በዛሬው ዓምዳችን ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎች የሚዛመዱ ዜናዎች በ19 70 ከታተሙት ጋዜጣዎቻችን የተወሰኑትን መርጠናል።ወረራዎችን ለመከላከል ሕዝቡ ደመወዙን በመስጠት እንዲሁም የንግድ አሻጥርን ለመከላከል ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች ይገኙበታል። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ አሁን ከሚታየው የንግድ አሻጥርም ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ዜናዎች አሉ።እንድታነቡት እንጋብዛለን።
የሶማሊያ ወረራ የከሸፈው የኢትዮጵያ አብዮት ትክክለኛ በመሆኑ ነው።
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
‹‹የአጉል ጀብደኝነት ፍፃሜ ›› በሚል ርዕስ ‹‹አፍሪካ ትሪቡን ›› የተባለው የሴኔጋል መጽሔት እብሪተኛው የዚያድ ባሬ ጦር በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ላይ የሰነዘረው ወረራ ሊከሽፍ የቻለው ኢትዮጵያ ትክክለኛ አብዮት በማካሄድ ላይ በመሆንዋና የኢትዮጵያ አብዮት የሶሻሊት ድጋፍ ያለው በመሆኑ ነው ሲል አስታውቋል።
መጽሔቱ ባሰፈረው ጽሑፉ የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያን የኦጋዴን ግዛት፤የኬንያን ሰሜናዊና ምሥራቅ ግዛትና የጅቡቲ ሪፐብሊክ በማጠቃለል ‹‹ታላቋ ሶማሊያ›› መፍጠር የሚለውን ሕልም በሕገ መንግሥቱም ጭምር ማፈሩን ጠቅሶ ይህ የግዛት ማስፋፋት ሙከራ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መርሆዎችን በተለይም ከቅኝ ግዛት በኋላ የተገኘው የድንበር ክልሎችን ማክበር የሚለውን መርህ የሚጥስ መሆኑን ጨምሮ አስታውቋል።
የሶማሊያ መንግሥት ባለፈው ሐምሌ ወር አመቺ ጊዜ ያገኘ መስሎት ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ቢያካሂድም ፤በመጨረሻ ድል ተመትቶ በምዕራብ አገሮች ሥር ወድቆ እንደሚገኝ ገልጧል። በአንፃሩ ኢትዮጵያ በዘረጋችው የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም መሠረት አብዮቷን በሚገባ ማራመድ ላይ መሆንዋንና አብዮቷም ከፈነዳበት ጊዜ ጀምሮ ያገኘቻቸው ድሎች ቀላል አለመሆናቸውን በማስረዳት ዛሬ አብዮታዊት ፓርቲ ለመፍጠር የሚስችሉት አመቺ ሁኔታዎች በመሟላት ላይ መሆናቸው ተጠቅሷል ።
የሐይቆችና ቡታ ጅራ አውራጃ ወህኒ ቤት ፖሊሶች የወር ደመወዛቸውን ሰጡ
አዋሳ ፤(ኢ-ዜ-አ) ድል በትግል የተሰኘው የሐይቆችና ቡታ ጅራ አውራጃ ወህኒ ቤቶች የወይይት ክበብ በሰሜን ግንባር ከሐዲ ተገንጣዮችን ለመደምሰስ ለዘመተው ጦር ስንቅ እንዲውል ከሐምሌ ፩ ቀን ፸ ዓ.ም. ጀምረው የአንድ ወር ደመወዛቸውን በአንድ ዓመት ለመክፈል መስማማታቸው ተገልጾዋል።
የሐይቆችና ቡታ ጅራ አውራጃ ወህኒ ቤት ፖሊሶች የውይይት ክበብ አባሎች ከዚህ ቀደም የ፩ ወር ደመወዛቸውን በ፩ ዓመት ለእና አገር ጥሪ ከፍለው የጨረሱ መሆናቸው ታውቋል። ሻምበል ወልደሚካኤል መብራ የሐይቆችና ቡታ ጅራ አውራጃ ወህኒ ቤት ፖሊስ አዛዥ እንዳስረዱት አባሎቹ በገንዘብ እርዳታ ብቻ ሳይወሰኑ በአስፈላጊው ጊዜ ወደ ጦሩ ሜዳ ለመሠማራ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
(ሐምሌ 9 ቀን 19 70 ከታተመው አዲስ ዘመን )
አርባ አራት ኬሻ በርበሬ ተደብቆ ተገኘ
(ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ)
በሕገወጥ መንገድ ከእህል ጋር የተከማቸ 44 ኩንታል በርበሬ በአዲስ ከተማ የእህል በረንዳ ተደብቆ መገኘቱን የንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር ማስታወቂያ ክፍል አስታወቀ። በርበሬው ተደብቆ ሊገኝ የቻለው በከፍተኛ ፮ የሚገኙ የዋጋ ቁጥጥር ኮሚቴ አባሎች ከአራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ጋር በመተባበር ባደረጉት አሰሳ ሲሆን የተያዘው በርበሬ በተመኑ ለሕዝብ ተሸጦ ገንዘቡ ለእናት አገር ጥሪ ገቢ እንዲሆን ተወስኗል። በውርስ ገቢ ከሆነው በርበሬ ጋር ሌሎችም በርከት ያሉ ሸቀጦችና የእርሻ ሰብሎች ተይዘው በሕጋዊ ተመን መገዛታቸውንና አለመገዛታቸውን በመጣራት ላይ መሆኑን የማታወቂያ ክፍሉ ገልጾ፤ የተያዙትን ሰብሎችና ዕቃዎች የሚያጣራ ኮሚቴ መቋቋሙን አስረድቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ በከፍተኛ ፱ በቀበሌ ፳ በተደረገው ቁጥጥር ፭ ነጋዴዎች ሕጋዊ ባልሆኑ መስፈሪያዎችና ሚዛኖች ሲጠቀሙ ተገኝተው በጠቅላላው ፻፷፭ ብር መቀጣታቸውን የማታወቂያ ክፍሉ ገልጾዋል። ይህ ከሕዝባዊ ድርጅቶች በተውጣጡ ኮሚቴዎች አማካይነት የሚካሄደው የዋጋ ቁጥጥር የሚዛንና መስፈሪያ ዕቃዎች ቁጥጥር ተጀምሯል። በሕዝባዊ ድርጅቶች የሚደረገው ቁጥጥር እየተጠናከረና እየሰፋ ስለሄደ በአብዛኛው ቀበሌ ሕዝቡ ከአሻጥረኛ ነጋዴዎች ብዝበዛ ለመዳን ችሏል። በዚህ መሠረት በሕዝባዊው ኃይል የሚካሄደውን የዋጋ ቁጥጥር ሥራ ለማጠናከር በከፍተኛ ፲፭ የአንድ የዋጋ ቁጥጥር አጠናካሪ ኮሚቴ መቋቋሙን የማስታወቂያ ክፍሉ ጠቅሶ በጣም ጥቂት በሆኑ ቀበሌዎች ግን ቁጥጥሩ የመላላት ሁኔታ መታየቱን አመልክቷል።
(ሰኔ 16 ቀን 19 70 ከታተመው አዲስ ዘመን )
ሰው ሠራሽ የዳቦ እጥረትን የሚቆጣጠር ኮሚቴ ተቋቋመ
(ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ)
አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የሚፈጥሩትን የዳቦ እጥረት ለመቆጣጠር የሚችል አንድ ልዩ ኮሚቴ መቋቋሙን የንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አስታወቀ።
ሰሞኑን የተቋቋመው ይኸው የተቆጣጣሪ ኮሚቴ በንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውስጥ ከዳቦ መጋገሪያ ባለንብረቶችና ወዛደሮች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ከተደረገ በኋላ መሆኑ ታውቋል።
የውይይቱም ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄደውን የዳቦ ማከፋፈልን ሁኔታ ለማሻሻልና ሥርዓት ለማስያዝ ሲሆን ፤በንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተመደቡት የደርግ አባል ፤የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች አጠቃላይ የከተማ ነዋሪዎች ማኅበራት፤ የመኢሠማ ተወካዮችና የሌሎችም ድርጅቶች አባሎች በውይይቱ ተካፋይ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ ማስታወቂያና የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ጨምሮ ገልጾዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ፺፰ የዳቦ መጋገሪያ ቤቶች ሲኖሩ ፤እነዚህ በየወሩ ፲፰ ሺህ ኩንታል የስንዴ ዱቄት እንደሚያገኙና ይህንንም የሚፈጩት ፲፫ የዱቄት ፋብሪካዎች መሆናቸው ተገልጾዋል።ቁጥጥሩን ለማካሄድ በተቋቋመው በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ከዳቦ ቤት ባለንብረቶችና ወዛደሮች ከሕዝባዊና መንግሥታዊ ድርጅቶች የተውጣጡ አባሎች የሚገኙበት መሆኑ ተገልጾዋል። ኰሚቴው የተቋቋመው በአንዳንድ ዳቦ ቤቶች ዱቄት ወስደው ጋግረው ለሕዝብ በማቅረብ ፈንታ ዱቄቱን በመሸጥ የሚጠቀሙበትን ለመቆጣጠር መሆኑን ክፍሉ አስታውቋል።
እንደዚሁም ደሞ ሻይ ቤቶች ከምግብ ድርጅቶች ድርሻቸውን ዱቄት ከወሰዱ በኋላ በተጨማሪ በዛ ያሉ ሰዎችን ወደ ዳቦ ቤቶች በመላክና እንዲሰለፉ በማድረግ ተጠቃሚውን ሕዝብ በመሻማት ከፍተኛ ችግር የፈጠሩ ስለሆነ ኰሚቴው እንደዚህ ያለው ስግብግብነት እንዲወገድ ለማድረግ ቁጥጥርን እንደሚያካሂድ ተገልጾዋል።
ከዚህ በቀር በጊዜው አጋጣሚ በመጠቀም ከዚህ በፊት የዳቦ ንግድ የሚያካሂዱ ግለሰቦች በየዳቦ ቤት በራፍ ሰዎች እየተሰለፉ ከድርሻቸው በላይ በመውሰድ በውድ ዋጋ ለተጠቃሚው ሕዝብ በመሸጥ ብዝበዛ የሚያካሂዱ መኖራቸው ስተደረሰበት ኰሚቴው ይህንና ሌሎችንም አሻጥሮች ለማጋለጥና ለማስወገድ የተቋቋመ መሆኑ ተገልጾዋል።
(ሐምሌ 9 ቀን 19 70 ከታተመው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013