የ2014 ዓ.ም የመጀመሪያው ወር የሆነው መስከረም ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያውያን ሁሌም እንደሚያደርጉት በዘመን መለወጫ “አሮጌውን አስተሳሰብ” ጥለው በአዲስ ብሩህ ተስፋ ይሞላሉ። ያቀዱትን ያሳካሉ። የቆየ ወዳጅነታቸውን ያጠነክራሉ። በዚያኛው ዓመት ያልተሳካውን እቅድ በአዲሱ በዳግም ተስፋ ለማሳካት ይታትራሉ።
በወርሃ መስከረም እንደየ ባህሉና እምነቱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን መጪው ግዜ የስኬትና የበረከት እንዲሆን ፈጣሪያቸውን ይለምናሉ። ለምሳሌ በመስከረም 17 በመስቀል ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል “ደመራ” በመደመር ሁሉም በአንድነት በመሰብሰብ “መስቀሉ የመገኘቱን” ብስራት ከማክበራቸውም በላይ የእምነቱ ተከታዮች አዲሱን ዓመት ከመስከረም አንድ ጀምሮ በደስታና በተድላ የማክበራቸውን ሚስጢር የሚገልጡበት ነው። የወሩን አጋማሽ በሙሉ ያለፈውን ግዜ አሸኛኘት አድርገው መጪውን ደግሞ በፍፁም ቅንነት የሚቀበሉበት ነው።
ሌላው የኢትዮጵያውያን የአዲስ ዘመን ማብሰሪያና ፈጣሪን የማመስገኛ በዓል “ኢሬቻ” ነው። ከተከበሩትና ከተቀደሱት የኦሮሞ ክብረ በዓሎች አንዱ ሲሆን፣ ከጥንታውያኑ የኦሮሞ አባቶች ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ ይነገራል፡፡ ‹‹ኢሬቻ እርጥብ ሣር፣ ቅጠል ቄጠማ አበባ ማለት ነው›› በማለት የኦሮሞ አባ ገዳዎች፣ ኢሬቻው ለእግዚአብሔር ምስጋና የምናቀርብበት ሥርዓት ነው ይላሉ፡፡ ‹‹አምና በሰላም በጤና 13ቱን ወር አስጨርሰኸናል፡፡ መጪውን ዓመት ደግሞ በሰላም እንድታደርሰን ይሁን፡፡
ይኸንን ለሰው ልጅ ለሁሉም ፍጥረት ብለህ የፈጠርከውን ንፁህ ውኃ በአንተ ኃይልአጣርተህ ያስቀመጥከውን በሐይቅህ ላይ ምስጋናህን እናቀርባለን፡፡ ውኃ ንፁህ ነውና፤›› በማለት ምስጋናቸውን ያቀርቡበታል። ምርቃቱ በየዓመቱ ከመስቀል በዓል በኋላ በሚመጣው እሑድ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል የሚወክል ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንን በአዲስ ዓመት ከሚወክሉ ከላይ ካነሳናቸው ከእነዚህ ክብረ በዓላት በተጓዳኝ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ጭጋጋማወቹ ሃምሌና ነሃሴን ሸኝተው መስከረምን ከብሩህ ብርሃን ጋር ሲቀበሉ የየራሳቸውን ተስፋና እቅድ ይሰንቃሉ። ሁሌም ያገኙትን ስኬትና ድል እያሰቡ በአዲስ ጉልበት ጥረታቸውን ይቀጥላሉ። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከሆኑም እንቅፋቱን እንዴት እንደሚሻገሩት ያልማሉ። ከሁሉ በላይ ግን ፅናትን እንደ አዲስ ይጎናፀፋሉ።
ብልሆች “ከፊት ለፊታችን ካለው አስቸጋሪ ቋጥኝ ስር ሁሌም መልካም እድል አለ” ይላሉ። አሁን ኢትዮጵያውያን መንገድ ላይ “ዘአረኝነት”ን ለማንገስ አገር ለማፍረስ የተኮለኮሉ በርካታ ቋጥኞች አሉ። እነዚህን እንቅፋቶች ደግሞ እንደ ሁል ግዜው በዘመን መለወጫ “ፈጣሪያችንን” በማመስገን እንዲሁም በመልካም ምኞት ብቻ የምንቀርፋቸው እንዳልሆኑ እየተገነዘብን ነው። ፈጣሪያችን ከዚህ በላይ ጥንካሬና ፅናት ከኛ እንደሚጠብቅ ለበጎ እንደሚፈትነንም እርግጥ ነው። ታዲያ እነዚህን ጭንጫዎች ከፊት ለፊታችን እንዴት ማንሳት ይቻለን ይሆን?
ከሁሉም በላይ መላው ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ከነበሩን ጥንካሬና አርበኝነት በላይ እጅግ የተለየና የተሻለ ዝግጁነት ሊኖረን ይገባል። ምክንያቱም በያዝነው ዓመት በርካታ እንቅፋት የሆኑ መሰናክሎች የስኬት መንገዳችንን፣ ሉአላዊነታችንን፣ አንድነታችንን፣ ከምንም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነታችንን ጥላሸት
ለመቀባት ከፊታችን ስለተጋረጡብን። ችግሮቻችን ካሳለፍነው ክረምት ካረበበው ደመና በላይ በዙሪያችን ቢያጠሉም የአሸናፊነት ስነ ልቦናችንና ጽናታችን ደግሞ ይህን ጭጋግ ገላልጦና ጥሶ የሚወጣ መሆን አለበት። ፈተናዎችን ተጋፍጠን መሰናክሎቻችንን ማለፍ ከቻልን የኢትዮጵያ ትንሳኤ እሩቅ እንደማይሆን ደግሞ ከዚህ የሚከተለው “የንጉስ ኢቫንና የፍራፍሬ ሻጩ ነጋዴው” ታሪክ በግልፅ ያስረዳናል።
በአንድ አገር ወስጥ ንጉስ ኢቫን የተሰኘ መሪ በግሪክ አገር ህዝቡን ያስተዳድር ነበር። በእርሱ አገዛዝ ዘመን ሰዎች በደስታ ይኖሩ ነበር። እሱም ደስተኛ ስለመሆናቸው ያውቅ ስለነበር እንደራሱ ቤተሰብ ይቆጥራቸው ነበር። የባልንጀሮቹን ፍላጎት ሁሉ ለማሟላት ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጓል። ይሁን እንጂ የዜጎቹን መልካምነትና ችግርን ተጋፍጦ የማለፍ ብቃት መፈተን ፈለገ።
በአንድ እለት ድንገተኛ ጉብኝት ለማድረግ ወሰነ። በድብቅም ከተማዎችን ለመጎብኘት ጉዞውን ጀመረ። የሚፈልገው ስፍራ ላይ ሲደርስም በመንገዱ መሀል የሚያልፉትን ሰዎች ለመፈተሽ አንድ ግዙፍ ቋጥኝ በመንገዱ መሃል ላይ ለማስቀመጥ ወሰነ። የእርሱ ወታደሮችም በመንገዱ ላይ ድንጋይ አስቀምጠው ሁሉም ቀጥሎ የሚሆነውን ለማየት በአቅራቢያው ባለው ቦታ ተደብቀው መከታተል ጀመሩ። ድንጋዩ የመንገዱን ግማሽ የሚሸፍን ሲሆን በመንገደኞች ላይም ሁከት ፈጥሯል። በእሱ አገዛዝ ይኖሩ የነበሩ ብዙ ባለፀጋ ሰዎች በመንገድ ይመጡ ጀመር። ነገር ግን መንገዱን ስለዘጋው ድንጋይ ማንም የሚያስብና ተጨንቆ የተዘጋውን መንገድ ለመክፈት የሞከረ አልነበረም። የተሽከርካሪውን እንቅስቃሴ ቢረብሽም ስለ ቋጥኙ ማንም የሚጨነቅ አይመስልም ነበር።
አንድ የፍራፍሬ ሻጭ ነጋዴ ግን ጭነቱን ይዞ በመንገድ ሲያልፍ ግዙፉን ቋጥኝ በማየቱ ጎዞውን አቆመ። ከዚያም ሸክሙን ወደ ጎን ትቶ ድንጋዩን ለማንቀሳቀስ ሞከረ። ከድንጋዩ ብዙ ለመግፋት ፣ ለማንሳት እና ለማንቀሳቀስ ከሞከረ በኋላ እንቅፋቱን ከመንገዱ ለማስወገድ ቻለ። በሁኔታው ንጉሱ በእጅጉ ተደስቶ ነበር። ዜጎቼ ችግርና መከራን በዚህ መንገድ ከፊት ለፊታቸው ማንሳት ይኖርባቸዋል ሲል አስቦ ነበር።
የፍራፍሬ ነጋዴው ድንጋዩን አንስቶ እንደጨረሰ ግን ቀጥሎ የተመለከተው ነገር በእጅጉ አስደንግጦት ነበር። ከድንጋይ በታች የተቀመጠ ግዙፍ ቦርሳ ነበር የተመለከተው። ቦርሳውን ወስዶ ሲከፍተው በውስጡ “ስጦታ ለእርስዎ ነው! አንድ ሺህ የወርቅ ሳንቲሞች አሉት” የሚል መልክት አገኘ። ፍራፍሬ ሻጩ ነጋዴ በጣም ተደሰተ። ንጉሱም ለግብዣ በቤተ መንግስቱ ጠርቶት በጥሩ ሁኔታ ሸለመው። በዚህም ለህዝቡ የዚህን ምስኪን ነጋዴ ታሪክ በስፋት እንዲነገር በማድረግ “በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመን እያንዳንዱ መሰናክል ዕድል አለው” የሚል ታላቅ ትምህርት አስተማረበት።
ኢትዮጵያውያዊነት የገጠመው ችግርም ንጉሱ በአስፋልቱ ዳር እንዳስቀመጠው ድንጋይ ይመሰላል። ዙሪያችንን የከበቡንን ጠላቶች ድል ማድረግ ከቻልን ፍራፍሬ ሻጩ እንዳገኘው ከረጢት ሙሉ ወርቅ ሁሉ እኛም “የኢትዮጵያን ትንሳኤ” እናገኛለን። ፈተናዎች ሁሉ እድል ይዘው አንደሚመጡ መረዳት እንችላለን። ለዚህ ነው “ቋጥኙን ስናነሳው የኢትዮጵያን ትንሳኤ እናያለን” እያልን ደግመን ደጋግመን የምንናገረው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014