ጊዜን የሚያነግሰው ሰው፤ የሚያረክሰውም እራሱ ሰው ነው።የትኛውም ዘመን በራሱ ወርቅነትን ተላብሶና ብሩህ ሆና ቀርቦ አያውቅም። ሰው በተግባሩ ዘመኑን ወርቅ ያደረገበት እንጂ ዘመኑ በራሱ ሰዎችን ወርቅ ያለበሰበት አጋጣሚ ፈፅሞ የለም።
ያለፈው ዘመን ወርቃማነት የመጪው ዘመን መንተብ ሆነ መፍካት ኃላፊዎቹ ሰዎች ነበሩ ወደፊትም ሰዎች ናቸው።ስለዚህ የዘመን ወርቃማነት የሚረጋገጠው በእኛ በዘመኑ ሰዎች እንጂ በዘመኑ አይደለም።
ወርቃማ ዘመን ዘመኑ በራሱ የሚጎናፀፈው የተለየ ወቅት ነው? ወይስ በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ያለበሱት ወርቅነት? ለኔ የዘመኑ ወርቅነት አልያም መልካምነት ውጤቱ የዚያ ዘመን ተዋናዮች ናቸው።ዘመን በራሱ ወርቅን አይለብስም።ወርቃማ ዘመን የምንፈጥረው እኛው ነን። የጊዜ ውብ መሆን አልያም ደግሞ በታሪክ ሲጠቀስ “ምነው ባይከሰት” መባል ዘመኑ በራሱ ልዩና ጥሩ መሆን ወይም መበላሸት ሳይሆን የዚያ ዘመን ሰዎች የሚያደርጉት በጎ አልያም እኩይ ተግባርና እሳቤ ውጤት ነው።ዘመኑ የተዋናዮቹ ስራ ውጤት ነው።ስራቸው በጎና መልካም ከነበር መልካምና ውብ ጊዜ ይፈጠራል።በአንፃሩ ደግሞ የዚያ ዘመን ሰዎች ስራና እሳቤ እኩይ ከነበረ የነተበ ጊዜን ይፈጥራል።
በሰፋ እይታ ሁሉንም አሻጋሪ በሆነና ቀና እሳቤ መነሻነት አሸናፊ የሆነ ሀሳብ ከፊት መርቶ ሁሉንም አግባብቶና በአንድነት አቁሞ የሚያተጋ ለዋጭ ሀሳብ ዘመን ያሳምራል።ነገር ግን ያልተሰራበትና ያልተለፋበት በጎና ወርቃማ ዘመን በተለየ መልኩ ካለፈው ዘመን ተለይቶ አምሮና ተውቦ በራሱ ብቅ የሚል አይደለም።ስለዚህ ወርቃማ ዘመን የሚወለደው ወርቃማ በሆኑ ምርጥ ሀሳቦች ነው።የሀሳቡ አመንጪ ደግሞ እዚህ ምድር ላይ የበላይነት የጨበጡ የዘመኑ ንጉሶች ሰዎች ናቸው፡፡
አዎ እኛ ሰዎች ነን ወቅትን ወርቅም ጨርቅም የምናደርገው።ውድም እርካሽም አድርገን የምናስገኘው። ሰው በራሱ በጎ ስራን ሰርቶ፣ ሰዎችን ጠቅሞና ለአገሩ መስዋዕትነት ከፍሎ ከሌላው ከፍ ብሎ መንገስ ሲችል ጊዜን ያነግሳል።“ጊዜ ንጉስ ነው” ከራሱ ከፍ አድርጐ ዘመኑን የሚያነግሰው እሱ እራሱን ሎሌ አድርና ዘመኑን አንግሶ ነው።በራስ እጅ መስጠት ማለት ይሄ ነው።
በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ “ጊዜ ንጉስ ነው” በሚለው ሀሳብ ላይ አልስማማም።ምክንያት ብትጠይቁኝ ደግሞ ጊዜን የሚያነግሰው ሰው መሆኑን እሞግታችኋለሁ።ለጊዜ ንጉስነት የምናላብሰው እኛ ሆነን ሳለ በራሱ ዑደት ለሚተመውና ለሚተካው ወቅት መስጠት ለምን? በእርግጥ የወቅቶች መለዋወጥና የዘመን መሸጋገር በራሱ የሚፈጥረው ተፈጥሯዊና መልካም ምድራዊ ለውጥ አለ።ነገር ግን ሰዎች በዚህ ለውጥ ውስጥ እራሳቸው እያስማሙና እያስታረቁ ያንን የወቅት መለዋወጥ በቁጥጥራቸው ውስጥ ማድረግና በወቅቱ የመንገስ ሙሉ መብት አላቸው፡፡
ጊዜ በአግባቡ ከሰራንበት የሚያነግሰው እኛን እንጂ እራሱን አይደለም።ዘመን በትክክል የሚፈልገውን ካቀረብንለት የሚስተካከለውና ወርቃማ የሚያደርገው እኛን እንጂ እራሱ ዘመኑን አይደለም።በክረምት ወቅት በሚያገኙት ዝናባማ የአየር ንብረት መሬት ቆፍረው በትጋት በሚቀብሩትና በሚዘሩት አዝርት ወቅቱ ተቀይሮ መዝራትና ማምረት የማይችሉበት ወቅት ላይ ንግስናቸው ማስጠበቅ ይችላሉ።ከዚህ በተፃራሪው ደግሞ በተገቢው ወቅት ሀላፊነትን ሳይወጡ ለጊዜ እራስን አሳልፎ መስጠትም ሌላው አማራጭ ነው።ይህ አማራጭ ግን እራስን ሎሌ አድርጐ ጊዜን ባለስልጣን ያስደርጋል፡፡
ቀድመው በሰሩት በመልካሙ ጊዜ በተጉት በክፉ ጊዜና ወቅት ይሸሸጋሉ።ክብራቸው ሳይጓደል አኗኗራቸው ሳይቀየር በነበሩበት ዑደት ይቀጥላሉ።ስለዚህ የእኛ ትጋት ዘመንን ሳይሆን እኛው ዘላለማዊ የጊዜ ነጋሽ ያደርገናል።የእኛ ስንፍና ደግሞ ዘመኑን አንግሰን እኛ የዘመኑ ሌሎዎች እንድንሆን በራሳችን ፈቅደን እጅ የሰጠን ደካሞች ያደርገናል።ስለዚህ ዘመንን ማንገስ ሳይሆን በእኛ ትጋትና ጥንካሬ በዘመኑ መንገስ ይኖርብናል።
የዘመን መለወጥ የወቅት መቀያየር በራሱ ለውጥ አይደለም።ለውጥ መልካም እሳቤ ባነገቡ፣ ቀና አስተሳሰብን በተላበሱና በጎ ውጥንን ባላቸው ሰዎች የሚመጣና በነዚሁ ሰዎች ያልተቆጠበ ጥረት የሚረጋገጥ ተግባር ነው። የዘመን ወርቅነት አልያም ጨርቅነት ውጤት እና ባለቤቶቹ እኛው ነን።የዘመኑ ወርቃማነት አረጋጋጮችና ተዋናዮች እኛ እራሳችን ነን። በእግጥ በተስተካከለና የዘመኑ ትውልድ ባቀናው ዘመን ላይ መገኘት ሁኔታዎች አቅሎ የተሻለው ዘመን መፍጠር ይቻል ይሆናል።ነገር ግን በራሱ የፈካና የደመቀ በራሱም የተለየ ዘመን ሊገኝ አይችልም፡፡
“ወርቃማ ዘመን ነበር” ሲባል ይሰማል የጊዜው ወርቃማነት መለኪያው በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ወርቃማ አስተሳሰብና ተግባር መሆኑን ማወቅ ይገባል።እንደ ዘመኑ ወርቃማነቱ አውጆ ሰዎቹን ወርቅ በወርቅ ያደረገ ሆኖ አልነበረም።ይህንን ጥሩ ያላልነው ዘመን ወደ ወርቃማ ዘመን የመለወጥ ሙሉ መብቱ ያለው እኛው ጋር ነው።ዘመኑን ወርቅ ለማልበስ ደግሞ ወርቃማ ሀሳብ ማፍለቅና መተግበር ይኖርብናል፡፡
በዘመን አቆጣጠር ከሌላው ዓለም ለየት የሚያደርገን 13ኛ ወር ጳጉሜን ላይ እንገኛለን።ይህ አሮጌውን ዓመት ጥለን ወደ አዲሱ ዘመን የምንሻገርበት ድልድይ ወደ አዲስነት የሚያቃርበን መሻገሪያ ብዙ ጊዜ ያለፈውን ገምግመን ለመጪው የምንዘጋጅበት ነው።ዛሬ ላይ ቆመን ነገርን ወርቃማ ለማድረግ መትጋትና ለዚያ መሰናዳት የእኛ ፋንታ ነው።
ያለፈውን ዓመት አገራዊ ሁኔታችን ሲታሰብ መልካም የሚባል አይደለም።መጪው ዘመን ደግሞ መልካም የማድረግና ከዘንድሮው እጅጉን የተለየ ማድረግ የእኛ ሀላፊነት ነው።አንድ ላይ ከቆምንና ኢትዮጵያዊነት መነሻ አድርገን መጪው ዘመን ለህዳሴና ለሰላም በጋራ ከተጋን የምንፈልገው ለውጥና መልካም ዘመንን መላበስ እንችላለን።መጪው ዘመንን ወርቃማ የማድረግ መብቱ የእኛ ነው።ዘመኑ በራሱ ይዞልን የሚመጣ ምንም የለም እኛ ለዘመኑ ልናቀርብለት ያሰብነው መልካምና በጎ ነገር ግን ዘመኑን መለወጥና መልካም ማድረግ ይችላል።መጪው አዲስ ዓመት ወርቃማ ማድረግ አልያም ዘመኑ ሲታሰብ የሚሸክ የምናደርገው እኛ ነን፡፡
ዛሬ ያለንበት ወቅት የእኛ ዘመን ነው።ዘመኑን ወርቃማ ማድረግ ደግሞ የእኛ ሀላፊነት።ሁሌም በታሪክ መዝገብ ላይ ሲጠቀስ “ያ ዘመን ወርቃማ ነበር” ለማሰኘት ዘመኑን የሚመጥን ወርቃማ ሀሳብ ሊኖረን ይገባል።ያንን አሻጋሪና አገር ለዋጭ ሀሳብ ደግሞ የሁላችንን ስምምነትና መፈቃቀድ ታክሎበት ዘመኑን ወርቅ ያለብሳል።ያኔ ይህቺ ውብ አገር በልጆችዋ የድል ወርቅን ታጠልቃለች።ያኔ ይህቺ ድንቅ አገር ወርቃማ ዘመንዋ ይበሰራል።አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013