በዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ከአገር ህልውና ጋር ተያይዘው የተዘገቡ ክንውኖችን ይዘናል፡፡ ዘገባዎቹ በ1960ዎቹ ላይ የተዘገቡና አሁን በሀገራችን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል አጀንዳ ያዘሉ ናቸው፡፡ የዚያድባሬው የሶማሊያ ወረራ በዓረብ መኮንኖች ይመሩ እንደነበር፣ የግብጽ፣ ሱዳንና ሳኡዲ አረቢያ ኢትዮጵያን በተመለከተ ስብሰባ በመቀመጥ ለሶማሊያ ድጋፍ እንዲደረግ እስከ መነጋገር የደረሱበትን ሁኔታ፣ ፕራቭዳ የተሰኘው የሩሲያ ጋዜጣ ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ የሚያውጠነጥኑትን ሴራ ማውገዙን የሚመለከቱ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
የሶማሊያን ጦርነት የሚመሩት የዓረብ መኰንኖች ናቸው
ቤይሩት፤(ሮይተር) ከአምስት የዓረብ አገሮች የተውጣጡ የመኰንኖች ቡድን፤ የዓረብ-ሶማሊያን ወታደራዊ ቅንብር እንደሚመራ በፓሪስ እየታተመ የሚወጣው ሳምንታዊ ጋዜጣ መግለጹን የሮይተርስ የወሬ ወኪል ከቤይሩት ባስተላለፈው ዜና ገለጸ፡፡
ዓረብና ኢንተርናሽናል ኦን-ናሃር የተሰኘው ቤይሩት ውስጥ የሚሠራጨው ይኸው ጋዜጣ ስለአቀረበው ዜና ሲያብራራ፤ ዜናውን በሚገባ ከሚያውቁት የአፍሪካ የዲፕሎማቲክ የወሬ ምንጮች ማግኘቱን ዜናው ጨምሮ ገልጿል፡፡ በዚህ ሪፖርቱ ይኸው ጋዜጣ በጦርነቱ ቅንብር ላይ የትኞቹ የዓረብ አገሮች እንደተካፈሉ አልገለጸም፡፡
የዓረብ ወታደራዊ እርዳታ ለሶማሊያ ታንኮችን፣ ከባድ መሣሪያዎችን፣ የጦር አውሮፕላኖችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን ጨምሮ እንደሚያቀርብ ጋዜጣው አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እስካሁን የሶማሊያን ፳፫ ሚግ ተዋጊ ጄቶች ማውደሟን ይኸው ጋዜጣ አረጋግጧል፡፡
(ነሐሴ 29 ቀን 1969 የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ግብፅ፣ ሱዳንና ሳዑዲ ዓረቢያ በምስጢር ስብሰባ አደረጉ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
ስለ አፍሪካ ቀንድና ስለ ቀይ ባሕር አካባቢ የሚከተሉትን አመራር በይበልጥ ለማስተባበር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር የግብፅ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት፣ የሱዳን መሪ ጃፋር ኤልኒሜሪና አንድ የሳዑዲ መንግሥት ተጠሪ በቅርቡ ምስጢራዊ ስብሰባ አድርገው እንደነበር ኤል ኳባስ የተባለ የኩዌት ጋዜጣ ባለፈው እሁድ አስታወቀ፡፡
ግብፅ ውስጥ በአሌክሳንድሪያ ከተማ በተደረገው በዚሁ ምስጢራዊ ስብሰባ ላይ ሳዑዲን ወክሎ የተገኘው የንጉሥ ካሌድ ልዩ አማካሪ ሼክ ከሚል አደም መሆኑን ጋዜጣው ጨምሮ ገልጿል፡፡
ይኸው የኩዌት ጋዜጣ ካይሮ የሚገኙና ለፕሬዚዳንት ሳዳት ቀረቤታ ያላቸውን የዜና ምንጮች በመጥቀስ እንደገለጸው፤ በምስጢር የተደረገው የሳዳት የኒሜሪና የአደም ስብሰባ ዓላማ ግብፅ፣ ሱዳንና ሳዑዲ አረቢያ በአፍሪካ ቀንድና ቀይ ባሕር አካባቢ ባለው ጊዜያዊ ሁኔታ አንፃር አመራራቸውን ይበልጥ ለማቀነባበርና ለማስተባበር የሚችሉበትን ዘዴ ለማጥናት መሆኑ ታውቋል፡፡
የዜና አገልግሎቶች ከኩዌት ባስተላለፉት ዜና መሠረት፤ ግብፅ፣ ሱዳንና ሳዑዲ ኢትዮጵያን ብቸኛ ለማድረግ ሙሉ ስምምነት ከመድረሳቸውም በላይ፤ በኢትዮጵያ ላይ የወረራ ጦርነት ለሚያካሂዱ ኃይሎችም ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት መስማማታቸውን በአረብ ባሕረሰላጤ አካባቢ ባሉ አገሮች ዘንድ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ የዜና ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ስለምታካሂደው የወረራ ጦርነት ሌሎች የዓረብ አገሮች ግልፅ እርዳታና ድጋፍ እንዲሰጧት ግብፅ፣ ሱዳንና ሳዑዲ ዓረቢያ በመገፋፋት ላይ መሆናቸውንም የውጭ አገር የዜና አገልግሎት ድርጅቶች አመልክተዋል፡፡
ሶማሊያ በበኩሏ ካይሮ ውስጥ ለተሰበሰበው የዓረብ አገሮች ማኅበር ጉባኤ ባቀረበችው አቤቱታ ላይ ለምታካሂደው የወረራ ጦርነት የዓረቦች ጦርነት ሆኖ መታየት ስላለበት የዓረብ አገሮች ማኅበር አባላትን ግልፅና ይፋ የሆነ ድጋፍና እርዳታ ማግኘት አለብኝ ብላለች፡፡
(ጳጉሜ 1 ቀን 1969 የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ሴራ ፕራቭዳ በጥብቅ አወገዘ
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እና አካባቢዋ ላይ በመካሄድ ላይ ያለው ሁኔታ በአፍሪካ አህጉር በማደግ ላይ የሚገኙትን አገሮች ክብርና ነፃነት ለማዳከም በኢምፔሪያሊዝምና በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የታቀደ አደገኛና አዲስ ሁኔታ መሆኑን ፕራቭዳ የተባለው የሶቪየት ኅብረት ኮሚኒስት ፓርቲ ልሳን ትናንት ገለጸ፡፡
ፕራቭዳ ትናንት ባወጣው አስተያየት ይኸው በኢምፔሪያሊዝምና በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የሚደረገው ሤራ በእሳት እንደ መጫወት የሚቆጠር መሆኑን አስመልክቶ ይህንኑ ሤራ በአፍሪካ በመላው ዓለም ሕዝቦች ላይ የሚውጠነጥኑት ክፍሎች ሁሉ በኃላፊነት የሚጠየቁ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
የሶቪየት ኅብረት ኮሚኒስት ፓርቲ ልሳን የሆነው ፕራቭዳ በዚሁ አስተያየቱ ኢምፔሪያሊስቶችና አድኃሪ የዓረብ አገር ገዥ መደቦችና ደጋፊዎቻቸው ሌላ አገር ኅብረተሰባዊነትን የዕድገቱ መመሪያ አድርጎ የመምረጡን ሁኔታ ማቆም እንደማይችሉ ገልጿል፡፡
ቀጥሎም አዲስ የሶሻልና የኢኮኖሚ ሥርዓት ፕሮግራም ያወጀው አዲሱ የኢትዮጵያ አመራር ተራማጅ ለውጦች በማድረግ ላይ መሆኑንና ከመላው ዓለም ተራማጅ ኃይሎችና ሶሻሊስት አገሮች ጋር የመረዳዳት አቋሙን በማጠናከር ላይ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ፕራቭዳ ከዚሁ በማያያዝ በኢትዮጵያ የሚካሄደው አብዮት በጣም እየገፋ መሔዱንና ይህም ርምጃው ኢምፔሪያሊስቶችንና አድኃሪያንን ያስደነገጣቸው መሆኑን ገልጿል፡፡ ስለዚህም የውስጥ ፀረ አብዮትን ከመደገፋቸውም ሌላ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ ግጭት እንድትጀምር በመገፋፋትና ተገንጣዮችን በማደፋፈር አገሪቱን በመገነጣጠል አሁን በመካሔድ ላይ ያለውን አብዮት ለማዳከም ጥረት እንደሚያደርጉ አስረድቷል፡፡
ቀጥሎም ኢምፔሪያሊዝም በአፍሪካ አህጉር የብሔሮች ነፃነት ንቅናቄዎችና ተራማጅ እንቅስቃሴን ለመግታት እንዲችል በምስራቅ አፍሪካ (በአፍሪካ ቀንድ) ክፍል ዋና ሠፈር የማዘጋጀት ተስፋ ያለ መሆኑን ገልጿል፡፡
የዓለም ኅብረተሰብ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው የኢምፔሪያሊስት ሤራ በጥብቅ እንደሚያወግዘው ፕራቭዳ አመልክቶ ቀና መንፈስ ያላቸው ሕዝቦች ሁሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሙሉ አባል በሆነች አገር የውስጥ ጉዳይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት እንዲቆም የሚጠይቁ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
ሐምሌ 10 ቀን 1969 ዓ.ም
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2013