በያዝነው የክረምት ወቅት ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ይሰማል:: አንዳንዶች የሐምሌ ክረምት ከባድ መሆኑንና የአየሩ ቅዝቃዜም እንዲሁ ማየሉን ሲገልጹ፣ የአረንጓዴ ዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ከተጠናከረ ወዲህ የተከሰተ የአየር ጸባይ ለውጥ ነው የሚል አስተያየት የሚሰነዝሩም አልጠፉም:: እንዲህ ያለውን አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች ከአዲስ አበባ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ሲሆን፣ ያለፉ የክረምት ወቅቶችንና በአሁኑ ክረምት መግቢያ ላይም የዝናቡ መጠን አነስተኛ ከመሆን ጋር በማያያዝ የሰጡት አስተያየት ነው:: ክረምቱ ከዚህም በላይ መክበድ አለበት የሚሉ ወገኖች ደግሞ ዝናቡ ጊዜ እየሰጠና መጠኑም ቢሆን ከፍተኛ እንዳልሆነ ይናገራሉ:: በሁለቱም አስተያየቶች መካከል ሰሞኑን የሚስተዋለው ጉም የለበሰ የአየር ጸባይ በተለየ ሁኔታ አነጋጋሪ ሆኗል::
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚትዎሮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ኃይለማርያም አስተያየቶቹን እርሳቸውም መስማታቸውንና የድሮ ክረምት መጣ ያሉ ሰዎች እንዳጋጠሟቸው አስታውሰዋል:: እንዲህ ያሉ የማወዳደር አስተያየቶችን ለመቀበል በመረጃ ማረጋገጥ እንደሚጠይቅ በመጠቆም እንደተቋማቸው ክረምቱ በተለየ ሁኔታ እንደማይታይና የክረምቱ አንድ አካል እንደሆነ ይገልጻሉ::
አቶ ክንፈ ክረምቱን መሠረት አድርገው አጠቃላይ ነባራዊውን ሁኔታውን እንዲህ አስረድተዋል:: ከ12 ወራቶች የክረምት ወቅቶች አራት ወራቶች ሲሆኑ፣ ክረምቱ ከግንቦት ወር ነው የሚጀምረው:: የ2013ዓ.ም ክረምት ከመግባቱ በፊት በተለይ በመካከለኛውና በምዕራብ የኢትዮጵያ አጋማሽ፣ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ጥሩ የክረምት ወቅት እንደሚሆን እንዲሁም በምሥራቁ አጋማሽ በአብዛኛው ክፍል ወደ መደበኛው የተጠጋ ዝናብ እንደሚኖር በአጠቃላይ ኢትዮጵያን በምዕራብና በምሥራቅ በመክፈል በተደረገ ቅድመ ትንበያ የክረምቱ አገባብና አወጣጥ ጥሩ መሆኑ ነው የተረጋገጠው:: ከአራቱ የክረምት ወራቶች ሰኔ ወር የክረምት መግቢያ በመሆኑ ይቆራረጣል:: አየሩ የሚሞቀው ከመሬት በመሆኑ ጸሐይ ወደ መሬት ስለሚገባ ዝናብ ቢዘንብም መሬቱ ይደርቃል:: መስከረም ወርም የክረምት መውጫ በመሆኑ ከሰኔ ወር ጋር በተመሳሳይ ዝናቡ ይቆራረጣል:: ሐምሌና ነሐሴ ወራቶች ግን ከፍተኛ ዝናብ የሚገኝባቸው ዋና ወቅቶች ናቸው:: በተለይም የሐምሌ ወር ተከታታይ የሆነ ዝናብ የሚገኝበት ሲሆን፣ በተለይም በመካከለኛውና በምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች በአብዛኞቹ ቦታዎች በየዕለቱ በሚባል ደረጃ ዝናብ ይኖራል:: በመሆኑም በዚህ ወር ቀጣይነት ያለው የደመና ሽፋን ሲኖር አየሩ ይቀዘቅዛል:: ምክንያቱም ቀን ላይ ደመናን አልፎ የሚመጣ ሙቀት መሬት ስለማይደርስ ቀጣይነት ያለው ደመናማና ዝናባማ የአየርጸባይ ይኖራል::
አቶ ክንፈ እይታን ስለሚጋርደው ጉም ክስተትም እንዳስረዱት ጉም በክረምት ወቅት የተለመደ ነው:: በተራራማ አካባቢዎች ከፍታውና መሬቱ ስለሚገናኝ በስፋት ይስተዋላል::በተከታታይ ደመና ሲኖር ጉም ያጋጥማል:: እንዲህ ያለው የአየርጸባይ ክስተት በሐምሌ ወር ብቻ ሳይሆን፣ ጥሩ ዝናብ በሚኖርበት ጊዜም በተመሳሳይ ሁኔታ ክስተቱ ይኖራል:: በአዲስ አበባ ከተማ በእንጦጦ አካባቢ የተለመደና በተደጋጋሚ ያጋጥማል:: በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍልም እንዲሁ ደመናው ተራራማውን ስለሚነካ በተመሳሳይ ይከሰታል:: ከኢትዮጵያ ውጪም ባሉ ሀገሮች እንዲሁ የሚያጋጥም በመሆኑ ይህ የተለመደ የአየርጸባይ ክስተት የተለየ ተደርጎ መወሰድ የለበትም:: እይታን የሚጋርድ ጉም በክረምት ወቅት የሚጠበቅ ነው። ይሄ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የአየርና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎቶች ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል:: በተለይም አውሮፕላን ከመሬት ሲነሳ መንደርደሪያው በግልጽ መታየት ስላለበት እይታን የሚጋርድ ነገር መኖር የለበትም:: በመሆኑም የኢትዮጵያ አየርመንገድ በሐምሌ ወር ላይ በተወሰኑ ቀናት እይታን የሚከለክል ደመና ወይንም በጉም መሸፈን ያጋጥመዋል:: ተሽከርካሪዎችም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ማሽከርከር ይኖርባቸዋል:: በነሐሴ ወር ፀሐይ ደመናውን ሰብሮ የመግባት ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ እይታን የሚከለክለው ደመና ወይንም ጉም እየቀነሰ የመሄድ ባህሪ አለው:: ያም ሆኖ ግን ኤጀንሲው በየጊዜው ያለውን የአየርፀባይ ሁኔታ በመከታተል የኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ ተሽከርካሪዎች ከአደጋ የጸዳ በረራ እንዲያካሂዱ መንገደኞችም በተለይም እግረኞች በጥንቃቄ መንገድ እንዲያቋርጡ ወቅታዊ የሆነ መረጃ በመስጠት ኃላፊነቱን ይወጣል::
በጉም የሚጋርድ የአየር ፀባይ ከጊዜ ወደጊዜ የሚለያይበት ሁኔታ ይኖር ይሆን ተብሎ ለተነሳው ጥያቄም አቶ ክንፈ ሲመልሱ ፤‹‹የክረምት ወቅት ከዓመት ዓመት የተለያየ ባህሪ ወይንም ፀባይ ያለው ሲሆን፣ ይሄን መሰረት በማድረግ ነው ትንበያ የሚሰጠው:: በቅርብም በሩቅም ያሉ ውቅያኖሶችን መሰረት በማድረግ ነው ትንበያ የሚካሄደው:: በዚሁ መሠረትም ያለፈው የክረምት ወቅት ከፍተኛ የዝናብ መጠን የተመዘገበበትና ጎርፍም ተከስቶ ሰዎችን ከአካባቢያቸው እስከማፈናቀል የደረሰ የተለያየ ጉዳት ያስከተለበት ጊዜ ነበር:: የአሁኑ ክረምት ከአምናው ጋር በንጽጽር ሲታይ የዝናብ መጠኑ አነስተኛ በመሆኑ ክረምቱ አነስ ያለ ነው:: በሚቀጥለውም ክረምት በዓለም ላይ ያለው ውቅያኖስ ከሙቀት ጋር የሚያያዝ ይሆናል›› ነው ያሉት::
በአጠቃላይ የአየር ፀባይ ለውጥ የወቅቶችን ባህሪ እየቀየረ መሆኑን ሳይንስ የተስማማበት ሂደት መኖሩን የጠቆሙት አቶ ክንፈ እንዳስረዱት፤ በዚህ ጊዜ በጣም ጥግ የያዘ የአየር ሁኔታ በጣም እየተጠናከረና ድብብቆሽ እየበዛ የመጣ ነው ። ጥግ የያዘ ነው ሲባል ዝናቡ ጠንካራ ፣ጎርፍ በማስከተል፣ ቅዝቃዜ በመጨመር፣ አነስተኛ ሲሆንም ጎርፍ በማስከተል ይገለፃል::ከዚህ አንፃር በዓለም ደረጃ በአውሮፓ፣ ቻይና፣ ህንድ ከፍተኛ ጎርፍ፣ በአሜሪካና በሩሲያ ደግሞ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ተከስቷል:: እንዲህ ያለውን ዋልታ ረገጥ የአየር ሁኔታ አንዳንዶች የአየርፀባይ ለውጥ ውጤት ነው የሚል አስተያየት ይሰጣሉ:: ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው በሌሎች ሀገሮች እንዳጋጠመው አይነት የወጣ የሚባል ክስተት አላጋጠመም:: የዝናቡ መጠን ከተወሰነ በላይ ከመደበኛ የወጣ ቢሆንም ግን እንደችግር የሚጠቀስ አይደለም::
ወቅቱ የግብርና ሥራ የሚካሄድበት በመሆኑ በእንቅስቃሴው ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ ይኖር እንደሆነም አቶ ክንፈ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ደመናው በቂ እርጥበት ሲኖር ወደ ዝናብ የሚቀየር በመሆኑ ይሄን ያህል እንደስጋት ተወስዶ መነገር ያለበት ጉዳይ አይደለም:: በትራንስፖርት እንቅስቃሴው ላይም ተጽዕኖ የሚኖረው እይታን ስለሚጋርድ በመሆኑ አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግ ነው:: ጊዜው አጭር ስለሚሆን የበዛ ጫናም አይደለም:: የግብርና ሥራ በቅዝቃዜና ዝናብም እየዘነበ የሚከናወን በመሆኑ እንደምክንያት ሥራ መስተጓጎል የለበትም:: አርሶአደሩም ይህንን የሚያወቅ በመሆኑ እንደችግር አያነሳውም::
በሀገሪቱ ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ ስላለው የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ለአየርፀባይ መለዋወጥ ስለሚኖረው አስተዋጽኦም አቶ ክንፈ እንዳስረዱት በርብርብ እየተከናወነ ያለውን መርሃግብር በማድነቅ ተጠናክሮ ከቀጠለና የተተከሉት የዛፍ ችግኞችም ጸድቀው ደን ደረጃ ላይ ሲደርስ እርጥበት ይዞ ለማቆየት የሚያግዝ በመሆኑ መጠኑ የጨመረ ዝናብ ለማግኘት፣ የተስተካከለ የአየርፀባይ በተለይም መደበኛ ክረምትና የበጋ ወቅቶች እንዲኖሩ ያስችላል::
እስካሁን የተተከሉት የዛፍ ችግኞች ግን ገና አልደረሱም:: የዛፍ ችግኞቹ በራሳቸው ውሃ የሚፈልጉ በመሆናቸው ውጤቱ ወደፊት ነው የሚጠበቀው::›› አቶ ክንፈ የክረምቱን ወቅት በአግባቡ በመጠቀም የግብርና ሥራንና የአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ማጠናከር፣ ለሚቀጥለው ሀብት ሆኖ የሚያገለግል ውሃን በመያዝ ክረምቱን እንደ ጥሩ ዕድል እንዲወሰድ መልዕክት አስተላልፈዋል::
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ያላት ድርሻ ዝቅተኛ ሆኖ ነገር ግን የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ሀገሮች መካከል አንዷ ነች፣ መገለጫውም በሀገሪቱ በተደጋጋሚ ድርቅና ጎርፍ መከሰት እንደሆነ በመግለጽ ከወቅቱ ዝናብ ጋር በማያያዝ አጠቃላይ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ማብራሪያ የሰጡን ደግሞ በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጀነራል ተወካይና የአካባቢ ስምምነቶች ድርድር ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንሱር ደሴ ናቸው::
እንደ አቶ መንሱር ገለፃ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ከማሳያዎቹ አንዱ የውቅያኖስ መዛባት ሲሆን፣ ያልተለመዱና ከመጠን በላይ የሆኑ ክስተቶች ይፈጠራሉ:: ድርቅ የነበረ አካባቢ ዝናብ የማግኘት፣ ዝናብ በሚዘንብበት አካባቢ ደግሞ እጥረት መከሰት እንዲሁም ሞቃታማ የሆነ አካባቢ መቀዝቀዝ ከመገለጫዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው:: በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል ቅድመ ትንበያዎች ያሳያሉ:: ኢትዮጵያም በተለያዩ የዓለምአቀፍ መድረኮች በምታገኘው የተሳትፎ ዕድል ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት የሚያስፈልግ ምላሽ ድጋፍ ማግኘት እንዳለባት ውይይትና ድርድር በማድረግ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች::
ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት በተፈጥሮ ከሚመጣው በበለጠ የሰው ልጅ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የበለጡ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ መንሱር፤ ታዳሽ ያልሆኑ እንደ ድንጋይ ከሰልና ሌሎችም ፋብሪካዎችን ለማንቀሳቀስ የሚውል የኃይል መጠቀም ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ መሆኑን ይናገራሉ:: እርሳቸው እንዳሉት ለዚህ በመንስኤነት የሚነሱት ያደጉ ሀገራት ናቸው:: በእነዚህና በተለያየ ምክንያት በሚከሰተው የአየርፀባይ ለውጥ ክረምቱን ተከትሎ የሚያጋጥመው ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን መኖርና ዝናቡ ደግሞ ጎርፍ በማስከተል የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይገለጻል::
ለአየር ንብረት ለውጥ መንስኤ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት ያደጉ ሀገሮች በታዳጊ ሀገሮች ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ግምት ውስጥ ያስገባ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ፣ የአቅም ግንባታና ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርጉ እንዲሁም መፍትሄ በሚያስገኙ ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ በኩል ሥራ እየተሰራ ነው:: በአጠቃላይ የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት በአንድ ጀንበር የመጣ ሳይሆን፤ ለረጅም ጊዜ የተጠራቀመ ክስተት ነው::
በኮሚሽኑ በኩል እየተከናወነ ስላለው ተግባርም አቶ መንሱር እንዳስረዱት፤ ከኮሚሽኑ ተልዕኮዎች አንዱ ለአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ምላሽ እንዲሰጥ ማስተባበር ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በእኤአበ2003 ላይ የተቀረጸውን ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስራተጂ በማስተባበርና በማስተግበር እየሰራ ይገኛል:: ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ እስትራተጂ ተግባሪ ከሆኑትና በሚኒስቴር ደረጃ ካሉት ግብርና፣ ንግድና ኢንዱስትሪ፣ ትራንስፖርት፣ ከተማ ልማት ፣ ኮንስትራክሽን ጨምሮ በድምሩ 12 የሚሆኑ አስፈጻሚ ተቋማት ይጠቀሳሉ:: ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆንም ሀብት በማፈላለግም ኮሚሽኑ የሚጫወተውን ሚናም ይገለጻል:: በቅርቡ ከተነደፈው የ10 ዓመት ሀገራዊ መሪ የልማት ዕቅድ ምሶሶዎች አንዱ አረንጓዴ ልማትን ማሳካት ሲሆን፣ እያንዳንዱ አስፈጻሚ ተቋምም ይህንኑ በዕቅዱ ውስጥ አካቶ መንቀሳቀስ ስላለበት በዚሁ መሠረት እየተሰራ ይገኛል:: እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ቀደም ሲልም ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል::
እንደ አቶ መንሱር ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት መዛባት ተጽዕኖ ተጋላጭ እንደመሆኗ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የሁሉም በመሆኑ ተያይዞና ተደጋግፎ መሥራትን ይጠይቃል::ኮሚሽኑም መረጃዎችን በመለዋወጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ትብብር ያስፈልጋል:: የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ላይም በዕቅድ በመተግበር ላይ ይገኛል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2013