የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በችግኝ ተከላ ረገድ እየተደረገ ካለው ርብርብ ጎን ለጎን የደን ጭፍጨፋን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ይሁንና በርካታ ሀገራት ለችግኝ ተከላ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ያሉትን ያህል የደን ጭፍጨፋን በመከላከል ረገድ እየሰሩት ያለው ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
በየዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ እየተተከለ ቢሆንም ጭፍጨፋን በመከላከል ረገድ ተገቢው ስራ ባለመሰራቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አመርቂ አይደለም። ከዚህ ጋር በተያያዘም በአሁኑ ወቅት ዓለም ከባድ ችግር ውስጥ ገብታለች፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ የሚከሰቱ የጎርፍ እና የሰደድ እሳት አደጋዎችም የዚሁ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ቶፋር ኋይት በአሜሪካ የሚኖር የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ነው፡፡ የወደፊቱ የዓለማችን ሁኔት ክፉኛ ያሳስበዋል፡፡ አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮች እየተባባሱ ከሄዱ ዓለም ከባድ ችግር ውስጥ ልትወድቅ ትችላለች የሚል ከባድ ስጋት ገብቶታል፡፡ ይህንን ችግር ለመከላከል ብሎም ለመቋቋም አዲስ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት የሆነ ፈጠራ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ የዓለማችን የወደፊት ሁኔታ ቢያሳስበው የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጨወትና እፀዋትን ከመጥፋት ለመታደግ የሚያስችል ፈጠራ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡
የተጣሉ የሞባይል ስልኮችን እና የፀሐይ ሀይል መሰብሰቢያ ፓነሎችን በመጠቀም ድምፅ መሰብሰቢያ መሳሪያውን መስራት መጀመሩን ያብራረው ቶፌር ኋይት፤ በደን መጨፍጨፍና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለመቀልበስ የሚያስችል ትልቅ ስራ በመስራት ላይ መሆኑን ነው የገለፀው፡፡ በዚህ ስራ ትልቅ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም አስረድቷል፡፡
‹‹አውት ሳይድ ቢዝነስ ጆርናል›› የተሰኘ መጽሄት እንዳስነበበው ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ከዓለም የደን ሀብት ውስጥ ግማሽ የሚሆነው ወድሟል። ውድመቱ በአሁኑ ወቅትም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በቶፈር ዋይት የተዘጋጀው የፈጠረ ውጤት ዋነኛው ማጠንጠኛም በደኖች ውስጥ ገብተው ደንን የሚጨፈጭፉ ሰዎችን ለደን ጠባቂዎች ማሳወቅ ነው። ፈጠራው የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ እና ሰዎች ተቀናጅተው ደንን ከውድመት የሚታደጉበት ይህ ስርዓት ሬይን ፎረስት ጋርዲያን (የደን ጠባቂ) የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል፡፡
መተግበሪያው በጥበቃ አካላት ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ የሚጫን ሲሆን በመቀጠልም መተግበሪያው በየትኛውም የደን ክፍል ያለውን ሰዎች እንዲሁም ዛፎችን ለመቁረጥ የሚያገለግሉ የስለታማ መሳሪያዎችን ድምጽ እንዲሁም የተቆረጡ ዛፎችን ከደን ውስጥ ለማውጣት የሚገቡ እና ይዘው የሚወጡ ተሸከርካሪዎችን ድምጽ እንቅስቃሴ በመከታተል ጥቆማ ያደርሳል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን በደን ውስጥ ያለ የትኛውንም እንቅስቃሴ መለየት የሚችል ነው። ከቅጠሎች መውደቅ እስከ አዕዋፋት ዝማሬ እና እንቅስቃሴ ብሎም እስከ አራዊት እንቅስቃሴ ያሉ አነስተኛ እና ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ከዚህ መተግበሪያ ሊያመልጥ አይችልም፡፡
ድምጾችን ሰብስቦ ወደ ተንቀሳቃሽ ስልኩ መተግበሪያ የሚልኩ ድምጽ የመሰብሰብ አቅም ያላቸው መሳሪያዎች በደኑ ውስጥ በሚገኙ ትላልቅ ዛፎች ላይ የሚታሰር ሲሆን፤ 10 የድምጽ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች በሚገኙ ትላልቅ ዛፎች ላይ ቢታሰሩ አንድ ሰፊ ደን ውስጥ ያለውን እቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ለመከታተል እንደሚያስችል የፈጠራው ባለቤት የሆነው ቶፈር ኋይት አውትሳይድ ቢዝነስ ጆርናል ለተሰኘው መጽሄት አብራርቷል፡፡
ቶፈር የፈጠራው ሀሳብ እንዴት ወደ አዕምሮው እንደመጣ ሲያስታውስ የዛሬ 9 ዓመት ገደማ ወደ ኋላ በሀሳብ ይሄዳል፡፡ እ.አ.አ በ2012 ቶፋር ኋይት ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን በኢንዶኔዥያ የጊቦን ጥብቅ ደንን እየጎበኘ በነበረበት ወቅት በአቅራቢያው ባለው ጫካ ውስጥ በኤሌክትሪክ እና በነዳጅ ሀይል የሚሰራ እንጨት ለመቁረጥ ጥቅም ላይ የሚውል የቼይንሶው የተሰኘ የእንጨት መቁረጫ ድምፅ ይሰማል። ከጓደኞቹ ጋር ድምጹን ወደሰሙበት አቅጣጫ ይሮጣሉ፡፡ ቦታው ሲደርሱ አንድ ሰው አንድ ትልቅ የሚያምር ዛፍ በመቁረጥ ላይ ነበር፡፡ እነሱ በቦታው ሲደርሱ ዛፉን ሲቆርጥ የነበረው ህገ ወጥ ግለሰብ በእጁ የያዘውን መሳሪያ ጥሎ ፈረጠጠ። ቶፈር በኢንዶኔዥያ ያጋጠመው ነገር በውስጡ ሲመላለስ ቆየ፡፡ የደን ጭፍጨፋ የሚያማምሩ ጥንታዊ ዛፎች ከማጥፋት ባሻገር የደን ጭፍጨፋ የተለያዩ አራዊቶች እና አዕዋፋት ዝርያዎችም እንዲጠፉ ምክንያት እንደሚሆን ገብቶታል፡፡
የ35 ዓመቱ የኢንጂነርንግ ምሩቁ ቶፈር ኋይት ይህን ውስብስብ ችግር እንዴት መፍታት እንደሚቻል ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ችግሩን ለማስቆም አስተማማኝ መንገድ ዛፎችን የሚጨፈጭፉ ህገ ወጥ ሰዎችን መቆጣጠር መሆኑን እርግጠኛ ሆነ፡፡ እነዚህን ህገ ወጥ ሰዎችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ማሰላሰል ጀመረ፡፡ የተጣሉ የሞባይል ስልኮችን ፣ የፀሐይ ፓነሎችን እና የተለያዩ የኮምፒዩተር ክፍሎችን በመጠቀም የእንጨት መቁረጫዎችን ድምጽ ከአእዋፋት እና ከአራዊት ድምጽ ለመለየት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል አሰበ፡፡ ይህንንም ሀሳብ ወደ ተግባር ከቀየረ ችግሩን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስራ መስራት እንደሚችል እርግጠኛ ሆነ፡፡
በትልቅ መነሳሳት ውስጥ ገብቶ የነበረው ቶፈር ወደ ሀገሩ አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ በፕሮጀክቱ ላይ መሥራት ጀመረ። ለፈጠራው አስፈላጊ የሆኑ የተጣሉ ስልኮች ለማግኘት ቀላል ነበር፣ ከፀሐይ ሀይል መሰብሰብቢያ ፓነሎችንም ማግኘት እንዲሁ ለሱ ቀላል ነበር፡፡ ነገር ግን የተጣሉ ስልኮች እና የጸሃይ ሀይል መሰብሰቢያ ፓናሎች ብቻቸውን በቂ አልነበሩም፡፡ ዛፎቹ ውስጥ እንቅስቃሴዎች በሚደረግበት ወቅት ከቦታው ርቀው ለሚገኙ የደን ጠባቂዎች መረጃ የሚያስተላልፍ ሶፍትዌር መፍጠር የግድ ነበር፡፡
በፕሮጀክቱ ላይ ለአንድ ዓመት ሲሰራ ከቆየ በኋላ ስራውን ጨርሶ የፕሮጀክቱን ውጤታማነት ለመሞከር ተመልሶ ወደ ኢንዶኔዥያ አቀና። ፈጠራው እንደሚሰራ እርግጠኛ አልነበረም፡፡ ሙከራውን ጀመረ፡፡ ለሙከራ የፈጠራ መሳሪያዎቹን በሰቀለበት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አንድ ሰው በዙሪያው ባለው ደን ውስጥ አንድ ዛፍ መቁረጥ ጀመረ። የስልኩ ማይክሮፎን ጩኸቱን ጀመረ። የደን ጥበቃ ቡድንም ዛፉ ወደሚቆረጥበት አቅጣጫ ከነፉ፡፡ ዛፎች የሚቆረጥበት አካባቢም ደረሱ፡፡ ቶፈር ዋይትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሄክታር ደንን ሊያድን የሚችል መሣሪያ እንደፈጠረ እርግጠኛ ሆነ።
‹‹ሰዎች የደን መጨፍጨፍ ’የሚለውን ቃል ሲሰሙ ወደ አዕምሮአቸው ወዲያውኑ የሚመጣው ስለዛፎች መቆረጥ እና መሬት ገላጣ ስለመሆን ነው›› የሚለው ቶፈር፤ ነገር ግን የዛፎች ጭፍጨፋ አሉታዊ ተፅዕኖ እጅግ ሰፊ መሆኑን ያለመረዳት ችግር አለ ይላል፡፡ በየቀኑ በጣም በርካታ ዛፎች እንደሚጨፈጨፉ ያብራረው ቶፈር፤ ዛፎች ካርቦን የመያዝ እና የማከማቸት አቅም ያላቸው መሆናቸውን ገልፆ፤ የዛፎች መቆረጥ በዛፎች ላይ የተከማቸውን ካርቦን ወደ ከባቢ አየር ከመልቀቅ ባሻገር ካርቦን ዳይኦክሳይድንም ወደ አየር እንደሚረጭ ያስረዳል፡፡
ፈጠራው የተለያዩ አዕዋፋት እና አራዊት እንቅስቃሴዎችን እና ድምጾችን የመቅረጽ አቅም ያለው እንደመሆኑ መጠን ከደን ጥበቃ ባሻገር ሌሎች ብዝሃ ህይወቶችንም ለመጠበቅ የላቀ ሚና እንደሚጨወት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በተለይም የተለያዩ አዕዋፋት እና አራዊት ባህሪዮችን እና ሌሎች ነገሮችን ለማጥናት ለዘርፉ ሊህቃን አዲስ እድል የሚከፍት እንደሚሆን የዘርፉ ሊህቃን እየተናገሩ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የደን መጨፍጨፍ ለአየር ንብረት ለውጥ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር በነዚህ ደኖች ውስጥ የሚኖሩ ነባር ጎሳዎች እንዲጠፉም ከፍተኛ አስተወጽኦ እያበረከተ መሆኑን የሚጠቁመው ቶፈር፤ ለዚህም በአማዞን ደን ውስጥ የሚኖሩ እና ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠውን ‹‹ቴምቤ›› የተሰኘውን ጎሳ እንደማሳያ አንስቷል፡፡ የደኖችን መመናመንን ለመቆጣጠር የሚያስችለው የሱ ፈጠራ ግን እነዚህንም ህዝቦችን ጭምር ከመጥፋት እንደሚታደጋቸው ነው ያብራረው፡፡
ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ እያደረገች ቢሆንም የደኖች ጭፍጨፋን በመከላከል ረገድ እየተሰራ ያለ ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ደኖች እየተጨፈጨፉ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ እየሆነች ትገኛለች፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ለነገ የማይባል ስራ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል በውጭ ሀገራት የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ ማለመድ በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ የፈጠራ ሰዎች መሰል ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መስራትም ያስፈልጋል፡፡
መንግስት ለችግኝ ተከላ የሰጠውን አይነት ትኩረት የደን ጭፍጨፋን ለመከላከልም ሊሰጥ ይገባል፡፡ የደን ጭፍጨፋ ለመከላከል የሚያያስችሉ የፈጠራ ስራዎችን የሚሰሩ ሰዎችን በማበረታታት እና አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ችግሩን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርብ ሊያደርግም ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የምርምር ተቋማት መሰል የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013