የዚህ ሳምንት የሳምንቱ በታሪክ ትውስታችን በዚሁ ሳምንት ህይወታቸው ያለፈው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ከ83 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን መስከረም ዘጠኝ ቀን 1931 ዓ.ም ነበር። ይህንን ምክንያት በማድረግ እንዘክራቸዋለን።
ኅሩይ የተወለደው በ1871 ዓ.ም ሸዋ፣ መርሐ ቤቴ አውራጃ፣ በታች ቤት ወረዳ፣ ረመሸት ቀበሌ፣ ደን አቦ ገዳም በተባለ ሥፍራ ነው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከነበሩት የወቅቱ የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ተመስክሮላቸዋል።
ወላጆቹ ያወጡለት ስም ገብረመስቀል ነበር። ገብረ መስቀል እንጦጦ ራጉኤል ደብር መጥቶ የመጻሕፍትን ትርጓሜ ከደብሩ ሊቃውንት በሚማርበት ወቅት ወልደጊዮርጊስ የተባሉት መምህሩ ‹‹ጎንደር በነበርኩ ጊዜ መምህሬ ስለሚወዱኝ ‹ኅሩይ› እያሉ ይጠሩኝ ነበር። ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ግን በዚህ ስም እየተጠራሁኝ አይደለም። አንተ የቀለም ቀንድ ስለሆንክና በምግባርህም የተወደድክ ስለሆንክ ‹ኅሩይ› የተባለውን ስሜን ትጠራበት ዘንድ ሸልሜሃለሁ›› አሉት፤ እርሱም ስሙን በደስታ ተቀበለ።
አባቱ ትምህርት ባለመማራቸው ምክንያት ስድብ ደርሶባቸው ያውቅ ነበርና በእርሳቸው የደረሰው በልጃቸው ላይ እንዳይደርስ ሲሉ ኅሩይን ከልጀነቱ ጀምሮ ትምህርት ላይ እንዲያተኩር አደረጉ። ኅሩይም በተወለደበትና በሌሎች ቦታዎችም በመዘዋወር የንባብ፣ የዜማና የድጓ ትምህርቶችን ከዘመኑ ሊቃውንት ተም ሯል።
ኅሩይ በእንጦጦ ራጉኤል ደብር የመጽሐፍ ትርጓሜን በሚገባ ተምሮ አጠናቋል። በቀሰመው ትምህርትም በአስተርጓሚነት አገልግሏል። በባሕላዊው ትምህርት የተሟላ እርካታ ማግኘት ያልቻለው ኅሩይ፣ አዲስ አበባ ስዊድን ሚሽን ትምህርት ቤት ገብቶ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተምሯል። ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ አረብኛ ቋንቋ ለመማር ጥረት ቢያደርግም ‹‹ኅሩይ ሰለመ›› የሚል አሉባልታ ስለሰማ ለጊዜው ትምህርቱን ለማቆም ተገዷል። በኋላም ከፈረንሳያውያን ሐኪሞች ፈረንሳይኛ ቋንቋን መማር ችሏል።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከ1910 እስከ 1914 ዓ.ም ድረስ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል። ከንቲባ ከመሆናቸው አስቀድሞ የከተማዋ ስራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል። በከንቲባነት የአገልግሎት ዘመናቸውም ቀደም ሲል በተለያዩ የአስተዳደር ስያሜዎች ይጠራ የነበረውን የከተማውን አስተዳደር ‹‹ማዘጋጃ ቤት›› ብለው በመሰየም እስካሁን ድረስ የዘለቀ ቋሚ ስያሜ ሰጥተውታል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደራዊ መዋቅር መልክ እንዲይዝ እንዲሁም በከተማዋ የመሰረተ ልማት ተግባራት እንዲከናወኑ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል።
በዓለም መንግሥታት ማኅበር የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መልዕክተኛ ቡድን አባል ነበሩ። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ብላቴን ጌታ ኅሩይ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒትር ነበሩ። ለአጭር ጊዜ ቢሆንም ብላቴን ጌታ ኅሩይ በጃፓን የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግስት አምባሳደር ሆነው ሰርተዋል። በጃፓን የነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያም በቴክኖሎጂ ታግዛ እንደጃፓን ጠንካራና ዘመናዊ እንድትሆን የሚያነሳሳ ምኞት ፈጥሮባቸው ነበር።
ከማይጨው ጦርነት በኋላ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የዲፕሎማሲ ትግል ለማድረግ ወደ ውጭ በተሰደዱበት ወቅት ብላቴን ጌታ ኅሩይም ከኢትዮጵያ ወጡ። ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ስለፈጸመችው የግፍ ወረራ ጀኔቫ ላይ ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ሲያስረዱ ኅሩይ ከጎናቸው ነበሩ።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከመንግሥታዊ ኃላፊነቶቻቸው ባሻገር በደራሲነታቸውም ይታወቃሉ። በርካታ የታሪክ፣ የጉዞ ማስታወሻ፣ የሃይማኖት፣ የልብወለድ፣ የግጥምና የጠቅላላ ዕውቀትን ጨምሮ ከ16 በላይ መጽሐፍትን አበርክተዋል። ከሥራዎቻቸው መካከል ‹‹ወዳጄ ልቤ›› የሚባለው መጽሐፍ በብዙዎች ዘንድ ታዋቂነትንና ተወዳጅነትን አትርፎላቸዋል።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ እንግሊዝን፣ አሜሪካን፣ ቻይናን፣ ፈረንሳይን፣ ኢጣሊያን፣ ግብጽንና ሌሎች አገራትን ጎብኝተዋል። የአገራቸውን ወደኋላ መቅረት ከአውሮፓውያኑ ዘመናዊነት አንፃር ባስተዋሉ ቁጥር ቁጭታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ይገልጹ ነበር። በአንድ አጋጣሚ ኢጣሊያን ሲጎበኙ በኢንዱስትሪው አማካኝነት የሚከናወነውን ድንቅ ሥራ ተመልክተው በመደነቅ ተከታዩን ሀሳብ አስፍረው ነበር።
“ለሀገራችን ለኢትዮጵያ የልብስና የእርሻ መኪና በግድ ያስፈልጋል። ኑሯችን ሁሉ ሸማ ለብሰን ነው እንጂ እንደ አውሮፓዎች የበግ ጠጉርና ሐር ዘወትር አንለብስምና አገራችን ጥጥ ለማብቀል የተመቸ ነውና ስለዚህ የሸማ መኪና ያስፈልገናል። ምግባችንም እህል ነው እንጂ እንደ አውሮፓዎች ሥጋና ዓሣ አትክልት ሁልጊዜ አናገኝምና አገራችንም አሳምሮ እህል ያበቅላልና ስለዚህ የእርሻ መኪና ያስፈልገናል። ይህንንም አስቀድሞ መንግሥት ገዝቶ ፋብሪካውን ቢያቆም መኳንንቱና ያገር ባለፀጎች ሁሉ እንደ ኩባንያ ገንዘብ እያዋጡ አንድ አንድ መኪና እየገዙ ፋብሪካ ያቆሙ ነበር። ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ያገኙበት ነበር”
ለንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የቅርብ አማካሪ በመሆን የሃይማኖትና የአስተዳደር ሕግጋትን እየተረጎሙና የአርትኦት ሥራዎቻቸውን እያጠናቀቁ እንዲወጡ ያደረጉት ታላቁ ዲፕሎማትና ደራሲ ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወልደሥላሴ እንግሊዝ ውስጥ በስደት ላይ ሳሉ፣ መስከረም ዘጠኝ ቀን 1931 ዓ.ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በዚያው እንዲፈፀም ተደረገ። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ምድር ከተባረረ በኋላም በ1940 ዓ.ም አስክሬናቸው ካረፈበት ቦታ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በመንበረ ፀባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል እንዲያርፍ በክብር ተደርጓል። በስደት ላይ የነበሩት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እንግሊዝ በነበረው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ስርዓተ ቀብር ላይ የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር።
‹‹አሁን የአዳምን ልጆች ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በአገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ ከኢትዮጵያም ከፍ ካሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው። ብልሃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስላደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ በቃ። በየጊዜው የጻፋቸው ከፍተኛ ባህሪውን የሚገልጹ መጻሕፍት፤ ይልቁንም በቤተ-ክህነትና በታሪክ እውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት። ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈለግ አልመሰለኝም። በአጭሩ ከጠባዩ ትልቅነት የሚሰማኝን ለመናገር ሳስብ ጊዜውን ሁሉ ቁም ነገር በመሥራት ማሳለፉ፤ ከራሱ ይልቅ የተቸገሩትን ለመርዳት መጣሩ፤ እውነትን፣ ፍርድንም ማክበሩና በአገር ፍቅር መቃጠሉ ትዝ ይሉኛል።
አገልጋዬና ወዳጄ ኅሩይ! በተቻለህ ስለአገርህ ሥራህን በሚገባ ፈጽመህ በምትሰናበትበት ጊዜ ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ። በክፉ አድራጊዎች የሚገፋ የዓለምን ፀጥታ የሚያናውጥ ነፋስ ምንም ቢያንገላታህና በታላቅ ፈተና ላይ ቢጥልህም ሊያሸንፍ አልቻለም። ታላቅና ቸር በሆነው ጌታ በተመደበው ሕግ ግን መታዘዝ ግድ ሆነብህ። ይህም ለያንዳንዳችን የሚደርሰን ዕድል ነው። አንተም እስከ መጨረሻ ከታገልክ በኋላ ዛሬ ደከመህ፣ አንቀላፋህም። በሥጋ ብትለየንም ስምህና ሥራህ በመካከላችን ይኖራሉ።
ኅሩይ፣ እግዚአብሔር ሲያስበን አጥንቶችህና መንፈስህ የሚሰፍሩበትን ቦታ እስኪያዩና ከአባቶችህ እስኪቀላቀሉ ድረስ በእንግድነት በመጣህበት በዚህ ሥፍራ በሰላም ዕረፍ።»
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከወይዘሮ ሐመረ እሸቴ ጋር ጋብቻ መስርተው ስድስት ልጆችን አፍርተዋል፤ብዙ የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅተዋል። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ጋር በመተባበር ጳጉሜን ሁለት ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የአራት ቀደምት ደራሲያንን ምስል የያዙ ቴምብሮች አስመርቆ ገበያ ላይ ሲያውል ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ምስላቸው በቴምብር ላይ ከታተሙላቸው ደራሲያን መካከል አንዱ ነበሩ። ጉለሌ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚም ያስገነባውን የስነ ጥበባት ማዕከል በስማቸው እንዲጠራ አድርጓል። የሕይወት ታሪካቸው ‹‹የብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ሥላሴ ታሪክ ፡ 1871 – 1931 ዓ.ም›› በሚል ርዕስ በኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተዘጋጅቶ ታትሟል።
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014