
በፊልም ታሪክ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑት እና ብዙ ተመልካች ካገኙት ፊልሞች መካከል አንዱ ‹‹ጌም ኦፍ ትሮንስ›› /Game of Thrones/ የተሰኘው ፊልም ባለ 8 ምእራፍ ፊልም ነው፡፡ በ207 ሀገራት እንደታየ እና በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሰበሰበ በሚነገርለት በዚህ ፊልም ላይ ረዥም ቆይታ ከነበራቸው ገጸባህርያት መካከል የሰላይ አለቆች ሆነው የሚሰሩት ቫሪየስ እና ሊትል ፊንገር የተባሉት ገጸ ባህርያት ሲያወሩ ‹‹ ሁከት መሰላል ነው ….›› / chaos is a ladder …./ ይላሉ፡፡
ይህን ንግግር ያነሳሁት በኢትዮጵያ በሚፈጠር ሁከት ወደ ሀብት ከፍታ ለመንጠላጠል ስለሚሰሩ ግለሰቦች ለማንሳት ነው፡፡ ብዙ ናቸው፡፡ ስራቸው እና ምኞታቸው አንድ ነው፡፡ ስራቸው በኢትዮጵያ የማይቆም ሁከት መፍጠር እና በዚህ ሂደት ትግራይን ሀገር ማድረግ ነው። ምኞታቸው ደግሞ ከዚህ ሰይጣናዊ ዓላማ ሀብት መሰብሰብ ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች በተለምዶው የጦርነት ነጋዴዎች / war enterpreneurs/ ይባላሉ፡፡ ሙያቸው ብዙ ነው። እንዳንዶቹ ነጋዴዎች ፤አንዳንዶቹ ምሁራን ፤ ሌሎች ደግሞ ጋዜጠኞች ፤ ዲሎቶማቶች ወዘተ… ናቸው፡፡ ግን መደበኛ ስራቸውን የሚጠቀሙት ለሽፋን ነው፡፡ ዋናው ተልእኮአቸው ግጭትን መቀስቀስ እና በዚያ ተንጠላጥሎ በሀብት እና በዝና ከፍ ማለት ነው፡፡
ሰሞኑን አንድ የደህንነት ሪፖርት ወጥቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር ነበር፡፡ ሪፖርቱ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች በተነደፈው ስትራቴጂ መሰረት አምስት ተግባራት የሚከናወኑ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል አሉታዊ የሚዲያ ዘገባ እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማካሄድ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻው የሚካሄደው ደግሞ ምሁራን ነን በሚሉ ጥቅመኞች እና ገንዘብ ከተሰጣቸው ማንኛውንም ነገር በሚሰሩ ተቋማት በኩል ነው፡፡
ሁሉንም እናውቃቸዋለን፡፡ አንዳንዶቹ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ኪሳራ የማትረፍ ልምድ ያላቸው ናቸው።እንደ ታምራት ላይኔ እና ያሬድ ጥበቡ ያሉት ማለት ናቸው። አንዳንዶቹ የሚወዷት ህወሓት ህይወት የሚኖራት ኢትዮጵያ ከሞተች ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ እንደ አሉላ ሰለሞን ፤ ስታሊን ገ/ስላሴ እና ሰለሞን ተካልኝ ያሉት ማለት ነው፡፡
እንደ ጄቲ ትሮንቪል እነ ማርቲን ፕላውት እነ ረሺድ አብዲ እነ ዊሊያም ዴቪድሰን የመሳሰሉት የውጭ ጠላቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ራሳቸውን በኢትዮጵያ ጉዳይ ኤክስፐርት ብለው ሾመዋል፡፡ ሁሉም መፍቀሬ ህወሓት ናቸው፡፡ ሁሉም ዓላማቸው አንድ ነው ፤ ገንዘብ ማግኘት። ገንዘብ እስካስገኘ ድረስ ደግሞ ህወሓት የምትላቸውን ነገር በሙሉ ለመጻፍ ችግር የለባቸውም፡፡
ህወሓት ምን ትላለች? ህወሓትማ ኢትዮጵያ ካልፈረሰች ትግራይ ሰላም አታገኝም ብላ ደምድማለች።ስለዚህም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል የሚገባ ከሆነም ለመግባት ቆርጣለች፡፡ የነ ረሺድ እና ፕላውት ስራም ወደ ሲኦል ከምትወርደው ህወሓት ጋር ኢትዮጵያን አብሮ ማስገባት ነው፡፡
እነዚህ ሃይሎች ትግራይ ሰላም የምታገኘው ኢትዮጵያ ስትፈርስ እንደሆነ በሙሉ ልባቸው አምነዋል፡፡ ይህንንም በይፋ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ ስታሊን ገ/ስላሴ ትግራይ ሚዲያ ሀውስ ላይ በቀጥታ ስርጭት “በህይወቴ ከምኮራባቸው እና ከምደሰትባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ኢትዮጵያ ስትፈርስ በህይወት ቆሜ ማየቴ ነው” ብሏል፡፡
አሉላ ሰለሞንም ይህን ደግሞታል፡፡ አሉላ “ኢትዮጵያዊነት ራሱን በራሱ ያጠፋ ማንነት ነው፡፡ እኛ ትግራዋዮች ከአሁን በኋላ ነጻ ነን፡፡ በመላው ዓለም የምትገኝ ትግራዋይ የራስህን ቤተ እምነት መስርት። የኢትዮጵያውያን ቤተ እምነት እንዳትሄድ፡፡ ከዚያች ከሀዲ ከሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ራስህን አግልል፡፡ ትግሬ ቄሶች የራሳችሁን ቤተ እምነት መሰርቱ፡፡ እንጀራ በርበሬ ስጋ ከኢትዮጵያውያን እንዳትገዙ፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡ በኢትዮጵያ ስም የሚጠሩ ሁሉንም ማህበሮች ተዉ፡፡ ኢትዮጵያ ተብሎ የሚጠራ ማንኛውንም ነገር ተዉ፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ሰላም እንዳትሉ፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጋር የተጋባችሁ በሙሉ ተፋቱ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲፈርስ መስራት አለብን፡፡ በዚህ ጦርነት ትልቁ ድላችን ኢትዮጵያ የሚል ነገርን በሙሉ ማራገፋችን ነው…” እያለ አለኝ የሚለውን ዘለፋ ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ አራግፏል፡፡
ሰለሞን ተካልኝም እንዲሁ ቀን ከሌት ኢትዮጵያን ሲራገሙ ከሚውሉ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሰውየው ሰሞኑን የአሸባራ ህወሓት ጦር ኩርኩም ሲበዛበት በብስጭት በፌስቡክ ገጹ ላይ ብቅ ብሎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቁርጠኛ መሆኑን ከብዙ ስድብ ጋር አብሮ የለጠፈ ሲሆን በኋላ ላይ አነስቶታል፡፡ ሰውየው ያን ልጥፍ ያንሳው እንጂ ሌሎች ልጥፎቹ በሙሉ ኢትዮጵያን በመስደብ እና ኢትዮጵያን ማፍረስ የትግራይ ህልውና መሰረት መሆኑን በመዘብዘብ ላይ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡
ሰሞኑን በዴንቨር በተካሄደ የተጋሩ አመታዊ የጭፈራ ድግስ ላይም “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” የሚለውን ፉክራ እና የተስፋ መቁረጥ ጭፈራ የመራው እሱ ነው፡፡ በጭፈራው ላይ “በቅርቡ ትግራይ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ ስትታይ ኢትዮጵያዊነት ወድቆ ይቀበራል” የሚል በታሪክ የሚዘገብ አሳፋሪ ንግግርም መሪው እሱው ነበር፡፡
ለአሉላም ሆነ ሰለሞን ወይም ስታሊን ኢትዮጵያን መስደብ የገቢ ምንጫቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ መረጋጋት ከስራ ውጭ ያደርጋቸዋል፡፡
ልክ እንደነዚህኞቹ ሁሉ እነ ማርቲን ፕላውት ፤ ጄቲ ትሮንቪል ፤ ረሺድ አብዲ እና ዊሊያም ዴቪድሰንም በኢትዮጵያ መፍረስ እና መክሰር ላይ ተንተርሰው ዘላቂ ገቢያቸውን የሚሰሩ ናቸው፡፡ ሁሉም ትግራይ ወደ ነፍሷ ከተመለሰች እና ቀልብ ከገዛች ብሎም ኢትዮጵያ ሰላም ከሆነች ከህወሓት የሚቆረጥላቸው ቀለብ ይቋረጣል። የነሱን ትንታኔ የሚፈልግ ሚዲያም ሆነ ተቋምም አይኖርም፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ መታመስ እና መፍረስ የነሱ ኢኮኖሚያዊ ህልውና መሰረት ነው፡፡
ራሺድ አብዲ መቀመጫውን ናይሮቢ አድርጎ ዋነኛ ተልእኮው አሁን በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሲዘልፍ መዋል ነው፡፡ የሚከፈለው ከህወሓት እና ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ ከጀመሩ ሀገራት የደህንነት ቢሮዎች ነው፡፡ ሰውየው የሁከት ነጋዴ ነው፡፡
ዊሊያም ዴቪድሰንም ከተራ ጋዜጠኝነት ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ ተንታኝ ምሁርነት ያደገ ሰው ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ በሚናገረው ሟርት የተነሳ የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ተንታኝ ሆኗል፡፡
ማርቲን ፕላውት እንዲሁ በምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ ከኔ በላይ አዋቂ የለም የሚል ጋዜጠኛ ነው፡፡ ትሮንቪልም እንዲሁ በድሮዋ መቀሌ ደሞዝ የሚቆረጥለት ፤ ውስኪ እና ሌላም ሌላም የሚቀርብለት የጌታቸው ረዳ ወዳጅ ነው፡፡ ሁሉም የነ አሉላ እና ስታሊን እንግሊዝኛ ቅጂዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ዳግማዊት ዩጎዝላቪያ እንደምትሆን ሲተነብዩ ነው የኖሩት፡፡ አሁን ደግሞ ያን የዩጎዝላቪያ ህልም እውን ለማድረግ የጁንታው ከፋዮቻቸው እና የምእራቡ ዓለም አለቆቻቸው ቁርጠኛ ሆነዋል፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት የሚለውን ደጋግመው እየሰበኩ ይገኛል፡፡
ደብረጽዮን ባለፈው ሰሞን ከውጭ ሚዲያዎች ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ህወሓት በዘላቂነት ሰላም ሆና በህይወት እንድትቆይ ስጋት የሚሆኑባትን ሃይሎች ለማስወገድ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ የሚያስወግዱት ደግሞ ያው ኢትዮጵያን መሆኑ ነው፡፡
ጌታቸው ረዳም በዚህ ሳምንት ከቢቢሲ ሀርድ ቶክ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ይህንኑ ደግሟል፡፡ መከላከያውን ማፍረስ እና መንግስትን ማውረድ በመጨረሻም ኢትዮጵያን ቢቻል ማፍረስ ባይሆን ማዳከም ቁርጠኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በአስገራሚ ሁኔታ የቢቢሲውን ቃለመጠይቅ ያደረገው ጋዜጠኛ ስቴፈን ሳከር እንኳ ህወሓት ለሰላም ቁርጠኛ አለመሆኑን እና እንዲያውም የተገንጣይነት አቋም ይዞ እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ነግሮታል፡፡ ነገር ግን አሁን እንደ ፈርኦን ልቡን ያደነደነው የአሸባሪው አመራር እና ተከፋይ አፈቀላጤዎቹ ኢትዮጵያን በመስቀል ላይ ለማዋል በይሁዳዊ ጉዞአቸው ጸንተዋል፡፡
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013