በፋሽን ሳምንቶች አልባሳት፣ አዳዲስ የዝነጣ የፈጠራ ውጤቶች ባህል፣ ልማድ ወግን የሚያንፀባርቁ ቁሳቁስን ጨምሮ የመዋቢያ ጌጣጌጦችና ሜካፖች ለእይታ ይቀርባሉ። በዚህም በዘርፉ ላይ ለዓመታት የቆዩ ባለሙያዎች አዳዲስ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁባቸው አጋጣሚዎችን ከማግኘት ባሻገር በደማቁ ትእይንት ላይ ተውበው የመታየት አጋጣሚው ይፈጠርላቸዋል።
በተለይ ይህን መሰል ዝግጅቶች የመገናኛ ብዙሃን ቀልብን በሰፊው ከመሳባቸው የተነሳ አዳዲስ ይፋ የሚሆኑ ስራዎች ለቀናት ለፋሽን ተከታዮች ስለሚቀርቡ አነጋጋሪነታቸው ይጨምራል። በፋሽን ሳምንቶች ውስጥ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ የፊልም ተዋንያን የሚደምቁበት አጋጣሚም ይፈጠራል። ይህ ብቻ ሳይሆን በውበት እና በተለያዩ ቁሳቁስ ላይ ዲዛይነሮችና የስነ ውበት ባለሙያዎች የተጠበቡበትን የፈጠራ ውጤት የሞዴሊንግ ክህሎት ያላቸው ቆነጃጅት የተዋቡበትና ዝግጅቱን ይበልጥ ልብ አንጠልጣይና ተወዳጅ የሚያደርጉበት ሁኔታም ይፈጠራል።
በዓለማችን ላይ እጅግ ከሚታወቁ የፋሽን ሳምንታት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት የፓሪስ፣ሚላን፣ ሎንዶንና ኒዮዎርክ ከተማዎች ውስጥ የሚዘጋጁት ሳምንታት ናቸው።
የፋሽን ሳምንቶች ለህዝብ ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ የተለያዩ አልባሳትና ጌጣጌጦችን በማሳየት የሚደረጉ ዝግጅቶች ናቸው። ይህ አይነት ፅንሰ ሃሳብ በይፋ መተዋወቅ የጀመረው በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ ዘመን በዋናነት አዳዲስ አልባሳትና የመዋቢያ ጌጣጌጦች ለገበያተኛው ማቅረብ በሚያስፈልግበት ወቅት ዲዛይነሮችና የፈጠራው ባለቤቶች በፓሪስ ጎዳናዎች ላይ ቆነጃጅቶች ስራዎቻቸውን እንዲያሳዩላቸው መመልመል ጀመሩ። በዚህ አጋጣሚ በአደባባዮችና ለእይታ ምቹ በሆኑ ስፍራዎች ላይ በዲዛይነሮች የተሰሩ የመዘነጫ ቁሳቁስ በይፋ አስተዋወቁ።
ይሄ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ የፋሽን አብዮት በመሆን እነዚህን ተወዳጅ ሳምንታት መፍጠር ቻለ። በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር ከ1900 እና ከዚያ በፊት የፋሽን ሳምንታት ቀስ በቀስ እያደጉ የመጡባቸው ጊዜያት መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ በፋሽን ሳምንቱ እንዴት ትታያለች፡፡ የተለያዩ የፋሽን ሳምንቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ሄድ መለስ እያሉ ቢታዩም ያን ያህል ዘርፉን ለማሳደግ በሚያስችል ሁኔታ ተጠናክረው ሲቀጥሉ አይስተዋልም፡፡ ለዚህም በዋናነት እንደ ችግር የሚጠቀሰው ደግሞ የፋይናንስ አቅምና በዘርፉ በቂ ባለሙያ አለመኖር ነው።
ዲዛይነር ሰናይት ጥበቡ ወደ ፋሽን ዘርፍ ሙያ የገባችው በቅርብ ጊዜ ነው። ዘርፉ ከልጅነቷ አንስቶ በውስጧ የተጸነሰ ፍላጎት መሆኑን ግን ገልጻ፤ በተለይ ይህን ሙያ እንደ ዋና ስራዋ አድርጋ እንድትይዘውና የዲዛይን ሙያዋን በትምህርት እንድታግዘው ልጇ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጓን ትገልጻለች። በተለይ የበዓል ቀናት ሲከበሩ ራሷ ዲዛይን እያደረገች ልጆቿን አልብሳ ወደ ትምህርት ቤት ትልክ ነበር። በልጆቿ የተወደደላት የፈጠራ ስራም ይበልጥ ሙያውን በትምህርት እንድታግዝ እንዳደረጋትና በፋሽን ዘርፍ ላይ ጠልቃ እንድትገባ እንዳደረጋት ለዝግጅት ክፍላችን ገልፃለች። ዲዛይነር ሰናይት የፋብሪክ ዲዛይን መስራችና ስራ አስኪያጅ ነች። ድርጅቷ በሀገራችን የፋሽን ዘርፍ አዲስ ነገር ይዛ መጥታለች፡፡
የፋብሪክ ዲዛይን አዲስ መንገድ
ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ በገርጂ አካባቢ በአልፎዝ ፕላዛ የጎዳና ላይ የፋሽን ትርኢት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ ለእይታ ምቹ በሆነ መንገድ አቅርባለች። በዚህም በአገር ውስጥ በሚመረቱ ጨርቆችና የዲዛይን ውጤቶች ኢትዮጵያውያን እንዴት መዋብ እንደሚችሉ ማሳየት ችላለች። ይህ የጎዳና ላይ የፋሽን ሾው አዳዲስ የፈጠራ ክህሎት የታከለባቸው ልብሶች የተዋወቁበት ነበር። ዲዛይነሯ ይህን መሰል የጎዳና ትርኢትም በየጊዜው በማቅረብ ባህል የማድረግ ራእይ ሰንቃ ተነስታለች።
ዲዛይነር ሰናይት ጥበቡ “ፋብሪክ ዲዛይን ጊዜን፣ ገንዘብን እንዲሁም የውጪ ምንዛሬን ከግምት በማስገባት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአልባሳቱ እንዲዋብ ለማድረግ ታስቦ እንደተቋቋመ” ትናገራለች። በተለይ አልባሳት በማንኛውም ጊዜ አስፈላጊና ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ጠቅሳ፣ ድርጅቷ ይህንን ፍላጎት ማሟላትን እንደ ግብ አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ ታስረዳለች።
ተሰጥኦና ትምህርት
“ተሰጥኦ በትምህርት ሲዳብር የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል” የምትለው ዲዛይነሯ በውስጧ የነበረውን ፍላጎትና ብቃት የበለጠ ማውጣት እንድትችል ትምህርቱ አግዟታል። በዚህም አምቃ ይዛቸው የነበሩ የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚቻል በትምህርት ቤት ውስጥ ተገንዝባለች።
“አንድን ልብስ ዲዛይን ስላደረግነው ብቻ ተቀባይነት ያገኛልና ይለበሳል ማለት አይደለም” የምትለው ዲዛይነር ሰናይት፣ በዋናነት ለየትኛው ቦታ፣ ጊዜና ለምን አይነት ሁኔታ ያስፈልጋል የሚለው መለየት ይኖርበታል በማለት ታስረዳለች። እርሷም ይሄን ታሳቢ አድርጋ በቀላል ወጪና በአገር ውስጥ በሚገኙ ጨርቆች አስውባ ዲዛይን እንደምታደርግና ለዝነጣ ታመቻቻለች።
በሌላ መልኩ ለተወሰነ ጊዜና ለአንድ ዝግጅት የሚደረጉ ባህላዊ አልባሳት ሁሌም ምቹ ሆነው መዋቢያ እንዲሆኑ አድርጋ እንደምትሰራና ዋና አላማዋም ይሄን አስተሳሰብ መቀየር መሆኑን ትገልፃለች። እጅግ ግሩም አልባሳትን ዲዛይን አድርገው የሚሰሩ ባለሙያዎች እንዳሉ ተናግራም ፣ ለተወሰነ ልዩ ቀናትና ለጥቂት የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ የሚደርሱ አልባሳት በመሆናቸው ይሄ አካሄድ መቀየር አለበት የሚል እምነት እንዳላት ትናገራለች። ከዚህ መነሻም የራሷን ስራዎች እንደምትሰራ ነው የምትገልፀው።
የፋሽን ትርኢትና ዲዛይን
ዲዛይነር ሰናይት ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው የሰራቻቸው አልባሳት ለእይታ እንዲበቁና እንዲተዋወቁ በቅርቡ እውቅ ሞዴሎችን ተጠቅማ የፋሽን ትርኢት አድርጋለች። በዚህም ዝግጅቱን በተለያየ አጋጣሚ ከተከታተሉ የዘርፉ ቤተሰቦች ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት ችላለች።
ዲዛይነሯ የዲዛይን ውጤቶቿን በማስተዋወቅ ረገድ ስኬታማ ትሁን እንጂ የመጣችበት መንገድ ግን እንቅፋት የበዛበት እንደነበር አልሸሸገችም። ተባባሪ አካላትን በሚፈለገው መንገድ አለማግኘት፣ የፋይናንስ እጥረት እንዲሁም አንዳንድ አካላት ለዘርፉ ትክክለኛ ግንዛቤ አለመያዛቸው ከመሰናክሎቹ ውስጥ ጥቂቱ መሆናቸውን ትጠቁማለች።
ይህም ሆኖ ግን የመጀመሪያ የሆነውን “የጎዳና የፋሽን ትርኢት” በአገር ውስጥ በቀላሉ በሚገኙ ጨርቆች የተሰሩ ውብ አልባሳትን በማስተዋወቅ ህብረተሰቡ ውስጥ “እንዲህም በቀላሉ መዘነጥ ይቻላል” የሚለውን ግንዛቤ መፈጠር ችላለች። አልባሳቱም ኢትዮጵያዊ ይዘታቸውንና የአለባበስ ስርአትን ባላፈነገጠ መንገድ እንዲሆኑ አርጋ በጥንቃቄ መስራቷን ትናገራለች። በተለምዶ “ጎጃም አዘነ” የሚባል ስያሜ ባላቸው ጨርቆች እንደተሰሩም ነው የምትገልጸው።
ዲዛይነር ሰናይት ተሻጋሪ ራዕይ አላት። አልባሳትን ዲዛይን ከማድረግ ባለፈ በቀጣዮቹ ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ “የዲዛይኒንግ ማሰልጠኛ” ትምህርት ቤት ለመክፈትና በጋርመንት ኢንዱስትሪ ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን አቅዳለች። “ህልሜን ለማሳካት እየሰራሁ ነው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን እንደማደርገው ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር የነበራትን አጭር ቆይታ አጠናቅቃለች።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2013