27ኛው የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር ዓመታዊ ውድድር ከትናንት በስቲያ በቢሾፍቱ ከተማ በተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች ተጀምሯል። ለሃያ አምስት ዓመታት ተካሂዶ ባለፈው ዓመት ብቻ በኮቪድ-19 ስጋት ሳይካሄድ የቀረው ይህ ውድድር ዘንድሮ የወረርሽኙ ጉዳይ ባይለይለትም እንደ አገር የተቀመጠውን የጥንቃቄ እርምጃ ተግባራዊ በማድረግ ለቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሚቀጥል ይሆናል። የወረርሽኙ ስጋት አሁንም ድረስ ባይቀረፍም በውድድሩ የሚሳተፉ የጤና ቡድኖች ራሳቸውን ከወረርሽኙ ለመከላከል አንዱ መንገድ ስፖርት መሆኑን በማመን ወደ ውድድሩ እንደገቡ ታውቋል። ማህበሩ ዓመታዊ ውድድሮችን በዚህ ዓመት ለማስቀጠል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ውድድሮቹ በዚህ ወቅት እንዲቀጥሉ የተደረገው ሌላው ማህበረሰብ ወደ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በስፋት እንዲገባ ለማነቃቃት ጭምር ነው። በዘንድሮው ውድድር ሃያ ሁለት የማህበሩ አባላት የሆኑ የጤና ክለቦች በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች ተከፍለው ውድድር ያደርጋሉ። በዚህም ከሃምሳ ዓመት በላይ አራት ክለቦች፣ ከአርባ ዓመት በላይ ዘጠኝ ክለቦች፣ ከሰላሳ አምስት ዓመት በላይ ዘጠኝ ክለቦች የሚሳተፉ ይሆናል።
በ1986 ዓ.ም ከሁለት የጤና ቡድኖች ተነስቶ ምስረታውን ያደረገው የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር አሁን ላይ የማህበራቱን አባላት ቁጥር ከአርባ ሦስት በላይ ሆነዋል። እነዚህ ማህበራትም በተለይም በየዓመቱ ክረምት ወራት ላይ በቢሾፍቱ የሚያደርጉት ዓመታዊ ውድድር ትልቅ እውቅናን ማግኘት ችሏል፡፡
የጤና ስፖርት ማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈራ ደንበል፣ማህበሩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ከማድረግ ባሻገር በርካታ ግቦችን ማሳካት እንደቻለ ይናገራሉ። የማህበረሰቡን በተለይም ከ35 ዓመት በላይ የሚገኙና በብሔራዊ ፌዴሬሽን ደረጃ ተመዝግበው ውድድሮችን የማያደርጉ ሰዎች በዚህ የጤና ስፖርት ማህበር በኩል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ማስቻል ማህበሩ ካሳካቸው ግቦች አንዱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ተፈራ፣ በዚህም በርካቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉና በየሳምንቱ ውድድሮችን በማሰብ ልምምድ እንዲሰሩ ማድረግ እንደተቻለ አስረድተዋል። ማህበሩ የሚያካሂዳቸው ውድድሮች የማስ ስፖርት ይዘት እንዲኖራቸው በማስቻልም ማህበራዊ ግንኙነቶች እንዲፈጠሩ እንዲሁም በሃዘንና በደስታ ጊዜ መተጋገዝ እንዲኖር በማድረግ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም አብራርተዋል፡፡ ማህበሩ ለበርካታ ዓመታት ውድድሮችን በእግር ኳስ ስፖርት ብቻ ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ አትሌቲክስና የተለያዩ የቤት ውስጥ ውድድሮች መካተት ችለዋል፡፡ በነዚህ ውድድሮቹ ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ግን መካሄድ አልቻሉም። ያም ሆኖ በዘንድሮው ውድድር ብስክሌት ስፖርት እንደተካተተ አቶ ተፈራ ተናግረዋል።
ማህበሩ ባለፉት 25 ዓመታት እነዚህን ተግባራት ሲፈፅም የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠሙት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ተፈራ፣ ዓመታዊ ውድድሮች ከከተማ ውጪ እንደመከናወናቸው የበጀት እጥረት ፈተና እንደነበር አስቀምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማህበሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካሆኑ አካላት ድጋፍ ሳይሻ የማህበሩ አባላት ከኪሳቸው በሚያወጡት መዋጮ እስካሁን መዝለቁን ተናግራዋል፡፡ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ ማህበሩ ጥያቄ ቢያቀርብም የሚሰማው እንዳላገኙ አክለዋል። ማህበሩ የመንግስት ድጋፍ እንደሚያስፈልገውና የሚመለከተው አካልም ያሉበትን ችግሮች ተረድተው ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ጠይቀዋል። ማህበሩ የሚያደርጋቸውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች አይነት የሚደግፈው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና መሰል ተቋማት ድጋፍ እንዳያደርጉም የአደረጃጀት ችግር እንቅፋት እንደሆነ ገልፀዋል። ይህም እንደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያሉ ተቋማት አገር አቀፍ ማህበራትን የሚደግፉ መሆኑና ማህበሩ ደግሞ አደረጃጀቱ እንደ አዲስ አበባ መሆኑ አንዱ እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል።
የማህበሩ መስራች ከሆኑ ሰዎች አንዱ የሆኑትና የመካኒሳና አካባቢ የጤና ስፖርት ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ፋኑኤል ደበበ የጤና ስፖርት ማህበሩ የረጅም ዓመት ታሪክ ያለው መሆኑን በማስታወስ አብዛኞቹ አባላት ከብሔራዊ ቡድን እስከ ከተለያዩ ክለቦች ተጫውተው ያሳለፉ መሆኑን ይናገራሉ። እነዚህ በስፖርቱ ያሳለፉ ሰዎች በስፖርቱ እንዲቀጥሉና ጤናቸውን እንዲጠብቁም ማህበሩ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በርካቶች በዚህ የጤና ስፖርት እንቅስቃሴ ተጠቃሚ መሆናቸውን በመጠቆምም የማህበሩ አባላት ከራሳቸው አልፈው ትውልድ እየተኩ እንደሚገኙና ከስፖርታዊ እንቅስቃሴው ባሻገር ቤተሰባዊ ትስስር መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል።
ውድድሩ በሚካሄድባት ቢሾፍቱ ከተማ ባለፉት ሃያ ዓመታት እየተጫወቱ የሚገኙት አቶ ደረሰ ተሰማ በበኩላቸው፣ የጤና ስፖርት ማህበራቱ በስፖርት ጤናን ከመጠበቅና አእምሮን ከማሳረፍ ባሻገር በማህበራቱ አባላት መካከል ፍቅርና መተሳሰብን መፍጠር እንደተቻለ ይመሰክራሉ። ይህ ውድድር በየዓመቱ በቢሾፍቱ መካሄዱም ለከተማውና ለነዋሪዎቿ እንደ ቱሪዝም እያገለገለ እንደሚገኝ አስተያየት ሰጥተዋል። በዚህም በከተማዋ በርካታ ተቋማትና ነዋሪዎች በኢኮኖሚ ደረጃ እየተነቃቁና የረፍት ጊዜያቸውንም በስፖርቱ ማሳለፍ እንዲችሉ ማድረጉን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የጤና ስፖርት ማህበር በኢትዮጵያ የተቋቋመ የመጀመሪያው የጤና ስፖርት ማህበር ሲሆን ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ የስፖርት ፍቅርና ዝንባሌ ያላቸውን የህብረተሰ ብክፍሎችን በተለያየ ምድብ ከፍሎ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ ግለሰቦችን በማካተት፤ ለአገር መጥቀም የሚችሉ ዜጎችን ከአልባሌ ሱስና ከአላስፈላጊ ስብዕናዎች እንዲሁም ከተለያዩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ጭንቀት በመጠበቅ ረገድ ለህዝብና መንግስት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013