በአንድ አገር ውስጥ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ በሆነ ምክንያት ትልቅ ችግር ካጋጠመ እና ችግሩን በመደበኛው የተቋማት እና የህግ አሰራር መቋቋም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ከተደረሰ ብሔራዊ የአገልግሎት ጥሪ ማስተላለፍ የተለመደ ነው:: የብሔራዊ አገልግሎት ጥሪ የሚባለው ደግሞ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ሁሉም ዜጋ አገልግሎት ሊሰጥበት የሚገባ የአገልግሎት አይነት ነው::
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ ምስጋናው ጋሻው እንደሚናገሩት፤ ብሔራዊ አገልግሎት ለጋራ አገራዊ ለሆነ ጉዳይ ከዜጎች የሚጠበቅ አገልግሎት ነው:: ይህ ብሔራዊ አገልግሎት በብዙ አገራት ከወታደራዊ ተሳትፎ ጋር የተያያዘ መሆኑ ይጠቀሳል:: በተለይ አገራት በውጭ ሃይል ወረራ ወይም ከውስጥ በአማፂያን ወይም በሌላ ሃይል የአገር አንድነት ወይም ህልውና አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ከመደበኛው የአገር መከላከያ ሰራዊት ወይም ከፖሊስ ወይም ከሌላ የፀጥታ ሃይል በተጨማሪ ዜጎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ የሚቀርብበት ሥርዓት ብሔራዊ አገልግሎት ይባላል::
ከጦርነት በተጨማሪ እንደመሬት መንቀጥቀጥ እና የእሳት አደጋ ማለትም ስፋት ያለው ቃጠሎ ሲያጋጥም፣ ጎርፍ ወይም ወረርሽኝ ሲመጣ አገራት በመደበኛው አሰራራቸው መቋቋም ካልቻሉ ብሔራዊ ጥሪ ያቀርባሉ:: በዚህ ጊዜ ዜጎች ይሳተፋሉ ማለት መሆኑን ይናገራሉ:: ይህ በአንዳንድ አገሮች በህግ በግዴታ መልክ የሚቀመጥ ሲሆን፤ አንዳንዶች ደግሞ በፍቃደኝነት ነገር ግን ሁኔታውን ሳቢ በማድረግ በማበረታቻ ዜጎቻቸውን የሚያሳትፉ መሆኑን ይናገራሉ::
የህዝብ ቁጥራቸው ትንሽ የሆነባቸው አገራት የመከላከያ ወታደር ቁጥር ያንሳል ብለው ከገመቱ ለምሳሌ እንደእስራኤል እና ኖርዌ የመሳሰሉ አገራት ብሔራዊ አገልግሎትን በህግ እንደ ግዴታ ያስቀምጣሉ::
መንግስት ማንንም ሰው ለወታደራዊ አገልግሎት በሚፈልግበት ጊዜ እምቢ ማለት አይችልም ይላሉ:: ይህ በአሜሪካም የተለመደ ሲሆን ከ1940ዎቹ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 18 ዓመት የሞላው እና ለወታደራዊ አገልግሎት አካላዊ እና አእምሯዊ ብቃት ያለው ዜጋ በሙሉ ሲፈለግ ግዴታ እንዳለበት የሚያስቀምጡ መሆኑን ያስረዳሉ::
ከኢትዮጵያ አንፃር የነበረውን እና ያለውን የህግ ማእቀፍ የሚያብራሩት አቶ ምስጋናው እንደሚያስረዱት፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የወታደር ሥርዓት ወይም ቋሚ ሰራዊት በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት የተጀመረ ነው:: ከዛ በፊት በህግ ያልተፃፈ ክተት ሲባል ሁሉም ዜጋ እየተሳተፈ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና ጦርነቶች በድል መወጣት ተችሏል ይላሉ::
እንደ አቶ ምስጋናው ገለፃ፤ መከላከያን የሚመለከት ህግ መውጣት ከጀመረበት ጊዜ ማለትም በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የነበረው ህግ ሲታይ ጉዳዩ ግዴታ ነው አይደለም የሚለው ግልጽነት ይጎድለዋል:: በደርግ ዘመነ መንግስት የወጣው የ1979ኙ ህገመንግስት ግን በውትድርና መሳተፍ መብትም ግዴታም መሆኑን በግልጽ አስቀምጦታል:: መንግስት ሲፈልገው ግዴታ ይሆናል:: መሳተፍ እፈልጋለሁ የሚል ዜጋ ከመጣ ደግሞ እንደመብት ተቀምጧል:: አንድ ሰው በአካልም በአዕምሮም ያለው ብቃት የተሟላ ከሆነ እንደመብት በውትድርና መሳተፍ ይችላል::
ከዛ በኋላ ያሉት ህጎች ደግሞ ከ1987ቱ ህገመንግስት የሚመነጩ ናቸው:: አሁን በስራ ላይ ያለው ህገመንግስት እንደ 1979ኙ ህገመንግስት በግልፅ አያስቀምጥም:: ነገር ግን የተለያዩ አንቀፆች ተገጣጥመው ሲታዩ ለወታደራዊም ሆነ ለሌላ ብሔራዊ አገልግሎት ግዴታ መሆኑን የሚሳዩ አንቀፆች አሉ ይላሉ:: ለምሳሌ በህገመንግስቱ አንቀፅ 18 ንዑስ አንቀፅ 4 ‹‹ለ›› እና ‹‹ሐ›› ላይ ወታደራዊ አገልግሎትን እምቢ ማለት እንደማይቻል ያስቀምጣል:: በሚደረግ ጥሪ መሰረት መሳተፍ ግዴታ መሆኑን በተዘዋዋሪ ይገልፃል ይላሉ::
ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ህሊናው የማይፈቅድለት ሰው በምትኩ የሚሰጠውን አገልግሎት የመፈፀም ግዴታ እንዳለበት የሚያስቀምጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ በሃይማኖት ክልከላ ከሌለበት ሰው ውጪ ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት ግዴታ መሆኑን ያስቀምጣል:: የህገመንግስቱ አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ ህገመንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር የሁሉም ዜጎች ግዴታ እንደሆነ የሚያስቀምጥ መሆኑንም አቶ ምስጋናው አብራርተዋል::
በህገመንግስቱ አንቀፅ 18 ንዑስ አንቀፅ 4 ‹‹ሐ›› ላይ የማህበረሰቡን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጨምር ነገር ሲያጋጥም ሁሉም ዜጋ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ሲታይ ወታደራዊ አገልግሎት ወይም ሌሎች የአገርን ደህንነት እና ህልውና የህብረተሰብን ህይወት አደጋ ላይ በሚጥሉ ጉዳዮች ላይ ዜጎች የመሳተፍ ግዴታ እንዳለባቸው ያስቀምጣል ብለዋል:: ይህ ግዴታ ዜጎች በሰላም ጊዜ የሚጠይቋቸው መብቶች ነፀብራቅ መሆኑንም ነው የህግ መምህሩ የሚያብራሩት::
ከህገመንግስቱ በተጨማሪ በአገሪቱ በወንጀል ህግ ላይም ስለብሔራዊ የአገልግሎት ግዴታ መቀመጡን ይናገራሉ:: በወንጀል ህጉ አንቀፅ 284 በግልጽ እንደተቀመጠው ወታደራዊ አገልግሎትን እምቢ ማለት ካለ በኋላ ጉዳዩን ሲያብራራው ማንኛውም ሰው በወታደርነት የመቀጠር ወይም የማገልገል ወይም የክተት አዋጅ ወይም የማስታወቂያ ጥሪ ሲተላለፍ፤ አለመፈጸም እና በወታደርነት እንዲመዘገብ ወይም በክተት አዋጅ መሰረት በየግንባሩ ቀርቦ እንዲያገለግል በግል በተደረገለት ጥሪ፣ በአደባባይ በተለጠፈ ማስታወቂያ ወይም በመገናኛ ብዙኃን በተነገረ ማስታወቂያ የተላለፈውን ትዕዛዝ ያልመፈጸም በቀላል እስራት ይቀጣል ይላል።
ወንጀሉ የተፈፀመው የጦር አደጋ ምልክት የተሰጠበት፣ የጦር ክተት የታወጀበት ወይም በጦርነት ጊዜ ከሆነ፣ ቅጣቱ ከአስር ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እስራት ይሆናል። የሚሉት አቶ ምስጋናው፤ ይህ ማለት ልክ አሁን ኢትዮጵያ በምትገኝበት ሁኔታ ላይ ይህንን አገልግሎት መስጠት ግዴታ መሆኑን እና አስር ዓመት እንደሚያስቀጣም ነው የተናገሩት::
በወንጀል ህጉ አድርጉ የተባለውን ማድረግ ግዴታ ነው፤ አታድርጉ የተባለውን ደግሞ አለማድረግ ግዴታ መሆኑንም አብራርተዋል:: ወታደራዊ ጉዳዮች የተደነገጉበት የአገር መከላከያ ሠራዊት አዋጅ 1100/2011 ላይም ምንም እንኳ ዝርዝር ጉዳዮችን ባይደነግግም የብሔራዊ ተጠባባቂ ሃይል መኖርን አስመልክቶ ያስቀምጣል ብለዋል:: ቋሚ ውል ይዞ ተቀጥሮ ወታደራዊ ሃይል ሆኖ ከማገልገል ውጭ የብሔራዊ ተጠባባቂ ሃይል እንደሚቋቋም በአዋጁ የተቀመጠ መሆኑን ጠቅሰዋል::
በተጨማሪ የብሔራዊ ተጠባባቂ ሃይል ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 327/1996 መኖሩን አስታውሰው፤ ይህም ዜጎችን ወታደራዊ ስልጠና እያሰለጠነ ተጠባባቂ ሃይል አድርጎ ማስቀመጥ ይችላል ማለት መሆኑን ተናግረዋል:: ተጠባባቂው በሚፈለግበት ጊዜ አገልግሎት ይሰጣሉ ማለት ነው ብለዋል::
በመጨረሻም አቶ ምስጋናው፤ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔራዊ አገልግሎት ማለትም ወታደራዊም ሆነ ሌላ አገልግሎት መሽጠት ግዴታ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል:: ነገር ግን ከህጉ በተጨማሪ ትልቁ ነገር የሞራል ግዴታ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ብሔራዊ አገልግሎት የህግ ግዴታ ነው አይደለም ብሎ መከራከር አይገባም ብለዋል:: የአገርን ህልውና ማስጠበቅ የሞራል ግዴታ መሆኑንም አስታውሰው፤ ትውልዱ ታሪካዊ ግዴታን መወጣት አለበት ለቀጣዩ ትውልድ ዕዳ እና የተበላሸ ታሪክ ማስተላለፍ እንደሌለበት ገልጸዋል::
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 14/2013