አይበለውና የውጪ ወራሪ ሀይል በትግራይ በኩል ቢከሰት የመጀመሪያው ግንባር ቀደም ተሰላፊ የመሀሉና የዳሩ ኢትዮጵያዊ መከላከያ ሠራዊት ወታደራችን ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትላንትና ከመካከልህ ሆኖ አብሮህ ቤት ሲሰራ፣ አብሮህ አዝመራ ሲሰበስብ፣ ትምህርት ቤቶችን ሲጠግን፣ ለኔ ልኑር ሣይል ለሕዝቡ ሲኖር የትግራይ ሕዝብ አንተም ታውቀዋለህ፡፡
የትግራይ እናቶች የልጅ ሞት ምን ማለት እንደሆን ከእናንተ በላይ የሚያውቅ የለም፡፡ ከአንድ ቤት ከአምስት እስከ አሥር ልጆቻችሁን ለጦርነት እሣት ስትገብሩ ያሣለፋችኋቸውን አስከፊ ዓመታት ከእናንተ ሕሊና ውጪ ማንም ሊገነዘበውና ሊያስታውሰው አይችልም፡፡
ወታደር ማለት ምን ማለት ነው? ከእያንዳንዷ ደሀ ቤተሠብ የተውጣጡ የደሀ ልጆች ማለት ነው፡፡ ዛሬ በማህበራዊና በተለያዩ የውጪና የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች የምናየው ልባችንን ሠብሮታል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንዴትም ባለ ሞራል እንዴትም ባለ ሁኔታ ውስጥ የራሣችንን ልጆች በጭካኔ ገድለን ጀግና ተብለን አናውቅም።ከዚያም ይልቅ ሕዝቡ ከሀገራችን ወታሮች ጎን ተሰልፎ ውሀ የሚያጠጣ፣ ቁስሉን የሚያክም እና ሥንቅ የሚያቀብል ሕዝብ መሆኑን እናንተም ስላደረጋችሁት ታውቁታላችሁ፡፡
የትግራይ ሕዝብ በደግነቱና በሀገር ወዳድነቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ከሌላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጋርም በየትኛውም ክልል እየነገደና እየሰራ በሠላም በሀገሩ ሲኖር ቆይቷል፡፡ ይኼ ዛሬ በክልላችሁ ገብቶ አንገቱን የደፋው ወታደር ምንአልባትም ከእናንተው የተወለደ የምስኪኗ ትግሬ እናት ልጅም ነው፡፡ ዛሬ ከእኛ ከወገኖቻችሁ ይልቅ የውጪዎቹ ትላንትና በቀኝ ካልገዛናችሁ፣ ካላንበረከክናችሁ ብለው ዛሬ ደሞ ተቆርቋሪ መስለው ከጥቂት የትግራይ “ተቆርቋሪ ነኝ” ባይ ሀገር ከሀዲዎች ጋር አብረው ዳግም ወደማያባራ እልቂትና ጦርነት እንድንወድቅ እየሰሩ ነው፡፡
እነዚሁ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎቻችን የትግራይ ሕጻናትና አረጋውያን ከአቅማቸው በላይ መሣሪያ ተሸክመው የሚያሣዩ ፎቶግራፎችን በፊት ገጽ ሽፋናቸው ላይ በማተም “ጀግኖች ናችሁ” በሚል የሽርደዳ ጨዋታቸውን እየተጫወቱብን በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን መሣቂያና መሣለቂያ የማድረጉን ተግባር ተያይዘውታል፡፡ ደግሞም እነዚያ በፎቶ ግራፍ የተመለከትናቸው ሕጻናት ሮጠው ያልጠገቡ ደጋፊና ተንከባካቢ የሚሹ ሲሆኑ፤ ረሀብ በቀጣው አንጀታቸው አቅማቸውንና ስብዕናቸውን የማይመጥን የጦር መሠዘሪያ ያውም በወንድሞቻቸው ላይ ሊደግኑ ሲገደዱ ማየት ለማንኛዋም የትግራይ እናት ይቅርና ለሌላውም አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ መጦር የሚገባቸው አረጋውያን በገዛ ልጆቻቸው አስገዳጅነት ቀያቸውን ጥለው መሣሪያ ከአቅማቸው በላይ እንዲሸከሙና ወገናቸውን እንዲወጉ መደረጉ ታሪክ የማይዘነጋው ታሪካዊ ስህተት ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ለመቅበር ለተነሱ ቅኝ ገዥዎች ደግሞ ጮቤ መርገጫ ከበሮ መደለቂያ መሆኑ ሁላችንንም አሣዝኖናል፡፡
እነዚህን ታሪክ የማይዘነጋቸውን ስህተቶች የሚፈጥሩት ደግሞ ከትግራይ ማህፀን በቅለው ትግራይን በጦርነት አድቅቀው የትግራይን ልጆች ለጦርነት ማግደው ሥልጣን ሲረከቡም ለራሣቸውና ለቡድኖቻቸው እንጂ ለትግራይ ሕዝብ የሚጠቅም ነገር እንዳልሰሩ አይተናል፡፡ ትላንትም ሆነ ዛሬ ውሃ የተጠማው የትግራይ ሕዝብ የውሀ ጠብታ ሣይገነቡ፤ መሠረተ ልማት ላጣው ሕዝብ በላቡ የገነባውን መንገድና መሠረተ ልማቶች ሣይቀር በማፈራረስ በደህናው ጊዜ ዞር ብለው ያላዩትን የትግራይን ሕዝብ “ወገኔ” በሚል የአዞ እንባ እያነቡ አልገዛልህም ያለውን በጭካኔ እየገደሉ ትላንትና ረግጠው የገዙትን ሕዝብ ዛሬም “ካለእኔ ላንተ አዛኝ የለህም” በሚል ሞራለ ቢስነት የባንዳነት ሥራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የሆነው ሆኖ ተጎጂው ምስኪኑና ደሀው የትግራይ ገበሬና ነዋሪው እንጂ የነሱ ልጆችማ በተንደላቀቀ ቪላና በአውሮፓ ሀገራት እየኖሩና እየተማሩ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ለዚያውም ከሕዝብ በተዘረፈ ረብጣ ገንዘብ፡፡
ለፖለቲካ ጥቅማቸው ሲሉ የትግራይን ሕዝብ ጋሻ አድርገው በየዓለም አደባባዮች እና ሚዲያዎች የተሰለፉት ሽብርተኞች መቼውንም ቢሆን ለትግራይ ሕዝብ የሚሆን ሐዘኔታና የትግራይን ሕዝብ የሚያሻግር ራዕይ የላቸውምና ራሳቸው አጥፍተውና ራሳቸው ገድለው “የትግራይ ሕዝብ ሆይ እንዲህ ሆንክ ተበደልክ” እያሉ መጮሀቸው፤ ኢትዮጵያ እንድትበታተን እና እንድትጠፋ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያመላክት ነው፡፡
የትግራይ ሕዝብ ምን ትላለህ? ማነው በክፉ ቀን የደረሰልህ? አንተም በክፉ ቀን ልጅህን የገበርክለት ወገንህ? እነዚህ ጥቂቶች ወይንስ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች?
ዛሬም ያልተኙት ርዝራዦችና ባንዳዎች ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ በተለያዩ ጊዚያትና ቀናት በተለያዩ ክልሎች ዘርን መሠረት ባደረገ ጥቃታቸው በርካቶች ሞቱ፤ በርካቶች ቆሰሉ፤ በርካቶች ተራቡ፤ በርካቶች ተጎሣቆሉ ተፈናቀሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ትዕይንት እስኪመስለን ድረስ በሚፈጥሯቸው ቡድኖችና ከሕዝብ በዘረፉት ገንዘብ መመኪያና መጠጊያነት ሲከውኑት የሆነው ሲሆን አንተ የትግራይ ሕዝብ ያኔም ታውቅ ነበር፡፡ ዘር ተነጥሎ ሲመታ ሲቸገር መቼም ሕዝብ አመዛዛኝ በመሆኑ ለአፀፋ በቀል አንዳችሁም ላይ እጁን አላነሣም፡፡ ያ መሆኑን ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ጠንቅቃችሁ የምታውቁት ነው፡፡
መንግሥት በታላቅ ትዕግሥት ከኢትዮጵያ ሕግና ሥርዓት ተነጥላችሁ በግዳጅ ምርጫ እንድታካሂዱ ሲደረግ ምንም ዓይነት ችግር ሣይፈጥርባችሁ በጀታችሁን ጭምር ሣያቋርጥባችሁ መኖሩን የምታውቁት ነው፡፡ ሆኖም አሸባሪው ሕወሀት ይባስ ብሎ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ በፈፀመው ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት በተቀሰቀሰው ውጊያ በማይካድራ የሚኖረው ሌላው ብሄር ዘር ተኮር ጥቃት ሲፈፀምበት ስብዕናችሁ ስለማይፈቅድ በቻላችሁት አቅም ሕይወቱን ለመታደግ ስትፍጨረጨሩ ጥቃት እንደተፈፀመባችሁ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል። እፍረተ ቢሶቹ ወያኔዎች በሚያደርጉት ትንኮሣ ሣቢያ በነበረው የተኩስ ልውውጥ የተጎዳኸው አንተው ነህና ቁስሉን ታውቀዋለህ፡፡ ምክንያቱም ከቀየህ ተሰደሀል፤ መንገላታትና ረሀብ ደርሶብሀልና፡፡
ታዲያ እስከ መቼ ይቀጥል? እስከመቼስ ነው የትግራይ ወጣት ተምሮ ለትውልድ በሚሻገር የሥራ ፈጠራና የልማት ሥራ ላይ እንዳይሣተፍ የሚደረገው? እስከ መቼስ ነው መጦር የሚገባቸው አዛውንቶች መሣሪያ ተሸክመው እንዲዋጉ የሚገደዱት? “ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው” እየተባለ እንደ ጀብዱ የሚፎከርብህ እስከ መቼስ ነው? ጡት ያልጠገቡ ሕጻናቶችህ በጦርነት ምክንያት የሥነ-ልቦና ቀውስ እንዲደርስባቸው የሚደረገው? ያልወለዷቸወን ሕጻናት በማስገደድ መሣሪያ አስታጥቆ ማዝመቱስ እስከ መቼ? ሠከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ልዩነት እንኳን ቢኖር አዳዲስ አስተሳሰቦችን ተቀብሎ ለጋራ ተጠቃሚነት የጋራ መግባባትን ፈጥሮ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ዕድገት ጉዞ የጀመረችውን ኢትዮጵያን ወደ በለፀገች ሀገር መለወጥ ሲቻል በወንድማማች ሕዝብ መካከል በእጅ አዙር ቀኝ ገዢዎች ምክንያት በተሴረ የሴራ ፖለቲካ ምክንያት ግጭት መፈጠሩ ለየትኛው ሕዝብ ምንም ሊጠቅም እንደማይችል ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
እኛ የምናውቀው የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ወገኑን ሲደግፍ ነው፡፡ ትግራይን ለበርካታ ዓመታት በጦርነት አድቅቆ ዛሬም ድረስ “ያንተው ነን” እያለ የዋሸህ ጥቂት ቡድን ዛሬም ከሀገራችሁ ሕዝብ ጋር ከፋፍሎና ነጥሎ ሊያስቀራችሁ እየተጋ መሆኑን ተገንዝባችሁ ወደ ሠላማዊ የኢትዮጵያዊነት ኑሯችሁ መቀላቀል ይኖርባችኋል፡፡ የትግራይ እናቶች ለቅሶና ሐዘን ማብቃት ይኖርበታል። ሽማግሌዎች መጦር መደገፍ፣ ሕጻናት በእናት ሀገር ፍቅር እየታነጹ መማር በእንክብካቤ ማደግ ይፈልጋሉ፡፡ መሠረተ ልማቶች መሟላት ይኖርባቸዋል፤ ወላድ እናቶች በእንክብካቤ ማጣት ምክንያት መሞት የለባቸውም፡፡ የጦርነት ትርፉ ኪሣራ ነው፡፡ መገንባት ከባድ፣ መናድ ግን ቀላል መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። በጋራ የምትገነባ እንጂ በተናጥል የምትፈርስ ሀገር የለችንም። በተነጣጠልን ቁጥር መፍረስ ትርፋችን ይሆናል፡፡ አብረን በሆንን ቁጥር ደግሞ ሀገር የምትባል መተኪያ የሌላት መኖሪያችንን ከብረት በጠነከረ ክንድ እንሠራታለን፡፡
ከአንፏቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም