በቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ በመካከለኛና ምስራቅ አፍሪካ(ሴካፋ),ዞን ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን ሳይሳካለት ቀርቷል። በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ንግድ ባንክ ቡድን የዞኑን ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች በጠቅላላ አሸንፎ ትናንት በፍፃሜው ጨዋታ ከኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ ጋር የተገናኘ ሲሆን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ተሸንፎ ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን ፈፅሟል።
በሜዳና በደጋፊው ፊት የተጫወተው ቪሂጋ ኩዊንስ አከራካሪና የዳኝነት ግልፅ አድሏዊ ውሳኔ በታየበት በሃያ ስምንተኛው ደቂቃ በጄንትሪክስ ቺካንጋዋ አማካኝነት በተቆጠረ ግብ መምራት ቢችሉም በሁለተኛው አጋማሽ ቪቪያን ማኮካ በራሷ መረብ ላይ ባስቆጠረችው ግብ ንግድ ባንክ አቻ መሆን ችሏል።
በውድድሩ በርካታ ግቦችን ማስቆጠር የቻለችውን ሎዛ አበራን ከጨዋታው መጀመሪያ አንስቶ በጥብቅ የመከላከል ስልት በርከት ብለው አላንቀሳቅስ ያሉት የቪሂጋ ኩዊንስ ተከላካዮች የጨዋታ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በዳኛ እርዳታ በሚያስብል ሁኔታ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በመጨረሻው ተጨማሪ አራት ደቂቃ ላይ ባገኙት ፍፁም ቅጣት ምት ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፈው መውጣት ችለዋል። ንግድ ባንክ በጨዋታው ምንም ያህል ብልጫ ቢኖረውም ዘወትር የሚወቀሱትን የአፍሪካውያን ዳኞች ግልፅ አድሎ የሚታይበት ውሳኔ አሸንፈው ዋንጫውን ማንሳት ሳይችሉ ቀርተዋል።
የአራት ጊዜ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴካፋው ቻምፒዮንስ ሊግ በምድብ ሁለት ከደቡብ ሱዳኑ ዩ ጆይንት ስታርስ፣ ከዛንዚባሩ ኒው ጄኔሬሽን እንዲሁም ከውድድሩ አስተናጋጅ አገር (ኬንያ) ክለብ ቪሂጋ ኩዊንስ ጋር መደልደሉ የሚታወስ ሲሆን፣ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው ለፍፃሜ ከደረሰው ቪሂጋ ኩዊንስ ጋር ባደረገው ጨዋታ አራት ለሁለት መርታቱ ይታወቃል። የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታም የዛንዚባሩ ኒው ጄኔሬሽንን 10 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል። ይህም ውጤት ቀሪ አንድ ጨዋታ እያላቸው በቀጥታ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ አድርጓቸዋል።
ያም ሆኖ ንግድ ባንኮች በካሳራኒ ስታዲየም ባደረጉት የምድቡ ሶስተኛ ጨዋታም ተጋጣሚያቸው የደቡብ ሱዳኑ ዩይ ጆይንት ስታር ላይ ግቦችን በማዝነብ ማሸነፍ ችለዋል። በጨዋታውም አምበሏ ሎዛ አበራ ስድስት ግቦችን ስታስቆጥር በውድድሩም ያስቆጠረቻቸውን የግብ መጠን ወደ አሥራ ሁለት ከፍ አድርጋለች። ቀሪዎቹን የንግድ ባንክ ግቦች መዲና አወልና ፀጋነሽ ወልደየሱስ እያንዳንዳቸው ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
ንግድ ባንክ በሶስት ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቻቸው ላይ ሃያ አራት ግቦችን ከመረብ ማሰረፍ የቻሉ ሲሆን ፤ ምድባቸውንም በበላይነት በማጠናቀቅ ግማሽ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ችለዋል። በግማሽ ፍፃሜው ፍልሚያም አስደናቂዋ አጥቂ ባስቆጠረችው ብቸኛ ግብ ከተጋጣሚያቸው የዩጋንዳው ሌዲ ዶቭስ ጋር በመደበኛውና በተጨማሪው የጨዋታ ክፍለጊዜ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተው ወደ መለያ ምት አምርተዋል። በዚህም ንግድ ባንኮች 5ለ3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የፍፃሜው ተፋላሚ ለመሆን ችለዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኬንያ ቆይታው የትናንቱን የፍፃሜ ጨዋታ ሳይጨምር አራት ጨዋታ አከናውኖ ሁሉንም አሸንፏል፤ 25 ግቦችን አስቆጥሮም 3 ግብ ብቻ ተቆጥሮበት ለፍፃሜ ደርሷል። የቡድኑ ፊውታራሪዎች ሎዛ አበራና መዲና አወልም የውድድሩ ክስተት ሆነዋል፤ ቡድኑ ካስቆጠራቸው 25 ግቦች ሃያ አንዱን ሎዛ አበራና መዲና አወል ከመረብ ማሳረፍ ሲችሉ፤ ሎዛ 13 መዲና ደግሞ 8 ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩን ከፍተኛ ግብ አግቢነት ከፍፃሜው ጨዋታ አስቀድመው መቆጣጠር ችለዋል።
ቪሂጋ ኩዊንስ የትናንቱን የፍፃሜ ጨዋታ በማሸነፉ ምስራቅ አፍሪካን በብቸኝነት በመወከል በግብፅ አስተናጋጅነት በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የሚሳተፍ ይሆናል። የሴካፋ ቻምፒዮን በመሆኑም ከዋንጫ በተጨማሪም 30ሺ የአሜሪካ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል። ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያተናቀቀው ንግድ ባንክ ደግሞ 20ሺ እንዲሁም ሶስተኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን 10ሺ ዶላር ሽልማት እንደሚያገኙ ይፋ ሆኗል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5/2013