ስንቶቻችን በደካማው መንፈሳችን ታስረን እየማቀቅን ይሆን? ፍላጎትና ድርጊታችን አልጣጣም ብሎን እምንባዝንስ ምን ያህሎቻችን ነን? «አንድ ዓይነት ነገር እያደረጉ የተለየ ውጤት መጠባበቅ እርሱ እብደት ነው» ይላሉ ስኬታማ ሰዎች የድላቸውን መነሻና ምክንያት ሲናገሩ። የዕለት ምቾታችን ውስጥ ታጥረን የወደፊት ሕይወታችን ያስጨንቀናል፤ ዛሬን ሳንቀይር ስለ ነገ እናስባለን። አንድ ዓይነት ድርጊት ውስጥ ሆነን የተለየ ውጤት እንጠብቃለን፣ አስገራሚ ስኬት እንመኛለን።
ይሄ ትውልድ እጅግ ከባድ በሆኑ ፈተናዎች የታጠረ ነው። ከዚህ ማቅ ውስጥ ለመውጣት ደግሞ አጥሮ ከያዘው ምቾት ከሚመስል እንቅፋት ውስጥ መውጣት ይኖርበታል። አሁን ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የተጋረጡበትን ችግሮች በጣጥሶ ማለፍ የማይታሰብ ነው። መድረስ ከፈለገ፤ ጉዞውን አንድ ብሎ መጀመር ይኖርበታል።
የወጣቱ ተስፋ የሆነችው ኢትዮጵያ ከያቅጣጫው እንደቆዳ በወጠሯት ችግሮች ተከባለች። የዚህች አገር መዳኛ ደግሞ ማንም ሳይሆን ተስፋው የሆነችው እራሱ ወጣቱ ትውልድ ነው። ለዚህ ነው አርቴፊሻል ከሆነው ምቾት ውስጥ ወጥቶ አገሩን ከጠላትና ከወራሪ ኃይል ሊታደጋት ይገባል የምንለው። ይህን እንዲያደርግ ደግሞ ይሄ ትውልድ «ኃይሉንና አቅሙን» ሊያውቀው ይገባል። ከዶሮዎች ጋር ያደገው ንስር ዘመዶቹ ሲበር ሲመለከት ልክ እንደ «ዶሮዎቹ» እንደቀናው ሁሉ ወጣቱም በጊዜያዊ ሱስና ለመንፈሱም ለስጋውም በማይጠቅሙ አተካራዎች ውስጥ ተጠምዶ አርበኝነቱንና አገር ተረካቢነቱን የዘነጋው ይመስላል።
በእርግጥ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሲነኩ እንደ ቀፎ ንብ የሚተምም እጅግ በርካታ አዲሱ ትውልድ እንዳለ መረዳት ቢቻልም ይሄንኑ የሚያክል አያሌ ወጣት በአልባሌ ቦታ ሆኖ ኃይሉንም ሞራሉንም እየገደለ መሆኑን መገንዘብ ቀላል ነው።
ለምሳሌ ያህል በቅርቡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍልወራሪው ትህነግ በኢትዮጵያዊነት ላይ በከፈተው አስከፊ ጦርነት ላይ ቀድሞ ከፊት የተሰለፈውና ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ አገር አፍራሾችን እየመከተ ያለው ይኸው ወጣት ቢሆንም በተመሳሳይ በፕሮፓጋንዳ የሚረበሸው፣ ተራ አሉባልታ ውስጥ የተጠመደው፣ በሱስ አቅሉን ስቶ አሁን ኢትዮጵያዊነት ምን ዓይነት ፈተና ውስጥ እንዳለ መገንዘብ ያቃተው የዚሁ ትውልድ ክፋይ ነው።
መብረር እየቻለ አቅሙን እንዳያገናዝብ የመፋዘዝ አባዜ ውስጥ ሰምጦ የሚገኝ፤ እውነትም የሚታደገው አንዳች ብልሃተኛ የሚሻ «ከጠፉት በጎች» መካከል የሆነ እጅግ በርካታ ወጣት በየመንደሩ እንዳለ እርግጥ ነው። በቅርቡ እንኳን የፍቅር አገር፣ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ አስኳል የሆነችው «ወሎ ደሴ ከተማ» ላይ አደንዛዥ እፅ የሆነ እንደ «ጫት» የመሳሰሉ ጉዳዮች መከልከላቸው ምን ያህል ወጣቱ እንዲነቃና ተደራጅቶ አካባቢውን እንዲጠብቅ እንዳገዘው መመልከት ጥሩ ምሳሌ ነው። ልክ እንደዚሁ ሁሉ የወጣቱን አቅም የሚገልጥና አሁን ያለበት አርቴፊሻል ምቾት እርሱንም አገርንም ገደል ይዞ እንደሚገባ የሚያስገነዝበው ብልሃት ይሻል። የሚቀጥለው አስተማሪ ታሪክ ደግሞ የአገሬ (ሁሉም ሳይሆን አንዳንድ) ወጣት ያለበትን ስሁት መንገድ በሚገባ ገልጦ እንደሚያሳይ እምነት አለኝ።
በአንድ ወቅት ለጋስ እና ደግ ልብ ያለው ንጉሥ ይኖር ነበር። ወፎችን እና እንስሳትን ይወድ ነበር። እናም በመንግሥቱ ውስጥ ትልቅ የወፍ መኖሪያ ነበረው። እንስሳትንና ወፎችን መጉዳት አይወድም። ለመብላትና ለስጋ ብሎ እንኳን አልገደላቸውም። ለአእዋፍ ለጋስነትቱና ቸርነት በማሳየቱ ምክንያት አድናቆትን በማግኘቱ፣ አንድ ነጋዴ ሁለት ውብ «ንስሮችን» በስጦታ አበረከለተለት። እነዚያ ሁለቱ ንስሮች የተለያዩ የአየር ንብረት ሁኔታዎች ውስጥ የነበሩ ናቸው።
ንጉሱ በስጦታው በመደሰቱም ነጋዴው አመስግኖ በግቢው ውስጥ ተቀጥሮ ለሚሰራው የወፍ አሰልጣኝ ለንስሮቹ ሁሉንም መገልገያዎችን እንዲያቀርብ እና በአገራቸው ውስጥ ምቾት እንዲሰማቸው እንዲያደርግ አዘዘው። ዋና አሠልጣኙ ወፎቹን ይንከባከብ ጀመር። ቀስ በቀስ ንስሮቹ ከአገሪቱ የአየር ሁኔታ ጋር መጣጣምና መኖር ጀመሩ።
ከዕለታት አንድ ቀን ንጉሱ ከንስሮች አንደኛ በፍጥነት ወደ ከፍተኛ ቦታ መብረር እንደቻለ በመስማቱ ሁኔታውን በዓይኑ ለመመልከት ፈለገ። ንጉሱ በመምጣቱ የአእዋፍ አሰልጣኙ ጭልፊቱን ከግቢው እንዲወጡ አደረገ። ይህ በኃይል ይበራል የተባለው ንስርም ልክ እንደተነገረው ሁሉ በጣም በፍጥነት መብረርና ትርኢት ማሳየት ቻለ። ትርኢቱን እንደጨረሰም በደቂቃዎች ውስጥ ወደ ቅጥር ወረደ። ንጉሱ በጣም ተገርሞ ለወፍ አሰልጣኙ እፍኝ የወርቅ ሳንቲሞችን ሸለመው። ትንሽ ሲቆይ ግን ስለ ሌላው ንስር ጠየቀው።
የአእዋፍ አሰልጣኙ ሌላው ጭልፊት አንድ ቀን እንኳን አንድ እርምጃ እንኳን እንዳልተንቀሳቀሰ እና በቅርንጫፉ ላይ እንደተቀመጠ በሐዘን ተናገረ። አሰልጣኙ ልክ እንደ አንደኛው ብቃት እንዲኖረው የሚቻለውን ሁሉ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም አሁንም ከተቀመጠበት ቅርንጫፍ ላይ ግን ሊያንቀሳቅሰው አልቻለም ነበር።
ንጉሱ ቀጣሪውን አለማማጅ በሁኔታው እንዳያዝን አፅናናውና ሌላውን ንስር በጥሩ ሁኔታ ለማሠልጠን ልምድ ያለው ሰው እንደሚያመጣ ነገረው። በንጉሱ ትእዛዝ መሠረትም በመላው ግዛቱ ማስታወቂያው ተነገረ።
ይህንን ማስታወቂያ የሰማው አንድ አዛውንት ወደ ንጉሱ ቤተ መንግሥት ደርሶ እንደ ሌላኛው እንዲበር እንደሚያደርግ አረጋገጠ። ንጉሱም አሠልጣኙ አዛውንቱን ወደ አእዋፋት መኖሪያ ወስደው ንስሩን እንዲያሠለጥኑለት ፍቃዱን ሰጠው። ለውጥ ካለ ለማየት በሚቀጥለው ቀን እንደሚጎበኛቸው ተናግሮ ነበር። በማግስቱ ቃሉን በሰጠው መሠረት በቦታው ተገኘ።
በተመለከተው ነገር ግን በእጅጉ ተገርሞ ነበር። ሌላኛው ንስር እንደ መጀመሪያው በፍጥነት ወደ ታላቅ ከፍታ ሲበርር በማየቱ በጣም ተደሰተ። ለአረጋዊው ሰው እፍኝ የወርቅ ሳንቲሞችን ሰጠው። ከዚያም አዛውንቱን ንስሩ በአንድ ቀን ውስጥ እንዲበር እንዴት ማድረግ እንደቻለ ተገርሞ ጠየቀው። አዛውንቱ ፈገግ ብሎ «ጭልፊት የሚቀመጥበትን የዛፉን ቅርንጫፍ ቆረጥኩ» ሲል መለሰለት።
ብዙዎቻችን እንደዚህ ነን። በተለይ አዲሱ ትውልድ። ለመብረር ክንፎች አሉን፤ እንዴት መብረር እና የት መብረር እንዳለብን ግን አናውቅም። ያለን አቅምና ኃይል አንገነዘብም። በዚህ ምክንያት ምንም የማድረግ አቅም እናጣለን። ወይም ከሌሎች የምናንስበትን አንድ ነገር እንሠራለን። ለመብረር ክንፍ እያለን እንኳን ዝም ብለን እንቀመጣለን! ትውልዱ ይንቃ የተቀመጠበትን ቅርንጫፍ ሰብሮ አገሩን ዳር ድንበሩን ይጠብቅ። ያን ካደረገ ዘንዳ ተስፋው እና የማንነቱ መገለጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ ታፍሮና ተከብሮ በደስታ ይኖራል።
የዮቶር ክንድ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2014