በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው በዓላት መካከል አንዱ ኢሬቻ ነው። ይህ ታሪካዊ እና ተወዳጅ ትውፊታዊ በዓል በአመት ሁለት ጊዜ ይከበራል። አንዱ በተራራማ ስፍራ ሌላው ደግሞ በወንዞችና ሀይቆች ዳርቻ። በብዙዎች ዘንድ በስፋት የሚታወቀው ግን የክረምቱ ወራት መጠናቀቅን ተከትሎ በወንዞች ወይም ሀይቆች ዳር የሚከበረው የመስከረሙ የኢሬቻ በዓል ነው። ይህ በዓል ፈጣሪ የክረምቱን ወራት አሳልፎ ለበጋው ስላደረሰ የሚከበር ነው። ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርበብት።
በአሉ በመላ ኦሮሚያ የሚከበር ሲሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በተገኘበት በስፋትና በድምቀት ሲከበር የኖረው በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ነው። ከሀገራዊው ለውጥ ወዲህ ደግሞ ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ሆራ ፊንፊኔ በደማቅ ሥነሥርዓት እየተከበረ ይገኛል።
የታሪክ እና ባህል ተመራማሪው አፈንዲ ሙተቂ ስለ በአሉ ማክበሪያ ምክንያት እንዳብራራው፤ ኢሬቻ በክረምቱ የወንዞች ሙላት ምክንያት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተ ዘመዶችና ልዩ ልዩ ጎሳዎች የሚገናኙበት በዓል ነው። በመሆኑም በበዓሉ የተገኙት ሁሉ ይቅር ይባባሉ። ገንዘባቸውን ለሌሎች ያበደሩ ሰዎችም እዳውን ይሰርዙላቸዋል።
በዓሉ የሚከበርበት ቀንም የዓመቱ መጀመሪያ ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ዓመቱ የደስታና የብልጽግና ይሆን ዘንድ የመልካም ምኞት መግለጫዎች ይጎርፋሉ። የሕዝቡ መንፈሳዊ መሪ የሆነው “ቃሉ” ለህዝቡና ለሀገሩ “ኤባ” (ምርቃት) ያደርጋል። ታዲያ ማንኛውም ሰው ወደ በዓሉ ስፍራ ሲሄድ አለባበሱን ማሳመር ይጠበቅበታል። በእጁም የወይራ ቀንበጥ፣ እርጥብ ሳር አሊያም የአደይ አበባን ይይዛል።
በዓሉ ስለሚከበርበት ቦታም ሲገልጽ፡- በነገድ ደረጃ የኢሬቻ በዓል የሚከበርባቸው ማዕከላት በሙሉ በሐይቅ ዳርቻ የሚገኙ ናቸው። ይህም ምክንያት አለው። አንደኛው ምክንያት የጥንቱ የኦሮሞ የዋቄፈንና እምነት “ፍጥረት የተገኘው ከውሃ ነው” የሚል አስተምህሮ ያለው በመሆኑ “ዋቃ” ፍጥረተ ዓለሙን በጀመረበት የውሃ ዳርቻ በዓሉንና የአምልኮ ተግባሩን መፈጸም ተገቢ ነው ከሚል ርዕዮት የመነጨ ነው። ይህ ርዕዮት በዋነኝነት ከሚፈጸምባቸው ስፍራዎች መካከል ቀዳሚው ደግሞ ቢሾፍቱ የሚገኘው ሆራ አርሰዲ ዋናው ነው።
የበዓሉ ታዳሚዎች ውብ ባህላዊ አልባሳትን ተጎናጽፈው ከቤተሰባቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸው ወዘተ ጋር በመሆን በዓሉ በሚከበርበት ወንዝ ተገኝተው ለፈጣሪያቸው ምስጋና ያቀርባሉ። በስፍራውም ወደ ስፍራው በሚያደርጉት ጉዞም ሆነ ሲመለሱ ደስታቸውን በተለያዩ ዜማዎች እና ውዝዋዜዎች ይገልጻሉ። በበዓሉ ላይ የማይገኝ የኅብረተሰብ ክፍል የለም፤ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ አዛውንቶች ፣አካል ጉዳተኞች.ወዘተ ይታደሙበታል። በዚህ ቀን የማይደሰት የለም፤ በዚህ ቀን ብቻ ሳይሆን ይህን ቀን መለስ ብለው ሲያስቡትም ይደሰታሉ።
አንድ ዓመት አንድ ቀን ላይ ግን ከዚህ የተለየ ክስተት ተፈጠረ። በቢሾፍቱው ሆራ አርሰዲ። በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የኢሬቻ አክባሪ ሕዝብ በሚገኝበት በዚህ ታላቅ ስፍራ። በ2009 ዓ.ም የአሬቻ በዓል በሚከበርበት ወቅት።
ያ ወቅት ለቢሾፍቱ፤ ለሆራ አርሰዲ፤ በሚሊዮን ለሚቆጠረው የበዓሉ አክባሪ ብሎም ለመላው ኢትዮጵያውያን ጥሩ ዓመት አልነበረም። በበዓሉ ላይ በተፈጠረ ችግር በርካታ ነፍሶች ተቀጥፈውበታል። በርካቶች ለጉዳት ተዳርገዋል፤ በዕለቱ መድረክ አካባቢ ተፈጠረ የተባለ ውዝግብን ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ እና እሱን ተከትሎ በተፈጠረ ትርምስ ነው በርካታ ሰዎች ለህልፈት የተዳረጉት።
ሁኔታውን የወቅቱ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቴሌቪዥን ቀርበው በበዓሉ ወቅት የተፈጠረውን ጠቅሰው የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸዋል። መንግሥት የሟቾቹ ቁጥር ከሃምሳ ጥቂት ከፍ የሚል ነው ሲል ሌሎች አካላት ግን የሟቾች ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠር እንደሆነ ጠቁመዋል።
በወቅቱ ሀገሪቱ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ነውጥ ውስጥ የነበረች ሲሆን፣ በተለይም በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች መንግሥትን የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች ተበራክተው ታይተዋል። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም ውስጥ ውስጡን እርስ በእርሱ ሽኩቻ ውስጥ ገብቶ ነበር። በ2008 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተጀመረው ተቃውሞ በተለይ በኦሮሚያ ተፋፍሞ በርካታ የሕዝቡ ጥያቄዎች ወደ አደባባይ ወጥተዋል። መንግሥትም በተቻለው አቅም ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ነበር።
የ2009 ዓ.ም የኢሬቻ በዓልም የደረሰው የተነሳው ተቃውሞ መንግሥት እንዳይስፋፋ በቁጥጥር ስር ለማድረግ ጥረት ላይ እያደረገ መሆኑን ተከትሎ መሆኑ ይገለጻል። እናም በስፍራው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጸጥታ አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ተደርጎም ነበር።
የተሰጋው ለመምጣት ግን ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም። አንድ ወጣት መድረኩ ላይ ወጥቶ ድምጽ ማጉያውን ነጥቆ ዳውን ዳውን ቲፒኤልኤፍ፤ ዳውን ዳውን ወያኔ የሚል መፈክር አሰማ። በቦታው የነበረው ሕዝብ በደስታ ተቃውሞውን አስተጋባለት። የትግሉ ምልክት የሆነውን እጅ የማጣመር ምልክት ሁሉም አሳየ።
መድረክ ላይ የነበሩት አስተናባሪዎች በድንጋጤ የሚይዙት የሚጨብጡት ሲጠፋቸው ይታይ ነበር። ከዚያን በኋላ ከጸጥታ ኃይሎች ተኩስ ተሰማ። ተኩሱ ትርምስ ፈጠረ። የሆነው ሁሉ ሆነ። ከሰዓታት በኋላ ከበዓሉ ስፍራ በርካታ አስከሬን ተለቀመ። በርካቶች ቆሰሉ፤ ሕፃናት፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ ወዘተ በተገኙበት የሚሊዮኖች መድረክ እንዲህ ዓይነት ክስተት ሲፈጠር ሊሆን የሚችለውን መገመት አይከብድም።
በወቅቱ መንግሥት አንድም ጥይት አልተተኮሰም፤ ሰዎች የሞቱት የተፈጠረውን ትርምስ ተከትሎ በመረጋገጣቸው ነው ቢልም የተለያዩ መረጃዎች ግን በጥይት የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሌሎች የሰብአዊ መብት ተቋማት መረጃዎች ግን ከዚህ የተለዩና የችግሩን ግዝፈት አውጥተው አሳይተዋል። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ችግሩ ግዙፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎች “በእሳት ላይ ነዳጅ“ በ2009 ኢሬቻ በዓል አከባበር የፀጥታ ኃይሎች ምላሽ` በሚል ባወጣው ሪፖርቱ መንግሥት በኢሬቻ 2009 በዓል አከባበር ላይ የፈፀመውን የሰብዓዊ መብቶች ጥስት በልዩ ሁኔታ በትኩረት ዳስሷል። ሪፖርቱ ከጥቅምት 2009 እስከ ነሐሴ 2009 በኢሬቻ በዓል ዕለት እና በዓሉን ተከትሎ በተፈፀሙ ሰብዓዊ መብቶች ጥስት ላይ ብቻ ትኩረት አድርጓል።
ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው 51 እማኞችን ጠቅሶ በተሰራው በዚህ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን ያጋለጠው ሪፖርት በአስር የኦሮሚያ ክልላዊ ዞኖች የሚኖሩ 26 ሰዎችን ምስክርነት አካቷል። በበዓሉ ላይ የታደሙ 15 ሰዎች የበዓሉን አከባበር በተመለከተ እና በዓሉን አከባበር ተከትሎ ስለተከሰተው ብጥብጥ አስረድተዋል። ሌሎች ጋዜጠኞች መምህራን እና በተለያዩ ሆስፒታሎች የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎችን እማኝነት ሪፖርቱ አስገብቷል።
ሂውማን ራይትስ ዎች በኢሬቻ በዓል የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ አንድ እማኝ፤“ከኔ በቅርብ ርቀት የወታደርም የፖሊስም ልብስ ያልለበሱ ሰዎች ወደሕዝቡ እየተኮሱ ሰዎች ሲገድሉ አይቻለሁ። አንድ ሰውዬ በቴፒ ዩኒቨርሰቲ መምህር የነበረን ሰው ተኩሶ ሲገድለው አይቻለሁ። መምህሩ በጣም ታዋቂ ነው፣ አውቀዋለሁ። ሲወድቅ አየሁት። ልረዳው አልቻልኩም ምክንያቱም እኔም ሕይወቴን ለማዳን እየሮጥኩ ነበር። ሌሎችም ሰዎች በጥይት ተመተው ሲወድቁ አይቻለሁ። ሰውነታቸው በጥይት ተመቶ ነው የወደቁት” ማለታቸውን ጠቁሟል።
በ2009 የኢሬቻ በዓል እንዳትሳተፉ ተብለው በመንግሥት የደህንነት አባላት እና በኦህዴድ ካድሬዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንደነበር የተናገሩ እማኞች ማስጠንቀቂያውን ችላ በማለት በዓሉ ላይ እንደተሳተፉ ገልፀው፤ ከበዓሉ በኋላ ወደ መንደራቸው ሲመለሱ ያለምንም የፍርድቤት ትዕዛዝ እንደታሰሩ እና በእስር ወቅትም ከባድ ድብደባ እንደደረሰባቸው መግለጻቸው ሪፖርቱ ጠቅሷል። እስር ይገጥመናል ብለው በፍራቻ ወደ ቤታቸው እንዲሁም መንደራቸው ያልተመለሱ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው በእነርሱ ምትክ እንደታሰሩባቸው ተናግረዋል።
ለበርካታ ዓመታት የኢሬቻ በዓል ላይ ተሳትፎ እንደነበራቸው የተናገሩ ግለሰብም እንዲህ ብለው እማኝነታቸውን ሲሰጡ፡– “ሌላ ጊዜ በኢሬቻ በዓል የከተማው ፖሊሰ ነበር ኃላፊነት የሚወስደው። እናወቃቸዋልን፣ ያውቁናል። የምናወራውን ያወራሉ። በዓሉ ለእኛ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያውቃሉ። ቦታውም ገደል መሆኑን፣ ጉድጓዱንም በደንብ ያወቁታል። በዚህ ዓመት የፌዴራል ፖሊሶች ነበሩ። የማላውቀውን ቋንቋ የሚናገሩ፤ በከባድ የታጠቁ። የኦሮሚያ ፖሊስ እንደዚህ አይታጠቅም። በዓሉን የወታደራዊ ተልእኮ ነው ያሰመሰሉት። “ብለዋል።
በወቅቱ ሀገሪቱን ይመራ የነበረው መንግሥት 55 ሰዎች በመረጋገጥ እና ጉድጓድ ውስጥ በመግባት ሞተዋል ያለ ቢሆንም፣ ሦስት ስማቸው ቢጠቀስ ለደህንነታችን ያሰጋናል ያሉ የቢሾፍቱ ሆስፒታል ሠራተኞች፣ የመንግሥት የደህንነት ኃይሎች ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ጋዜጠኞች እና ሌላ ማንም ቢጠይቃችሁ `የሞቱ ሰዎች ቁጥር 55 ነው፤ የሞታቸው ምክንያት ደግሞ ተረጋግጠው ነው` ብላችሁ መልሱ ስለመባላቸው ለሂውማን ራይትስ ዎች አጋልጠዋል።
ነዋሪነቱ ሻሸመኔ የሆነ የ21 ዓመት ወጣት የ2009 ኢሬቻን አስመልክቶ፡–“በበዓሉ ቦታ ስደርስ በፊት የማውቀው ኢሬቻ በዓል እና የማየው ኢሬቻ አንድ አልሆንብኝም። የወታደር መኪናዎች ሁሉም ቦታዎች ላይ ነበሩ። በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ ስጠጋ የኦሮሞ የበዓል ልብስ የለበሱ የደህንነት ሰራተኞች ሰዎችን እያሰሩ ሲወሰዱ አየሁ። ተራ ልብስ የለበሱ ደህንነቶችም ሰዎችን ሲያሰሩ አይቻለሁ። የኢሬቻ ጠቅላላ መንፈስ በቦታው አልነበረም። የሆነ የፖለቲካ ስብሰባ ነበር የሚመስለው እንጂ ባህላዊ ወይንም ሃይማኖታዊ በዓል አይመሰልም ነበር።“ ማለቱን ለሂወማን ራይትስ ዎች በወቅቱ ገልጿል።
በ2009 ኢሬቻ በዓል ላይ የሞቱትንም ሰዎች አስመልክቶ ሂውማን ራይትስ ዎች መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ስለተጠቀሙት አግባብ ያልሆነ ኃይል ገለልተኛ የሆነ አጣሪ እንዲያቋቁም፣ ቤተሰቦች ስለጠፉባቸው፣ ስለሞቱባቸው የቤተሰቦቻቸው አባላት አግባብ የሆነ መረጃ እንዲሰጣቸው እንዲሁም በዓሉን ለማክበር በቦታው ስለተገኙ ብቻ ወይም በበዓሉ ላይ በነፃነት የመናገር መብታቸውን ስለተጠቀሙ ብቻ የተከሰሱ እና የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱና ክሳቸውም እንዲነሳ ጠይቋል።
የሆነ ሆኖ መንግሥት ከበዓሉ በኋላ በሰጠው ማስተባበያ ሟቾች የሞቱት በተተኮሰባቸው ጥይት ሳይሆን በተፈጠረ ትርምስ መሆኑን ለማስረዳት ሞክሯል። ነገር ግን ይህ ማስተባበያ ብዙም ችግሩን ሊደብቀው አልቻለም። እንዲያውም በተቃራኒው ሕዝብን በማስቆጣት ተቃውሞው እንዲጠነክር አድርጓል። ከዓመት በኋላም በ2010 መጋቢት ላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መስመርን የቀየረ ለውጥ እንዲከሰት የራሱን ሚና ተጫውቷል።
በአሁኑ ወቅት የኢሬቻ በዓል ከቢሾፍቱ ባለፈ በአዲስ አበባም በድምቀት መከበር ጀምሯል። በዓሉ ጥንትም በአዲስ አበባ ይከበር እንደነበር ይገለጻል። ከብዙ ዘመናት በኋላ ነው በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ በሚል መከበር የጀመረው ከ2011 አንስቶ ነው። ይህም ሁኔታ በዓሉ ከኦሮሞ ሕዝብ ሀብትነት ወደ መላው ኢትዮጵያውያን ሀብትነት እንዲሸጋገርም እያደረገ ነው። በዓሉን በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ለማስመዝገብ የተለያዩ ሰነዶች ተዘጋጀተው እየተሰራ ይገኛል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2014