ክረምት ይወዳል፤ ክረምት የነፍሱ ደስታ ነው። ሰማይ ሲደማምን ጉም ሲውጠው ቀዬው ትዝታ ይወስደዋል። አብዛኞቹ የልጅነት ትዝታዎቹ በክረምት የተፈጠሩ ናቸው። አድጎ እንኳን የክረምት ጸጋ አልሸሸውም። ትላንትም ዛሬም በክረምት ጸጋ ውስጥ ነው።
እየዘነበ ነው። እጆቹን ደረቱ ላይ አጣምሮ እትት ይላል። በዝናብ ውስጥ ሆኖ እንደ እማማ ተዋበች አረቄ የሚናፍቀው የለም። ከአንድ ህንጻ በር ላይ እንደቆመ ከፊት ለፊቱ ጥላ የያዘች አንድ ሴት ተመለከተ። ሳቀ፤ ብዙ አይነት ሳቅ። ምስጋናን፣ አሜንታን የሚናገር ሳቅ።
ክረምት ሁሌም ለእሱ ጸጋው ነው፤ በዘነበ ቁጥር ፈጣሪ አብሮ ከዝናቡ ጋር መና የሚጥልለት ይመስለዋል። የዛሬው የክረምት ጸጋው ከፊት ለፊቱ የምትመጣው ሴት መሰለችው። ከዝናቡ ለመሸሽ፤ በጊዜ ወደ ቤቱ ለመድረስ ያለው አማራጭ ሮጦ ወደ እሷ መሄድ ነው።
እሺ ትለኝ ይሆን? በግድም ቢሆን አብሬአት እሄዳለሁ እንጂ ጸጋዬን የትም አልጥልም እያለ ከራሱ ጋር እያወጋ ተጠጋት። አለባበሷ በዝናቡ ውስጥ ወንድነቱን ተፈታተነው። ከዝናቡ ሽሽት ቦርቃቃ ሸሚዙን ወደ አናቱ ስቦ ‹እናት! እባክሽን አስጠልይኝ…› አላት አይኗን በአይኑ እየተማጸነ።ወደ ጎን አየት አድርጋው በአይኗ ወደ ጃንጥላው እንዲገባ ጋበዘችው።
እትት እያለ አጠገቧ ቆመ፤ ጃንጥላው ስር። አጠገቧ ሲቆም መጀመሪያ ያገኘው ሽቶዋን ነበር፡ ከዛ አለባበሷን። የእጆቿን፣ የእግርዋን ቅላት ተመለከተ። እንደዛ ቀን በሴት ልጅ ጠረን ተማርኮ አያውቅም። ጥሩ ይቀባሉ የሚላቸው ኤደንና ሜሪ እንኳን የእሷን ያክል መአዛ አላገኘባቸውም። በአለባበሷ የምታስቀናው ቤቲ እንደ እሷ ለብሳ አይቷት አያውቅም።
ዝናብ እከላከል ብሎ በገባበት ሌላ እንግዳ ስሜት ተጠናወተው። በሽቶዋ እየታጠነ መሄድ ብቻ አልፈለገም፤ወሬ መጀመር አለበት። ይሄን መልካም እድል ዝም ብሎ ማሳለፍ አልፈለገም። የክረምት ጸጋ በህይወቱ ሁሉም ቦታ መና ሆኖ ይከተለዋል ፤ የዛሬው ግን ከሆነው ሁሉ ሌላ ሆነበት።
ማውራት አለበት፤ ተዋውቆ፤ ስልኳን ተቀብሎ፣ የሆነ ያልሆነውን ቀባጥሮ የሆነ ነገር መፍጠር አለበት። ‹በጣም ነው የማመሰግነው። አላት ምንም አይደል።› ስትል መለሰችለት። ከቬቶቨን ዜማ የላቀ ድምጽ ከአንደበቷ ተሰማ። እየቆየ የሚሰማ፤ እየቆየ የሚሞዝቅ ድምጽ።
እዚህ ጋ መዋሸት አለበት፤ ያገኛትን ሴት ሳይዋሽ ቤቱ ገብቶ አያውቅም። ለሀጢአት የሚሆን ብዙ አቅም፣ ብዙ ጉልበት አለው። ‹‹መኪናዬ ጋራዥ ገብታ ሰሞኑን ተቸገርኩ›› አላት።
‹አንዳንዴ ያጋጥማል፤ ህይወት ሁሌም እንዳሰብናት አትሆንም።› ስትል መለሰችለት ፤ በቅድሙ ሙዚቃዊ ድምጽ።
ብዙ ሴቶችን የመኪና ስም ጠርቶ አደናብሮ ያውቃል። ይቺኛዋ ግን ሌላ ሆነችበት። እስካሁን ፊቷን አላየውም፤ በአለባበሷና በድምጽዋ እንደተዋጠ ነው።
‹የት ሰፈር ነሽ?› አላት ወደሚሄድበት መሄዷ እያስገረመው።
‹እዚሁ አካባቢ ነኝ…›
‹እዚህ አካባቢ ማለት?› አንድ ሰፈር እንዳይሆኑ እየሰጋ።
‹ለጊዜው እዚህ ነኝ.. ሰሞኑን ነው ከለንደን የመጣሁት።›
‹ኦ በጣም ደስ ይላል።› እንደዛ ከሆነማ በደንብ መተዋወቅ አለብን። ለንደን ሁለተኛ ሀገሬ ናት፤ ብዙ ጊዜ እመላለሳለሁ። እያወራ አየት አደረጋት። ከዝናቡ መብረቅ ጋር ተመሳሰለችበት። ቀይ እንደ ምድጃ እሳት የሚንበለበል ፊት ታየው። በላቀ ሰማይ ስር የቆመ ይመስለዋል..በማያባራ የሀሴት ውስጥም።
‹ለስራ ጉዳይ ነው የምትመላለሰው? ጠየቀችው።›
‹አዎ! አስመጪ ነኝ፤ ከስራ ባለፈ አንዳንድ የቢዝነስ
ሚቲንጎችን እዛ ነው የምናደርገው።› በማለት የህይወቱን ትልቁን ውሸት ዋሸ።
‹በጣም ደስ ይላል።›
በወሬ መሀል ጎኗን ታከከው፤ እንደ ረመጥ የሚፋጅ ገላ ወደ ነፍሱ ሰረገ።
‹አንተ እዚህ ሰፈር ነህ?›
‹እዚህ የምረዳቸው ድሆች አሉ፤ እነሱን ጠይቄ ልመለስ እየሄድኩ ነው።›
‹ኦ! በጣም ደስ ይላል።› መልካም ሰው ይገዛኛል።
‹ጥሩነት ለራስ ነው።› ደሞ ሁሉም ሰው ሌላው እንዲያገለግል የተፈጠረ ነው። ይሄን አባባል የት ነበር ያነበበው? ትዝ አለው ታክሲ ውስጥ ነው። በየንግግሮቹ መሀል የታክሲ ላይ ጽሁፍ ሳይጠቀም አልፎ አያውቅም። የታክሲ ላይ ጥቅሶች ሴት በማደናገር ላይ ትልቁን አስተዋጽኦ አድርገውለታል። ሙቀት ፍለጋ ወደ ዳሌዋ ተሳበ፤ ነካት። ነዘረው፤ ዘላለማዊ ንዝረት። ገፋው ዝንታለማዊ ግፊት።
እስካሁን አብረው ናቸው፤ በአንድ መንገድ ወደ አንድ ሰፈር መሄዳቸው እያስገረመው ነው። ቤቱ ደርሷል፤ ቤት ከመግባቱ በፊት ስልኳን ተቀብሎ ሊለያት ፈልጓል። እንዳሰበውም ስልኳን ተቀብሎ ነገ እንደሚገናኙ ነግሯት ተለያዩ።
ዝናቡ አባርቶ ስለነበር ራሱን ችሎ ለመሄድ አልቸገረውም። በመንገዱ ሁሉ ቀይዋ ሴት ነበረች። ነገ ደርሶ ዳግም እስኪያገኛት ድረስ ተናወጠ። የክረምት በረከት ሁሌም እንዳረሰረሰው ነው። በልጅነቱ ውስጥ የተጻፉ በርካታ ክረምት ወለድ ትዝታዎች አሉት። ከሁሉም ዛሬ ይበልጣል። በባለ ጃንጥላዋ ሴት ድምጽና ውበት እየተገፋ ከሚያውቀው አንድ ጠጅ ቤት ደረሰ። ከእማማ ተዋቡ ጠጅ ቤት። ማታ ሲሆን እዚች ቤት ጠፍቶ አያውቅም። ጀምበር ወደ ምዕራብ ስታገድም መገኛው ይሄ ቤት ነው።
ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲል የአከራዩ የጋሽ ፍሰሀ ማስጠንቀቂያ ትዝ ስላለው ወደ ቤቱ አመራ። ጋሽ ፍሰሀ ሁሉንም ተከራይ ጠርተው ከሁለት ሰዓት በላይ ማምሸት እንደማይቻል ከመናገራቸው በፊት ከዛ ጠጅ ቤት ታዝሎ ነበር የሚወጣው። እኩለ ሌሊት ሳይሆን ቤቱ ገብቶ አያውቅም ነበር።
የተከራየበት ግቢ ሲደርስ ከአከራዩ ከጋሽ ፍሰሀ ቤት ሞቅ ያለ የሳቅና ጨዋታ ድምጽ ተሰማው። ወደ ቤቱ ሊገባ ሁለት እርምጃ ሲቀረው የጋሽ ፍሰሀን ድምጽ ከኋላው ሰማ።
‹ምን ሆነህ ነው የጠፋኸው? ቤትህ ስንት ጊዜ ተመላለስኩ መሰለህ? ትናንትም እቤት አላደርክም፤ እሱን ሌላ ጊዜ እናወራለን› ሲሉ ጋቢያቸውን ወደ ትከሻቸው እያጣፉ ጠየቁት።
‹ያው ስራ አይደል፤ እዛው አምሽቼ ገና እየገባሁ ነው። አላቸው።› በለመደው ውሸት።
‹ና በዚሁ ቤት ግባ፤ ሁሉም ተከራዮች አሉ። አንተ ብቻ ነው የጠፋኸው።› አሉ ቆመው እየጠበኩት።
ዛሬ ቀኑ ምንድነው? ወሩን፣ ዓመቱን አሰበው፤ ፕሮግራም ሊዘጋጅበት የሚችል ምንም የለም። በቃ እንደለመዱት ወይ ቤት ኪራይ ሊጨምሩብን ነው አሊያም ደግሞ ሁለት ሰዓቱን ወደ አንድ ሰዓት ዝቅ ሊያደርጉት ነው እያለ በማሰብ ወደ ቤቱ ሊገባ ያለውን ትቶ ተከተላቸው።
እሳቸው ከፊት እሱ ከኋላ እየተከተለ ወደ ቤት ገቡ። ቤት ሲደርስ በድንጋጤ ክው ነበር ያለው። መንቀሳቀስ አቅቶት ውሃ ሆነ። ቀይዋን ባለጃንጥላዋን ሴት አያት።
‹ይቺ ልጄ ናት፤ ሰርካለም ትባላለች። ትላንት ነው ከለንደን የመጣችው። ተዋወቃት አሉ ወደ ልጃቸው እየጠቆሙ።›
በቆመበት ደርቆ ቀረ።
‹ምን ይገትርሃል ና እንጂ። ጋሽ ፍሰሀ ቆጣ አሉ።›
ፊቷን ለማየት አቅም አጥቶ ሄዶ በሁለት ጣቱ ሰላም አላት።
‹ትንሳኤ ይባላል። እንዴት ያለ ድንቅ አናጢ መሰለሽ። አረቄ ይወዳል እንጂ ማለፊያ ልጅ ነው። እዛች ትንሿ ክፍል ነው የሚኖረው።› አሉ ለልጃቸው እያስተዋወቁት።
ትንሳኤ በተቀመጠበት ላብ አሰመጠው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2014