ማንም እንደሚያውቀው፣ አገር አገር ሆና እዚህ የደረሰችው በልጆቿ ነው። ኢትዮጵያም አገር ነችና ይህ ፍፁም እውነት ለእሷም ይሰራል። በተለይ ከጥንታዊት አገርነቷ አኳያ ያላለፈችበት መንገድ፣ ያልተራመደችው መሰናክል የለምና ከማንም በላይ አንድ አገር በልጆቿ እዚህ ስለ መድረሷ ቀዳሚ ማሳያ ነች።
አገርን በየፈርጁ ለመታደግ በየዘርፋቸው ደፋ ቀና የሚሉ በርካቶች ሲሆኑ አንዱም የአገር መከላከያ ሰራዊት ሲሆን፤ ከእሱም ውስጥ አንዱ አገርን በ”ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት” ዘርፍ በመሰማራት ለአገርና ወገን ቤዛ መሆን ነው። (ሰነዶች እንደሚያስገነዝቡት የ”ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት” አላማ ሁለት ሲሆን፣ አንዱ ከአገር መከላከያ ጎን በመሆን የአገርን ሉአላዊነት ማስከበር፤ ሌላው ደግሞ መልካም ስብእናን የተላበሰ ትውልድ መፍጠር/መገንባት ናቸው።)
በዘመነ ደርግ ከተከናወኑት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ …. ተግባራት መካከል አንዱ ይኸው በ1976 ዓ.ም በተደነገገው አዋጅ መሰረት የተከናወነው፤ በ”ለአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሁሉም ዘብ ይቁም!!!” በሚል መሪ ቃል ይመራ የነበረው የ”ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት” ነበር።
የ”ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት” ለአምስት ተከታታይ ዙሮች (ከ1976 እስከ 1978 ዓ.ም) የተካሄደ ሲሆን በ1ኛው ዙር 52ሺህ 684፤ በ2ኛው ዙር 28ሺህ 112፤ በ3ኛው ዙር 22ሺህ 108፤ በ4ኛው ዙር 20ሺህ 370፤ እንዲሁም በ5ኛው ዙር 15ሺህ 622 ወጣቶች (ምንጭ፡- “የኢትዮጵያ ሠራዊት እና የጦርነቶች ታሪክ – ከአክሱም ዘመነ መንግስት እስከ ኢፌዴሪ” መጽሐፍ) ተመልምለው፣ ሰልጥነውና በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሰማርተው ከመደበኛው ሰራዊት ጎን በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል። ከእነዚህም መካከል የዛሬው እንግዳችን አንዱ ነው።
እንግዳችን በዚሁ በ”ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት” ተሰማርቶ አገሩን ያገለገለ፣ ላገሩም የወጣትነት እድሜውን ብቻ ሳይሆን ደሙን ያፈሰሰና አካሉን የገበረ ጎልማሳ ሲሆን ታሪኩ የሚከተለውን ይመስላል።
አባስ አሊ ይባላል። ተወልዶ ያደገው እዚሁ አዲስ አበባ ተክለ ሀይማኖት አካባቢ በወቅቱ ስያሜ ከፍተኛ 3፣ ቀበሌ 30 ነው። ገና በአፍላ ወጣትነቱ ሳለ ከመንግሥት 4ኛው ዙር (1978 ዓ.ም) የ”ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት” ጥሪ ተላለፈ፤ ተመዘገበ፤ ወደ ደዴሳ ማሰልጠኛ ማእከል አቀና፤ ከተተ። ስልጠናውንም አጠናቆ ከባልደረቦቹ ጋር ከደዴሳ በደብረ ዘይት፤ ከዛም በባህርዳር አድርገው ወደ ኤርትራ። ወደዛ ያመራው ጦር በተለያዩ የውጊያ ግንባሮች ሲሰማራ እሱ የከረን ግንባር ደርሶት ወደዛው ገሰገሰ። በስራ ላይ ስልጠናም ከባዱ ዘርፍ ደረሰውና ፈንጂ አምካኝነትን በመሰልጠን መሀንዲስ ሆነ።
ምንም እንኳን እንደማንኛውም ብሄራዊ ወታደር የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎቱን በሚገባ ቢያጠናቅቅም ጦርነቱ እየተባባሰ በመሄዱ ጭራሽ ዳግም ጥሪ ተደርጎ ከእሱ በፊት የነበሩት፤ በ1ኛ እና 2ኛ ዙር አልግሎታቸውን አጠናቀው የተመለሱት ሁሉ እንደገና ወደ ግንባር እንዲከትቱ ተደረገ። እሱም ግዳጁን ፈፅሞ መመለሱ ቀረና በዛው ቀጠለ። በሂደትም በመንግስት በተወሰነው መሰረት ወደ መደበኛ ወታደርነት ተዛወረ።
“በዛ በኩል ሻእቢያ፣ በዚህ በኩል የዛሬው ጁንታ ወያኔ ወጥረውን ነበር” የሚለው ወታደር አባስ ውጊያው ቀላል እንዳልነበርና በወቅቱ የነበረው ሰራዊት ለእናት አገሩ ሲል ከፍተኛ መስዋእትነትን እንደከፈለ ሀዘንና ደስታ በተቀላቀለበት ስሜት ይናገራል። በጠላት ጥይት ካጠገቡ የተለዩ፣ መኮንንን የመሳሰሉ ጓደኞቹን በማስታወስ በትካዜ ገድላቸውን ይናገራል። ያ ሁሉ የሆነው፤ ያ ሁሉ ወገን የረገፈው ለዚህች ለአንዲት ኢትዮጵያ እንደነበርና አሁን ላይ የሚያየው ነገር አልጣጣም እያለው በደፈረሰ ስሜት የጁንታውን ከሀዲነት በአፅንኦት ያወግዛል።
“አሁን በአካል ጉዳተኝነትህ ምን ይሰማሀል?” ላልነውም ትከሻውን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ፣ ኮራ ብሎ “ኩራት!!” ካለን በኋላ “ኩራት ነው የሚሰማኝ፤ ለአገሬ ለኢትዮጵያ ስዋጋ
ስለሆነ አካሌን፣ እግሬን ያጣሁት ሁሌም ደስተኛ እንጂ እንዲህ ሆንኩ ብዬ አዝኜም ሆነ ሙሉ አካል ካላቸው የተለየ ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም።” የሚል ነበር የ22ኛ ተራራ ክፍለ ጦር ባልደረባው ወታደር የሰጠን መልስ።
ስለ አሁኑ ዘመን ወጣቶችም አንስተንለት “ወጣቱ እንዳባቶቹ ጀግና፣ አገሩን ወዳድ፣ ለአገሩ ጥሩ ጥሩ ነገር መስራት ላይ ማተኮር፣ አገሩ ከድህነት የምትወጣበትን መንገድ መፈለግ ላይ ማተኮር፤ ጊዜ፣ ጉልበትና እውቀቱን ለአገሩና ለወገኑ የሚጠቅም ተግባር ላይ ማዋል … ላይ ነው ማተኮር ያለበት እንጂ ከማይጠቅመው፣ ለአገርም ለወገንም ከማይበጅ አስተሳሰብ ጋር አብሮ መሄድ የለበትም። ፌስቡክ ምንም አይጠቅምም፤ ይህ ደግሞ የታየ ጉዳይ ነው። ወጣቱን የግለሰቦችና ቡድኖች መጠቀሚያ ማድረግ ህዝብንና አገርን ጎዳ እንጂ ሌላ ምንም ያተረፈልን ነገር የለም። ስለዚህ ወጣቱ ከምንም በላይ አገርን ማስቀደም ነው ያለበት። ምንም አይነት የአገር ፍቅር ከሌለው ጋር አብሮ መጓዝና መጠቀሚያ መሆን የለበትም። በተለይ እዚህች አገር ላይ ከታላላቆቹ የበለጠ ተጠቃሚው ወጣቱ ነውና አገሪቱ የእሱ መሆኗን ተገንዝቦ ለአገሩ ነው መስራት ያለበት እንጂ ሊጎዳት አይገባም።” በማለት ረዘም ያለ ሀሳቡን አካፍሎናል።
“የሰሜን ጦር ግንባር ውሎ እንዴት ነበር?” ብለነውም ነበር። “ከባድ ነው። ከባድ ነበር፤ ከዚህ ሻእቢያ፣ ከዚህ ወያኔ፤ በጎንደር በኩል በማፍረስና ማቃጠል ላይ የተሰማራው የአያልነሽ ጦር ጋር ነበር ፍልሚያው። ብቻ ከባድ ነበር።” ሲልመልሶልናል – ከረን አካባቢ “ፍልፍልታ” እምትባል ግንባር ላይ (በ1981 ዓ.ም) ከጠላት በተወረወረ ከባድ መሳሪያ እግሩን ያጣው፤ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባቱ ወታደር አባስ አሊ።
ብሔራዊ ወታደር ሆኜ በወር 20 ብር የኪስ ገንዘብ (ለሳሙናና ለአንዳንድ ጉዳዮች የሚውል) ብቻ እየተከፈለኝ ነው አገሬን ያገለገልኩት። ወደ መደበኛም ከተዛወርኩ በኋላ 90 ብር ነበር የማገኘው። በዚህ ሁኔታ ነበር ሰራዊቱ ለአገሩ ዋጋ ሲከፍል የነበረው። ዛሬ ያ ስለሆነ እየተሰማኝ አይደለም እየነገርኩህ ያለሁት፤ እንደውም በነፃ በማገልገሌ ኩራት ነው የሚሰማኝ። ይህን የምነግርህ ለአገርና ለወገን ከፍተኛ መስዋእትነት ይከፈል የነበረ መሆኑን ለመግለፅ ነው የሚለው ወታደር አባስ ይህ ጀግንነት፣ ይህ አርበኝነት፣ ይህ ለአገር ከፍተኛ መስዋእትነትን የመክፈል ስሜት ምንግዜም መቀጠል ያለበት የዜጎች ግዴታ መሆኑንም ወታደራዊ ስነልቦናን በተላበሰ ስሜት ይናገራል።
ወታደር አባስ ለአገርና ለወገን ማገልገልም ሆነ የአገር ፍቅር ስሜት የእሱ ብቻ ወይም በእሱ ላይ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነም ነግሮናል።
ወታደር አባስ እንደነገረን ከሆነ ሶስት ወንድማማቾች መከላከያን ተቀላቅለው በሰራዊቱ አባልነት አገልግለዋል። ከሶስቱ እሱና አንደኛው ወንድሙ አሁን በህይወት ሲገኙ (እዚሁ አ.አ) አንደኛው ወንድማቸው እስካሁን የት እንዳለ እንኳን እንደማይታወቅ፤ ለማወቅ ያደረጉትም ጥረት እንዳልተሳካ፤ እዛው ግንባር እንደሄደ እንዳልተመለሰ፤ ይህም
እስካሁንም ድረስ ግራ እያጋባቸው እንደሚገኝ ይናገራል።
ወታደር አባስን ስለወቅታዊው ሁኔታም አንስተንለት ነበር። በተለይ እንደ አንድ የሰራዊት አባል፤ በተለይም እንደ አንድ አካሉን ለአገሩ ሉአላዊነት ሲል መስዋእትነትን እንደከፈለ ሰው ምን እንደሚሰማው ጠይቀነው ነበር። እንዲህ ነው ያለው፤
ይህ ጁንታው ሴይጣን ነው። ድሮም እናውቀዋለን። 27 አመት ሙሉ ሲዘርፍ፣ ሲገድል … ቆይቶ አሁንም አገር አፈርሳለሁ ሲል ትንሽ እንኳን አላፈረም። በ27 አመት ውስጥ ወጣቱን ለጫት፣ ለመጠጥ፣ ለሲጋራ …. ዳርጎት ሄደ። አሁንም መልሶ ወደ ባሰ ሊከተው ይፈልጋል። መጥፋት ነው ያለበት። ደግሞ ኢትዮጵያ አትፈርስም። እኛም እንደዚህ የሆንነው እንድትፈርስ አይደለም። ህዝቡ፣ በተለይም ወጣቱ ይህንን አይፈቅድለትም። ከሁሉም በላይ በመከላከያችን ጀግንነት እተማመናለሁ። ያለ ምንም ጥርጥር ከሀዲው ጁንታ ይመታል፤ ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያጠፋቸዋል።
ወታደር አባስ አሊ – ዛሬ
ወታደር አባስ ዛሬ የሚገኝበት አጠቃላይ ሁኔታ ትናንት ካቆየው አገራዊ ውለታ ጋር የሚመሳሰል አይደለም። ከላይ እንደጠቀስነው ወታደር አባስ አገሩን እስከሚችለውና አንድ ዜጋ ማድረግ ያለበትን ከፍተኛውን ተግባር ለአገሩ ፈፅሟል። ይህን የአርበኝነት ተግባር ይፈፅም እንጂ የዛሬው ሕይወቱ ያንን አያሳይም። ወይም “የውለታው ትሩፋት ይህ መሆን ነበረበት ወይ?” የሚል ጥያቄን ያስነሳል።
“አጠቃላይ ኑሮህ ምን እንደሚመስል እስኪ ለአንባቢያን ንገራቸው” አልነው። ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት መሆኑን፣ ገቢው በግለሰብ ደረጃ እንኳን ማኖር የምትችል አለመሆኗን፣ ከአንድ ሺህ ብር ባልበለጠ የጡረታ ገቢ (እሱም ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከ500 ብር በላይ ጭማሪ በመደረጉ እዚህ የደረሰ) እንደሆነ፤ ከእሱ ጋር አራት፤ አልጋ ላይ ከዋሉት አባቱ ጋር አምስት ቤተሰቦችን እንደሚያኖር፤ በዚህች የጡረታ ገቢው ላይ መርካቶ (ምእራብ ሆቴል) አካባቢ በመንቀሳቀስ፣ በጓደኞቹም ትብብር የተወሰነች ሳንቲምን በማግኘት ኑሮውን እንደሚደጉም፤ በፈራረሰች የቀበሌ ቤት ውስጥ እንደሚኖሩና ሌላውንም በዝርዝር ይናገራል።
“መልካም ነገርስ የለም?” አልነው፤ “አለ” ካለን በኋላ “አሁን ያለነው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ዶ/ር ዐብይ በያዙት እቅድ መሰረት ቤታችን ፈርሶ በብሎኬት እየተሰራ በመሆኑ ነው። እሱ ተሰርቶ እስኪያልቅ ድረስ ነው መጠለያ የገባነው።” በማለት እየተደረገለት ያለውን አድራጎት ከመጣው አገራዊ ለውጥ ጋር አያይዞ በፈገግታ ይገልፃል።
ወታደር አባስ ይህንን ይበል እንጂ ወገቡን አስሮ ሶስቱንም ልጆቹን ያስተምራል። በማስተማሩ ሂደትም በመንግስት የተጀመረው በትምህርት ቤቶች የሚካሄደው የተማሪ ምገባ ፕሮግራም ያገዘው ሲሆን፤ ልጆቹ ሌሎች ጉዳዮች እንዳይጎሉባቸው አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ያደርጋል። ይህን የሚያደርግበትን ምክንያትም “በአሁኑ ዘመን ልጆች መማር አለባቸው። ይህም የሚሆነው ያለ ትምህርት ምንም የሚሆን ነገር ስለሌ” መሆኑን ይናገራል።
“በኑሮህ ደስተኛ ነህ?” ስንለው መልሱ ፈጣን ነበር፤ “አይደለሁም።” “ለምን?” ላልነውም “እኔ ለአገሬ ያደረኩትን፤ እኔ ለአገሬ የሆንኩትን ያህል አገሬ ለእኔ እያደረገችልኝ አይደለም። ሌላው እንኳን ቢቀር በዚህ ደረጃ ልቸገር አይገባም ነበር። ያም ቢሆን ግን አገር አገር ነውና አገሬን አልጠላም፤ አገሬን እወዳለሁ። በአገሬ ጉዳይ ምንም አይነት ድርድር የለኝም። ደሞም ነገ ከነገ ወዲያ የተሻለ ቀን ይመጣል፤ የተሻለ ኑሮ እኖራለሁ ብዬ አስባለሁ። እጠብቃለሁም።” በማለት ነው የመለሰልን።
በአዲሱ አመት ለኢትዮጵያና ለአጠቃላይ ህዝቡ የምታስተላልፈው መልእክት ካለህ በማለት አዲስ ዘመን በጋበዘው መሰረት የሚከተለውን ምኞቱን አስተላልፏል።
እኔ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምመኘው ሰላምን ነው፤ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ አብሮነትን፣ ተከባብሮና ተዋዶ መኖርን ነው የምመኘው። ለአገሬም ፍፁም ሰላም የሰፈነባት እንድትሆን፤ ጦርነት የሌለባት አገር እንድትሆን፤ እንዲሁም ከድህነት እንድትወጣና እንድትበለፅግ ነው የምመኘው። ለሁላችንም መልካም አዲስ አመት!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2014