ከራስ መጀመር ጥሩ ነው። ለእውነተኛ መንፃት ትክክለኛ ጅማሮ እሱ ከማለት ይልቅ እኔ እነሱ ከማለት በፊት እኛ ማለት ተገቢ ነው። እኔ ለአገሬ ምን አደረኩ ወይም እኛ ለዚህች አገር ምን ሰራን? እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን ተወጥተናል ወይ የሚለውን መጠየቅ ፈለኩ። ጎበዝ ይህንን ጥያቄ ወደ እናንተ ለማቅረብ ያነሳሰኝ አንዲት ጋናዊት ሰሞኑን ስለኢትዮጵያ ያለችውን ካደመጥኩ በኋላ ነው። በልጅትዋ አንደበት ለገዘፈችው ለዚህች ታላቅ አገር እኔ ያበረከትኩት አነሰብኝ። በተለይ አሁን በወሳኝ ሰዓት ምን አደረኩ? ምንስ እያደረኩ ነው ወደፊትስ ምን ለማድረግ አቅጃለሁ ብዬ እራሴን መመርመር ፈለኩ።
ለጥያቄዬ መነሻ የሆነችኝ ልጅ ጋናዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለችም፤ እስዋ ስለ ኢትዮጵያ ያለችውን ሰማሁ ኢትዮጵያን የገለፀችበት መንገድ ተመለከትኩና እኔ ስለኢትዮጵያ ያደረኩት ከሚዛን ጎደለብኝ። ልጅትዋ ምን አድጋ ነው ለምትሉኝ ደግሞ ልንገራችሁ። ይህቺ ቆንጅዬ ጋናዊት አገርዋ ላይ በተደረገ የቁንጅና ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክላ ስለ አገሬ ኢትዮጵያ የተናገረችው እየሰማሁ ጆሮዬ ጠገበ፣ ልቤ በደስታ ቀለጠ፣መንፈሴ እረፍትን ተጎናፀፈ።
ይህቺ የቁንጅና ውድድር ላይ ኢትዮጵያን በተለየ መልኩ ያስተዋወቀችው ቆንጆ ኢትዮጵያዊ እንጂ ፈፅሞ ጋናዊ አትመስልም። በወኔ ኢትዮጵያን ስትገልፅ በኩራት የኢትዮጵያን ታሪክ ስታስረዳ ተደመምኩ ከዚያም እራሴን እንድጠይቅ አደረገችኝ። በእስዋ መነፅር እራሴን አገሬን መልካም ነገርዋን ለማስተዋወቅ ምን አደረኩ ክፋትዋን ለማስወገድ ታላቅነትዋ ለማለበስ ምን ሰራሁ ብዬእራሴን ጠየኩ።
ይሄኔ የእኔ ተግባር ተራ መሆኑ፤ የእኔ ጥረት ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተረዳሁ። ይህቺ ወጣት ጋናዊ ናት ግን ስለ አገሬ ኢትዮጵያ ያወራችው እኔ ኢትዮጵያዊው እስካሁን ስለ አገሬ ካደረኩት ይገዝፋል። ይህቺ ቆንጆ ወጣት ስል እኔ አገር ያስተዋወቀች እኔ አገሬን ለዓለም ከገለፅኩት ጋር አይወዳደርም። ስለ አገሬ አገርዋ ባልሆነ ወጣት የተነገረው ገዘፈብኝና እራሴን ታዘብኩት።
ወገን እኛ ግን የት ነው ያለነው? ኢትዮጵያ የምትጠብቅብን ተወጥተናል? ከእኛ ለዚህች አገር የሚገባውን አድርገናል? ይህ ነው ጥያቄዬ። እያንዳንዳችን መልሳችን አይ በፍፁም ከሆነ አደጋ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያችን በተሰማራንበት መስክ ሁሉ አጥብቃ የምትፈለገን ጊዜ ላይ ናት። ከውጭና ከውስጥ የተጋረጠባት ስጋት በእኛው በውድ ልጆችዋ በተባባረ ክንድ ካልቀረፍን በቀር የመጣው ሁሉ ይከፋል።
ዛሬ ኢትዮጵያ እጆችዋን ዘርግታ የልጆችዋን ብርቱነት ትሻለች። ልጆችዋ በጋራ እንዲጠብቅዋትና ከተጋረጠባት አደጋ እንዲገላግልዋት በብርቱ ትፈልጋል። ይሄኔ ነው የእኛ ልጅነት መረጋገጥ ያለበት። ይሄኔ ነው፤ አገሬ እምዬ ቤቴ ያለናት ይህቺን ውብ አገር እውነትም ሁለ ነገራችን መሆንዋን በተግባራዊ ምላሽ መረጋገጥ ያለበት።
ዛሬ በአጥፊው ቡድ የበዙ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለዋል። ኢትጵያን ሊንዱ ባቀዱ ቡድኖች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ኢትዮጵያውያን ተቸግረዋል። እኛ ደግሞ በቻልነው ከወገኖቻችን መቆም በምንችለው ሁሉ እነዚህን ወገኖቻችንን መርዳት ያለብን ጊዜ ላይ ነን። በክፉ ቀን ነቅና ወዳጅ የሚለየው ዛሬ በተፈጠረው መልካም ያሆነ ገጠመኛችን ጠላታችን ማሸነፍ የሚያስችለንህብረታዊ አንድነት መታጠቅ ይኖርብናል።
ያኔ አገራችን አሸናፊነትዋ ይቀርባል። ይህቺ ሁሉም ድል አድራጊ የሆነችው አገር ዛሬም ድል ማድረግዋ ይቀጥላል። ልጅትዋ ኢትዮጵያዊ ሳትሆን ስለኢትዮጵያ ባለችው መልካም ነገር በዚያ ውድድር ላይ አሸናፊ ያደረጋት የኢትዮጵያ አምላክ ሳይሆን አይቀርም። እኛም ስለኢትዮጵያ ከልባችን ስንሰራ የኢትዮጵያ አምላክ ይረዳናል።
ጎበዝ ኢትዮጵያ የራስዋ አምላክ አላት፤ የሚባለው ለአባባል እንዳይመስልህ። ይህቺ ውብ አገር የሚጠብቃት አምላክ መኖሩን ካለፉት ታሪኮችዋና ዛሬ እየሆነ ካለው ብዙ መረዳት ትችላለህ። ወዳጄ እንደጠላቶችዋ ተደራራቢ ሴራና እንደ ሀያላኑ ጥረትና ፉከራ ዛሬ የቆምንባት ምድር እኛ የምንጠራባት ኢትዮጵያ የምትባል ሳይሆን በቀረች ነበር። ግን አምላክ ይጠብቃታልና ብርቱ ልጆች አሏትና እስከዛሬ ፀንታ ቆይታለች። ነገም በእርግጠኝነት ተጠብቃና ፀንታ ትኖራለች።
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በወራሪው ቡድን ምክንያት፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ወገናችን ችግር ላይ መውደቁ ደጋግመን እየሰማን ነው። ይሄኔ ለወገናችን አለኝታ መሆናችንን ማስመስከር ከጎናቸው መሆናችን ማረጋገጥ ይገባል። ወገን አገር ስትፈልግ ካልተገኙ ወገን ባሻው ጊዜው አለሁ ካላሉት ከባድ ነው።
የወዳጅ እና ጠላት መለያው ክፉ ቀን ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ሊያድንዋት ሌትቀን በሚለፉ ብርቱ ልጆችዋና ሊበትንዋት ከሚያሴሩ ጠላቶችዋ ጋር ፍልሚያ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ልጅ መሆን አልያም አለመሆን እውነተኛነት መለያው ቀን ላይ ነን። እናም በዚህ ደመናማ ወቅት ብርሃን ሆኖ መገኘት በዚህ ወሳኝ ጊዜ የቁርጥ ቀን ልጅ ሆኖመገኘት ያስፈልጋል።
በእርግጥ ይህቺ የጀግኖች መገኛ የሉዓላዊነት ምሳሌ የሆነች አገር አሸናፊነትዋ እርግጥ ነው። ነገር ግን ለዚህ አሸናፊነትዋ እኛ ምን አበረከትን ምንስ አስተዋፅዖ ነበረን ብለን እራሳችን የጠየቅን ቀን መልስ ካጣን ከባድ ነው። በዚህ ወሳኝ ሰዓት እራስን ሰጥቶ ወገንን ማዳን እራስን ከፊት አሰልፎ አገር መጠበቅ ይገባል። በዚህ ክፉ ቀን ሰው ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል። እውነተኛ ሰውነትን የተላበሰ ሰው ሆኖ ሰውን መርዳት የተቸገረን ወገናችንን መርዳት ይገባል።
ሁለት የተለያየ ቀን አለ፤ አንዱ ብረሃናማና ፍካት የተላበሰ ሌላው ደግሞ ጭጋጋማና ፅልመት የለበሰ። ሁለቱም ተፈጥሯዊ ሂደት ነውና ይፈራረቃሉ። ሌላም አይነት ሁለት መልክ ያላቸው ቀናት አሉ። አንደኛው የደስታና የፍስሐ ሌላኛው ደግሞ የኀዘንና የትካዜ። በእነዚህ ተፈራራቂና ተለዋዋጭ ቀናት የማይለወጥ ሰው ሆኖ መገኘት ይገባል። ብርሃኑ እንዲፀና፣ ጭጋጉ እንዲገለጥ፣ ደስታው እንዲቀጥል፣ ፍስሀው እንዲዘልቅ ደግሞ ህብረትና አንድነት ወሳኝ ነው። በአብሮነት ሳቅ ይበረክታል።
አዎ እውነተኛ ወዳጅ ከጠላት የሚለየው እንዲህ ባለ ቀን ነው። እንጂ ነገ መውጣቱ አይቀርምና በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ፀሀይ ሲወጣ፤ ደመናው ሲገፈፍ ሁሉም አለው ቢላት ምንም ነው። ይሄኔ ነው ለሀገር ካስማ ለወገን ጥላው ሆኖ መገኘት። ወገን ዛሬን ተካፍለህ በልተህ ነገ አብረህ ከወገን ጋር መሻገር የዜግነትም የሰብዓዊነትም ግዴታህ ነው። በሴራ የተጎዱትን ወገኖችን አግዝ ሳትሰስት ያለህን እንካችሁ በል፤ አገርህ ከጠላቶችዋ ለመጠበቅ ሉዓላዊነትዋን ከተዳፈረው አጉራ ዘለል አጥፊ ነፃ ለማድረግ ደግሞ ቆርጠህ ተነስተህ ቆራጥ እርምጃን ውሰድ። አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2014