እናኑና ቀብራራዬ…. የተሰኙ የሙዚቃ ሥራዎቹ ከብዙዎች ጋር አስተዋውቀውታል። በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድም ዝናና ዕውቅናን ያስገኙለት የበርካታ ሥራዎች ባለቤትና ታዋቂ ድምፃዊ ነው። በሙዚቃ ሥራው ከሌላው በተለየ መልኩ በራሱ ቅላፄና የአዛዜም ስልት ብቅ ማለቱ በቀላሉ እውቅናን እንዲጎናፀፍ ጠቅሞታል። ‹‹ሂፕ ሆፕን›› ኢትዮጵያዊ ለዛ አላብሶ በልዩነት ያቀነቅነዋል። አገራዊና ማህበረሰባዊ ትውፊቶችን የሚዳስሱ የግጥም ይዘቶችን አሰናድቶ ለዛ ባለው ድምፁ በማንጎራጎር የሙዚቃ አፍቃሪያን አጀብ ያሰኘ ወጣት ድምፃዊ ነው።
በዛሬው የዝነኞቹ ገፃችን ተጋባዥ አድርገን ያቀረብነው ድምፃዊ አብለኔ ብርሀኔ ነው። ከእርሱ ጋር በነበረን ቆይታ አጠቃላይ ሥራዎቹ፣ የሕይወት ተሞክሮውን፣ ማህበራዊ ልምዱን፣ የዕረፍት ቀን ውሎውና ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ያለውን እይታ በተመለከተ በርካታ ቁም ነገሮችን አንስተን አውርተነው ለእናንተ በዚህ መልክ አሰናድተን አቀረብን፤መልካም ንባብ።
ብዙዎች በሥራዎቹ ላይ በሚጠራበት ስሙ ነው የሚያውቁት፤ ‹‹አብሌክስ›› ይሉታል። የመዝገብ ስሙ ግን አብለኔ ብርሀኔ ይባላል። ገና የ27 ዓመት ወጣት ሲሆን የተወለደው ጎላሚካኤል አካባቢ ነው። ፒያሳ፣ ሸራተን እና ሌሎች ጥቂት የአዲስ አበባ ሰፈሮች ላይ የልጅነት ጊዜውን በተለያየ አጋጣሚ እየተዘዋወረ ሕይወትን ያጣጣመባቸው የልጅነት ጊዜውም ያሳለፈባቸው ሰፈሮች ናቸው።
ከሀሁ እስከ ምረቃ
4 ኪሎ የሚገኘው ስላሴ ካቴድራል ትምህርት ቤት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለበት ትምህርት ቤት ነው። በትምህርቱም ከፊት ከሚሰለፉት ጎበዝ ተማሪዎች ተርታ የሚመደብ ነበርና በጥሩ ውጤት አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተመድቦ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ቤተሰቦቹም ጉብዝናውን አይተው ትምህርቱ ላይ እንዲገፋ ግፊት ያደርጉበትም ነበር።
ብርቱ ተማሪ መሆኑና በጥሩ ውጤት ማጠናቀቁ ግን በተማረበት ሙያ ተቀጥሮ መስራት አልያም ደግሞ የተማረውን ወደ ተግባር መለወጥን እንዲያስብ አላደረገውም። ከዚህ ይልቅ ወደ መክሊቱ ተጠጋ። የእርሱ ፍላጎትና ህልም ከልጅነቱ ጀምሮ በሙዚቃው ዘርፍ የራሱን ተፅዕኖ መፍጠር ነበር። የእርሱ ዕጣ ፈንታ ኪነ ጥበብ ነበረና ወደ ልጅነት ምኞቱና ሊያሳካው ወደሚፈልገው ጥበብ ቀረበ።
የዘርፈ ብዙ ክህሎትና ሙያ ባለቤትነት
ለእሱ የተሰጠው ሙዚቃ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በሞከረው ሁሉ ርቆ የተጓዘና ምኞቱን ያሳካ ነው። በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ ስኬታማና ውጤታማ የሆነው አብለኔ ከአፍላ ወጣትነቱ ጀምሮ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችንም ያዘወትር ነበር። በጅምናስቲክ የተዋጣለት አክሮባቲስትም ነበር። በተጨማሪም በቴኳንዶ ከፍተኛ ደረጃ የሚባለው የጥቁር ቀበቶ (ብላክ ቤልት) ደረጃ ደርሷል።
የተዋጣለት የማስታወቂያ ባለሙያም ነው። ለአምስት ዓመታት የሐረር ቢራ አምባሳደርም ሆኖ ቆይቷል። የማስታወቂያ አዳዲስ ሀሳቦችን በመድረስና ማስታወቂያዎችን በማዘጋጀት ወይም ዳይሬክት በማድረግም ይሳተፋል።
ፍቅር ከሂፕሆፕ ጋር
ከልጅነቱ ጀምሮ የሂፕ ሆፕ ሙዚቃን ማድመጥ ሀሴት ያጎናፅፈው ነበር። በተለይም ኢስት ኮስትና ዌስት ኮስት የሚባሉት የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ስልቶች የቱፓክ ሻኩርና ሌሎች ዘፋኞች ሂፕሆፕን የራሳቸው ለማድረግ እና በሙዚቃ ስልቱ ከፍ ብሎ ለመታየት የሚደርጉትን ጥረት ትኩረት ሰጥቶ ይከታተልም ነበር። በተለይ በሙዚቃ ስልቱ የጥቁሮች የተለያየ ማንነትን የአኗኗር ስልትና ልዩ ልዩ እሳቤ ይመለከት ስለነበር እጅጉን የሚወደው የሙዚቃ ስልት እንዲሆን ተፅዕኖ እንዲፈጥርበት አደረገው። ወደ ሙዚቃው የተሳበበት አጋጣሚ ይሄው ነው።
አብለኔ ከአገራችን እጅጉን የሚያደንቃቸውና ሥራቸውን የሚያወድስላቸው ቀደምት ዘፋኞች እነ የሜሪ አርምዴ፣ ባህሩ ቃኘውና አስናቀች ወርቁ የመሳሰሉ የክራር አጨዋወት ስልታቸው ከሂፕሆፕ ስልት ጋር የተቀራረበ በመሆኑ አብዝቶ ያደምጣቸውም ነበር። የሚጫወቱበት የሙዚቃ ስልትም ከሂፕ ሆፕ ጋር እጅግ የቀረበና በዘርፉ ‹‹ፊሪ ስታይል›› የሚባለው የሂፕ ሆፕ ዘርፍ የተቀራረበም ነው። እነዚህ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ታላቅ አበርክቶ ያላቸው የሙዚቃ ባለሙያዎች ለአብለኔ አርዓያዎች እንደሆኑት ይናገራል።
ጉዞ ወደ ኪነት
በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ሁሉ ወደ ኪነ ጥበቡ ለመግባት ብርቱ ፍላጎት ነበረው። ቀድሞ ያደምጣቸው የነበሩ የሂፕ ሆፕ የሙዚቃ ስልቶች እና በኢትዮጵያዊ ቀለም ወደ ራሱ ስልት ለማምጣት ጥናት ማድረግም ጀመረ። የሦስተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ ወደ ሙዚቃ የሚቃርበው አንድ አጋጣሚም ተፈጠረለት።
የሙዚቃ ሥራ ስቱዲዮ ከነበራቸው በቅርብ ከሚያውቃቸው ጓደኞቹ ዘንድ መመላለስና ውስጡ ያለውን የሙዚቃ ፍቅር ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስቱዲዮ ውስጥ መግለፅና መሞከር ጀመረ። እዚያ ስቱዲዮ ውስጥ የነበሩ ወዳጆቹና ጓደኞቹም ሙዚቃ ሥራቸው ነበረና ያበረታቱትና አብረውት አንድ ሥራ ሊሰሩ መወጠን ጀመሩ። በሂደትም በውጭ አገር ‹‹ሳይፈር›› በመሰኘት/ ሁለትና ከዚያ በላይ አርቲስቶች የሚያቀነቅኑበት ስልት/ አንድ ጉዳይ ሁለትና ከዚያ በላይ በመሆን በሂፕሆፕየሙዚቃ ስልት የመግለፅ ተሞክሮን ወደ ኢትዮጵያዊ ቀለም ለውጠው በራሳቸው መንገድ ለመስራት አቅደው እንቅስቃሴ ማድረግ ውስጥ ገቡ።
በዚህም ‹‹ሳይፈር አቢሲኒያ›› በሚል መጠሪያ አንድ ሥራ ለሕዝብ ለማድረስ ቻሉ። የሙዚቃ ስልቱም ዳርክ ሂፕሆፕ የሚሰኝ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አብለኔን ከሕዝብ ጋር ያስተዋወቀው ሥራውም ይህ ነው። ቀጥሎም ሳይፈር አቢሲኒያ ሁለትና ሦስትን በተከታታይ ለሕዝብ በማቅረብ ተወዳጅነትን ማትረፍ ቻለ። በተለይ በሳይፈር አቢሲኒያ ሦስት ላይ እነ ቴዲዮና መርከብ ቮኒካና የቴዲዮ ወንድም ሚኮዮ ከአብሳላት ጋር ልዩ ጥምረት ፈጥረው የሰሩት የተዋጣለት ሥራ ስለነበር ሙዚቃው በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነትን አገኘ።
አብለኔ ከድምፃዊነቱም ባሻገር የተዋጣለት ግጥምና ዜማ ደራሲም ነው። ከአምስት በላይ የሚሆኑ ተደማጭና ተወዳጅ የግል ሥራዎቹን ግጥምና ዜማ ከማዘጋጀቱም በተጨማሪ ለሌሎች ድምፃውያን የዘፈን ግጥሞችና ዜማዎችን በመድረስ እጅግ ተወዳጅነት ያላቸው ሥራዎች ጥንካሬ መገለጫም ነው። በተለይ በሂፕ ሆፕ ስልት ለሚያቀነቅኑ ድምፃውያን በርካታ ግጥምና ዜማዎችን በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል። ለአርቲስት ሚኪ ሸዋ «ሸግዬ ሸጊቱ» የተሰኘው ሥራ ላይ ከግማሽ በላይ ሥራዎቹ የአብለኔ የግጥምና የዜማ ሥራዎችናቸው። በተጨማሪም በቅርቡ ለሕዝብ የሚቀርቡ የእሱ አሻራ ያረፈባቸው ሥራዎችም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
በቅርብ ጊዜ ለሕዝብ የሚቀርብና የድሬዳዋ አካባቢ ባህልና ትዕውፊት ላይ ያተኮረ በይዘቱም ለየት ያለ የሙዚቃ ሥራ በመስራት ላይ የሚገኘው አብለኔ ወደፊት በዘርፉ ጠናካራና አገርን የሚያስተዋውቁ ሥራዎችን በመስራት የራሱን አስተዋፅኦ የማበርከት ፅኑ አላማ አለው።
የእረፍት ጊዜ ልምድ
ሙያዎቹን የተመለከቱ ዕውቀትን ሊስጨብጡት የሚችሉ ትምህርታዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር፣ አገራዊና ዓለምአቀፋዊ ታሪክ፣ ባህልና ልዩ ልዩ ዕሴቶች ላይ የሚያተኩሩ መጽሐፍትን ማንበብ በእረፍት ጊዜው የሚያዘወትረው ልምዱ ነው። አንዳንዴም የልቦለድ ይዘት ያላቸው መጽሐፍትን ጊዜ ሲያገኝ ያነባል። ትያትር መመልከት ደግሞ እጅጉን የሚወደውና አዲስ ትያትር ለመድረክ ሲበቃ አነፍንፎ ማየት ተደጋጋሚ የዕረፍት ጊዜ ልምዱ ነው።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ በአብለኔ እይታ
በእርግጥ የሙዚቃው ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያመጣና የተሻሻለ ቢሆንም አገሪቱ ካላት ሰፊ ዕድል አንፃር ብዙ ሊሰራበት እንደሚገባ የሚያስረዳው አብለኔ፤ ባህላችንና ፍልስፍናችንን ለሌሎች በማስተዋወቅ ሙዚቃችንን ልንጠቀምበት እንደሚገባ ያስረዳል።
ሙዚቃ በወጉ ከተጠቀሙበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ተዝቆ የማያልቅ በርካታ ባህልና እሴት ባለቤት የሆኑ አገራት ከያንዳንዱ ልምድና ባህል የተቀዳ የሙዚቃ ስልት አሳድገውና በተገቢው ሁኔታ ለዓለም አቅርበው ማንነታቸውን፣ እምነትና ፍልስፍናቸውን ለሌላው በማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ በማድረግ ከሙዚቃው ኢንዱስትሪ በጣሙን ተጠቅመዋል። ኢትዮጵያ በርካታ ባህል የሚገኝባትና የተለያዩ ብሔረሰቦች የሙዚቃ ምት ባለቤትና የየራሳቸው ፍልስፍና ያላቸው ኪናዊ ፀጋዎቻቸው የበረከቱባት እንደመሆንዋ እነዚህን ሀብቶች እስከዛሬ በአግባቡ መጠቀም ላይ ውስንነት አለባት።
አሁን ላይ በተለያዩ ድምፃውያን የሚቀርቡ ባህልንና ኢትዮጵያዊ ቀለም የተላበሱ ሥራዎች መበርከታቸው ይበል ያሰኛል የሚለው ድምፃዊው፣ የሙዚቃ ኦንዱስትሪው መነቃቃትም እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ይናገራል። በተለይ በኢትዮጵያ ባህልና ትውፊት ላይ የሙዚቃው ዘርፍ ጠንካራ ሥራዎች መሰራት ይገባዋል። ከስፋቱ አንፃር እስካሁንም ምንም እንዳልተነካና ብዙ መስራት እንደሚገባ ይናገራል።
የሙዚቃ ባለሙያዎችና የዘርፉ ተዋናዮች በኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፍ ላይ የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ ወደሚፈለገው የእድገት ደረጃ ማድረስ ይቻላቸዋል የሚለው ድምፃዊ አብለኔ፤ በተለይ ድምፃውያን በአገራችን ባህል እና የማህበረሰቡ ትውፊታዊ ገፅታዎቿን የሚያስተዋውቁ ሥራዎች በራሳቸው መንገድ ቢያቀርቡ የተሻለ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ያስረዳል።
አሁን አሁን ላይ በሙዚቃው ዘርፍ በአፍሪካና በተለያዩ ዓለምአቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች እየቀረቡ ተወዳዳሪና ከሌሎች ጋር ቀርበው አሸናፊ መሆን መጀመራቸው የሙዚቃው ኢንዱስትሪ እድገት እያመጣ መሆኑን ያሳያል ያለው ድምፃዊው፣ ዕድሉ ስላለ ከዚህ በላይ መስራትና ውጤታማ መሆን እንደሚገባም ይጠቁማል።
መልዕክት ለኢትዮጵያውያን
«እንደ አገር ሰፊና ያልተነካ ሀብት ባለቤቶች መሆናችን ተቀብለን ሁላችንም በተሰማራንበት መስክ ጠንክረን ከሰራንና አገራችንን የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ ትኩረት ካደረግን ሁላችንም ውጤታማ መሆን እንችላለን። በተረፈ አሁን ያለንበት ዘርፈ ብዙ ችግር ተቀርፎ፤ ወደፊት ሰላማዊና ያደገች ለሕዝቦቿም ምቹ የሆነች አገር እንድትኖረን ጥረት እናድርግ፤ አገራችንን ፈጣሪ ሰላም ያድርግልን። » በማለት መልዕክቱን እንካችሁ ብሏል። እኛም ከዚህ ወጣትና ዝነኛ ድምፃዊ ጋር የነበረን በቆይታ ያሰናዳነውን ጽሑፍ በዚሁ አበቃን ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2014