ልጆች እንዴት ናችሁ በክረምት የዕረፍት ጊዜ እናንተ እንድታነቡ የሚያበረታታ አንድ የመፅሐፍ ኢግዚቢሽን ተዘጋጅቷል፤ ከሀምሌ 15 እስከ ነሐሴ 10 በሚቆየው በዚህ የመጽሐፍ እና ንባብ ድግስ አራት ኪሎ፣ ከቱሪስት ሆቴል ዝቅ ብሎ ኢክላስ ሕንፃ፣ ከአዲሱ መጽሐፍት ቤት አጠገብ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከአስራ አምስት በላይ መፃሕፍት ሻጮች የተሳተፉበት በዋሊያ መፃሕፍት መደብር የተዘጋጀ ነው።
ታዲያ እናንተ እመማና አባባን አስፈቅዳችሁ ክረምቱን በነባብ የምታሳልፉበትን መፅሐፍቶች አስገዙ እሺ።
በዚህ ኤግዚቢሺን የሚገዟቸውን መጽሐፍቶች እየመረጡ ያገኘኋቸው አባትና ልጆችም ክረምቱን በማንበብ ጠቅላላ እውቀታቸውን በማሳደግ ሊያሳሊፉ ያሰቡ መሆኑን ነግረውናል።
ሕፃን ሮቤለ ተከሰተ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ሮቤል አማርኛ መፃሕፍትን ማንበብ ይወዳል። የተለያዩ መፃሕፍቶችን በማንበብ ፈጣን አንባቢ ለመሆን የቻለ ሲሆን፤ በሱ ዕድሜ ክልል ያሉ ልጆችም መፃሕፍትን እንዲያነቡ ይመክራል።
የሮቤል ታላቅ እህት የሆነችው ተማሪ አና ተከስተ መፅሐፍ ማንበብ በጣም እንደምትወድ ነግራኛለች። መፅሐፍት ኤግዚቢሽኑ ላይ የመጣችውም ቤት ያለውን ለዕድሜዋ የሚመጥን መፅሐፍ አንብባ ስለጨረሰች እንደሆነ ትናገራለች።
ሌሎች አዳዲስ ከዚህ በፊት ያላነበበቻቸውን በርካታ መፃሕፍትን በኢግዚቢሽኑ መመለከቷ እንዳስደሰታት የምትናገረው አና ዛሬ የመረጠቻቸውን አስገዝታ ለማንበብ እንደጓጓች ትናገራለች።
የአስር ዓመት ዕድሜ ያላት አና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን መፅሐፍትን በፍጥነት ማንበብ ትወዳለች። እስከአሁንም ደረስ ብዙ የተለያዩ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ታሪኮች ማንበቧን ነግራናለች።
ልጆች ከመፅሐፍት ማግኘት ያለባቸውን ነገር መውሰድ አለባቸው፤ ይህም ሲባል ብልህ እንዲሆኑ ውሸት እንዳይናገሩ ታላላቆቻቸውን የሚያከብሩ እንዲሆኑ መክራለች። መታዘዝ፣ ታማኝነት፣ ሰዓት አክባሪነት፣ ጓደኝነት፣ ልግስና ፣መታዘዝ፣ ፍቅር፣ ንፅሕና ፣ጥረት……… የመሳሰሉትን ባህሪያት ለማዳበር ጎበዝ አንባቢዎች መሆን እንደሚገባችሁ አና መክራችኋለች።
የነ አናና ሮቤል አባት አቶ ተከሰተ ተሾመ በምህንድስና ሞያ የተሰማሩ ስው ናቸው። ልጆቻቸውም አስፈላጊ እውቀቶችን ከመፅሐፍት ማግኘት የሚገባቸው መሆኑን ይናገራሉ። ለልጆች ተብለው የተዘጋጁ እያንዳንዱ ታሪክ አጠር ያለ እና ለማስታወስ ቀላል ነው:: ተረቶቹ በልጆቻችን ላይ ተገቢ ያልሆኑ ባህሪያት በመለየት ለማስተማር አስፈላጊ የሆነውን መልካም ባህሪ ለመቅረጽ እና ለማሻሻል ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣት ያስችላል የሚሉት እኚህ አባት ለልጆቻቸው ሀገር በቀል ባህሎችን ታሪኮችን የሚያውቁበት መፅሐፍት መግዛት ያስደስተኛል ይላሉ። ልጆች ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ ሞባይል ስልኮችና ፊልሞች ላይ የመጠመድ ባህሪን ያሳያሉ፤ ይህ ግን ወላጆች ሊያስተካክሉት የሚገባ ባህሪ መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ባለው ጊዜ ምንም ዓይነት የቴከኖሎጂ ቁሳቁሶች አልነበሩም ያኔ ግን ማህበራዊ ትስስሩ መፅሐፍት እየተዋዋሱ ማንበቡና ሌሎች ጥሩ ጥሩ ልጆች ታንፀው ራሳቸውን ሆነው የሚያድጉበት ጊዜ ነበር። አሁን ግን የሚታየው ነገር ሁሉ በሞላበት ሰው ማንነቱን እያጣ ነው። እዚህ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ይላሉ።
ወላጆችና ልጆች የክረምት ጊዜያቸውን በጋራ በማንበብ ማሳለፍ እንደሚገባቸው መክሬ ልሰናበታችሁ ነው። መልካም የዕረፍት ጊዜና ከምታውቁት ተጨማሪ እውቀት እንዲኖራችሁ የሚሆንበት መልካም የክረምት የዕረፍት ገዜ ይሁንላችሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013