
ዓለማችንን ካፒታሊስቶች ይዘውሯታል፡፡ በመሆኑም ለሁሉ ነገር መለኪያ ፍላጎት እና አቅርቦት አለው። ለሁሉም ነገር መስፈሪያ ወይም ዋጋ ያወጣል ወይ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላ። ዋጋ ካላስገኘ ምንም ነገር አይደረግም።ዋጋ ካስገኘ ደግሞ ሁሉም ነገር ይደረጋል፡፡ጦርነትም ቢሆን፡፡
በዚህም መሰረት ዋነኞቹ ካፒታሊስቶች ምንም አይነት ጦርነት የሚያስነሳ ችግር ቢገጥማቸው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራውን በማሰብ አይዳፈሩም ፤ በድርድር ያልፉታል። በተቃራኒው ሌላው ሀገር ላይ መሳሪያ የሚሸጥበት የጦርነት እድል ካገኙ ቆስቁሰው ለማስነሳት አይሰንፉም፡፡ ለእነሱ ዋናው ነገር ገበያ ማስገኘቱ ላይ ነው፡፡
ለዚያም ነበር ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ወደ ጦር መማዘዝ ሳይገባ በፊት በሽምግልና ብዙ ለመስራት የተሞከረው፡፡ ግን አልሆነም፡፡ጦርነቱ ተካሄደ ..በሸባሪው ህወሓት ቆስቋሽነት የተጀመረው ዘመቻ ያስከተለው ጦስ የመከላከያን ወጪ ሳይጨምር በ8 ወር ውስጥ የፌዴራሉን መንግሥት 100 ቢሊየን ብር አስወጥቶታል፡፡
የዋጋን ጉዳይ ሳስብ ይህ 100 ቢሊየን ብር ብልጭ አለለኝ፡፡ ለሰብዓዊ ተግባር፣ የወደመ መሠረተ ልማትን መልሶ ለመተካትና ህዝብን እንደ ፊቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣ ሀብት በመሆኑ በእኛ እይታ ትልቅ ስራ የተሰራበት ነው፡፡ እንዳው ግን በዚህ ግዙፍ ሀብት ጦርነት ባይኖር ኖሮ ምን ምን ልናደርግበት እንችል ነበር ስል አሰብኩ፡፡
መቼም ዘንድሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ራስ ምታት ከሆኑበት ጉዳዮች አንዱ የዘይት ዋጋ በየጊዜው መጨመር ነው፡፡ዘይት ውድ እና ብርቅ ሆኗል፡፡ታዲያ ይህን ብርቅ የሆነ ነገር አሁን ወደተራ መደበኛ የምግብ ቁሳቁስነት የሚያወርዱ እና ዘይትን በቀላሉ እንድናገኝ ያስችላሉ የተባሉ ሁለት ፋብሪካዎች በዚህ ዓመት ተመርቀዋል፡፡
አንደኛው የአቶ በላይነህ ክንዴ ነው፡፡ወደ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገደማ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ሌላኛው የአቶ ወርቁ አይተነው ነው፡፡እሱ ደግሞ ወደ 5 ቢሊየን ብር ገደማ ወጥቶበታል፡፡እያንዳንዳቸው 3 ሺ ሰው ገደማ መቅጠር የሚችሉ እና ብዙ የውጭ ምንዛሬን የሚያስቀሩ ናቸው፡፡ እንግዲህ ይሄን 5 ቢሊየን ለጦርነቱ ባወጣነው 100 ቢሊየን ብናሰላው 10 የአቶ በላይህን 10 የአቶ ወርቁን የሚያህሉ የዘይት ፋብሪካዎችን ማቋቋም እንችል ነበር ማለት ነው፡፡ወይም በዚህ ህወሓት በቀሰቀሰው ጦርነት 20 ግዙፍ የዘይት ፋብሪካዎች ወድመዋል ማለት ይቀላል።
ከዘይት ሳንወጣ መቼም ዘይት ያለ ዱቄት አይሆንምና 100 ቢሊየን ብር ምን ያህል የዱቄት ፋብሪካ ያቋቁማል ብንል ለዚህ ጥሩ የቅርብ ምሳሌ የሚሆነን ሚያዝያ ላይ ደቡብ ወሎ ላይ የተቋቋመው እናት የዱቄት ፋብሪካ ነው፡፡ ይህ ፋብሪካ በ85 ሚሊየን ብር የተቋቋመ ሲሆን ለ150 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሮ በቀን 500 ኩንታል ዱቄት ያመርታል፡፡ በሙሉ አቅሙ ቢሆን ደግሞ የዚህን እጥፍ ሰው ቀጥሮ እጥፉን ያመርታል ተብሏል፡፡ እንግዲህ ይህን ቁጥር ይዘን 100 ቢሊየን ምን ያህል የዱቄት ፋብሪካ ሊሰራ ይችላል ብለን ብንጠይቅ 1ሺ 174 የጠቀስኳቸውን አይነት ፋብሪካዎችን ማቋቋም ይችላል ማለት ነው፡፡
100 ቢሊየን ብሩን አሁን ውድ ከሆኑ ነገሮች መሀከል አንዱ በሆነው ስኳር ፋብሪካ ብንተምነውስ ምን ያህል የስኳር ፋብሪካዎችን መስራት ይቻል ነበር? ለዚህ ቀላሉ መንገድ አሁን ያሉ የስኳር ፋብሪካዎችን ዋጋ መተመን ነው፡፡መንግሥት በቅርቡ ስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ባለሀብቶች ለማስተላለፍ የዋጋ ተመን ያወጣ ሲሆን በዚህም መሰረት በሀገሪቱ ያሉ 13 የስኳር ፋብሪካዎች አጠቃላይ ሀብት እና ንብረት 88 ቢሊየን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ስለዚህ ይህ ጦርነት የነዚህን 13 ፋብሪካዎች ጠቅላላ ሀብት እና ንብረት በልቷል ማለትም እንችላለን፡፡
አሁን በሀገር ደረጃ ውድ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ሲሚንቶ ነው፡፡በሀገሪቱ ያሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚቀርቡት ምርት እና የሚፈለገው የሰሚንቶ መጠን አልተመጣጠነም፡፡ይህን ሲሚንቶ እጥረት ይቀርፋሉ ከተባሉ ፋብሪካዎች መካከል ደግሞ አንዱ በቅርቡ ሰሜን ሸዋ እንሳሮ ላይ የመሰረት ድንጋዩ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የተጣለለት ፋብሪካ ነው፡፡
ይህ ፋብሪካ በ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚገነባ ሲሆን መስታወት እና ጂፕሰምም ያመርታል ተብሏል።ለ10ሺ ሰው ገደማም የስራ እድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል። አሁን ባለው ምንዛሬ ፋብሪካውን ለመገንባት የሚያስፈልገው 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በገንዘብ ሲመነዘር ወደ 96 ቢሊየን ብር ገደማ ነው።ይህም ማለት አሁን ለዚህ ጦርነት ወጪ የተደረገው ብር ይህን 10ሺ ሰው የሚቀጥር እና የሲሚንቶ እጥረት የሚቀርፍ አንድ ግዙፍ ፋብሪካን ሊገነባልን ይችል ነበር ማለት ነው፡፡
የሲሚንቶ ፋብሪካም ይሁን የዘይት ወይም የዱቄት ፋብሪካ ለማንቀሳቅስ የኤሌክትሪክ ሀይል ማምረት ግድ ነው፡፡ለዚህም ሲባል በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ እየተረባረብን ነው፡፡ነገር ግን አሁን 100 ቢሊየን ብር ያስወጣን ጦርነት ባይቀሰቀስ ምን መስራት እንችል ነበር ቢባል በቀላሉ የህዳሴ ግድብን ለመጨረስ ተጨማሪ ወጪ አንጠይቅም ነበር የሚል መልስ እናገኛለን፡፡
ስለ መብራት ካነሳን አይቀር ሌላኛው ወሳኝ መሠረተ ልማት መንገድ ነው፡፡ከመንገድ አንጻር ይህ ጦርነት ምን አሳጥቶናል ብንል ኪሳራው በዝቶ ይታየናል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት በዚህ ዓመት ለመንገድ ግንባታ 43 ቢሊየን ብር የመደበ ሲሆን ይህን ከ100 ቢሊየኑ አንጻር ብናየው ህወሓት የቆሰቆሰው ጦርነት የፌዴራሉ መንግሥት ለሁለት ዓመታት ለመንገድ የበጀተውን በጀት ወስዷል ማለት ነው።ከትምህርት ቤት አንጻርስ ብናየው በሱም አንጻር ብናየው ቁጥሩ አስደንጋጭ ነው፡፡100 ቢሊየን ብር ምን ያህል ትምህርት ቤቶችን አሳጣን ለማለት የተጠቀምነው ዘንድሮ ትምህርት ቤት በመገንባት የበረቱት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን የፌስቡክ ገጽ ማየት በቂ ነው። ቀዳማዊት እመቤቲቷ እስካሁን ለአንድ ትምህርት ቤት ከ15 ሚሊየን ባልበለጠ ወጪ በርካታ ትምህርት ቤቶችን የገነቡ ሲሆን ከነዚህ መካከል የቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ሀዊ ጉዲና ወረዳ ያስመረቁት ኢፈ በሊቃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት በሁለት ፈረቃ 1800 ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን ለግንባታውም 13 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ወጥቶበታል፡፡ይህን በ100 ቢሊየን እናስላው፡፡ውጤቱም ይህ ጦርነት 7ሺ 246 የኢፈ በሊቃን አይነት ትምህርት ቤቶችን የምንገነባበትን ገንዘብ በልቷል ማለት ነው፡፡
ከጤና ተቋማት አንጻርም ብናየው ውጤቱ አሳዛኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በቅርቡ ሰኔ ወር ላይ በአማራ ክልል ሰከላ ወረዳ የተመረቀው እና 10ሺ ህዝብን የሚጠቅመው ጤና ጣቢያ 10 ሚሊየን ብር ብቻ የፈጀበት ሲሆን፣ ይህም ማለት ህወሓት የቆሰቆሰው ጦርነት 10ሺ መሰል ጤና ጣቢያዎችን አፍርሷል ማለት ነው፡፡
እንዲህ እያልን ብንቀጥል ዘንድሮ ህግ ለማስከበሩን ተከትሎ ለሰብዓዊ ድጋፍ፣ በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ለመሳሰሉት ብቻ የፌዴራሉ መንግሥት ያወጣው ገንዘብ መንግሥት ዘንድሮ ከሰበሰው 279 ቢሊየን ብር ገቢ ሲሶውን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ወይም በሌላ መልኩ ኢትዮ ቴሌኮም ዘንድሮ ካገኘው 55 ቢሊየን ብር ገቢ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካተረፈው 23 ቢሊየን ብር ተደምሮ ይበልጣል ማለት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ደግሞ የሚሆንብን ከጦርነቱ በፊትም ሆነ አሁን ሰላምን በሚጸየፉት እና ውጊያ ባህላችን ነው በሚሉት በእነ ጌታቸው አሰፋ እና ደብረጽዮን ጥጋብ ነው፡፡
መንግሥት ይህን ያህል ሀብት ለትግራይ ህዝብ ማዋሉ ትክክል ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን እርግፍ አርጎ ትቶ ነው ለትግራይ ህዝብ መድረስ ላይ የሰራው፡፡ ይህን ቁርጠኝነቱንና ድካሙን አሸባሪው ህወሓትና ደጋፊዎች አንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት በዜሮ ቢያባዙትም ኃላፊነት እንደሚሰማው መንግሥት ለትላልቅ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሊውል የሚችል ሀብት መድቦ የትግራይን ህዝብ ታድጓል፡፡
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013