በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በሰላም ማስከበር ዙርያ በመተከል ወንበዴዎችን በማደን የተሠራን ሥራ ይዘናል ቀርበናል፡፡ ግጥምጥሞሽ ሆኖ ዛሬም አካባቢው ላይ አሁንም ለሚታየው ሰላም መደፍረስ ፀጥታ ኃይሉ በመናበብ መሥራት እንዳለበት የዛኔው ሰላም አስከባሪ ስራ በማሳያነት አነሳን፡፡ ሕገወጥ ንግድን በመቆጣጠርና በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ያጠነጠኑ ዜናዎችም አዲስ ዘመን የቀድሞ ዕትሞችን ስናገላብጥ ያገኘናቸው መረጃዎች ናቸው፡፡
ልጅ ወልዳ የጣለች ተከሰሰች
ከተወለደ በግምት 3 ቀን ይሆነዋል ፤የተባለው ሕፃን ልጇን ከግንፍሌ ወንዝ ዳር ጥላ በዚሁ ምክንያት የተከሰሰችው ፀሐይ ተገኝ ወህኒ ገባች፡፡ ዕድሜዋ ፳ ዓመት የሚሆናት ኮረዳ የወለደችውን ልጅ ከወንዝ ዳር ጥላለች በመባል የተከሰሰችው ነሐሴ ፮ ቀን ከቀኑ ፲፩ ሰዓት መሆኑን የአቃቤ ሕጉ ክስ ያመለክታል፡፡
ተከሳሿ የወለደችውን ልጅ ለመጣል ዋነው ምክንያት ምን እንደሆነ ከፍርድ ቤት ለቀረበላት ጥያቄ ስትመል ከአልባሌ ሰው በመጽነሷ ችግሯን ለመበገር ባለመቻሏ መሆኑን አመልክታለች፡፡ ፀሐይ ጳጉሜ ፫ ቀን አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ቀርባ ለጠበቃየምትከፍለው የሌላት መሆኗን ብታመለክት የመንግሥት ጠበቃ እንዲከራከርላት ታዟል፡፡
ተጥሎ የተገኘው ሕፃን ሕይወቱ ካለፈ በኋላ በአንድ ተላላፊ መንገደኛ ታይቶ በአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አማካይነት አስከሬኑ ለምርመራ ወደ ሐኪም ቤት መላኩ ታውቋል፡፡ በጣቢያው አማካይነት በተደረገው መከታተል የጣለችው ሴት ወዲያው ተገኝታ ሁኔታው በምርመራ ተጣርቶ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡ ተከሳሿም የነገሩ ፍሬ በፍርድ ቤት አግባብ እስቲጣራ በቀጠሮ ማረፊያ ቤት ቆይታለች፡፡
(ጳጉሜ 4 ቀን 19 62 ከወጣው አዲስ ዘመን )
ከመተከል 50 ወንበዴዎች በአዳኝ ቡድን ተያዙ
ብረ ማርቆስ (ኢ/ዜ/አ/)፡- በመተከል አውራጃ አስተዳደር በሠፊው ሕዝብ ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ሲያደርሱ የቆዩት ፶ ወንበዴዎች ሰሞኑን ውንብድና ለማጥፋት በተሰማራው አዳኝ ቡድን ተይዘዋል፡፡
በሻለቃ አበበ ደስታ የአውራጀው ፖሊስ አዛዥ በአቶ ደስታ ተሰማ የጓንጉ ወረዳ አስተዳዳሪና በግራዝማች ተደሰ ጀምበሬ የሚመራው ይኸው የአዳኝ ቡድን ወንበዴዎቹን የያዘው ከሰኔ ፲፭ ቀን እስከ ፳፮ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ/ም/ ድረስ ባደረገው አደን መሆኑን በአውራጀውበተቆጣጣሪነት የተመደቡት የዐሥር አለቃ ያለው ሺበሺ ገልጠዋል፡፡
የተያዙትም ወንበዴዎች በፖሊስ ጣቢያና በወህኒ ቤት የሚገኙ ሲሆን፤ የወንበዴዎቹ አዳኝ ቡድን አሁንም የማደን ተግባር እደቀጠለ መሆኑን የአውራጃው አስተዳዳሪ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
( ሐምሌ 1 ቀን 19 67 ከወጣው
አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የሞጆ ከተማ ሕዝብ ለሥራ አጦች መጠለያ አሠራ
ናዝሬት (ኢ.ዜ.አ.)፡- በየረርና ከረዩ አውራጃ በሎሜ ወረዳ የሚገኘው የሞጆ ከተማ ሕዝብ ገንዘብና ጉልበቱን በማስተባበር፤ በከተማው ለሚገኙ ፵፱ ወዛደሮች አንድ መጠለያ ቤት ሠርቶ ማስረከቡን የወረዳው አስተዳዳሪ ገልጠዋል፡፡
ሕዝቡ ይህንን የመጠለያ ቤት በኅብረት ሠርቶ ያስረከበው ያለ በቂ ሥራ በከተማ ውስጥ ይዘዋወሩ የነበሩን እነዚህ ፵፱ ወዝአደሮች ችግር በመመልከት መሆኑ ተገልጧል፡፡ አቶ ተስፋዬ ጣሰው የተባሉ በጎአድራጊም ለቤቱ ክዳን የሚሆን ፻ ቆርቆሮ በግል ገዝተው መስጠታቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ በተጨማሪ ገልወጠዋል፡፡
ከዚሁም በቀር የሞጆ አካባቢ የኅብረት ማኅበር አባሎችና የወረዳው የእርሻ ሚኒስቴር ሠራተኞች ለእነዚሁ ችግረኞች ወዝአደሮች ፪ ጋሻ ተኩል መሬት አርሰው ማስረከባቸው ተገልጧል፡፡
(መስከረም 8 ቀን 1968 የወጣው
አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ሁለት ሕገወጥ ነጋዴዎች 5500 ብር መቀጫ ተፈረደባቸው
ድሬ(ኢ.ዜ.አ)፡- በድሬ ከ፪ የታወቁ ነጋዴዎች ከተወሰነው ዋጋ አስበልጠው በመሸጥና የመብል ዘይት የንግድ ሚኒስቴር ያልመዘገበውን የምግብ ዘይት ለሕዝቡ በማከፋፈል በቀረበባቸው ክስ 5500 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የድሬዳዋ 3ኛ ወንጀል ፍርድ ቤት ትናንት ፈረደ፡፡
ከተቀጡት ነጋዴዎች ውስጥ ሐጂ ሙሜ አህመድ የተባሉት ከድሬዳዋ ጥጥ ኩባንያ በውክልና አንድን ኪሎ ቁርጥራጭ ጨርቅ በ0.75 ሳንቲም ከተረከቡ በኋላ ለአነስተኛ ነጋዴዎች አንዱን ኪሎ ቁርጥራጭ ጨርቅ ከ6 ብር እስከ 10 ብር እየሸጡ ብዙ ዓመት ሲጠቀሙ በመቆየታቸው በአነስተኛ ልብስ ሰፊዎች አመልካችነት በድሬዳዋ አውራጃ አስተዳዳሪ በአቶ ሳሙኤል ተፈሪ አማካይነት ጉዳዩ ከሕግ ፊት ቀርቦ በማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው 3000 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ተወስኖባቸው ገንዘቡን ወዲያውኑ ከፍለዋል፡፡
ሐጂ በዚህ ሥራ መጠቀም የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ1964 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ባዘጋጀው የፍርድ ሀተታ ገልጦ፤የድሬዳዋ ጥጥ ኩባንያ ግን ተከሳሹ እስከአሁን ምን ያህል ኪሎ ጨርቅ እንደወሰዱና ምንያህል ጥቅም እንዳገኙበት ሲጠየቅ ‹‹ለዚህ የተለየ መዝገብ የለንም›› በማለት ሳይገለጥ መቅረቱ ተገልጧል፡፡
እንደዚሁም አቶ ያኒዮር ጋሲት የተባሉ ድሬዳዋ የሚገኘው የዘይት ፋብሪካ ባለቤት ለቸርቻሪ ነጋዴዎች ፩ን ኪሎ የመብል ዘይት በ፩ ብር ከ፷፭ ሳንቲም ማከፋፈል ሲገባቸው ብር ከ፹፬ ሳንቲም በመሸጣቸውና ንግድ ሚኒስቴር ያልመዘገበውን የዘይት ዓይነት ሠርተው ዋጋውን ሳይተምኑ ፩ን ኪሎ በ፪ ብር ፴፭ ሳንቲም ሲሸጡ በተቆጣጣሪዎች ተደርሶባቸው ለቀረበባቸው ክስ በምስክርና በማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት ፪ሽህ፭፻ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ወስኖባቸው ተከሳሽም ገንዘቡን ወዲያውኑ ከፍለዋል፡፡
ተከሳሹ ሊሸጥ ከሚገባው በላይ በመሸጥ በጥር ፩ ቀን ፷፯ ዓ/ም/ ፵፬ ሽህ ፫፻፴፫ብር ከ፳፫ ሳንቲም ማግኘታቸውን በፍርድ ቤቱ በፍርድ ሀተታቸው ተገልጧል፡፡
(ሰኔ 26 ቀን 1967 ከወጣው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014