ዓለማችን በተፈጥሮ ያሸበረቀችና የተዋበች ነች። ለፍጥረታት ሁሉ መኖሪያ ምቹ የሆነችው ምድራችን በቀለማት የተሰባጠረና እጅጉን ማራኪ የሆነ ገፅታን የመላበሷ ምስጢር ረቂቅ ነው። በዋነኝነት ይህን መስህብ እንድናጣጥም የሚያደርጉት ደግሞ በአፈጣጠራቸው ልዪ የሆኑት “ቀለማ”ት በመልክአ ምድሮች ላይ መገለጣቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሰው ልጅ የተሰጠውን ድንቅ አእምሮ ተጠቅሞ የቀለማትን ሚስጥር ገልጦ ዓለማችንን ለመኖር ምቹ እንድትሆን ማድረግ ችሏል።
በዛሬው የፋሽን አምዳችን ላይ ይህን ውብ ስብጥር እንድንታደል ያደረገንን ጉዳይ እንመለከታለን። በዋናነት ግን የሰው ልጅ “የቀለማትን” ከመረዳትና ከማድነቅ በዘለለ የፈጠራ ክህሎቱን ተጠቅሞ ውበትን ለመጠበቂያና ለመዘነጫ የማድረጉን ጉዳይ እንዳስሳለን። በተለየ መንገድም የፋሽን ኢንዱስትሪውና ቀለማት ትስስርን በዝርዝር እናያለን።
የሰው ልጅ በስሜት ህዋሳቶቹ ታግዞ የምድር በረከት የሆነውን የተፈጥሮ ፀጋ ያጣጥማል። ይመለከታል፣ ይቀምሳል፣ ያሸታል፣ ይዳስሳል እንዲሁም ይሰማል። ታዲያ በነዚህ ፀጋዎቹ ደስታውን ያገኛል። ይሁን እንጂ የመኖሩን ትርጉም የሚገልጥበት ጥበብ በተጨማሪ የታደለ ነው። ከዚህ መሃል ደግሞ “የፋሽን አልባሳት ዲዛይንና የቀለማት ትስስር” ይገኝበታል። ለመሆኑ “የፋሽን አልባሳትና ቀለማት” ትስስር በምን መልኩ ይገለፅ ይሆን?
ዲዛይነር ዮርዳኖስ አበራ ትባላለች። የዮርዲ ዲዛይን ባለቤትና መስራች ነች። ባህላዊ አልባሳትን በዘመናዊ መንገድ ዲዛይን በማድረግ ምቹና ተለባሽ እንዲሆኑ ትሠራለች። የኢትዮጵያን አልባሳት ለማስተዋወቅም እንዲሁ። ይህን ሥራ ከ12 ዓመት በፊት የጀመረች ሲሆን፤ እውቅ ዲዛይነሮች ከሚባሉት ተርታ የምትሰለፍና ለሙያው ማደግ የድርሻቸውን ከተወጡት ውስጥ የምትመደብ ናት። እኛም ቀለማትና የፋሽን አልባሳት ቁርኝት ምን ይመስላል ስንል ጠየቅናትና የሚከተለውን ምላሽ ሰጠችን።
“ኢትዮጵያውያን በደስታ ግዜ የብሩህነት መገለጫ የሆነውን ነጭና በተለያየ ቀለማት ያሸበረቀውን ጥለት፣ እንዲሁም ጎላ ብለው የሚታዩ የቢጫ፣ ቀይና አረንጓዴ አልባሳትን ያዘወትራል። በሃዘን ግዜያት ደግሞ ደብዘዝ ብለው የሚታዩ ልብሶችን በተለይ ጥቁር ቀለም ይጠቀማል” በማለት በዋናነት ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ ቀለማት ቢኖሩም በተለያየ የአገሪቱ አካባቢዎች ግን በእጅጉ የተሰባጠሩ ቀለማት በአልባሳት ላይ እንደምንጠቀም ትገልፃለች።
እርሷም አልባሳቶችን ዲዛይን ስታደርግ ከዚህ መነሻ መሆኑን ገልፃ በተለይ የአዲስ ዓመት መለወጫን የሚወክለው “አደይ አበባ” ቢጫ ቀለምን እንዲሁም የደስታና የብሩህ አስተሳሰብ የሚያላብሰውን የነጭ ቀለም አጣምራ የተዋቡና ምቹ አልባሳትን ታዘጋጃለች።
ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ቀለማት ላይ “በሃበሻ ቀሚሶችና ነጠላዎች” ላይ ኢትዮጵያውያን የሚጠቀሟቸው ጥለት በስብጥር ቀለማት እየተጠቀመች ወደ ገበያው እንዲደርሱ እንደምታደርግ ነግራናለች። አሁን አሁን ወጣቱ ለቀለም ያለው እይታና አረዳድ እየሰፋ በመምጣቱ ደማቅ እይታ ያላቸው ቀለማትን እየተጠቀመ እንደሚገኝም ነግራናለች።
ቀለም፣ ስነልቦናና ፋሽን
ስለ ቀለም ስነ ልቦና በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። ፈላስፎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የጥበብ ሰዎች እንዲሁም በርካታ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች የቀለማት አፈጣጠርና ስብጥር አጥንተዋል። የራሳቸውን መላ ምት ሰጥተዋል። ሁሉንም ለመለየት ያዳግት እንጂ ከ10 ሚሊዮን በላይ ቀለማት እንዳሉም መረጃዎች ይጠቁማሉ። ታዲያ እነዚህ ሁሉ ቀለማት የራሳቸው በሰው ልጆች ስሜት ላይ አሉታዊና አዎንታዊ ስነ ልቦናዊ ተፅእኖ አላቸው። ለዚህም ነው የፋሽን ዲዛይነሮች አልባሳትን ዲዛይን በሚያደርጉበት ወቅት ከውበት አንፃር ብቻ ሳይሆን “ከስነ ልቦና ውቅርና ተፅእኖ” አንፃር የሚቃኙት።
ሰናየት ጥበቡ ትባላለች። የፋብሪክ ዲዛይን ባለቤት ነች። ባሳለፍነው ሳምንት በመንገድ ላይ ያደረገችውን የፋሽን ትርኢት አስመልክቶ እንግዳችን አድርገናት ነበር። ዛሬ ደግሞ ቀለም በፋሽን አልባሳትና በተጠቃሚው ላይ ያለውን ስነ ልቦናዊ ተፅእኖ በማስመልከት አናግረናታል።
“ቀለማት በሁላችንም ላይ ተፅእኖ አላቸው። በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ደማቅ ቀለማትን እንፈራለን። ደብዘዝ ያሉ ቀለማት ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ለበዓላትና ለልዩ ልዩ ዝግጅቶች ካልሆነ በቀር ደማቅ ቀለማት ያስፈሩናል።
ምቾት አይሰጡንም” በማለት አሁን አሁን ግን ይሄ አመለካከት እየቀረ ወጣቶች ወደ ደማቅ ቀለማት ምርጫ እያዘነበሉ መምጣታቸውን ትናገራለች። ስራዎቿን ዲዛይን ስታደርግም ይህንን ታሳቢ ለማድረግ እንደምትጥር ትገልፃለች።
“በክረምት ወቅት ጥቁርና ፈዘዝ ያሉ በበጋ ደግሞ ደማቅ ቀለም ያላቸው አልባሳት በአገራችን ይዘወተራል” የምትለው ዲዛይነር ሰናየት ጥበቡ ይሄ ሊሆን የቻለው ጥቁር ቀለማት ሙቀትን የመፍጠር አቅም ስላላቸው መሆኑን ትናገራለች።
ይሁን እንጂ በዋናነት ቀለማት የተለያዩ ማህበረሰባዊ ስነልቦናን የሚወክሉ ከመሆናቸው አንፃር አንዱ አካባቢ በስፋት በአልባሳት ላይ የሚዘወተሩት በሌላኛው ወገን ተመራጭ ላይሆኑ እንደሚችሉ ትናገራለች።
“በኢትዮጵያ ወስጥ ጥቁር ቀለም ያለው ሙሉ በሙሉ መልበስ ከሃዘን መገለጫ ጋር በስፋት ይያያዛል” የምትለው ሰናየት ቀደም ባሉት ዘመናት ይህን ማድረግ የማይመረጥ ቢሆንም ይሄ ስነ ልቦናዊ እይታ ግን አሁን አሁን እየተተወ መምጣቱን ትናገራለች። ሰናየት የራሷ የቀለም ምርጫ “ግራጫና ጥቁር” ነው። የምትፈራውና ምቾት የማይሰጣት ቀለም ደግሞ “ደማቅ ዶቃ ቀለምና ደማቅ ሰማያዊ ቀለም” ነው። በብዛት በዲዛይን ስራዎቿ ላይ የምትጠቀመው የጨርቅ ቀለም ግን የማህበረሰቡን ስነ ልቦና የወክላልና ተፈላጊነት አለው የምትለውን ነው።
እንደ መውጫ
ከባለሙያዎቹ እንደተረዳነው ማህበረሰባችን በጣም ደማቅ ቀለማትን በእለት ተእለት አልባሳቱ ላይ እንደማይጠቀምና ምቾት እንደማይሰጠው ነው። ይሁንና አሁን አሁን በከተሞች አካባቢ በተነሳው የፋሽን አቢዮት ቀለማትን ደፍሮ የመጠቀምና በእነርሱ በተቃኙ አልባሳት የመዋብ ልምዱ ቀስ በቀስ እየዳበረ መጥቷል።
ይህ ሂደት የአለባበስ “የባህል አቢዮት” ይቀይራል የሚል አመለካከት የሚይዙ ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ ጭምር እያደረገ ነው። በተጨማ በቀለማት ላይ የሚኖረን አመለካከት፣ እይታና ግንዛቤንም አሁን ካለው በእጅጉ እንደሚያሰፋው ይጠበቃል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013