መላው ኢትዮጵያዊ ዘመን ተለውጦ ዘመን ሲተካ፤ አሮጌውን ሸኝቶ አዲሱን ዓመት ሲቀበል፤ እንደ አደይ አበባ ፍካት እንደ ቄጤማው ልምላሜ ሁሉ በተስፋ ፍንጣቂ ይሞላል። እንደ ንስር እራሱን አድሶ ለስኬት፣ ለፍቅርና ለአንድነት ቃልኪዳን በማሰር ከወዳጅ ዘመዱ ጋር ይሰባሰባል። ተፈጥሮ ጭጋጉንና ጉሙን ሸኝታ በብርሃን ድምቀት እንደምትሞላው ሁሉ ኢትዮጵያውያኖቹም በይቅርታ፣ በፍቅርና በብሩህ ተስፋ ይሞላሉ።
አዲስ ዓመት ሁሌም ይናፈቃል። ሁሉም የአገሬ ሰው በዚህ ጊዜ በደስታ ይቅበጠበጣል። ከላዩ ላይ እርጅና የሚለውን ስሜት ገፍፎ ደምቆና አምሮ ይታያል። በሸኘው ዓመት ያገኘውን ድል በአዲሱ ደርቦ ደራርቦ ስኬታማ ለመሆን ያቅዳል። ማንፀባረቁ የፊት ገፅታው ላይ ሲገለጥ፣ ማማሩ ደግሞ ከባህላዊ እሴቱ በተቀዳው ማራኪ አልባሳት በማጌጡ ላይ ይታያል። በአጠቃላይ አዲስ ዓመት ሁሌም አዲስ ሁሌም ፍካትን የሚሻበትና “አሃዱ” ብሎ ዳግም የሚነሳበት ወቅት ነው።
ሁሌም አዲስ ዓመት “አዲስ” ነገር የሚታይበት ነው። በተለይ በ”ፋሽኑ” ዘርፍ። ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች በእንቁጣጣሽ በዓል ጊዜ በውብ ባህላዊ አልባሳት የሚሰናዱበትና በከተማዋ ሽር ብትን የሚሉበት ነው። በዓሉ መስከረም አንድ ላይ ከመከበሩ አስቀድሞ በጳጉሜን ቀናቶች በመዲናዋም ሆነ በሁሉም የአገሪቱ ከተማዎች እና ገጠራማ አካባቢዎች ወጣቶች በባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ አድርገው ይታያሉ።
የአልባሳትና የጌጣጌጥ ነጋዴዎች እንቁጣጣሽ ከመምጣቱ አስቀድሞ ሱቆቻቸውን በባህላዊ አልባሳት ይሞላሉ። ንግዱ በያቅጣጫው ይሟሟቃል። በተለይ ዲዛይነሮች አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር “አደይ አበባንና ባህላዊ ስርዓቱን” መነሻ በማድረግ ልዩ ልዩ የመዋቢያ አልባሳትንና ጌጣጌጥን ያስተዋውቃሉ። ሸማቾች ሱቆችን ያጨናንቃሉ። ለመሆኑ አዲስ ዓመት ሲመጣ የፋሽን ዲዛይነሮች፣ በፈጠራ የተካኑ ወጣቶች በምን መልኩ ሥራዎቻቸውን ወደ ገበያ ያቀርባሉ? ሸማቾችስ ምን ዓይነት አልባሳትና የዲዛይን የፈጠራ ውጤቶች ቀልባቸውን ይገዙታል? የዝግጅት ክፍላችን “አዲስ ዓመትና ፋሽን” በሚል እንደሚከተለው ከእንግዶቻችን ጋር ተጨዋውቷል።
በረከት ግርማ ይባላል። የቤኪ የቲሸርትና ስቲከር ፕሪንቲንግ ባለቤት ነው። “የሌይ አውትና ዲዛይን” ባለሙያ ቢሆንም ቀለል ያሉ አልባሳትን ዲዛይን የማድረግ ክህሎት አዳብሯል። ወቅትን ጠብቀው በሚመጡ በዓላትና ዝግጅቶች ላይ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በቲሸርቶች ላይና በተለያዩ ቀላል ልብሶች ላይ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን በማከል ይሠራል። በበዓል ቀናት ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚወክሉ ሥራዎች ያትማል። ለምሳሌ ያክል በዘንድሮው አዲስ ዓመት ክነሐሴ ወር ጀምሮ እጅግ በርካታ ቲሸርቶችን በነማተም ለገበያ ማብቃት ችሏል። በቲሸርቶቹ ላይም የኢትዮጵያውያንን አዲስ ዓመት የሚወክል አደይ አበባ እንዲሁም የተለያዩ ባህሎችን የሚያንፀባርቁ ምስሎችን፣ የአገር ልብስ ጥለቶችን በማዋሃድ ቲሸርቶቹን ለሽያጭ ማቅረቡን ነው የሚናገረው።
“በከተማዋ በባህላዊ እሴቶች ያጌጡ ቲሸርቶች ረጃጅም ቀሚስ መሆን የሚችሉ በፊደላት የተዋቡአልባሳት ይታያሉ” የሚለው ዲዛይነር በረከት ወጣቱ በአዲስ መንገድ ባህሉንና መገለጫውን እንደሚያስተዋውቅና በዚያም እንደሚያጌጥ ይናገራል። እርሱም ፍላጎቱን መሰረት በማድረግ በየጊዜው ዲዛይኖችን በመለመዋወጥና ፍላጎትን ለማሟላት ይሠራል። በዋናነት ግን ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊ እሴት እንዳይለቁና የበዓሉን ድባብ የሚያደምቁ መሆናቸውን በቅድሚያ እንደሚያረጋግጥ ነው የሚገልጸው።
ሕፃናትም ቤተሰቦቻቸው መርጠውና ተጨንቀው በአዲስ ፋሽን ሲያስጌጧቸው፣ ውበታቸውን ሲጠብቁላቸውና በአደባባይ አምረው እንዲታዩላቸው ጥረት ሲያደርጉ መመልከት የተለመደ ነው። በተለይ በዓል ሲመጣ ከሁሉም በተለየ መንገድ ሕፃናት በአልባሳትና ጌጣጌጥ ይዋባሉ። የዓመት በዓሉ ድምቀት ሆነው “ወዲያ ወዲህ” ሲሉ መመልከት ከምንም በላይ ያስደስታል። ታዲያ የፋሽን ኢንዱስትሪው በየጊዜው አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን እያከለ የሕፃናት ጌጣጌጥና አልባሳትን ወደ ገበያው ይዞ ብቅ ይላል። ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል ደግሞ ዲዛይነር ትዕግስት ብርሃኑ ትገኝበታለች።
ዲዛይነር ትዕግስት የተወለደችውና ያደገችው ዝጎራ በሚባል አካባቢ በእስቴ ወረዳ በደቡብ ጎንደር ነው። በጊዜው እንደማንኛውም የአካባቢው ልጅ ከጎረቤት ተጫውታ አስኳላ ገብታ የልጅነት ጊዜዋን አሳልፋለች። ይሁን እንጂ አባቷ ጎበዝ ነጋዴ ስለነበሩ የእርሳቸውን ባህሪ እንድትወርስ የራሴ ያለችውን ተሰጥኦ ያለምንም ችግር እንድታዳብር ትልቅ ዕድል ከፍቶላታል። ከልጅነት ጀምሮ ጠንካራ ሠራተኛና ለስኬቷ የምትተጋ ያደረጋት የእርሳቸው አርአያነት ሲሆን፤ ትምህርቷን ከመከታተል ባለፈ ቤተሰቦቿን አቅሟ በፈቀደ መንገድ በሥራ ታግዛቸው ነበር።
ይህቺ ትጉህ ዲዛይነር ሁሌም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ሕፃናት በባህል አልባሳት እንዲንቆጠቆጡ ተግታ ትሠራለች። በተለይ በእንቁጣጣሽ በዓል ላይ ልዩ ልዩ ዲዛይኖችን ትሠራለች “ሕፃናት በጌጣጌጥና አበባ የተንቆጠቆጠ አልባሳት በበዓላት መልበስ በእጅጉ ያስደስታቸዋል” የምትለው ትዕግስት እርሷም ይህን ታሳቢ በማድረግ ልብሶቹን ሠርታ ለገበያ እንደምታቀርብ ትናገራለች። ለሕፃናቱ ፍላጎት ደግሞ በዋናነት የአገራችን የዘመን መለወጫ መገለጫ የሆነውን “አደይ አበባ” እንደምትጠቀም ትናገራለች። ይህን ኢትዮጵያዊ ውበት የሚያላብስ የተፈጥሮ ስጦታ በአልባሳት ላይ ብቻ ሳይሆን በፀጉር ላይ በሚሰካና ውበትን በሚያላብስ ልዩ “የአደይ አበባ” ስቲከር ሠርታ እንደምታቀርብም ነግራናለች።
እንደ መውጫ
ከመብላትና ከመጠጣት ባሻገር የሰው ልጅ እርካታን ከሚጎናጸፍባቸው መንገዶች አንዱ ውበት ነው። በተለይ የዓመት በዓላት ሲደርሱ ደግሞ ይሄ ጎልቶ ይታያል። በየትኛውም ባህል ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ውበትን በተቀበሉት ልክ ይስማሙበታል በተስማሙት ልክ ደግሞ ይደነቁበታል፤ ይደምቁበታል። በመረጡትና በተሰማሙበት ልክም ቆንጆ ሆነው መታየትን ይፈልጋሉ። አምረውና ተውበው ለመታየት ደግሞ ማህበረሰቡ ያመነበትን ወይም የተቀበለውን የመዋቢያ ዓይነቶች ይጠቀማሉ። ለዚያም ነው ኢትዮጵያውያን የዓመት በዓል በመጣ ቁጥር በውብ ባህላዊ አልባሳቶቻቸውና ማጌጫዎቻቸው አምረው የሚታዩት።
የዮቶር ከንድ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014