ድሮ ድሮ አፍቃሪዎች ፍቅራቸውን ለመግለጽ የተወጋ ልብ ያለበት ደብዳቤ ይልካሉ፡፡ የአሁኖቹ አፍቃሪዎች ምንአይነት ደብዳቤ ለአፈቀሩት ሰው እንደሚልኩ አላውቅም፡፡ በተለይም ተማሪዎች አካባቢ በጦር የተወጋን ልብ በመልእክት አድርጎ በጥንቃቄ እንዲደርሰው ለተፈለገው አካል እንዲደርስና ምላሽ እንዲሰጥበት ይጠበቃል፡፡ በጦር የተወጋ ልብ የደብዳቤው ዋና መሆኑ በፍቅር የተወጋ መሆኑን ለማሳየት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ተማሪው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነው፡፡ የክፍሉ ተማሪ ከሆነች ልጅ ፍቅር ይይዘውና ስሜቱን እንዴት እንደሚገልጽላት እየተጨነቀ እየተጠበበ ነው፡፡
ጉዳዩን ለቅርብ ጓደኛው ያማክረዋል። ጓደኛውም በመጀመሪያ በጽሁፍ ፍቅርህን ግለጽላት ብሎ ይመክረዋል፡፡ ምክር ተቀባዩም አፍቃሪ የተባለውን ሊያደርግ የጽሁፍ መልእክቱን አዘጋጀ። ከብዙ መጠበብ በኋላ ያዘጋጀውን ጽሁፍ ሲያነበው ፈጽሞውኑ የልቡን የሚገልጽ ሳይሆን ቀርቶ የጻፈውን ቀደደው፡፡ መልሶ ሌላ ይጽፋል፤ አሁንም የጻፈው ሊያረካው ሳይችል ይቀርና ይቀደዋል፡፡ እርሱ ውስጥ የሚሰማውን በጽሁፍ መግለጽ ባለመቻሉ ሌላኛውን ጓደኛ ያማክራል፡፡ ይህኛው ጓደኛ ደግሞ “የፍቅር ደብዳቤ በመጻፍ ልምድ ያላቸው ልጆች ስለአሉ በእነርሱ አታጽፍም፡፡ በተለይ እከሌ ቢጽፍልህ ጉዳዩ አለቀ ማለት ነው፡፡” ብሎ ይመልስለታል፡፡
አፍቃሪም እርሱ ውስጥ ያለውን ስሜት ሌላ ሰው እንዲጽፍ ማድረግ የቸገረው እርጉዝ ያገባል ቢሆንበትም ለተባለው ልጅ ሃላፊነቱን ሰጠው፡፡ የጨረሰ ደብዳቤ ያዘጋጃል የተባለውም ልጅ በሚያማምሩ ቃላት የተከሸነ፤ በተወጋ ልብ ምስል የታጀበ የፍቅር ደብዳቤ አዘጋጅቶ የልፋቱን ዋጋ ሂሳብ ለመቀበል ተዘጋጅቶ በቀጠሮው ቦታ ደረሰ፡፡ የቸገረው አፍቃሪም ሂሳቡን ከፍሎ ደብዳቤውን ተቀብሎ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቤቱ ሄዶ ደብዳቤውን ሲያነበው በልጁ አጻጻፍ ቢደነቅም አሁንም በውስጡ ያለውን ስሜት በሚገባ የሚገልጽለት ሆኖ ስላላገኘው በንዴት ደብዳቤውን አቃጠለው። ተበሳጨ፤ አለቀሰ፤ ምንድን ነው እየሆነብኝ ያለው? እራሱን ጠየቀ፡፡ አጭር መልስ አላገኘም፡፡ መሻቱ አንድና አንድ ነበር የሚሰማውን ስሜት በቃላት ገልጾ ያፈቀራትን ወጣት የእራሱ ማድረግ፡፡ ነገር ግን ያ ስሜትን በልቦለዳዊ ቃላት በሚያማምሩ አረፍተ ነገር ውስጥ በሙላት ሊያገኘው አልቻለም፡፡
ከብዙ ግራ መጋባት ውስጥ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለለት፡፡ ባለፈው አመት በተመሳሳይ ሁኔታ ከተማሪ ፍቅር ይዞት የተቸገረ በራሱ መንገድ ከችግሩ የወጣ ተማሪን አስታወሰ፡፡ ይህ ተማሪ የእርሱ የቅርብ ጓደኛ ባይሆንም የእርሱን ምክር መስማት የግድ መሆኑን አመነ፡፡ በአካልም ተገናኙ፤ ጉዳዩንም አስረዳው። የሚሰማውን ስሜት በሙሉ ነገረው፡፡ ያፈቀራትን ተማሪ ሲያይ የሚሰማውን የፍቅር ስሜት፤ ነገርግን ይህን ስሜት በአካል ለመግለጽ እንደሚፈራ፤ በጽሁፍ ለመግለጽ ደግሞ ሙከራው እንዳልተሳካ በአጭሩ በችግር ውስጥ መሆኑን አስረዳው። ምክር ለመስጠት የተሰየመው እርሱም በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ያለፈው ተማሪ ደግሞ በጥሞና ሲሰማ ቆይቶ “በመጀመሪያ ከተወጋው ልብ ላይ ጦሩን ንቀለው። ጦሩን መንቀል እንድትችል እርሷን እንደማንኛውም ሰው በሰውነት ተመልከት፤ በመቀጠል እርሷን መግለጽ ወደ ምትችልበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ጥንካሬዋንና ድክመቷን እወቅ፡፡ እርሷን በጥንካሬና በድክመት መግለጽ የምትችልበት እውቀት ስለ እርሷ ሲኖርህ ያኔ ያለማንም ድጋፍ ስሜትህን ልትገልጽላት ትችላለህ” አለው፡፡
መካሪው የሚለው አፍቃሪው አልገባውም፡፡ ምንድን ነው ከልቤ ላይ ጦሩን መንቀል? እስከአሁን እርሷን መግለጽ ያልቻልኩ ሰውዬ እንዴት በቀላሉስ አደርገዋል? እውን እኔ ከእርሷ ጋር ቁጭ ብዬ ሀሳቤን ማስረዳት እችላለሁ? ብሎ ራሱን ይጠይቅ ጀመር፡፡
የመነሻ ታሪካችንን በጉዞችን መሃል ላይ እየተመለስንበት አብረን የምንዘልቅበት ይሆናል፡፡ የአፍቃሪው መካሪ በሰነዘራቸው ሦስት አቅጣጫዎች ላይ ማእከል አድርገን የተወጉ ልቦችን እያሰብን ስለ ፈውሳቸው እንመክራለን፤ በሰፊው የልብ መወጋት ውስጥ፤ በፍቅርም በተቃራኒውም፡፡
ከልብ ላይ ጦሩን መንቀል
ጠቢቡ ሰለሞን እንዲህ አለ አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና (ምሣሌ 4፡23)፡፡ ልብ የሕይወት መውጫ የሚለው አገላለጽ በልብ በኩል የሚወጣውና የሚገባው ረጅሙን አቅጣጫ የመወሰን ጉልበቱን በሚገባ አያሳይም ትላላችሁ? ልባችን ውስጥ የሚሆነውን ስሜት ቃላት ሊገልጹ የማይችሉበት የሕይወት ጉዞ ውስጥ አልፈን ይሆናል፤ ምናልባትም በእዚህ ወቅት እያለፍን፡፡
አንባቢው አሁን ባለበት ቦታ ሆኖ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ይቃኝ፡፡ በልባቸው ውስጥ ምን ይዘው እየኖሩ እንደሆነ ለማወቅ ይመርምር፡፡ አስረግጦ ይህን ማለት ይችል ይሆን? በእርግጥ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ልብ የሕይወት መውጫ ናት ሲባል የሕይወት መላ አቅጣጫ የሚብላላባት መባሉ ነው፡፡ መንገድ ላይ ያየነው ሰው ሁሉ የልብ ሁኔታ ይህ ነው ማለት የማንችል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
በሕይወት ጉዟችን ላይ ጥብቅ ተጽእኖ የማሳደር አቅም ያለባቸውንስ? የእናታችንን፣ የአባታችንን፣ የእህቶቻችንን፣ የወንድሞቻችንን፣ የሥራ ባልደረቦች፣ የጓደኛቻችንን፣ የእጮኛችንን ወይንም የትዳር አጋራችን፣ የአከራያችን፣ የአበደረንን ግለሰብን፣ አብሮን ንግድ የሚነግድ አጋራችንን፣ አብሮን ኮሚቴ የሆኑ ሰዎችን ወዘተ። ከእኒህ ሰዎች መካከል ደግሞ በተለየ ሁኔታ እጅግ በጣም የምንቀርባቸው የተወሰኑ ሰዎች መኖራቸው እሙን ነው። በጣም የምንቀርባቸውን ለይተን አውጥተን በምን ያህል ልባቸውን የምናውቅ ነን? ከእነርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ጤንነቱንስ እንዴት ነው? ብለን እየጠየቅን እንዝለቅ፡፡
የግንኙነት ችግር አለ ብለን የለየናቸውን ልቦች ደግሞ እንዴት ጤንነታቸውን ልንመልስ እንደምንችል ስራዬ ብለን አስበንስ እናውቅ ይሆን? ዝም ብሎ በውስጣችን ችግሩን ይዞ አብሮ መኖር? ወይንስ መፍትሄ መፈለግ፡፡
መካሪና ተመካሪ የሆኑት ሁለቱ ተማሪዎች ጨዋታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከልብ ላይ ጦርን ስለመንቀል ትርጉምም መካሪው እያብራራ ነው፤ በችግሩ ያለፈው መካሪ፡፡ “ከልብ ላይ ጦርን መንቀል ማለት የተጓዳንበትን ነገር ከልባችን እያወጡ የመሄድ ህክምና ነው፡፡ አንተ እርሷን ማናገር እንዳትችል የሆንከው፤ ሃሳብን መግለጽ የተቸገርከው በፍቅር ሳይሆን በፍቅር ውስጥ በሆነብህ ጉዳት ነው፡፡ በማፍቀርህ እየተጎዳህ ያለህበትን ነገር በቅድሚያ አስተካክል፡፡ ይህ መሆን የሚቻለው እርሷን ፍጹምና እጅግ ልዩ የሆነች አድርገህ ከማሰብ ወጥተህ እንደማንኛችንም ሰው እንደሆነች አምነህ በመቀበል ነው፡፡
ይህን ሊያደርግልህ የሚችለው ደግሞ ጠንካራና ደካማ ጎኖቿን ማወቅ እንዲሁም መመልከት ስትችል ነው፡፡ ስሜትህን ደብቀህ እንደ ማንኛውም ሰው ቀርበህ ደካማና ጠንካራ ጎኗን ስትረዳ ያኔ የከበበህ ልዩ ስሜት ጠፍቶ መሰረት ወዳለው ፍቅር ውስጥ የምትገባ ወይንም የማትገባ መሆንህን ታውቀዋለህ፡፡ በርቀት ተመልክተን ያንን ሰው በአይን ብቻ አይተን በሚሰማን ስሜት ውስጥ መጎዳት እንጂ እውነተኛ ፍቅር አይመሰረትም።” እያለ ማብራሪያውን ሰጠው፡፡
መካሪው ሲቀጥል እንዳንተ እንዲህ በመሰለ ሁኔታ ተፋቅረው ወደ ትዳር ገብተው አብረው መዝለቅ ያልቻሉ ሰዎች ለምን እንዲያ የሚሆኑ ይመስልሃል? በእጮኝነት ጊዜያቸው መላእክት መስለው እራሳቸውን እያቀረቡ አብረው መኖር ሲጀምሩ ቤታቸው የሞት ጣር የሚሆንባቸውስ ለምን ይመስልሃል? እያለ በጥያቄ ውስጥ ምክሩን ቀጠለ፡፡ በማሳረጊያውም መካሪው አለ በአጭሩ እርሷን በጥንካሬዋና በድክመቷ ላይ በምታውቃት ጊዜ ያኔ ተገናኝተን ቀጥሎ ስላለው ነገር እናወራለን፡፡ በእርግጠኝነት ያኔ ከልብህ ላይ ጦሩ ተነስቶ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ ብሎት ተለያዩ። አፍቃሪው በአይን ፍቅር እንዲህ የመሰለ ውስብስብ ውስጥ መግባቱ አስገርሞት ከመካሪው ያገኘውን ምክር ለመተግበር ራሱን እንዴት እንደሚያዘጋጅ እያሰበ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ከልብ ላይ ጦሩን ለማንሳት፡፡
ልባችንን ስንመለከት በእከሌ ወይንም በእከሌት ተጎድቻለሁ ብለን የምንቆጥረው ብዙ ነገር ሊኖር ይችላል። የጉዳቱ መጠን ቀላል፤ መካከለኛ ወይንም ከባድም ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ነገር ግን እርግጠኛ መሆን እንችላለን እርሱም የጉዳት መጠኑ ተጎዳን ባልንበት ሰው አስቀድሞ በነበረን ልብ የሚወሰን መሆኑ። በአባት መጎዳትና በሌላ ተራ ሰው በተመሳሳይ ነገር መጎዳት ትርጉሙ አንድ ሊሆን በፍጹም አይችልም። በእናትም ሆነ በሌላ የቅርብ ሰውም እንዲሁ፡፡ በጣም የእኔ ብለን ልባችንን በሰጠነው፤ ሚስጥራችንን ባካፈልነው ሰው የምንጎዳበት መጎዳት ከሌላው ሰው ጉዳት ጋር ተመሳሳይ ሊሆን አይችልም። የተወጋው ልብ የተወጋበት ጥልቀት በሰውዬው ሁኔታ ይወሰናል የሚባለው ለእዚህ ነው፡፡ እብድ ሰደበኝ ብሎ ክስ የሚመሰርት ሰው ሊኖር መቻሉ አጠራጣሪ ነው። ህጻን ልጅ ያለእኔ ፈቃድ መጥቶ አካሌ ላይ ወጣብኝ ወይንም ቀረበኝ ብሎ ቅሬታ የሚያቀርብም አለመኖሩ እንዲሁ፡፡
በጦር የተወጋ ልብ ይዘን ወይንም በጦር የተወጋ ልብ በአጠገባችን ኖሮ መፍትሄ የምንፈልግ ከሆነ በቅድሚያ ልናየው የሚገባን የተወጋንበትን ሰው ነው፡፡ ለእዚያ ሰው የሰጠነው ቦታ የውጋቱን መጠን የጨመረው በመሆኑ ወደ መፍትሄው ለመድረስ ለሰውዬው የምንሰጠውን ቦታ ማስተካከል ነው፡፡
ከእዚህ ቀደም ተመልክተነው ሚስጥር ጠባቂ የመሰለን ሰው እንዲያ ሆኖ ባለመገኘቱ የተጎዳን ከሆነ ከእዚህ ሰው ጋር አሁንም በህይወት ጉዞ ውስጥ የምንኖር ከሆነ ስለሰውዬው ያለንን መረዳት ማስተካከል የፈውስ መንገዱ አቅጣጫ ነው፡፡ ግለሰቡ ካለበት ድክመት እንዲወጣ መርዳት የሚከተል ስራችን፡፡ የተወጋንበትን ጦር ልባችንን ላይ አድርገን በህመም ውስጥ ከመኖር መስተካከል የሚኖርበትን ምልከታችንን አስተካክልን የመራመድ አዋጩ መንገድ፡፡
አንዳንድ ሰዎች እንዴት “በአንተ/በአንቺ በተደጋጋሚ እጎዳለሁ?”ብለው ሲጠይቁ እናደምጥም ይሆናል፡፡ በተደጋጋሚ መጎዳት የተጎዳንበትን ሰው በተደጋጋሚ ከማመን ውስጥ የሚወጣ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ አማኝነት ደግሞ በራሱ ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን እምነት ከእውቀት ውስጥ መሆን መቻሉ ላይ ማሰብ ይፈልጋል እንጂ፡፡ ሳናውቅ ተጎድተን ብዙ ዋጋ ከከፈልን በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ለመጎዳት መቅረብ ሳይሆን ጉዳት እንዳይኖር አስቦ መራመድ የተገባ ነው፡፡ አዲስ አመት ሲመጣ ግብ ከምናደርጋቸው ነገሮች መካከል ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ትርጉም በመስጠት ማስተካከል አንዱ ቢሆን መልካም ነው፡፡
በምድር ላይ እስካለን ድረስ ከሰው ተለይተን ልንኖር አንችልም፡፡ አብረን የምንኖር፤ አብረን የምንጓዝ ስለሆንን። አብረን ወጥተን፤ አብረን የምንገባ፡፡ አብረን በብዙ መስመሮች የምንገናኝ፡፡ ሌሎች ድካም እንዳለባቸው እኛም ድካም ያለን ፍጡራን፡፡ ስለሆነም እስከመጨረሻው ተቆራርጦ ነገርን ከማስቀረት አንዳችን ሌላችን ላይ በፍርድ መንገድ ሳይሆን በእውቀት የሆነን ግንኙነት ለመመስረት መስራት የተሻለው ነው፡፡ ፈራጅ ሆነን አንድ ሰው አይቀየርም ብለን መደምደምም ስህተት ነው፡፡ ትናንት በተጎዳንበት መንገድም ዳግም ለመጎዳት መቅረብም ስህተት ነው፡፡ መፍትሄው እርምጃችንን ወይንም የቅርርባችንን እርቀት በመተዋወቅ ማድረግ ነው፤ እርሱ ደግሞ ጦሩን ነቅሎ እንዴት ጦሩ ወደ ልባችን እንደገባ ከመጠየቅ ውስጥ የምንደርስበት፡፡
በልባችን የሚያልፈውን ጦርን ፍራቻ በእውቀት የሆነን እምነትን ስንፈልግ የቱንም እድሜያችንን ብንጠቀም ሰውን አውቀን ልንጨርሰው አንችልም፡፡ ልንገልጸው በምንችልበት ደረጃስ? የሚለው ጥያቄ ወደ ሁለተኛው ነጥብ ያስፈነጥረናል፡፡
ያለድጋፍ መቆም
ያለድጋፍ መቆምን ራስን ችሎ ሰዎችን መያዝ ከመቻል አንጻር እንመልከተው፡፡ የፍቅር ደብዳቤው በአፍቃሪው ቢጻፍም እንዲሁም በሌሎች ሲጻፍም እውነተኛ ስሜትን የሚገልጽ አለመሆኑ ትምህርቱ ወዲህ ነው፡፡ ድጋፍ ፍለጋ አንድ ሰው የሚሄደው እርሱ ጋር አቅም ሲጠፋ ነው፡፡
በዙሪያችን ያሉ ሰዎች በተለይም በህይወት ጉዞ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸውን ሰዎች ተቆጣጥሮ በህይወታችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድሩ ማድረግ የራሳችን ሃላፊነት አድርገን ማየት አለብን። የአባታችንን ወይንም የእናታችንን ወይንም በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነትና ባህሪ አይተን ትዳርን የምንፈራ እንሆን ይሆናል፡፡ በእዚህ ጊዜ በራሰችን ቆመን ትዳርን መምራት እንቸገርና ለትንሹም ለትልቁም በሌላ
ሰው ምክር ላይ ጥገኛ ሆነን ልንኖር እንችላለን፡፡ በሰዎች ላይ ጥገኛ መሆን የሚያስገኝልን አቅም እንደ ሰዎቹ ነው፡፡ አንዱ መካሪ ጥሩ የፍቅር ደብዳቤ ማዘጋጀትን ሲመክር ሌላው ደግሞ ከተሞክሮው ሊመክር ይችላል፡፡ ሁሉም የሚሰጠው ያለውን ነውና፡፡
የሰዎች ምክርና ድጋፍ አስፈላጊነቱ ባያከራከርም በራስ መቆምን ግን ሊተካ አይችልም፡፡ በራስ ቆሞ በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን ከመረዳት አልፎ ወደ መምራት የሚያሸጋግር ነው፡፡ በእውቀት የሆነን እርምጃ መራመድ ለማህበራዊ ወረታችን እጅግ ወሳኝ መሆኑን ሁሌም መረዳቱ ተገቢ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች የሰዎችን የስሜት መለዋወጥ እያዩ በራሳቸው ላይ አላስፈላጊ ጭንቀትን የሚጨምሩ ሆነው እናያቸዋለን፡፡ እርግጥ ነው ለሰው ስሜት መጠንቀቁ ተገቢነት አለው፡፡ ነገር ግን ውጫዊው ነገር በተቀያየረ ቁጥር ነገራችንን እየቀያየርን ስንራመድ መሰረት የሌለው ኑሮን እንድንኖር እንገዳደለን፡፡ እርሱ ደግሞ በእግር መቆም ላይ አያደርሰንም፡፡ በእግር መቆም አስፈላጊነት አለው፡፡ በራሳችን ስንቆም ጠንካራ ምግብም ልንመገብ እንችላለን፡፡ መሰረት ያለውን ስራ እየሰራን ወደፊት ማየትንም እንዲሁ።
ያለድጋፍ ለመቆም የጠራ የሕይወት ራእይ፣ በራእይ ውስጥ የሆነ የሕይወት ጉዞ ሰዎችን በዙሪያችን ማድረግ፣ እንደ ሰው፣ እንደ አማኝ፣ እንደ ዜጋ ልንኖር የሚገባውን በሃላፊነት የተሞላን ኑሮ መኖር ለሰዎች ዋጋን መስጠት ወዘተ ያስፈልጋል፡፡ በእዚህ መንገድ የሚደረገው ጥረት ፍሬ ያለው እንዲሆን ሁሌም በሁለት እግር ቆሞ መመላለስን ይጠይቃል፡፡ ውጫዊው ነገር ተለዋዋጭነቱ ብዙ እንደመሆኑ፤ ስለውጫዊው ነገር ያለን መረዳት ውስንነት ያለበት እንደመሆኑ፤ ወዘተ በራስ መቆም ትልቅ ድል ነው፡፡
በቤተሰብ ድጋፍ ላይ አመታትን አስቆጥረው ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት ወይንም ለሥራ ከቤተሰብ ሲለዩ የሚቸገሩ ሰዎችን ተመልክተን ይሆን? በእግር ለመቆም እያንዳንዱን እድል መጠቀም አስፈላጊ ነው። ከባድ ውሳኔዎችን መወሰን በሚያስችል፤ ለውሳኔያችን ጭንቅላታችንን የሰውን ምክር ወዘተ ተጠቅመን ነገር ግን በራሳችን የምንወስን ሰው መሆንም እንዲሁ፡፡
አፍቃሪው በራሱ ስላልቆመ እዚህም እዚያም ሄደ፡፡ ያፈቀራትን በጥንካሬና በድካም ካወቃት በኋላ ስሜቱን ሊገልጽላት የሚገባ ሆነ የማይገባ መሆኑን ሲወስን ከእውቀት የሆነን አቅም አገኘ፡፡ ማለትም በራሱ ቆመ። ከስሜት ሳይሆን ከእውቀት የሆነ በእግር መቆም፡፡ መዳረሻውም በእግር የቆመ ሰው ውሳኔ ላይ መገኘት፡፡
አንባቢው ምናልባት በሰዎች ምክንያት ያጣውን ነገር እያሰበ ይሆን ይህን ጽሁፍ እያነበበ ያለው? የተወጋ ልቡን እያስታመምም ቆሞ ያለመም ሊሆን ይችላል። መቆም መፍትሄ አይደለም፡፡ መፍትሄው ጦሩን ነቅሎ ጥሎ በእውቀት ውስጥ መፍትሄን መፈለግ ነው። እውቀት በዲግሪና በማስተርስ ወረቀት የሚገለጽ ያደረገውስ ማን ነው? አንድን ሰው ማወቅ በሚቻልበት ልክ በማወቅ ውሳኔን መወሰን መቻል እኮ ምናልባትም የሕይወታችንን አቅጣጫ በጉልህ የሚወስን ውሳኔን ለመወሰን የሚረዳን ሊሆን ይችላል፡፡
ሕይወትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመኖር። ትርጉሙ ደግሞ በእግር በመቆም ውስጥ የሚገለጽ ለማድረግ ከየአቅጣጫው በተወረወረ በፍቅርም ይሁን በጸብ ከገባ ጦር ራስን ነጻ አድርጎ በእግር መቆም የተሰመረበት መልእክት ነው፡፡
አሁንም የሰው ልጅ ልብ አስቸጋሪ መሆኑን ሳንክድ ነገም በሁሉም ጥንቃቄ ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የሚመጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቦታን በመስጠት ሰውን አውቆ ከሕይወታችን አንጻር በመግለጽ አቅም ውስጥ የተሻለው ነገር መኖሩን ስለምናምን፤ በእግር መቆምን። ከተወጋ ልብ ሰውነት ወደ በእግር የቆመ ሰውነት፡፡
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2014