የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስትና የልጅ በእድሉ አይደግ መጽሐፍ ደራሲ ዶክተር ሄኖክ ዘውዱ አካባቢያዊ አደጋዎችና የጤና ጉዳቶች በተመለከተ በዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ በስፋት የሚያጋጥሙና የህፃናት ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ በመሆናቸው በተለይ በዚህ በክረምት ወቅት ልጆች ቤት ስለሚውሉ ጥንቃቄ ይወሰድ ይላሉ። በአደጋዎቹ ላይ ወላጆች በቂ እውቀትን ካካበቱ ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ የህፃናት ጤናን ማጎልበት የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው።
ብዙ ጊዜ የሚከሰቱ የህፃናትን ጤና ከሚያስተጓጉሉ አደጋዎች መካከል – ቃጠሎ (በፈላ ውሀ፣ በእሳት፣ በኤሌክትሪክ) – ውሃ ውስጥ የመስመጥ አደጋ – የመኪና አደጋ – መታፈን (በጢስ) – መውደቅ (ከፍ ካሉ ቦታዎች፣ከፎቅ) – መርዝና መድኃኒትን ሳያውቁ መውሰድ – ትንታ ተጠቃሽ ናቸው። ምንም እንኳን በአገራችን የጥናት ዳሰሳ ባይኖርም እንደ አሜሪካ ባሉ የበለፀጉ ሀገራት እስከ 40 በመቶ ያህል ከአምስት ዓመት በታች የህፃናት ሞት የሚከሰተው በአደጋዎች ምክንያት ነው። በተለይም በዚህ ዘመን ተላላፊ ሕመሞች በክትባትና በህክምና ጉዳታቸው እየቀነሰ ሲመጣ አደጋዎች የሚያስከትሉት ተፅዕኖ እየጎላ መጥቷል።
በየሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍሎች ውስጥ መርዝ የጠጡ ህፃናት፣ ከኮንዶሚኒየም ፎቅ ወድቀው የተጎዱ ህፃናት፣ ወንዝ ለዋና ገብተው የሚሰምጡ፣ እንዲሁም የፈላ ውሀ ተደፍቶባቸው ሰውነታቸው የተቃጠለ ህፃናትን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ማየት የተለመደ ነው። በመሆኑም ወላጆች እነዚህን ነገሮች ከግምት በማስገባት ቅድመ መከላከል ላይ ማተኮር አለባቸው። እንዲሁም መጠነኛ የሆነ የድንገተኛ ህክምና እርዳታ እውቀት ማዳበር ያስፈልጋቸዋል። በዋነኛነት ወላጆች ህጻናትን ከአደጋ መከላከልና ጉዳትን ከማስቀረት አንፃር የሚከተሉትን ተግባራት መከታተል አለባቸው፡-
- መድኃኒቶችንና መርዞችን ህፃናት ከማይደርሱበት ስፍራ
- ማስቀመጥ፣ እንዲሁም የተለዩና አጥብቀው የሚዘጉ መገጣጠሚያዎችን በመክደኛቸው ላይ ማድረግ፤
- • ህፃናትን የመንገድ ሥርዓትንና የትራፊክ ሕጎችን ማስተማር የእግረኛ መንገድ አጠቃቀምንና የግራ መስመርን ይዞ መሄድን ማሳወቅ
- • ህፃናትን ሙሉ ስማቸውንና የመኖሪያ ቤት አድራሻ ከነስልክ ቁጥራቸው ማስጠናት
- • በቤት ውስጥ ህጻናት በሚደርሱበት ቦታ የጦር መሳሪያ አለማስቀመጥ፣
- • በእድሜ ከፍ እያሉ ሲመጡና ተገቢ ሲሆን የዋና ልምምድና ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ፣
- • የኮንዶሚኒየም ወይም የመኖሪያ ህንፃዎች ደረጃዎችንና መወጣጫዎች ደህንነት ማስጠበቅ፣ ህፃናት ብቻቸውን እንዳይወጡ ማድረግ፣
- • የፈላ ውሀ ወይም የተጣደ ወጥ እያለ ህፃኑን ትቶ አለመሄድ ወይም ለሌላ ህፃን እንዲጠብቀው አለመፍቀድ፣
- • በቤት ውስጥ ያሉ ሶኬቶች ደህንነት ማረጋገጥ፣ የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን በቀላሉ ህፃናት እንዳያገኟቸው ማድረግ፣
- • በምግብ ሰዓት እያኘኩ ማውራት፣ መሳቅና መሮጥን መከልከል እንዲሁም ትክክለኛ የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተማር፣
- • በቤት ውስጥ ያሉ ባሊዎችና በርሜሎችን በውሀ ከተሞሉ መዝጋት፣ ህፃናት እንዳይጠጓቸው ማድረግ፣ በሚያስፈልግ ጊዜ ብቻ በውሀ መሙላት፣
- • ስፖርታዊና አካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ደረጃ በደረጃ በክትትል እንዲያደርጉ ከማድረግ በተጨማሪም ወላጆች መጠነኛ የሆነ የድንገተኛ ህክምና እውቀትና ክህሎት
- እንዲኖራቸው ማስቻል የአደጋዎችንና ጉዳቶችን ተፅእኖ ለመቀነስ ያስችላል ይሉናል።
- ወላጅነት እረኝነት ነውና ልጆቻችን በተገቢው መንገድ እንዲያድጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ከሚከተሉት አደጋዎች እናስጥላቸው።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2/2013