ምርጫ 2013ን ተከትሎ የመንግሥት ምስረታ ዋዜማ ላይ እንገኛለን። ከበረከቱ ሀገራዊ ጉዳዮች ውስጥ የመንግሥት ምስረታው ቀዳሚው ሰሞነኛ ትኩረት ሆኗል። አሸናፊው ፓርቲ ተፎካካሪዎችን አብረው እንዲሰሩ ስልጣን በመስጠት ያሳየው አዲስ ባህል እንዲሁ ትኩረትን የሳበ ሰሞነኛ አጀንዳ ነው። ሹመት የተሰጣቸውና የተቀበሉት ስማቸው በምክር ቤቶቹ እየተሰማ እከሌ ተሾመ፤ እከሌ ባለበት ቆየ፤ እከሌ ከቦታው ተነሳ ወዘተ የሚለው ወሬ በድምቀት እየተሰማ ነው።
ምክርቤቶቹ ተከፍተው የክልል መስተዳድራቸውን መርጠው፤ የተመረጠው ደግሞ ካቢኒውን እየመረጠ በመቀበልና በመስጠት ውስጥ ቀናቱ እየተገለጡ ነው። ተቀባዩ ሰጪው ሲሆን እያየን ነው። ለምሣሌ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ስልጣን የተሰጣቸው ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከንቲባነትን ከምክርቤቱ ተቀብለው፤ እርሳቸው ደግሞ ለካቢናቸው አባላት ሹመትን ሰጡ። መቀበል መስጠት። ቀድሞ መቀበል፤ ከእዚያ መስጠት። የተሰጠው ደግሞ አንዳች ነገር ሊሰጥ ሃላፊነትን መቀበል።
የዛሬውን ጽሁፍ ከገጠር መጥተው አዲስ አበባ ላይ በከተሙ ሁሉ ወንድማማቾቹ ወግ እንጀምር። ወንድማማች ናቸው፤ አብረው የሚኖሩ። ከገጠር ቀድሞ የወጣው ታላቅ ወንድም የአዲስ አበባን ገባ ወጣ ከለመደ በኋላ ተከታይ ወንድሙን አስክትሏል። ወንድማማቾቹ ኑሮን ለማሸነፍ ማለዳ ተነስተው በየመስካቸው ሲሰሩ ቆይተው ማምሻውን ወደ ጠባቧ ቤታቸው ይመለሳሉ። ቤት ውስጥ ካለው ንብረት ውስጥ ትልቅ ዋጋ የሚያወጣው አባታቸው የሰጣቸው የድሮ ቴፕ ነው።
ታላቅየው ማምሻቸውን ጣቢያ እየቀያየረ ሬድዮን የመስማት ልማድ አለው። ታናሽየውም በጊዜ ሂደት የምሽት ራዲዮን ደንበኛ ነው። የራዲዮ ሰዓት አብቅቶ ወደ መኝታ ሲሄዱ የእለቱ ማጠናቀቂያ የታላቅ ወንድሙ ንግግር ይደመጣል፤ እርሱም “የዛሬው ዜናን እንደተለመደው ስንሰበስበው መቀበልና መስጠት ነው” ይላል። መቀበልና መስጠት ሳይል በፍጹም ቀኑን ዘግቶ አያውቅም። ታናሽ ወንድሙም የእለቱን መደበኛ መርሃግብር መጠናቀቁን እና የእንቅልፍ ኮሪደር ላይ መድረሱን የሚያውቀው የታላቅ ወንድሙን መቀበልና መስጠትን ሲሰማ ነው።
ሁለቱ ወንድማማቾች በአንዱ የእረፍት ቀናቸው ስለ መቀበልና መስጠት እያወሩ የእግር ጉዞ እያደረጉ ነው። ታናሽዬው “ጋሼ” አለ። ታላቅ ወንድሙን ጋሼ ብሎ ነው የሚጠራው። “አቤት” ሲል መለሰለት። “በምድር ላይ ያለው መሰረታዊ ችግር ምን ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው። ታላቅ ወንድምም ለአፍታ ከራሱ ጋር ከተማከረ በኋላ ንግግሩን ጀመረ “ወንድሜ ጥያቄህ ቀላልም ከባድም ጥያቄ ነው። ቀላል የሚሆነው በእኔ ዙሪያ ያሉ ችግሮች መሰረታዊ ምክንያታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አስቤ በቀላሉ መመለስ ስለምችል ነው። ጥያቄህ ግን በምድር ላይ ያለውን ሁሉ ስለሆነ ደግሞ ድምዳሜ መስጠት አስቸጋሪ ይሆናል። በእኛ ዙሪያ የምናየው ችግርን ለሁሉም አባዝተን እንየው ካልከኝ በቀላሉ ልመልስልህ እችላለሁ። እርሱም የመቀበልና መስጠት መዘናፍ ነው።” ሲል መለሰ። “ምን ማለት ነው ወንድም ጋሼ?” ሲል አቋረጠው። ወንድም ጋሼም ምላሹን ቀጠለ፡፡
“ሁሌ ዜና ስንሰማ እንደምነግርህ በሁሉም ዜና ውስጥ መቀበልና መስጠት አለ። መቀበልና መስጠት ሚዛናዊ በሆነ ጊዜ ነገሮች መስመር ይዘው ይሄዳሉ፤ ፍትሃዊነትም ያብባል። ሚዛን በተዛነፈ ጊዜ ደግሞ ቀውስን ያመጣል። መቀበል ብቻ ላይ ስናተኩር፤ ወይንም መስጠትን ብቻ ግብ ስናደርግ ህይወት ሚዛን ትስታለች። ህይወት ሚዛን ስትስት ደግሞ አላስፈላጊ ኪሳራ ውስጥ ይከተናል። የህይወት ኪሳራ ለእኔ የመቀበልና የመስጠት ልዩነት ነው።
የተቀበልከውን ይዘህ የማትሰጠው ከሆነ አንተ ጋር ሁሉን ሰብስብህ በሰበሰብከው ነገር ትጠፋለህ። መስጠትን ብቻ ትኩረት ስታደርግ ደግሞ ምንም እስከማይኖርህ ድረስ ትደርስና አንተም ትጠፋለህ። ለምሳሌ የአከራያችን ቤተሰብ ለምን እንደሚታመስ ታውቃለህ? አባት ለቤተሰቡ መስጠት የሚገባውን የወር አስቤዛ ወጪ ለመስጠት ግልጽነት ስለጎደላቸው ነው። አባት ከቤተሰቡ በላይ ሊቀርበው የሚገባ ባልኖረው ነበር። ነገር ግን ቤተሰቡን እያስራበ በውጭ ግን ደግነት ያበዛል ብለው የቤተሰቡ አባላት ያዝኑበታል። ይህ የተዛባ የመስጠት ህይወት ነው።
እኛ መስሪያቤት አለቃዬና አንዱ ጓደኛዬ ሰሞኑን የመረረ ጥል ውስጥ ናቸው። የተጣሉበትም ምክንያት በጊዜ ማድረስ የሚገባውን ስራ በተደጋጋሚ ማድረስ ባለመቻሉ ነው። አሰሪዬ ደሞዝ እየሰጠ፤ ከሰራተኛው መቀበል የሚገባውን ካላገኘ ችግሩ ይፈጠራል። መፍትሄው የመቀበልና መስጠትን ሚዛን መጠበቅ ነው የምልህ ለእዚህ ነው።
እኔም አንተን አዲስ አበባ ሳመጣህ ሌሎች ወንድሞቼም ሆኑ እህቶቼ ያንን ይፈልጋሉ ነገር ግን አሁን በእኔ ገቢ በተከራዮቼ ማኖር የምችለው አንድ ሰው ነው ስለእዚህ አንተን አመጣሁ። በግብታዊነት ሁሉንም ወንድሞቼንና እህቶቼን ባመጣ ሁላችንም መሰረት ሳንይዝ ችግር ውስጥ እንገባለን። ሕይወት ሚዛንን መጠበቅን ትፈልጋለች የምልህ ለእዚህ ነው። ይህም ሚዛን በመቀበልና በመስጠት ውስጥ የተቃኘ ነው።
ዜናው ሁሉ መቀበልና መስጠትን ያሳያል። ለመቀበል በመስጠት የተቃኘ የመቀበል ልብ ያስፈልጋል፤ ለመስጠት ደግሞ በመቀበል የተቃኘ የመስጠት ልብ ያስፈልጋል። ሕይወትን በመቀበል ነው የጀመርነው። እያንዳንዳችን እንደ ግለሰብ ለመጸነሳችን ሆነ ለዘጠኝ ወራት በእናታችን ማህጸን ውስጥ ለመቆየታችን ያደረግነው አስተዋጾ የለም። ከተወለድንም በኋላ በእናታችን ጡት በኩል ምግብ ለማግኘት ውል ያሰርነው ነገር የለም። ከአምላክ በመቀበል ሕይወትን ጀምረናል፤ ከእርሱ ለመቀበል በመጠበቅ ነገር ግን ምንም ባለመስጠት ሕይወትን እንቀጥል ብንል ግን አይሆንም። የእናታችንም ጡት ይደርቃል በራሳችን የምንመገበውን መፈለግ ይኖርብናል። እርሱም በመስጠት ውስጥ ይገኛል። ጉልበታችንን እውቀታችንን ሰጥተን ሥራ ሰርተን የምንቀበል እንሆናለን። በምድር ላይ አቅም አለው የምንለው ሰው ሁሉ ተቀባይ ነው፤ ደግሞም ሰጪ።”
መስጠት
መቀበል ከመስጠት ቢቀድም፤ የመስጠት ልብ ከመቀበል በፊት ያስፈልጋል። ለመስጠት አስቦ መቀበልን ማድረግ ጤናማ መቀበል ስለሚሆን መስጠትን አስቀድመን እናንሳ።
በእያንዳንዱ ቀን ውስጥ እየሰጠን የሆነውን ነገር እንመርምር። ለቤተሰብ ፍቅርን መስጠት፣ ለራሳችን ጊዜ መስጠት፣ ሥራችንን በአግባቡ በመስራት መስጠት፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች የምናጋራውን ይዘት በጥንቃቄ መርጦ በማጋራት መስጠት፣ በተሳፈርንበት የህዝብ ተሽከርካሪ በሚገባ ባህሪ በመገኘት መስጠት፣ ሚስጥርን በመጠበቅ መስጠት ወዘተ።
መቀበል የሚችል ሁሉ መስጠት ይችላል። የመቀበልና የመስጠት ጊዜ የሚለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለዓመታት የተቀበልነውን ለዓመታት ልንሰጥ ወይንም ለዓመታት የተቀበልነው በጥቂት ቀናት ልንሰጥ እንችላለን። ዋናው ቁምነገር ለመስጠት ዝግጁ በሆነ ልብ ውስጥ መመላለሳችን ነው።
ሕይወት በመስጠት ውስጥ ትርጉም እንዳላት በመስጠት ውስጥ ታሪካቸው ልባችንን የተቆጣጠሩትን ማሰብ ነው። በመቀበል ተጽእኖን ማሳደር አይቻልም፤ በመስጠት እንጂ። እራሳቸው ላይ ትኩረት አድርገው ከአንድ ትምህርት ወደ ሌላ ትምህርት እየተሸጋገሩ እድሜ ልካቸውን ትምህርትን ፍለጋ የሚተጉ ግለሰቦች አሉ። ልናደንቃቸው ይገባል። ነገር ግን ግን የተቀበሉትን ለመስጠት ምን ያህል ጊዜያቸውን አውለውታል የሚለውን አብረን ማሰብም ይኖርብናል።
የመስጠት አስፈላጊነት ተቀብለን ለምናውቅ ሁሉ ግልጽ ነው። ሰዎች አክብረው ሲቀበሉን ምን ይሰማናል? ሃዘን ወይንስ ደስታ። ጥርጥር የለውም ምላሹ ደስታ ነው። ይህን ደስታ እኛም ለሌላው ልናጋራ እንደሚገባ ማመን አለብን። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የምንሰጠው ነገር እንዳለ ማመን አለብን። ሕግን አክብሮ ስራን ከመስራት እስከ ለእምነታችን መሰደድ ድረስ የመስጠት ህይወት የእኛነታችን መገለጫ ሊሆን ይገባል።
ኢትዮጵያውያን እስከአሁን ድረስ የሚያወሩት ደግሞም የሚዘምሩለት የአድዋ ድል መነሻው መስጠት ነው። የአሁኑ ትውልድ የተቀበለው የነጻነት መንፈስ ሕይወታቸውን በሰጡት ቀደምት የሀገሪቱ ዜጎች የተገኘ ነው። ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ከእንቅልፍ ጋር እየታገሉ በቀን በለሊት የሚተጉት የህክምና ሰዎች እየሰጡት ያለው አገልግሎት ትርጉም የሚሰጠን እነርሱን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስናገኝ ነው። “ጥበቡ የምድረበዳው እረኛ” በተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለአስራ አንድ ዓመታት ራሱን ለሌሎች የሰጠን ዶ/ር ጥበቡ ኃ/ስላሴ የተባለን የሕክምና ሰው እናገኛለን። መጽሐፉን በማንበብ እንዴት ባለ አስቸጋሪ ዓመታት ውስጥ በመስጠት ሕይወትን እንደኖረ መረዳት እንችላለን።
የመስጠትን ህይወት በምናስብበት ጊዜ መርህ ልናደርጋቸው የሚገቡ ሦስት ነጥቦችን እናንሳ፣
1ኛ፡- መስጠት ማንም መቀበል የሚችል ሁሉ ሊያደርገው የሚችል ነው። በሕይወት ያለህ ሰው ነህ፤ እንግዲያውስ መስጠት የምትችለው ብዙ ነገር አለ። ለማን ምን መስጠት እችላለሁ ብለን በመጠየቅ ሕይወታችን በሌሎች ሕይወት ውስጥ መልካም ተጽእኖን የሚፈጥር ልናደርገው እንችላለን። ባለንበት ዘመን አይደለም በሕይወት ያለ ሰው የሞተ ሰው እንኳን የዓይን ብሌኑን አስቀድሞ ከተናዘዘ በሞቱ ጊዜ መስጠት የሚችል ነው። ሁላችንም መስጠት የምንችለው ነገር አለ። መስጠት የምንችለውን ነገር አውቀን ለመንቀሳቀስ መሞከር ከእኛ ይጠበቃል። በመስጠት ውስጥ ደግሞ ፍሬን እናፈራለን። እርሱም መልካም ፍሬ ነው።
2ኛ፡- መስጠት መቻል የምንቀበለውን ያበዛዋል። ደንበኛ ተኮር ሆነው፣ የደንበኛን ችግር ለመፍታት በመስጠት ልብ ንግዳቸውን የሚያሳልጡ በምትኩ የሚቀበሉት አላቸው። በኢኮኖሚክስ ሰራተኛ በጉልበቱ ክፍያ፤ ኢንተርፕሪነሮች ደግሞ በትርፍ መልክ ክፍያቸውን እንደሚያገኙ ያስተምራል። በመስጠት ቅኝት የተያዙ ደንበኞች ደግሞ ይባዛሉ። የነጋዴው ሥራም ከአንድ ቅርንጫፍ ወደ ሌላ ቅርንጫፍ ይሰፋል። መስጠት መቻል መክሰር አይደለም። ነገ የምንቀበለውን ዛሬ ላይ ማዘጋጀት መቻል እንጂ። ለደሃ የሰጠ እንኳን ለእግዚአብሔር እንዳበደረ ነውና። በብዙ አይነት መንገድ የሚከፈል ብድር።
3ኛ፡- መስጠት በአስተውሎት ካልሆነ መባከን ይሆናል። አስተውሎት በጎደለው ሁኔታ ያለንን መበተን እርሱ መስጠት አይደለም። ሁሉም ነገር ሚዛንና አስተውሎት ይገባዋል። አቅማችንን ያለቦታው መስጠት እንዲሁ በአስተውሎት ያልሆነ መስጠት ነው። ከዶክተሮች ሁሉ የተለየ በአንድ ዘርፍ በልዩ ሁኔታ ትምህርትን ያደረገ ሰው የባለሙያ እጥረት ባለበት የእርሱ ግን ሙያ በሆነው ላይ አተኩሮ ከመስራት ወጥቶ እንዲሁ በመስጠት ስሌት ሁሉንም ነገር ልስራ ቢል ውጤታማ ሊሆን አይችልም፤ መባከን እንጂ።
ብዙ ወዳጅ አፍርቶ የጊዜ ሰሌዳችንን በሙሉ በማህበራዊ ኑሮ መሙላት እንዲሁ ውጤቱ ብክነት ሊሆን ይችላል። ዘመደ ብዙ … ተብሎ እንደሚተረተው። በመሆኑም መስጠት በአስተውሎት ካልሆነ መባከን ነውና ከመባከን ለመዳን መስጠት በአስተውሎት መሆን አለበት።
መቀበል
በእናትና ልጅ፣ በባልና ሚስት፣ በወንድምና እህት፣ በአሰሪና ሰራተኛ፣ በመሪና ተመሪ፣ በሰባኪና ምእመናን ወዘተ መካከል የመስጠትና መቀበል፤ የመቀበልና መስጠት ተጨባጭ ክንውን አለ። በሁለቱም አካላት መካከል መቀበልም አለ ሰጪነትም አለ። የእናቱን ጡት እየጠባ ያደገው ልጅ አድጎ ለእናቱ ደጀን ሆኖ ይገኛል፤ እዚያም ሳይድረስ መስጠቱ በብዙ ነገር ይገለጣል።
ተማሪው ወደ ተማሪ ቤት የሚያቀናው ሊቀበል ነው፤ መምህሩ ደግሞ ሊሰጥ። መምህሩ ለተማሪው የሚሰጠው ይኖረው ዘንድ ወደ መምህራን ማሰልጠኛ የሄደው ሊቀበል ነበር፤ ያስተማረው መምህር ደግሞ ሊሰጥ። ማንም ከመቀበል መስጠት ጋብቻ ሊያመልጥ እንደማይችል በዙሪያችን ያሉ ሁሉ ይመሰክራሉ።
ስለ መቀበል ለብቻው እንመልከት። መቀበልንም በመርህ ማእቀፍ ውስጥ እንመልከት። በመቀበል እረገድ በበረታንበት ይበልጥ እንድንበረታ፤ በደከምንበት እንድናስተካከል ነጥቦችን እናንሳ። መቀበልን በተመለከተ በአጭሩ ቁልፍ አራት ነጥቦች አሉ።
1ኛ፡- መቀበል የደካማነት ምልክት አይደለም። አንዳንዶች የሚቀበሉ ሰዎችን ደካሞች ስለሆኑ አድርገው ያስባሉ፤ ይህ ስህተት ነው። በስንፍናቸው ምክንያት ኑሯቸውን ለመቀበል ብቻ መድበው የሚመላለሱ ሊኖሩ ይችላሉ። እነርሱን ማለታችን አይደለም። በጥቅሉ መቀበልን ከደካማነት ጋር ማነጻጸር ተገቢ አለመሆኑን ለማንሳት እንጂ።
ህጻን ከእናት የሚቀበለው ደካማ ስለሆነ አይደለም፤ የሚሰጥ ይሆን ዘንድ መሰራት ስላለበት ነው። የቅርብ አለቃ ያስፈለገን ደካማ ስለሆንን አይደለም ስራ በስርዓት ይመራ ዘንድ የሃላፊነት ክፍፍል ስለሚያስፈልግ እንጂ። ለመሆኑ ማን አለ በስራው ላይ የሚጠይቅ የበላይ የሌለው? ማንም። ከእግዚአብሔር በስተቀር። የትኛውም አይነት ሰጪነት በውስንነት እንዲሁም መቀበል መቻልም እንዲያው ነው።
2ኛ፡- መቀበል የእድገት በር ነው። ማደግ ትፈልጋለሁ፤ እንግዲያውስ ለመቀበል ዝግጁ ሁን። የአባትን ምክር ተቀበል፣ የእናትን ተግሳጽ ችላ አትበል፣ የአለቃን ትእዛዝ ተቀበል፣ የመምህርህን ትምህርት ተቀበል፣ የህክምና አገልግሎት ሰጪውን አመስግን፣ የእድር ዳኛው እየሰጠህ ላለው አገልግሎት ቦታ ይኑርህ ወዘተ። በመቀበል ውስጥ ማደግ አለ፤ በማደግ ውስጥ ደግሞ ወደ መስጠት መድረስ አለ።
ስንፍናን ለመሸፈን ተብሎ በስርቆትም ሆነ ባልተገባ መንገድ እጃችን የሚገባን ማንኛውንም ነገር እያልን እንዳይደለ ግንዛቤ ያሻል። መቀበል የእድገት በር ነውና በበሩ በኩል እለፍ። ለመቀበል ጊዜ ስጥ፤ ለመስጠት ተዘጋጅ።
3ኛ፡- መቀበል በመስጠት ልብ ሊቃኝ ይገባዋል። መቀበል እኛ ጋር አስቀምጠን ለራሳችን በሰራነው አጥር ውስጥ ከሆነ ኪሳራ ነው። ፍሬ የሌለባት በለስን ማን ሊንከባከባት ይደክማል። ፍሬ የማይገኝበት ተማሪ ላይ መምህሩ እንዴት ቅሬታ አይግባው። የመምህር ደሞዙ የዘራው የትምህርት ፍሬ አፍርቶ ትውልድ ሲቀረጽ መሆኑን ማን ያጣዋል። መቀበል በመስጠት ልብ ይቃኝ ዘንድ ዘወትር ሊታሰብ ይገባዋል።
ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆኑ ለመቀበል ብቻ የደከሙ መጨረሻቸው እንደማንኛውም ሰው በጠባቡ ጉድጓድ ውስጥ ነው። እኒህ ሰዎች ለሌላው ከመቆረስ በራሳቸው ዙሪያ ቁሳቁስ ሰብሰበው በጠራራ ጸሃይ ሌላ ሙቀት ጨምረው ሕይወትን ጣእም አልባ አድርገው ፍጻሜያቸው በመንገዳቸው የተቀረጸ ይሆናል። በሃጥእ አትቅና፤ ሃጥእ ስለ መስጠት ሳይሆን ስለ መቀበል ብቻ የሚኖር ነው። የሚቀበለውም መታነጽን በማይሆንለት ለመስጠት ህይወት በማያገናኘው መንገድ ነውና። ስለሆነም መቀበልህ በመስጠት ልብ ቅኝት ውስጥ መሆኑን እርግጠኛ ሁን።
4ኛ፡- መቀበል ዝቅ ማለትን ይጠይቃል። አጠገባችን ያለ ሰው ሁሉ ትምህርት ቤት ነው። ገንዘብ መቀበል አትችል ይሆናል፤ ቁሳቁስ በስምህ አያዞር ይሆናል ነገር ግን አጠገብህ ያለው ሰው ከተጓዘው የትናንት ጉዞ ለአንተ ነገር የሚሆን ትምህርት ግን ልታገኝበት ትችላለህ። ከሰነፍ ሰው እንኳን አንተ ጠቢብ ከሆነ እውቀትን ታገኛለህ። የስንፍናው መጠን ሰነፍ ምን ያህል በስንፍና እርቀት ላይ ሊያደርስ እንደሚችል ትመለከታለህ።
ባሎች ሆይ ከሚስቶች ፍቅርን ተቀበሉ፤ ይህ ፍቅር ግን እናንተ በሰጣችሁት ፍቅር ልክ ጣፋጭ ነው። ልጆች ሆይ ከቤተሰቦቻችሁ ፍቅርን ተቀበሉ፤ ይህ ፍቅር ግን እናንተ በሰጣችሁት ፍቅር ልክ ውብ ነው። ለሁላችንም ስሌቱ ያው ነው። በመስጠት ውስጥ መቀበል ይዘራል፤ በመቀበል ውስጥ መስጠት ይጸነሳል።
ትኩረታችን የምንቀበለው ላይ ብቻ አይሁን። አሁን ምን መስጠት እንደምንችል እናስብ። አያሌ ነገሮችን በማንኛውም ቦታ መስጠት እንችላለን። እንስጥ ደጋግመን እንስጥ በቀጥታም ባይሆን በሌላ መንገድ እንቀበላለን። ይቅር ያለ ይቅር ይባላል፤ መለኮታዊ ይቅርታን አልፈልግም ቢል እንኳን ጤንነቱን የውስጥ እረፍቱን ይቀበላል። እንስጥ! በህይወት መኖራችን ብቻ ለመስጠት ብቁ ያደርገናልና።
የሕይወት ወቅቶች አሉ፤ መስጠት እየፈለገን መስጠት የማንችልበት። የሕይወት ወቅቶች አሉ፤ መቀበል ፈልገን የማንቀበልበት። ምን አይነት ወቅት ይሆን? እንዴትስ እንለፈው?
መስጠት በማንችልበት ጊዜ
በሕይወት ጉዞ ውስጥ የስሜት መዋዠቅ ከሚፈጥሩ ክስተቶች መካከል የመስጠት ህይወታችን አንዱ ነው። እናት ልጇን የምትመግበው በማጣቷ የተነሳ ህይወቷን ለማጥፋት መወሰኗን ከዜና አውታሮች ሰምተን አዝነናል። ተመሳሳይ አይነት አሳዛኝ ክስተትን መስማት የተለመደ ነው። መስጠት የሚገባን ሆኖ ሳለ መስጠት የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ስንገባ የሚፈጠረውን መቃወስ እንዴት መግታት እንደሚገባን ማሰብ ይኖርብናል።
ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ቤተሰብን መርዳት እንዳለበት የሚያምን ምሩቅ የሚፈጠርበት ስሜት እንዲሁም መስጠት እየፈለግን መስጠት አለመቻል ውስጥ ያለውን የሥነ-ልቦና ጫና መመልከት እንችላለን። አባትና እናት ለልጆች፣ ልጆች ለቤተሰቦች፣ ታላቅ ወንድም ለታናሾች፣ ታላቅ እህት ለታናሾች፣ ወዘተ ይህ ስሜት ይፈጠራል።
ይህን በመሰለ የሥነ-ልቦና ውጥረት ውስጥ ላሉ ሰዎች መስጠትና መቀበልናን በልዩ ሁኔታ መመልከት አለበት። መስጠት በማንችልበት ጊዜ ውስጥ ስንሆን መፍትሔው ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ሌሎች መስጠት የምንችላቸውን ለመስጠት ጥረት ማድረግ ነው። እናት ልጇን ልትመግብ ሳትችል ስትቀር የሚፈጥርባት ተጽእኖን ለመግታት ለልጇ ብላ መንገድ ብትወጣ ማድረግ የምትችለው ተግባር ነው። ይህ ቀላል ውሳኔ አይደለም ነገር ግን ራስን ከማጥፋት የተሻለው ነው። ከእዚያ መለስ ልጇን ለማደጎ ለመስጠት መሞከር በአቅራቢያዋ ያሉ ቤተሰቦችን እገዛ መጠየቅ ወዘተ አማራጭ መንገድ አለ። መስጠት በማንችልበት ጊዜ ክብራችንን ጥለን መስጠት የምንችለውን መፈለግ የተሻለው መንገድ ነው።
የዩኒቨርሲቲ ምሩቁ የሚጠብቀውን ሥራ ማግኘት ባልቻለ ጊዜ የማይጠብቀውን ሥራ ለመስራት ውሳኔ ላይ መድረስ አለበት። በተመረቀበት ሙያ ሥራን እስኪያገኝ ድረስ መስራት የሚችለውን ማንኛውንም ስራ በመስራት የመስጠት ህይወትን ሊኖር ይችላል። ባለ ዲግሪ ተብሎ የተነገረለት ሰው እቃ ተሸካሚ ቢሆን ሊከብደው ይችላል። እቃ ተሸክሞ፣ ጫማ ጠርጎ፣ ጥበቃ ሆኖ ወዘተ መስራት የማይጠብቀው ነው።
ዛሬ ላይ ባለዲግሪ ሆነው የቀን ሥራ የሚሰሩ አሉ። ዛሬ ላይ ባለዲግሪ ሆነው የትራፊክ አስተናባሪ የሆኑ አሉ፤ በሌላም አስቀድመው ባልጠበቁት ሥራ ላይ የተሰማሩ። መስጠት እየፈለገ መስጠት አለመቻል ወደ ውድቀት ሳይሆን ወደ ሌሎች የመስጠት አማራጮች መሄድን የሚጋብዝ መሆን አለበት። ሕይወትን በመጋፈጥ እንጂ በመሸነፍ ትርጉሟን ማግኘት ስለማይቻል።
መቀበል በማንችልበት ጊዜ
መቀበል እንደሚገባን የምናስበው ነገር ግን እንደምናስበው መቀበል ያልቻልንበት ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል። ልጅ ከአባትና እናት ማግኘት እንዳለበት የሚያስበው ነገር ግን በተጨባጭ ያላገኘው ነገር ወደ ቤተሰብ ግጭት ይወስዳል። ታዳጊዎች እንዲሁም ወጣቶች በመሰል ቤተሰባዊ ግጭት ውስጥ የበረከተ አሉታዊ ተጽእኖዎች ሲፈጠሩ እንመለከታለን። እንዲህ በሚሆንበት መንገድ ጊዜ መፍትሔው እኔ ያላየሁት በሌላኛው ወገን ጫማ ምን ይመስላል ብሎ መመልከት መቻል ነው።
በህመም ላይ መመገብ የሚገባውን ያህል መመገብ ያልቻለ እንዲሁ መቀበል እየተገባው መቀበል ያልቻለ ነው። ተመሳሳይ ክስተቶች በተለያዩ መንገዶች ያጋጥማል። መፍትሄው በሌላኛው ሰው ጫማ ውስጥ ሆኖ መመልከት፣ የደረሰውን እውነታ መቀበል ወዘተ ነው።
ወደማሳረጊያው እንምጣ እውቁ አልበርት አንስታይን እንዲህ አለ “The value of a man resides in what he gives”። መስጠት ውስጥ የሰውነታችን ዋጋ መኖሩን የሚያሳይ። ለመስጠት ደግሞ መቀበል። መቀበል በመስጠት ልብ። በሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት እንጨርስ “የሚመክርም ቢሆን በምክሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር::”
ሠናይ የመቀበልና መስጠት ጊዜ። አሁኑኑ በየትኛውም ቦታ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014