ፉከራና ቀረርቶ ሽለላና ቀስቃሽ ግጥሞች ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ፈጥረው ለድል ግስጋሴያቸው የሚጠቀሙባቸው ሀብቶቻቸው ናቸው። ኢትዮጵያውያን የአገራቸው ዳር ድንበር ተደፈረ ሉዓላዊነታችሁ ጥያቄ ላይ ወደቀ ሲባሉ አብረው ወደ ግንባር በመትመም ጠላትን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ዳር ድነበርና ነፃነታቸው ጠብቀው ለዘመናት ቆይተዋል።
ጦር ሜዳ ላይ ከስነ-ጽሁፍ ዓይነቶች ስነ-ቃል እና ግጥም ይጠቀሳሉ ፤ ስነቃልና ግጥም ሃሳብን ለመግለጽ ለዛና መዓዛ ያለው የተዋዛ እና በአጭር መልኩ የሚቀርብ፤ አመች እና የማያሰለች ነው። ሁሉም እንደ ሀገሩ ቋንቋና ባህል ፣ ግጥምን በተለየ መልኩ ቢጠቅምበትም ስነ-ቃል በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለየት ያለ ቦታና አገልግሎት አለው። ቀረርቶው ሽለላውና ፉከራው ቅኔዎችና የአዝማሪ ግጥሞች ሁሉ ከስነ ቃልና ግጥም የሚመደቡ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ስነ-ግጥምን በተለያየ መልኩ ይጠቀሙበታል ለኀዘን፣ ለደስታ፣ ለጦርነት ፣ ለፍቅር፣ ለጥላቻ ፣ ለእምነት መግለጫ ፣ በየዘመኑ የሚሾሙ ባለስልጣናትን አገዛዝ ለመግለጽና ማለትም ለማወደስና ለማሞገስ እንዲሁም ለማኮሰስ ለመውቀስ ስነ-ቃልን ይገለገሉበታል። በተለይ ምሳሌያዊ አነጋገሮች በተወሰኑ ሐረጎች ሃሳብን ጨምቀው የመግለጽ እምቅ አቅምና ውበት አላቸው፡፡ ለምሳሌ የጠቀስናቸውን ከጦርነትና ከጀብዱ ጋር የተያያዙ ምሳሌያዊ አባባሎች ለአብነት እነጥቀስ፡- ጎራዴ ለወንበዴ ሱቅ ለነጋዴ፣ ጎራዴና ምስጥ ውስጥ ለውስጥ ፣ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም ፣ ፎክሮ መሸሽ ታሪክ ያበላሽ ፣ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን ፣ያመነታ ተመታ፣ረጅም ጦር ባይወጉበትያስፈራሩበት፣ጦር ሲመጣ ዛቢያ ቆረጣ እና ሳይገድሉ ጎፈሬ ሳያጣሩ ወሬ የሚሉ ብሂሎችን መጥቀስ ይቻላል።
ሥነ ቃል በቃል የሚነገሩት የሚተርቱት የሚገጥሙት የሚያዜሙት እና የሚቀኙት (ቅኔ) በተወሰነ ማኅበራዊ አጋጣሚዎች የሚከወን ቃላዊ ፈጠራ ሲሆን ልዩ ልዩ ክስተቶች የህይወት መልኮች መግለጫ ኪነጥበብ መሆኑን ዘሪሁን አስፋው በሥነ ጽሁፍ መሠረታውያን መጻፋቸው ጠቅሰውታል፡፡
የዚህ ወግና ባህል ባለቤቶች በሆነችው ኢትዮጵያ ሥነጽሁፍና ሥነቃልና ግጥሞች ያዝናናሉ ያጽናናሉ (ያጽናናሉ ያልነው በውጊያ የተሸነፉትን መሆኑ በክብር መዝገብ ይመዝገብልን ) ወኔን ይጭራሉ፣ ጀግናን ይፈጥራሉ በሚል እምነትና እሳቤ ነው። ከላይ እንደገለጽነው ሥነጽሁፎች አገር በወረራ ሳለች ፈሪን የሚገስጹ፣ ተዋጊን የሚያበረታቱ ወይም ወኔን የሚቀሰቅሱ ፣ መጥፎ አለቃን ወይም ጦር መሪን የሚወቅሱና የሚያኮስሱ ይገኙባቸዋል፡፡ ራስ መኮንን ወደ አድዋ በዘመቱ ጊዜ አዝማሪ በዚህ በበረሀ በዚህ በፀሐይ ርትተህ መኮንን ትሄዳለህ ወይ ብሎ ተቀኝቷል፡፡ የመጨረሻው ንጉሥ ቀ.ኃ.ሥ በጣልያን በአምስት ዓመቱ ወረራ በማይጨው ጦርነት ተሳታፊ ነበሩ፤ በወቅቱ በግጭቱ የንጉሡ ሠራዊት ተሸነፈ፡፡ ምክክር ተደረገና በዲፕሎማሲያዊ መድረክ እንዲከራከሩ በወቅቱ ወደ ነበረው መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ሄዱ፡፡ የዛኔ ሁኔታውን የተመለከቱ ባለ ቅኔዎች በሽሙጥም እንዲህ ብለውም ነበር፡፡ በወቅቱ ገጣሚ ዮፍታሄ ንጉሤ
«ያልተገራ ፈረስ ጠቅል እያላችሁ ፣
ይኸው ፈረጠጠ ባህር ገባላችሁ»
ብለው ተቀኝተው ነበር ፡፡ ጠቅል የንጉሡ የፈረስ ስም ሲሆን ንጉሡ አባ ጠቅል በሚል ስያሜ ይጠሩ ነበር፡፡
በወቅቱ በርግጥ ንጉሡ በጀኔቫ ያደረጉት ንግግር ታሪካዊና ትንቢት መሳይም ነበረ፡፡ ‹‹ እንዲህ ዓይነት ወረራ ሲፈጸምብን የመንግሥታት ማኅበር እንደ መቋቋሚያ ዓላማዎቻችን መሠረት እኛን ካልረዳችሁን በመጪው ጊዜ ከናንተ መሀል ጉልበተኛው ሌላውን ይወረዋል፡፡ ›› ብለው ነበር ፤ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተቀስቅሶ ንጉሡ እንዳሉትም እነሂትለር እነሱኑ (ፈረንጆቹን) ቀጠቀጡ አንቀጠቀጡ፡፡በአገር የቀሩ አርበኞችም ትግላቸውን ቀጠሉ፤እነ ራስ አበበ አረጋይ በወቅቱ ጦርነት ሲያደርጉ አዝማሪ
በለው በሙዳይ በለው በሙዳይ
ያን ሽንታም ሰላቶ(ጣሊያን) አበበ አረጋይ
(ሙዳይ የመሣሪያ አይነት ነው) ብሎ ገጥሞላቸው ነበር፡፡ሽንታም ያልነው የተሰመረበት ቃል ዋናው ቃል ለጽሁፍ ጸያፍ ስለሆነ ቀይረነው መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን፡፡
በአምስቱ ዓመት የጣልያን ወረራ ጊዜም ባለቅኔው ጸሐፌ ተውኔት ዮፍታሄ ንጉሤ በስደት በሱዳን ሆነው ወኔ የሚጭሩና ተስፋ የሚፈጥሩ ግጥሞች ገጥመው ነበር
«ጎበዛዝቴ ሆይ ወይ ቆነጃጅቴ፣
ምንኛ ነደደ ተቃጠለ አንጀቴ፣
እንመለሳለን ባዲሱ ጉልበቴ፣
እናንተም ተምርኮ እኔም ተስደቴ፡፡»
* * *
« አዳም አባታችን ደከመህ ምንኛ፣
ስናውቅ እንዳለብህ በገነት ምቀኛ፣
በገዛ ርስታችን ሲገባ ምቀኛ፣
ወደ ውጪ አንቀርም ተለይተን እኛ፡፡ »
“ሰሚ ያጡ ድምጾች” ከሚለው መጽሀፍ በግጥም ይቀርቡ ከነበሩ በትውፊት የተገኙ ሥነ-ቃሎችን መካከልም ከላይ እንደገለጽነው ወኔ የሚጭሩ ፈሪን የሚያንጨረጭሩ (የሚያበሳጩ) ናቸው። ወደዚያው እንለፍ።
በለው በለው ሲል ነው የጋሜ ኩራቱ፣
ሴትም ትዋጋለች ከረጋ መሬቱ።
ሂድ ሲሉት ካልሄደ፣ ና ሲሉት ካልመጣ፤
ስደደው ጎበዙን እጁን ይዞት ይምጣ።
ሱሪህን ከፍ አድርግ፣ ጎራዴህን ቀና፤
ከዚያም ቤት ከዚህም ባለድል ነህና።
ከላይ የጠቀስናቸው ሥነቃሎችና ግጥሞች ሀገርኛ ልክና መልክ ያላቸው ናቸው፡፡ ዜጋው አገሩን ከወረራ ለማዳን እየታገለ ነው፡፡ የኪነጥበብ ሰዎችም የድርሻቸውን ለመወጣት እየጣሩ ነው፤ ውጤቱን የምናየው ይሆናል፡፡ አዲሱ ዘመን ተስፋ የሚያጭር ብሥራት የምንሰማበት በጦርነቱ ያዘኑት እምባቸው የሚታበስበት የታላቁን ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ብርሃን የምናይበት ነው፡፡ የዜጎች ትብብር ግን አሁንም መጠናከር አለበት፤ ሠራዊቱና ሚሊሻው ውስጥ ተሰግስገው የሚያሤሩትንና የመንግሥት ምንደኛ የባንዳ ቅጥረኛ ሆነው
ጠላትማ ጠላት ምንጊዜም ጠላት ነው
አስቀድሞ መግደል አሾክሻኪውን ነው
እንደሚባለው በሁለት ቢላዋ የሚበሉትን ማጋለጥና ለፍትሕ ማቅረብ ትኩረት ይሰጠው፡፡ ህብረታችን ጠንክሮ አንድነታችን በርትቶ በጋራ ከቆምን ሁሌም አገራችንና ህዝባችን ነፃነታቸውን ጠብቀው ሁሉም ይቀጥላሉ፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2014