ከወራት ሁሉ እንደ መስከረም ስሙ ተደጋግሞ የሚጠራ ወር ይኖር ይሆን ? አይመስለኝም። ሌሎቹ ወራት የሚጠሩት በራሳቸው ወር ውስጥ ነው። ከዚያ ባለፈ ደግሞ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ሊነሱ ይችላሉ።
መስከረምን የምንጠራው ግን በመስከረም ወር ብቻ አይደለም፤ ዓመቱን ሙሉ የምንጠራበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በእርግጥ የሰኔ ወር ትንሽ ሳይፎካከረው አይቀርም። ምናልባት ሁለቱን ስመ ጥር እንዲሆኑ ያደረጋቸው የክረምት ወር መግቢያና መውጫ ስለሆኑ ይሆን? በሌላ በኩል ደግሞ ለተማሪ ሁለቱም ወሮች ልዩ ስሜት አላቸው። የሰኔ ወር ተማሪ የሚለያይበት፤ የመስከረም ወር ደግሞ ተማሪ የሚገናኝበት ነው።
በተለይ ጎበዝ ተማሪ መስከረምን በጣም የሚወደው ሲሆን ሰነፍ ተማሪ ደግሞ ሰኔ ወርን ይወደዋል (አባባሉ እኮ ግን ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል ነበር)። እኔ ግን የመስከረም ወርን ነበር የምወዳው፤ ጎበዝ ተማሪ ሆኜ አይደለም፤ የምወዳት የትምህርት ቤታችን (ኧረ የክፍላችን) ልጅ ስለነበረች ነው።
እንዲያውም ሰነፍም ስለነበርኩ ነው፤ ማለቴ የግብርና ሥራ ላይ ሰነፍ ስለሆንኩ ከዚያም ለመገላገል ጭምር ነው። ለሰነፍም ይሁን ለጎበዝ መስከረም በተማሪ አፍ ተደጋግሞ ይጠራል። ይሄ ነገር በተማሪ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ለመንግስት ሰራተኛውም ሆነ ለግል ሰራተኛው የሰኔ እና የመስከረም ወር የተለየ ቦታ አላቸው፤ ለመንግስትም እንደዚያው ነው። ለገበሬውም የተለየ ቦታ አላቸው። ስለዚህ ሰኔ እና መስከረም ስመ ጥር ናቸው ማለት ነው። ስመ ጥር ማለት ግን ዝነኛ ማለት ነው አይደል?(ዝና ለአርቲስት ብቻ ነው ያለው ማነው?)
መስከረም ግን ለምን ስመጥር ሆነ?
በበጋም በክረምትም እኮ ስሙን እንጠራዋለን። ለምሳሌ በአባባል እንኳን ብንሄድ ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም፣ ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ፣ መስከረም በአበባው ሰርግ በጭብጨባው፣
የመስከረም ዝናብ ከላም ቀንድ ይለያል…›› ከቃል ግጥሞችም ይሄን እንጥቀስ፤
ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፤
ወፍጮውም ሲያጋምር መስከረም ዘለቀ።
መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ
እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ።
አባባ እገሌ የሰጠኝ ሙክት
ከግንባሩ ላይ አለው ምልክት
መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት።……………የሚሉ ስነ ቃሎች አሉ። በሰው ስም ከሄድንም ብዙ መስከረም የሚባሉ ሰዎች አሉ። ሴቶች ቢበዙም መስከረም የሚባሉ ወንዶችም አሉ።
መስከረም ግን የጥበብ ምንጭም ነው ልበል? ለነገሩ ባይሆን ነበር የሚገርመው፤ የልቦለድ ጽሑፎች መጀመሪያ እኮ ከተራራ፣ ከሰማይና ከወንዝ ርቆ አይርቅም፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ መስከረም ላይ ያምራሉ። መስከረም በስሙ እኮ ብዙ ግጥም አለ፤ የገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹ደስ ይላል መስከረም››ን ልብ ይሏል። ዘፈንማ ስንቱ ይቆጠራል? እንዲያውም የበዓል ሰሞንም ስለሆነ ዘፈን እንገባበዝ። መጀመሪያ የጥላሁን ገሠሠን፤
ክረምት አልፎ መስከረም ሲጠባ
የኔ ቆንጆ ተጊጣ ተውባ
አምራ ደምቃ በአበቦች ታጅባ
ያቻትና መጣች ውብ አበባ።
ቆይ ቆይ አንድማ ያጣላል፤ መቼስ የበዓል ሰሞን አይደል? እነሆ የሀመልማል አባተን፤
የክረምቱ ወር አልፎ ለበጋው ለቋል
ሜዳው፣ ሸንተረር ጋራው በአበቦች ደምቋል
ሸሞንሟናዬ ውብ ሽቅርቅሩ
ድረስ በዓውዳመት በአገር መንደሩ
በወራት መጀመሪያ በአዲስ ዓመቱ መግቢያ
በል ፈጥነህ ድረስልኝ በዘመድ መሰበሰቢያ….።
በነገራችን ላይ መስከረም እንዲህ ስሙን እንድንደጋግመው ያደረገን በምክንያት ነው። አባባሎች እንኳን ራሳቸው ምክንያት አላቸው። ለምሳሌ ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› ይባላል። መስከረም
የአዲስ ዓመት መግቢያ ነው። እናም በዓመቱ ውስጥ የሆነ አስገራሚ ነገር መኖሩ ስለማይቀር ነው እንዲህ የተባለው፤ ይሄ አባባል ግን ዘንድሮ በጣም ይሰራል አይደል? እንዲያውም አባባሉን የፈለሰፉት አበው እንደባለፈው ዓመት አይነት አስገራሚ ነገር በበዛበት ዘመን መሆን አለበት። በእውነት የዘንድሮ መስከረም የጠባው እኮ ብዙ ጉድ አሰምቶን ነው።
‹‹ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ›› የተባለው
ደግሞ ለሰነፍ ገበሬ ነው። በሰኔ ገበሬ ትጉ መሆን አለበት። ሞኝ ከሆነ ግን ዝም ብሎ ይቀመጣል፤ ክረምቱ ካለፈ በኋላ መስከረም ላይ ቢነቃ ዋጋ የለውም፤ መስከረም ሰብል አምሮ የሚታይበትና እረፍት የሚገኝበት እንጂ ለዘር የሚሯሯጡበት አይደለም።
‹‹የመስከረም ዝናብ ከላም ቀንድ ይለያል›› የምትለዋ አባባል የዋዛ እንዳትመስላችሁ። ይሄ ደግሞ ለመስከረም ወር ዝናብ የተባለ ነው። የመስከረም ወር ዝናብ አንድ አካባቢ እየዘነበ ከሆነ ሌላ አካባቢ አይዘንብም፤ ለምሳሌ አራት ኪሎ እየዘነበ ፒያሳ ላይዘንብ ይችላል፤ ያው የላም ቀንድ የተጠጋጋ ነውና ለግነት የተጠቀሙት ነው።
‹‹ያረሰማ ጎበዝ…›› የተባለውም በምክንያት ነው። ያላረሰ ገበሬ ብዙ ጊዜ ክረምት ላይ ይቸገራል። ምክንያቱም ቀለቡ ከበጋ ወቅት አያልፍም፤ ክረምት ደግሞ ሥራ የሚሰራበት ወቅት ነው። ጎበዝ ገበሬ ግን በጋ ክረምት አይቸገርም፤ እናም ዓመቱን ሙሉ ከቤቱ ይጋገራል፣ ይቦካል፣ ይፈጫል፤ ለዚህ ነው ‹‹ወፍጮውም ሲያጋምር መስከረም ዘለቀ›› የሚባለው።
ሌሎች ወሮች እንግዲህ እንዳትቀየሙኝ፤ መስከረም ይደጋገማል አልኩ እንጂ ሁሉም ይጠራሉ። ሁሉም የሚታወቁበት አላቸው። ለምሳሌ ጥቅምት ብርዳማ ነው(ኧረ አሁኑ ጀምሯል)፣ ጥር የሰርግ ወቅት ነው (ስንደርስበት እናወራበታለን)።
በሉ እንግዲህ የበዓል ሰሞን ስለሆነ የምንሰናበተውም በዘፈን ነው(በሬዲዮ ጋዜጠኞች ቀናሁ መሰለኝ)። በአረጋኸኝ ወራሽ ዘፈን እንሰናበት!
እሰይ አበባው እሸቱ ደርሷል
ሰፈር መንደሩ አረንጓዴ ለብሷል
ገደል ሸለቆው ታጥሮ በአበባ
አደይ አበባ እንበል መስከረም ጠባ
የሰላም የፍቅር የፍሃ አዝመራ
ሸጋ ሸጋ ታብቅል እሰይ ምድር ታፍራ
የመከራ ዘመን ያዘን ስቃይ ያብቃ
ሀብት በመስከረም ይሄው ትታይ ደምቃ
መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ
ቤት ለእንቦሳ በሏት የልቤን እንግዳ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2014