“እናንተ ግን ሥራችሁን ቀጥሉ !! የኢትዮጵያ አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን!!” እነዚህ ቃላት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ስማቸው ገዝፎ ከሚጠራው አርቲስቶች መሀከል አንዱ የሆነው የአርቲስት አለማየሁ እሸቴ የመጨረሻ ቃላት ናቸው፡፡ የተናገረውም ለጋዜጠኛ ሀብታሙ ቦጋለ ነበር። መልከ መልካሙ እና ዘናጩ አለማየሁ እሸቴ የልብ ህመም ያስቸግረው ነበር፡፡ ለህክምና ወደ ጣልያን ለመሄድ ትኬት ቆርጦ ተዘጋጅቶም ነበር፡፡ ከመሞቱ ከሰአታት በፊት ሀብታሙ ስልክ ደወለለት፡፡ የመደወሉ ምክንያትን ሀብታሙ እንዲህ ያስረዳል፡፡
“ስለ ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የፊታችን ሀሙስ በሚለቀቀው የሙዚቃ አልበም ላይ ከፀጋዬ እሸቱ – ከግርማ ተፈራ – ከዘቢባ ግርማ እና ከጠረፍ ካሳሁን (ኪያ) ጋር ለተጫወተው ሙዚቃ ክሊፕ ቀረጻ ቅዳሜ ያለንን ቀጠሮ ለማስታወስ ትናንት 8:53 ላይ ደውዬለት ነበር፡፡ ድካም ባዘለ ድምጽ “ሄሎ!”አለኝ፡፡ የድምጹ ድካም አሳስቦኝ “ምነው ጋሼ ሰላም አይደለህም እንዴ?” አልኩት፡፡”ልቤን እያመመኝ ነው። ወደጣልያን ሀገር ለህክምና ልሄድ ትኬት ቆርጫለው…..እናንተ ግን ሥራችሁን ቀጥሉ !! የኢትዮጵያ አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን!!” ብሎኝ ተሰነባበትን፡፡” ይላል፡፡ ይህ ስንብት ግን ወደ ጣልያን ብቻ አልነበረም ፤ ወደማይቀረውም አለም እንጂ። አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ሀሙስ ለአርብ አጥቢያ ለህክምና በሄደበት ሆስፒታል በህክምና ላይ እያለ ይህችን አለም ተሰናበተ፡፡ ነገር ግን የተለየን እንደ ማንኛውም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ አምላክ ከኛ ጋር እንዲሆን መርቆን ነው፡፡
መልከ መልካሙ እና ዘናጩ አለማየሁ እሸቴ ስራዎቹ አፍ አውጥተው የሚናገሩለት ግዙፍ ሙዚቀኛ ነበር፡፡ የሙዚቃ ተመራማሪው እና የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ የሆነው አርቲስት ሰርጸ ፍሬስብሀት ስለ አለማየሁ ከፍታ እንዲህ ሲል ያስረዳል “በኢትዮጵያ ሙዚቃ የሬኮርዲንግ ታሪክ ውስጥ የተሣኩ እና ጥራታቸው ከፍ ያሉ ከ400 በላይ ምርጥ ሥራዎችን ያበረከተው ዓለማየሁ እሸቴ፣ “ጌሪ ኮፐር”፣”ኢትዮጵያዊው ኧልቪስ”፣ “ዓለማየሁ ቴክሱ፣ ነጭ ነው ፈረሱ” እየተባለ በአድማጮቹ የአድናቆት ቅጽሎች የተወደሰው ዓለማየሁ እሸቴ፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት እንዲያገኝ ያደረገ ድንቅ ድምፃዊ ነበር። “ወርቃማው” እየተባለ ለሚጠቀሰው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን፣ የመጀመሪያው ተጠቃሽ ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ነበር።”
በ1934 ዓ.ም እዚሁ አዲስ አበባ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አቅራቢ ከአባቱ አቶ እሸቴ አንዳርጌ እና እናቱ ወ/ሮ በላይነሽ ዮሴፍ የተወለደው አለማየሁ በ2 ወሩ እናቱ ወደ ወሎ ይዘውት ሄዱ። በሶስት ዓመቱ ግን ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ እንደዘመኑ ልጅ የአብነት ትምህርት ከተማረ በኋላ እድሜው ከፍ ሲል በትምህርት አስፈላጊነት ላይ ጽኑ አቋም ባላቸው አባቱ ጥረት አሁን አብዮት ቅርስ የሚባለው ያኔ ሲ ቲ አይ የሚባል አዳሪ የሚሲዮን ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በትምህርት ቤቱ በሚማራቸው መንፈሳዊ ዝማሬዎችም ጉሮሮውን ሞረደ፡፡ ከዚያም ተምሮ ሀገር እንዲያገለግል የሚፈልጉት ከአባቱ ምኞት በተቃራኒ በ1955 ዓ.ም የፖሊስ ኦርኬስትራን ተቀላቀለ፡፡ ላለፉት 58 ዓመታት ኢትዮጵያን በሙዚቃው ሲያረሰርሳትም ኖረ፡፡ “አዲስ አበባ ቤቴ” ፤ “የወይን ሃረጊቱ” ፤ “የሰው ቤት የሰው ነው”፣ “ደንየው ደነባ”፤ “ትማርኪያለሽ”፣ “ወልደሽ ተኪ እናቴ” « እዬዬ »፣ « ማሪኝ ብዬሻለሁ » ውዴ ባለቤቴ « ስቀሽ አታስቂኝ» ፣ «ማን ይሆን ትልቅ ሰው » ፣ « እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ» እና መሰል ስራዎቹ በህዝብ አፍ ላይ ታትመው የቀሩ ሙዚቃዎች ናቸው፡፡
ተማር ልጄን ፤ ተማር ልጄ
ወገን ዘመድ የለኝ ሀብት የለኝም በጄ
ስማኝ ልጁ ሌት ጸሀይ ነው
ላልተማረ ሰው ግን ቀኑም ጨለማ ነው
ይህን ዘመን የማይሽረው በጣም ግዙፍ ሙዚቃ የተጫወተውም ተወዳጁ አለማየሁ እሸቴ ነው፡፡
ቅንጡ የሚባል ህይወትን የኖረው ጋሽ አለማየሁ ለግማሽ ክፍለዘመን የዘለቀ ትዳር አለው፡፡ ባለቤቱን ወ/ሮ አየሁ ከበደን እናቱን በሚጠራበት ስም “አባዬ” ነው የሚላት፡፡ የእናቴ ምትክ ናት ይላል፡፡ በጄነራል ጽጌ ዲቡ ትእዛዝ ከደብረማርቆስ ለቫዮሊን ትምህርት የመጣችው ወ/ሮ አየሁ እና ጋሽ አለማየሁ ትዳር የመሰረቱት በ1957 ዓ.ም ሲሆን 7 ልጆች እና 4 የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡
ጋሽ አለማየሁ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ሀገሩን አገልግሏል። ረዳት ፕሬፌሰር ነቢዩ ባዬ ይህን እንዲህ በማለት ያስረዳል። ”ሰሞኑን/ላለፉት ሦስት ሳምንታት/ በስራ እየተገናኘን ነበር። እጅግ የሚወዳትን ኢትዮጵያ ሀገሩን የተመለከተ የጥበብ ስራ ለመስራት ደፋ ቀና ስንል ነበር። ከውጥኑ መካሪያችን ነበር። ከርሱ በታች የተኮለኮልነውን ሁሉ ለሀገር መቆም ምን እንደሆነ እያስረዳ በስብሰባ ከነግርማው፣ ከነ ሙሉ ንቃቱ እና ወኔው “ስለሀገሬ በማንኛውም ነገር አለሁ…” ይል ነበር። “አይዟችሁ በልምዳችን አይተናል በአጭር ጊዜ ትልቅ ስራ መስራት እንችላለን” ይለን ነበር። ስለሀገር የሚሰራ ሙዚቃ ግጥሙ ጠበቅ ጠለቅ ያለ መሆን አለበት በማለት ገጣምያንን በአረጋዊ አቅሙ አፈላልጓል።” ይላል፡፡ በቀጣይ ሳምንት የሚወጣ ስለ ኢትዮጵያ የተዘፈነ አዲስ ሙዚቃም ከሌሎች አርቲስቶች አዘጋጅቶም ነበር፡፡
ይህ የጋሽ አለማየሁ ስራ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም እውቅና አግኝቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር የታላቁ አርቲስት ሞት እንደተሰማ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት እንዲህ ብለዋል፡፡ ”ሀገሩን አጥብቆ በመውደድና ለሀገሩ ከልብ በመሥራት ለብዙ ከያንያን አርአያ የሆነው ዓለማየሁ እሸቴ ማረፉን ሰምቼ እጅግ አዝኛለሁ። ሰሞኑን ወጣትና አንጋፋ ከያንያን ስለ ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጀ ሙዚቃ እንዲያወጡ ሲያስተባብር እንደነበር አውቃለሁ። ሥራዎቹ ኢትዮጵያን ከፍ እንዳደረጉ ይኖራሉ። ለኢትዮጵያ የሠራ ያርፋል እንጂ አይሞትም።”
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም