የዘንድሮን አዲስ ዓመት እኛ ኢትዮጵያውያን በተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ ሆነን ተቀብለነዋል። ምንም እንኳን መተኪያ የሌላት አገራችን በምጥ ውስጥ ብትሆንም እንደ ነገሩም ቢሆን የተፈናቀሉ ወገኖቻችንንና በችግር ውስጥ የወደቁ ኢትዮጵያውያንን እያሰብንም ቢሆን ደመቅመቅ አድርገን ለመዋል ጥረት አድርገናል።
ከ2013 የተረፈው ችግራችን ወደ 2014 ተሻግሯል። ይሁን እንጂ እንቅፋት የሆኑብንን እባጭ ጠላቶቻችንን አፍርጠን ዳግም ቀጣዩን ዓመት በተስፋ ለመቀበል በአንድነት ቃል የገባንበትም አዲስ ዓመት አንድ ብለን እንደጀመርን ግን ምንም ጥርጥር የለንም። ለዚህ ነው ዛሬ ካለፉት ስህተቶቻችን መማር ያሉብን በርካታ ጉዳዮች ስለሚኖሩ እንደሚከተለው እያነሳን እርስ በእርስ ልንማማር ይገባል።
እኛ ኢትዮጵያውያን አሁን «የህልውና ጦርነት» እያደረግን ነው። ይህ ትግል ደግሞ ከአንድ አቅጣጫ ሳይሆን በዙሪያችን ባሉ ሁሉም አካላት የተከፈተብን ነው። በዋናነት ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ መሽጎ የሚገኘው ትህነግ፤ በተለያዩ አቅጣጫዎች እንደ ፈሪ ከቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ እየገባና እየወጣ ንፁሃንን የሚገድለው ሸኔ በጋራ ከውስጥ ሆነው አገር ከሚያፈርሱ አካላት ጋር ተባብረው እየሰሩና እናት አገራቸውን እየወጉ ያሉበት ጊዜ ነው። በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከምን ጊዜውም በተለየ ሁኔታ መንግሥትና ሕዝብ ይህን ኃይል ለመመከት በርካታ ሥራ ሰርቷል። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች የዘረጉትን የፕሮፓጋንዳና የጥፋት መረብ በሚፈለገው ልክ መበጣጠስና ስኬታማ ድል ማስመዝገብ ግን አልተቻለም።
በተለይ ግንባር ላይ የሚገኘውን ድል በፕሮፓጋንዳው ሜዳ መድገም ተስኖን ብዙ ነጥቦችን መጣላችንና ዋጋ መክፈላችን ያሳለፍነው ዓመት ትዝታችን ነው። ታዲያ ይሄን ከምዕራባውያን ፍላጎት ጋር ተሳስሮ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ህልም ለማምከን የተዘረጋ መረብ እንዴት ማምከን ይኖርብናል። ይህን ከማየታችን በፊት በመንግሥትም ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ የነበሩትን ደጋማ ጎኖች መመልከቱ ተገቢ ጉዳይ ነው።
ከ2013 መሻገር የሌለበት ሽንቁራችን
መንግሥት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለማድረግ ያደረገውን እንቅስቃሴ በመግታት «የተናጠል ተኩስ አቁም» ካወጀ ከሁለት ወራት በላይ አስቆጥሯል። እስከምናውቀው ድረስ ይህን ውሳኔ መንግሥት ያሳለፈው አርሶአደሮች የክረምቱን የዝናብ ወቅት ተጠቅመው እንዲያርሱና እንዳይራቡ ብሎም ሕዝቡ አሸባሪው ኃይልን በጉያው የመያዙን ጉዳይ በጥሞና እንዲያስብበትና አጋልጦ ለመስጠት የማሰቢያ ጊዜ እንዲያገኝ በሚል ነበር። ሆኖም ይህን የመንግሥትን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ትህነግ ይብሱኑ ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርገነዋል ብሎ በማወጅ የአማራና የአፋር ክልሎችን ወርሮ በሕዝቡ ላይ እጅግ ዘግናኝ እልቂትና ለመንገር የሚከብድ መከራን እያደረሰ ነው።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ምዕራባውያን ሚዲያዎችና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትበቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን መከራ ችላ ብለው አሁንም በትግራይ ክልል ትህነግ እየፈጠረ የሚያወራውን ፕሮፓጋንዳ ማስተጋባት አላቆሙም። ይህ እውነታ የሚያመላክተን እነርሱ «እውነታውን» ለመሸሽ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር እኛ የያዝነውን «ሃቃችንን» ለማሳየትና ለመሞገት የምናደርገው ጥረት አሁንም ክፍተት እንደሚታይበት ነው።
በእርግጥ በማህበራዊ ድረ ገፅም ሆነ በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች ግለሰቦችና ለአገር የሚያስቡ አካላት መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍና እየፈተነን የሚገኘውን ፕሮፓጋንዳ ለማክሸፍ አስመስጋኝ ሥራዎች እየሰሩ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ በተቀናጀና በትላልቅ «የሎቢስት» ካምፓኒዎች እየተመራ የተከፈተው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማጠልሸት ፕሮፓጋንዳ ሙሉ ለሙሉ ማክሸፍ አልተቻለም።
እውነት ጫማዋን እስክታስር ውሸት ብዙ ርቀት ትሮጣለች እንደሚባለው የትህነግ አምላኪ ድልብ ዲያስፖራዎች፣ በዓለም አቀፍ አደባባይ ላይ ያለ ሃፍረት ሲንደባለሉና የአዞ እንባ ሲያነቡ አብረዋቸው ድንኳን ጥለው የሚቀመጡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ተቋማት አሁን በአማራና በአፋር ክልል በመቶ ሺዎች ሲፈናቀሉ የት ይግቡ የት ልናውቅ አልቻልንም። ሆኖም ይህ የእነርሱ ግብ ከመሆኑ አንፃር ብዙም ልንገረም አይገባም።
ይልቁኑ እኛ ስንበደል፣ ሰብአዊነት ሲረገጥ፣ ሴቶች ሲደፈሩ፣ ሕፃናት በጭካኔ ሲገደሉ በበቂ መረጃና በተቀናጀ የዲፕሎማሲ ሥራ የተደበቀውን እውነት በራፋቸው ድረስ በመውሰድ «አውቀው ቢተኙም» በግድ ቀስቅሰን ልናሳያቸው ይገባል። ከዚህ አንፃር መንግሥትም ይሁን በበጎ ፍቃድ ፕሮፓጋንዳ የመመከትና እውነትን የማጋለጥ ሥራውን የሚሰሩ አካላት «የመጨረሻውን ኃይል አሟጠው» እና ዲፕሎማሲያዊ ጥበብን አክለውበት ከ2013 ወደ 2014 የተሻገረውን የህልውና ትግል በድል ልንቋጨው ያስፈልጋል።
በዚህ በያዝነው አዲስ ዓመት እውነታውን ያልተገነዘቡ አሊያም ደግሞ ተገንዝበው ዓይናቸውን የጨፈኑ ምዕራባውያን ከአገር አፍራሽ የእናት ጡት ነካሽ ኃይሎች ጋር አብረው ለቅሶ እየተቀመጡ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የመሞከራቸውን ሃቅ ዋጥ ልናደርገው ይገባል። ይህን ማድረግ ከቻልን እያንዳንዱን ሽንቁር እየተከታተልን የመድፈን አቅም ይኖረናል። በተለይ ይህንን ስሁት አካሄድ ማንኛውንም መስዋእትነት ከፍሎ መመከት ያስፈልጋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባረጀው የዲፕሎማሲ አካሄድ አሁን የተጋረጠብንን ፈተና መወጣት እንደማይቻል መንግሥት የተረዳው ይመስላል። ይህን ሥራ የሚያስተባብሩ ተቋማትንም ለመለወጥ ጠንክሮ እየሰራ እንደሆነ እየተመለከትን ነው።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማሲ አካሄዱን፣ መድረኩን የሚያሳልጡ ባለሙያዎችንና ባለስልጣናትን አካሄድ ሁሌም ቢሆን ያለማቋረጥ ደግሞና ደጋግሞ መፈተሽ እንደሚኖርበት ለመጠቆም እንወዳለን። ይህ ሲሆን አብረናቸው ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የምንሰራቸውን አገራት በወዳጅነታቸው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ከመቻላችን ባሻገር ለአዲሱ 2014 ዓመት የተሻገረውን የትህነግ አሸባሪ ኃይል እብሪት በግንባር ላይ ከሚገኘው ድል ጋር ተደምሮ በዲፕሎማሲውና በፕሮፓጋንዳው አፍረክርኮ እስከወዲያኛው ማጥፋት እንደሚቻል እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ለዚህ ነው በተደጋጋሚ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን በጥልቀት ይፈትሽ እያልን የምንጮኸው። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2014