ሶስት የዓለም፣ 12 ኦሊምፒክ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ብሄራዊና አካባቢያዊ ክብረወሰኖች የተሰበሩበት የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በታሪክ ‹‹ምርጡ›› ተሰኝቷል። ከስፖርተኞች ብቃትና ከተመዘገቡት ክብረወሰኖች አለፍ ሲል ደግሞ በእርግጥም ኦሊምፒኩ አስደናቂና የማይዘነጉ ትዕይንቶች በስፋት የታዩበት መሆን ችሏል ።
በአጠቃላይ በኦሊምፒኩ ውድድር ከተካሄደባቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ አትሌቲክስ ሲሆን፤ ለ10 ቀናት ሲካሄድ በሰነበተው ውድድር፤ አስደሳችና አስደናቂ ጉዳዮች፣ ልብ ሰባሪ ክስተቶች፣ አስደናቂ ቃለ ምልልሶችና ንግግሮች፣ ጡጫና መገጫጨት፣… የመሳሰሉትን አስተናግዷል። ከሁሉም በላይ ግን የኦሊምፒክን አስኳል ሃሳብ በተግባር ያሳዩ ሊባሉ የሚችሉ ሰዋዊና ወንድማማችነትን አጉልተው ያሳዩ ክስተቶች ተስተውለውበታል። የዓለም አትሌቲክስ ከመካከላቸው የተመረጡ 10 አይረሴ ጉዳዮችን መርጦ ካስመለከታቸው ዘገባዎቹ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
ወዳጅነት እስከ መሸናነፍ
በወንዶች 1ሺ500 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ላይ የታየው ተፎካካሪነትና የወዳጅነት ስሜት የብዙዎችን ልብ የነካ እንዲሁም ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ነው። ነገሩ እንዲህ ነው፤ ከኦሊምፒኩ አስቀድሞም በዚህ ርቀት የሚታወቁት ሁለት አትሌቶች የተለመደውን የአሸናፊነት ግምት አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ካለፉት የውድድር ውጤቶች በመነሳት ቅድመ ግምቱ ወደ አንደኛው አትሌት ያደላ ነበር። አትሌቶቹ ኬንዊው ቲሞቲ ችሪዮት እና ኖርዌጂያዊው ጃኮብ ኢንጌብሪጅትስ በተለያዩ መድረኮች ተገናኝተዋል፤ የፉክክራቸው መጨረሻ የሚደመደመውም በምስራቅ አፍሪካዊው አትሌት ነበር። ሁለቱ በተገናኙባቸው ያለፉት 12 ውድድሮች ቻምፒዮኑ ችሪዮት ሲያሸንፍ ኖርዌያዊው ደግሞ እርሱን ተከትሎ በመግባት ይታወቃሉ።
ላለፉት 12 ወራት ግን ሁለቱም በውድድሮች ላይ ሳይገናኙ ወደ ቶኪዮ አቀኑ። የማጣሪያ ውድድሮችን አልፈው ፍጻሜው ላይ ሲደርሱም በድጋሚ ፉክክራቸውን ለዓለም ማሳየት ጀመሩ። ሁለቱ ፈጣን አትሌቶች ለሃገር ክብር ነውና የሚሮጡት አሸናፊ ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ውድድሩን እጅግ አከረሩት።
ውድድሩ 400 ሜትሮች ሲቀሩት ግን ችሪዮት እንደለመደው አፈትልኮ በመውጣት ወደ አሸናፊነቱ መገስገስ ጀመረ፤ 200ሜትር ላይ ደግሞ የምንጊዜም ተፎካካሪው ጃኮብ ከየት መጣ ሳይባል ቀዳሚ ሆነ። ችሪዮት ሊደርስበት ስላልቻለ ጃኮብ 3፡28፡33 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ የመጨረሻዋን መስመር ረገጠ። ይህም ሰዓት ለአትሌቱ፣ ለአውሮፓ እንዲሁም ለኦሊምፒክ አዲስ ክብረወሰን መሆኑ ተነገረ። ችሪዮት ተከትሎት የመጨረሻዋ መስመር ላይ ሲደርስ ሰዓቱ 3፡29፡01 ሲል ቆጥሯል። የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ችሪዮት በመሸነፉ አልከፋውም፤ ይልቁንም መገረምና በጃኮብ ብቃት መደነቁን በሚያሳይ መልኩ የእጁን ጌጥ አንድም በማስታወሻ አንድም በሽልማት መልክ አውልቆ ለምን ጊዜም ተፎካካሪው አደረገለት።
ጃኮብ ከሜዳሊያውና በሃገሩ ከሚጠብቀው ማበረታቻ አስቀድሞ በዚያች የደስታ ቅጽበት ውዱን ሽልማት ተጎናጸፈ። በኋላ ላይ ስለ ሁኔታው የተጠየቀው ችሪዮትም ‹‹ከክፍሌ ስወጣ ዛሬ አንድ ሰው እኔን ማሸነፍ ከቻለ የእጄን አምባር እሸልመዋለሁ ስል ለራሴ ነግሬው ነበር›› ሲል መለሰ።
ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ እርሱን ተከትሎት የገባው እንግሊዛዊው ጆሽ ኬር አጨራረስ ሲሆን፤ አትሌቱ ከኬንያዊው ጋር እኩል ሊባል በሚችል ደረጃ በማይክሮ ሰከንዶች ተበልጦ (3፡29፡05) ሶስተኛ ሆነ። በርቀቱ የመጨረሻ መስመር ላይ የታየው የአትሌቶቹ ብቃት እንዲሁም ብርቱ ተፎካካሪነታቸው ተወዳዳሪዎቹ ምን ያህል አቅማቸው ተቀራረቢ እንደሆነ የሚመሰክር ነበር።
ሁለት አሸናፊዎች
በዚህ ኦሊምፒክ አዲስና የማይረሳ ታሪክ ያጻፉት ኦሊምፒያኖች ደግሞ ጣሊያናዊው ጂያንማርኮ ታምቤሪ እና ኳታራዊው ሙታዝ ባርሺም ናቸው። ሁለቱ የከፍታ ዘላዮች ከዚህ ኦሊምፒክ አስቀድሞም የጠነከረ ጓደኝነት ነበራቸው። እንዳጋጣሚ ሆኖም ሁለቱም የረጅም ጊዜ ጉዳት ውስጥ ቆይተው ከሜዳ ርቀው በቶኪዮ ኦሊምፒክ ነው ወደ ውድድር የተመለሱት። ታምቤሪ ጉዳት የደረሰበት ከሪዮ ኦሊምፒክ አስቀድሞ ሲሆን፤ ባርሺም ደግሞ እአአ ከ2018 ጀምሮ ጉዳት ላይ ቆይቷል።
በኦሊምፒኩ ሁለቱም የወርቅ ሜዳሊያ ለማግኘትም የየሃገራቸውን መለያ ለብሰው ከውድድር ስፍራው ተገኙ። ሁለቱም ተመሳሳይ ውጤት በማስመዝገባቸው ሊለያዩ የሚችሉበትን አማራጭ ከውድድር መሪዎቹ ለመስማት ተሰየሙ። ዳኞች የመለያ አማራጫቸውን በማስቀመጥ ላይ ሳሉ ግን ባርሺም ቀልጠፍ ብሎ ‹‹ሁለታችንም የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት እንችላለን?›› ሲል ጠየቀ። ዳኛው ‹‹ይቻላል›› ከማለታቸው ቀጥሎ የሚሉትን መስማት ሳያስፈልጋቸው አትሌቶቹ እርስ በእርሳቸው ደስታቸውን በመተቃቀፍ ይገልጹ ጀመር። ድላቸው በዚሁ ጸንቶም ሁለቱም አትሌቶች በእኩል የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ታሪካዊ አትሌቶች ሆነዋል።
በለንደንና በሪዮ ኦሊምፒኮች የነሃስ እና የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ እንዲሁም የ2017 እና 2019 ቻምፒዮናው ባርሺም የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆኑ ህልሙን እንደሞላለት ገልጿል። ከውድድሩ በኋላ በሰጠው ቃለ ምልልስም ‹‹በጣም ደስ ብሎኛል፤ አስገራሚ ነበር፤ ሜዳሊያውን ከታምቤሪ ጋር መጋራቴ ደግሞ ይበልጥ አስደሳች ያደርገዋል›› ሲል ሃሳቡን አንጸባርቋል። የሆነው ሁሉ ህልም የመሰለው ታምቤሪ በበኩሉ በገጠመው ጉዳት ወደ ስፖርቱ ዳግመኛ የማይመለስ የመሰለው መሆኑን ጠቅሶ የምንግዜም ህልሙ ለስኬት እንደበቃ መግለጹን ሲኤንኤን በድረገጹ አስነብቧል።
ባለማስታወሻዋ አትሌት
ሌላኛዋ በኦሊምፒኩ የታየችና በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ግርምትን የጫረችው አትሌት ደግሞ ኒኮላ ማክድሮሞት ናት። ይቺ አውስትራሊያዊት የከፍታ ዝላይ አትሌት ፍጻሜውን ጨምሮ አንድ ውድድር አድርጋ ስታበቃ ወደ ጥግ ትሄድና ማስታወሻዋ ላይ አንዳች ነገር ታሰፍራለች። ታዲያ ነገሩ ሲጣራ የኒኮላ ጽሁፍ ማስታወሻ ሳይሆን ግምገማ ሆኖ ተገኘ፤ በውድድሩ ላይ ያሳየችውን ብቃት በመመዘን ልክ እንደ ልጅነቷ ከ10 ውጤት ትይዛለች። አስደናቂው ደግሞ ራሷ በምታርመው ፈተና አንዴም 10ከ10 አግኝታ አለማወቋ ነው፤ ሁሌም ሊሰራበት የሚገባ ነገር አለ ስትልም ታብራራለች። በኦሊምፒኩ 2ነጥብ02 ሜትር በመዝለል የብር ሜዳሊያ ስታስመዘግብ የኦሺንያ ሃገራትን ክብረወሰን ማስመዝገብም ችላለች።
ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በነበራት ቆይታም ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ከ10ሩ 9 እንድታመጣ የረዳት እንጂ 10ከ10 እንዳላስገኘላት ተናግራለች። በለበሰችው የብሄራዊ ቡድን መለያ ላይም ይህንኑ በማስታወሻዋ የምትይዘውን ምዘና ቅጂ አስፍራ ታይታለች። ኒኮላ ነገሮችን በማስታወሻዋ የመመዝገብና የስነጽሁፍ ዝንባሌ ያደረባት በልጅነቷ መሆኑን ትገልጻለች። የ9 ዓመት ታዳጊ ሆና ስፖርት እንደጀመረችም በኦሊምፒክ የመሳተፍ ህልሟን በግጥም መልክ አስፍራለች። ከዓመታት በኋላም ህልሟ እውን ሆኖላት ከነማስታወሻ ደብተሯ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ሃገሯን ለማስጠራት በቅታለች።
የአያቱ ጀግና
ሌላኛው የኦሊምፒኩ የተለየ ገጠመኝ ልብ ሰባሪ፤ ግን ደግሞ አስደሳች መጨረሻ ያለው ነበር። የታሪኩ ባለቤት ደግሞ አሎሎ ወርዋሪው አሜሪካዊ አትሌት ረያን ክሩዘር ነው። አትሌቱ ከውድድር ባለፈ በአሸናፊነት የኦሊምፒክ ክብረወሰንን በመስበር ለሃገሩና ለራሱ ታሪክ አጽፏል። ክሩዘር 23ነጥብ30 ሜትር በመወርወር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚነቱን እንዳረጋገጠም በወረቀት ላይ አንዳች ነገር ጽፎ ለስፖርት ቤተሰቡ አሳየ። ጽሁፉም ‹‹አያቴ አሸንፈናል፤ የ2020 ኦሊምፒክ ቻምፒዮን ሆኛለሁ›› ይላል።
ይህን የተመለከቱም ከወረቀቱ ጀርባ ያለውን ታሪክ ለማወቅ ባደረጉት ጥረት ይህንን ተረዱ። በክሩዘር ህይወት ውስጥ ወንድ አያቱ ትልቅ ስፍራ አላቸው፤ አያትም በተመሳሳይ። የአያትና የልጅ መዋደድ ተፈጥሯዊ ቢሆንም የእነርሱን ልዩ የሚያደርገው አያቱ የክሩዘር ቀንደኛ ደጋፊው በመሆናቸው ነው።
የተፈጥሮ ግዴታ ሆነና ግን በልጃቸው ብቃት እጅግ የሚተማመኑት አያት ልጃቸውን ከትልቁ የስፖርት ውድድር ለመመልከት ሳምንት ሲቀራቸው ላይመለሱ ይቺን ዓለም ጥለው አሸለቡ። የተመኙት ግን አልቀረም፤ የልጅ ልጃቸው ውድድሩን በአሸናፊነት ተወጥቶ እርሳቸውንም በዓለም ህዝብ ዘንድ አሳወቃቸው። ከውድድሩ በኋላ ስለ አያቱ ሲናገርም አያቱ ከመሞታቸው አስቀድሞ ባሉት ጊዜያት የመስማት ችሎታቸው በመቀነሱ ከቤተሰቡ ጋር የሚግባቡት በጽሁፍ ነበር፤ ሆኖም ሁሌም እንዲበረታ ይነግሩት ነበር። ‹‹ማሸነፌን ቢያውቅ እጅግ ይኮራብኝ ነበር፤ ቢሆንም እዚህ አብሮኝ እንዳለ ይሰማኛል። ይህ የተለየ ቀን ነው›› ሲል ከልብ መሰበር በኋላ ያገኘውን ደስታ አጣጥሟል።
እንደ ወርቅ
ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በሴቶች የአሎሎ ውርወራ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል አነዷ ኒውዝላንዳዊቷ ቫሌሪ አዳምስ ናት። ይህቺ አትሌት በተለያዩ ውድድሮች ላይ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችንና ክብሮችን ስትጎናጸፍ ከአምስት ዓመታት በፊት በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ላይ ግን ጉዳት በማስተናገዷ ያገኘቸው የብር ሜዳሊያ ነበር። ካስተናገደችው ከባድ ጉዳት ለማገገም እየተጣጣረች ባለችበት ወቅት ደግሞ እርግዝና ተከተለ። በቀጣዮቹ ዓመታትም መንታ ልጆቿን ከመንከባከብ ጎን ለጎን ወደቀደመ ብቃቷ ለመመለስ ጠንክራ በመስራት በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሶስተኛ ተሳትፎዋን ለማድረግ በቃች። ውድድሩን በነሃስ ሜዳሊያ ብታጠናቅቅም ደስታዋ ግን የወርቅ ሜዳሊያ እንዳጠለቀ አትሌት ነበር። ደስታዋን የልጆቿን ፎቶ በመያዝ የገለጸች ሲሆን፤ ‹‹ሴት ጠንካራ ናት፤ እናት መሆን ትችላለች ከዚያም በውድድር ላይ ትካፈልና በድጋሚ ወደ እናትነቷ ትመለሳለች›› ስትል ሴቶችን የሚያነሳሳና የሚያበረታ መልዕክት አስተላልፋለች።
የቶኪዮ ኦሊምፒክን አንዱ ልዩ የሚያደርገው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከተመልካች ውጪ መካሄዱ ነው። አዘጋጆቹ ግን ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በዘየዱት መላ አሸናፊ አትሌቶችን በተንቀሳቃሽ ምስል ከቤተሰቦቻቸው ጋር ደስታቸውን እንዲጋሩ አስችለዋል።
ካናዳዊው የ200 ሜትር አሸናፊ አትሌት አንድሬ ደግራሴ ከድሉ በኋላ በስታዲየሙ በነበረ ስክሪን ሁለት ልጆቹንና ባለቤቱን በማግኘት ደስታቸውን ሲገልጹ ተመልክቷቸዋል። ይህን በማየቱ በእጅጉ ተደስቷል ። ህንድን ለመጀመሪያ ጊዜ በአትሌቲክስ ስፖርት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ያደረጋት ነራጅ ቾፕራ በማህበራዊ ገጾች የነበሩት 143ሺ ተከታዮች ድሉን ተከትሎ በአንዴ ወደ 3ነጥብ2 ሚሊየን ማደጋቸውም ሌላኛው የማይዘነጋ የኦሊምፒኩ ክስተት ነው።
በየትኛውም መርሃ ግብር ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ማገልገል ጀግና ቢያሰኝም በቶኪዮ የታዩት በጎ ፈቃደኞች ግን የተለዩና የማይዘነጉ የኦሊምፒኩ ክስተቶች መሆናቸውን የዓለም አትሌቲክስ መስክሯል። ከኦሊምፒኩ መክፈቻ እስከ መዝጊያ በነበሩት ጊዜያት አትሌቶች ሲያሸንፉ፣ ቃለምልልስ ሲያደርጉም ሆነ ከውድድር መልስ በፈገግታ የታጀበ ድጋፍ ሲያደርጉላቸው መሰንበታቸውንም አያይዞ ጠቁሟል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2013