ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በእለት ተእለት ሕይወታቸው ላይ ተጠምደዋል፤ ሰራተኛው በየቢሮው፣ ነጋዴው በየንግድ ስራው፣ ባለጉዳዩ ጉዳዩ ባለበት ስፍራ ወዘተ. ተገኝተዋል። በጉዞ ላይ ያለውም በጉዞ ፣ ስብሰባ ላይ ያለውም ስብሰባ ላይ፣ ወዘተ።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከካቢኔያቸው ጋር ስብሰባ ላይ እንደነበሩም የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች ያመለክታሉ። በእለቱ ግን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ። ቡራዩ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመቆጣጠር በግዳጅ ላይ የቆዩ የታጠቁ ወታደሮች የአዲስ አበባ ጎዳናዎችን እያሳበሩ ወደ ቤተ መንግስት እየገሰገሱ ነበር። ይህ እንቅስቃሴ ከጦሩም ሆነ ከጦሩ አመራር እውቅና ውጭ ነው።
ወታደሮቹ ለስልጠና ብላቴ የነበረው የአግአዚ ሁለተኛ ክፍለ ጦር የኮማንዶ ጦር አባላት ሲሆኑ፣ በጅግጅጋ እና በጌድኦ ግዳጃቸውን ተወጥተው ቡራዩ አካባቢ ችግር ሲፈጠር ደግሞ በዚያም ተሰማርተው ቆይተዋል። ታዲያ እነዚህ ከ5 ሻለቃ የተውጣጡ ወታደሮች የቡራዩ ግዳጃቸውን አጠናቅቀው ሲወጡ ነበር በጥቂት ክፉ ሀሳብ ጠንሳሾች እየተነዱ ብዙ ችግር ውስጥ የከተታቸውን ጉዞ የጀመሩት፤ ወደ 4 ኪሎው ቤተመንግስት የመሄድ ሀሳብ።
ጦሩ ገስግሶ መሀል 4 ኪሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ደረሰ። ይህን ተከትሎም በቤተ መንግስቱ ዙሪያ ያለ የትራፊክ እንቅስቃሴ ተቋረጠ። ወታደሮቹን እየመሩ የመጡት ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማናገር እንደሚፈልጉ በስፍራው ለሚገኙ ጠበቂዎች ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማናገር ከፈለጉ በቅድሚያ ትጥቃቸውን እንዲያስቀምጡ ምላሽ ተሰጣቸው። እነሱ ግን በጄ አላሉም። ብዙ ውይይት እና ክርክር ተካሄደ። በመጨረሻም ትጥቃቸውን አስቀምጠው ለመግባት ተስማሙ። ወደ ውስጥ እንዲገቡም ተፈቀደ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በተረጋጋ መንፈስ ወታደሮቹን ተቀብለው በትህትና አስተናገዷቸው። ስፖርት እንዲሰሩም አደረጉ። ከዚያም መጣን ስላሉበት ጉዳይ ለመነጋገር ወደ አዳራሽ እንዲገቡም አደረጉ። ከውይይቱ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈገግታ ተሞልተው ከወታደሮቹ ጋር ተቃቅፈው መግለጫ ሰጡ።
ወታደሮቹም ጉዳያችንን ጨረስን ብለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለያዩ። ይህ ሁሉ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት ፈገግታ አልተለየም ። ነገር ግን ውስጣቸው ብስጭት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንንም ከቀናት በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሲሰጡ በሚገባ አስረድተዋል።
ለህዝብ እንደራሴዎቹ ማብራሪያውን ሲሰጡ ወታደሮቹ ወደ ቤተ መንግስት የመጡበት መንገድ ኢ ህገ መንግስታዊ እና አደገኛ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አላማውም የተጀመረውን ለውጥ መቀልበስ እንደነበር ተናገሩ።
የቤተ መንግስቱ የጥበቃ ሀይልም ሆነ ሰራዊቱ ለዚህ አደገኛ ላሉት ተግባርም የሀይል ምላሽ ያልሰጠው የለውጡን ገጽታ እንዳያበላሽ ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚያም እንዴት ወታደራዊ ሳይንስን እና የውትድርና ልምዳቸውን ተጠቅመው ጦሩን እንዳረጋጉ አብራሩ። ያን ጦሩን እና ህዝቡን የማረጋጋት ስራ ሲሰሩ ግን ውስጣቸው እርር ድብን እያለ እንደነበር ገልጸዋል። አደጋውን በብልሀት ለቀለበሱበት መንገድም ከምክር ቤቱ አባላት ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተቸሯቸዋል። በወቅቱ የጦሩን እንቅስቃሴ በተመለከተ የመረጃ እጥረት እንደነበር ያመኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንዳንድ መንግስታቸውን የሚቃወሙ ሀይሎች ሳንገለው አመለጠን እንዳሉም ጠቁመዋል።
በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊቲ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰአረ መኮንን ነበሩ። እሳቸውም ከቀናት በኋላ በሰጡት መግለጫ ወደ ቤተ መንግስት የመጣው ጦር ስናይፐር እና ብሬልን ጨምሮ ከፍተኛ መሳሪያ የታጠቀ እንደነበር አስታውቀዋል። የመጣበት ሰዓት የሚኒስትሮች ስብሰባ ይካሄድበት የነበረበት ሰዓት መሆኑን በመጥቀስም፣ ከደመወዝ ጥያቄ ያለፈ ሌላ አይነት አላማ እንደሚኖረውም ተናገሩ። የወታደሮቹን ተግባር መመሪያ የጣሰ፣ ጋጠወጥ ስራ ነው ያሉት ሲሆን፣ ጦሩ በድርጊታቸው ማፈሩን እና መቆጣቱንም መግለጻቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በድርጊቱ የተሳተፉት በሙሉ ወደ ብላቴ ማሰልጠኛ መግባታቸውን እና አስተማሪ የሚሆን እርምጃ የሚወሰድባቸው እንደሚኖሩም አስታውቀዋል። ወታደሮቹም በፈጸሙት ድርጊት መጸጸታቸውን ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል።
የወታደሮቹም ጉዳይ ከህዳር 13 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2011 በቆየ ፍርድ ሂደት ሲታይ ቆይቶ፣ ሁለት መቶ ገደማ ከሚሆኑት ኮማንዶ ወታደሮች በ66ቱ ላይ የፍርድ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል። በውሳኔው መሰረት አንድ ተከሳሽ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት፣ ሦስት ተከሳሾች በ13 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 11 ተከሳሾች በ12 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል።
ሌሎች 12 ተከሳሾች በ11 ዓመት ጽኑ እስራት፣ አራት ተከሳሾች በ10 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 16 ተከሳሾች ከ9 ዓመት እስከ ዘጠኝ ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት፣ ሁለት ተከሳሾች ደግሞ የስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ተላልፎባቸዋል።
10 ተከሳሾች ከሰባት ዓመት ከስድስት ወር እስከ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራት፣ አምስት ተከሳሾች ከስድስት ዓመት ከስምንት ወር እስከ ስድስት ዓመት እና አንድ ተከሳሽ በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸውም መረጃዎች ያብራራሉ። በተጨማሪም ከ66ቱ በተጨማሪ ሌሎቹ የሰራዊት አባላት አስተዳደራዊ ቅጣት ተወስኖባቸዋል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ከ500 ሰው በላይ በተገኘበት ግልጽ ችሎት ነው።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም