ ያለባትና የተጻፈባት፤ ከጎንደር ቀድሞ ቤተመንግሥት የታነጸባት፤ የሊቃውንቱ መሰብሰቢያ ጉባኤ መጠለያቸው የነበረችው እንፍራንዝ አሁን ላይ በጫት እጅጉን ተቸግራለች። የአካባቢው ነዋሪዎች አብዛኞቹ ይህ ነገር (ያሳዝናቸዋል) የሚያሳዝናቸው ናቸው። በጣም ወጣት የሆኑ ልጆች በእኩለ ቀን በየጥላው ስር ምንጣፍ አንጥፈውና ጫት ይዘው ታዝበናል።
ልጅ አባቱ ላመረተው ምርት ቅርብ ነውና፤ የአካባቢውና የከተማው ወጣቶች በጫት ሱስ በብዛት ስለመያዛቸውም ተደጋግሞ የሚነሳ ሆኗል። ይህንኑ ጉዳይ ወጣቱ መምህር አራጋው ገበየሁ ያነሳዋል። መምህር አራጋው ጫትን ከከተማዋ ለማስወገድና ለማውጣት ከሚደረገው ጥረት ውስጥ ድርሻውን በላቀ ሁኔታ እየተወጣ ያለ ሰው ነው። በእንፍራንዝ የነበረውን የወይን ተክል አንስቶ አሁን በጫት የመወረሩ ነገር ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ የተሰማውን ይገልጻል።
ነገሩን በሀዘኔታ ከማለፍ በዘለለ ግን ለውጥ ለማምጣት መተባበር እንደሚያስፈልግ ነው የሚያነሳው። እርሱን ጨምሮ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ታድያ ይህን ችግር ለመቅረፍ በሚያስችል ፕሮጀክት ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል። የጎንደር ዙሪያ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ውበት መስፍን በበኩላቸው «እኔም ኃላፊነቴን እወጣለሁ» ብለዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንፍራንዝ ከተማ እንደተከታተሉ ያነሱት አስተዳደሩ፤ ትምህርታቸውን ከከተማዋ ርቀው አጠናቀው በተመለሱ ጊዜ የሆነውን አይተው፤ «እንፍራንዝን ገደሏት!» እል ነበር አሉ። ታድያ አሁን ኃላፊነቱን ስለተረከቡ ነገሩን ለማስተካከልና ወጣቱንም ከጫት ሱስ ለመታደግ እንደሚሠሩ ይናገራሉ። አያይዘውም በቅርቡ በስፋት ማንጎ እየተመረተ እንደሆነና ለጫት አምራቾች አማራጭ በማቅረብ የጫትን ተፈላጊነት ለመቀነስ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። ይህም እንዲቃናና እንዲሰምርላቸው እንመኛለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
ሊድያ ተስፋዬ