የተማሪዎች መመዝገቢያ ወቅት በሆነው የነሐሴ ወር መጨረሻ አካባቢ አንድ መረጃ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። ይሄውም እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ዓመታዊ ክፍያ ያለባቸው የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ነው።
እንግዲህ እዚህ ትምህርት ቤት የሚያስተምር አቅም ያለው ሀብታም ስለሆነ ለከፋዮች አያስጨንቃቸውም እንበል! ዋናው ጥያቄ ግን ያለው አገራዊ ፋይዳ ምንድነው? ከዚህ ትምህርት ቤት የሚወጡ ልጆች ምን የተለየ ነገር ያገኙ ይሆን? ቅጥ ያጣ ቅንጦትና ምቾት በበዛ ቁጥር አካባቢያቸውን የመመርመርና የማወቅ ዝንባሌያቸው አይቀንስም ወይ? የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና አካባቢውን ያላወቀ ትውልድ ለአገሩ ምን አይነት ችግር ፈቺ ምርምር ይሰራ ይሆን?
ምናልባት ይሄ የጥቂት ትምህርት ቤቶች (ምናልባትም የአንድ ትምህርት ቤት ብቻ) ሊሆን ይችላል። የዋጋ ውድነት እና ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ግን ተደጋግመው ሲነገሩና ሲታዩ የቆዩ ናቸው።
አሁን ወቅቱ የትምህርት መጀመሪያ ነውና እስኪ እነዚህን ነገሮች እናስተውል።
እንደምናየውም፣ እንደምንሰማውም፤ የግል ትምህርት ቤት ተመራጭ ነው የሚባልበት ምክንያት ለትምህርት ጥራት ተብሎ ነው (ከግል ትምህርት ቤት የወጣ ተመራማሪ ባንሰማም)።
የግል ትምህርት ቤት ለሀብታም ልጆች የሆነበት ምክንያት ደግሞ ከመክፈል አቅም ጋር ተያይዞ ነው። ድሃ ወላጅ ለግል ትምህርት ቤት የሚሆን የመክፈል አቅም ስለሌለው የመንግስት ትምህርት ቤት ያስገባል። ጉዳዩ ከክፍያ ጋር መሆኑ ነው ነገሩን የፉክክር ያደረገው። የሀብታምና የባለሥልጣን ልጆች ለስማቸው ክብር ሲባልም ቢሆን የግል ትምህርት ቤት ይገባሉ ማለት ነው።
እኔ ያልታየኝና ያልገባኝ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ‹‹አለ›› የተባለው የትምህርት ጥራት ነው። ምናልባት የተማርኩት የመንግስት ትምህርት ቤት ስለሆነ የግሉን ስለማላውቀው ይሆናል። ለጊዜው ወላጅ ስላልሆንኩ ልጅ በማስተማርም በቅርበት አላየሁትም። ይሄ ማለት ግን ስለግል ትምህርት ቤቶች ምንም አላውቅም ማለት አይደለም። የሙያዬም ባህሪ ነውና ተደጋጋሚ ሥራዎችን ሰርቻለሁ። ብዙ ነገሮችን ታዝቤያለሁ። በቅርበት ከማውቃቸው ጓደኞቼ ብዙ ገጠመኝ አስተውያለሁ። በትምህርት ቤቶች እየገባሁም ለማስተዋል ችያለሁ።
ለማንም ሰው ግልጽ ከሆነው ስያሜያቸው ልጀምር። የግል ትምህርት ቤት ሆኖ አገራዊ ስያሜ ያለው ብዙም አላጋጠመኝም። እንዲያውም የአንዳንዶቹ ቃሉን እንኳን ለመጥራት ማስታወሻ ለመያዝ የሚያስገድዱ ናቸው። ትርጉማቸውን ለማወቅም የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ወይም የኢንተርኔት መረብን መበርበር የሚያስገድዱ ናቸው። የሚገኘው ትርጉም አንድ የውጭ አገር ታሪክ ይነግረናል። ቃሉ ብቻ ሳይሆን ሀሳቡና ክስተቱ ራሱ የውጭ ይሆናል።
በአገር ባለውለታዎች፣ በአገር ውስጥ ቋንቋ፣ በአገር ውስጥ ታሪክ፣ አገር ውስጥ በተከሰተ መልካም ክስተት ተሰይመው የሚታየው የመንግስት ትምህርት ቤቶች ናቸው። የትምህርት ቤቱ ስም ራሱን ችሎ አንድ ነገር ያስተምራል። እቴጌ መነንም ሆነ የካቲት 12 የኢትዮጵያ ታሪክ እና የኢትዮጵያ ሰዎች ናቸው። ምኒልክ ትምህርት ቤትም ሆነ በላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት የኢትዮጵያ መሪዎችና አርበኞች ናቸው። ኮከበ ጽባህም ሆነ ምሥራቅ ጎህ ኢትዮጵያዊ ስያሜ ያላቸው ናቸው።
እነዚህ ስያሜዎች ቀላልና ተራ ነገር አይደሉም። ለታዳጊ ሕጻናትና ልጆች ብዙ ነገር እያሳወቁ ነው። በየትኛውምአጋጣሚ የትምህርት ቤቶች ስም ሲጠራ የባለታሪኮች ስም እየታወሰ ነው። አፌ ላይ የመጡትን ጠቀስኩ እንጂ የብዙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ስያሜ አገራዊ ስም ያለው ነው። እንግዲህ አንዱ የታዘብኩት ነገር ይሄ የስያሜ ልዩነት ነው። ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ልጆች፣ አድገው አገራቸውን ለሚያገለግሉ ልጆች የግል ትምህርት ቤት በአገራዊ ስያሜ ቢሰየም ምን ችግር አለው? ወይስ ውጭ አገር ካሉ የስያሜው ባለቤቶችና ባለታሪኮች በማስታወቂያ መልክ የሚያገኙት ጥቅም አለ ይሆን?
ሌላው የግል ትምህርት ቤቶች ላይ በሰፊው የሚነሳው ሐሜት ትኩረታቸው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ላይ መሆኑ ነው። ምንም ችግር የለውም! ነገሮችን ለመረዳት፣ ዓለም አቀፍ ሰው ለመሆን እንግሊዘኛ ወሳኝ ነው። ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የእንግሊዘኛ ችሎታ የሚጠይቁ ናቸው። እንግሊዘኛ ፈጣን መሆን የማያከራክር ጥቅም አለው፤ እንዲያውም በዚህ ዘመን ግዴታ ነው።
ችግሩ ግን እንግሊዘኛ ብቻውን ዕውቀት ነው ወይ ነው! የቋንቋ ጥቅም ለመግባባት ነው። እንግሊዘኛ ማወቅ ብቻውን የፊዚክስ ተመራማሪ አያደርግም። የኬሚስትሪ ሊቅ አያደርግም። የተፈጥሮን ምሥጢር ለመመርመር አገርኛ ነገሮችን ማወቅ የግድ ይላል። ‹‹አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ያስቀጣል›› በማለት የአገር ውስጥ ቋንቋን መጣል የትም አያደርስም።
ምናልባት ልጆቹ ትምህርት ሲጨርሱ ከአገር ውጭ እንዲሰሩ ይሆን? ለአገራቸው እንዲያገለግሉ ከሆነ የአገሩን ቋንቋና ባህል አራግፎ የጣለ ትውልድ አገር ሊረከብ አይችልም። ለምሳሌ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ የሚሆን ከሆነ፤ ወይራ፣ ጽድ፣ ዋንዛ፣ እሬት፣ ፌጦ…… የመሳሰሉ አገር በቀል ሀብቶችን ማወቅ ነበረበት። የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ የሚሆን ከሆነ፤ ዓድዋን፣ የገዳ ሥርዓትን፣ ሽምግልናን፣ አሸንዳን፣ ጨምበላላን ማወቅ አለበት። እነዚህን ነገሮችየሚያውቀው ከአካባቢው ሰዎች ነው። ከአካባቢው ተረትና ምሳሌዎች ነው። የአካባቢው ተረትና ምሳሌዎች፣ ተረኮች፣ ታሪኮች ደግሞ የተሰነዱት በእንግሊዘኛ ሳይሆን በአገሩ ቋንቋዎች ነው። ከእነዚህ ነገሮች የራቀ ተማሪ የማያውቃትን አገር ነው የሚረከብ።
እነዚህ ነገሮች የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ በብቃት እየተሰጡ ናቸው ማለቴ አይደለም። እንዲያውም ቢያንስ በእንግሊዘኛው እንኳን የግል ትምህርት ቤቶች ሊሻሉ ይችላሉ። የመንግስት ትምህርት ቤት በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰማው ቅሬታ ግደለሽነትና ክትትል ማጣት ነው። መምህሩ ከፈለገው ወር ሙሉ ክፍል ላይገባ ይችላል። ክፍል ውስጥ ገብቶም እንደፈለገው ቀልዶ ሊወጣ ይችላል። በዝርክርክነት የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ ያለው ውድቀት ይከፋል። ዳሩ ግን ምን ዋጋ አለው! ከፍተኛ ቁጥጥር ቢያደርጉም የግል ትምህርት ቤቶች ልጆችን ከአገራዊ ነገሮች እያራቋቸው ነው።
ትኩረቴን የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ያደረኩበት ምክንያት የጥራት ማሳያ ናቸው ሲባል ስለምሰማ ነው። የትኛው ምጡቅ ተመራማሪ እንደወጣ ስላልሰማሁ ነው። እንግሊዘኛ ላይ መራቀቅ ብቻውን ተመራማሪና የፈጠራ ሰው ሊያደርግ ስለማይችል ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የሀብታምና የባለሥልጣናት ልጆች ብቻ መሆኑ ነው። የሀብታምነት መለያው ጎበዝና ተመራማሪ ተማሪ ከመፍጠር ይልቅ የትምህርት ቤቱ ስም ብቻ መሆኑ ነው። የመንግስት ባለሥልጣን የመንግስትን ብቃት እያቆለጳጰሰ ልጁን የሚያስተምር ግን የግል ትምህርት ቤት ነው። በየደረሰበት ግን የመንግስትን የትምህርት ጥራት ያወድሳል። ይሄ ባለሥልጣን የመንግስትን የትምህርት ጥራት አያምንበትም ማለት ነው፤ ወይም ደግሞ የግል ትምህርት ቤት ብቻ የሚያስተምር ለስሙ ክብር ብቻ ነው ማለት ነው።
የግል ትምህርት ቤቶች ልዩነታችሁን በፈጠራችኋቸው ልጆች እውቀት አሳዩን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2014