የማዕድን ዘርፍ በተለያዩ አደጋዎች የተከበበ ነው። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማዕድን ቁፋሮ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች ለተለያዩ አደጋ ተጋለጡ የሚል ዘገባ መስማት የተለመደ ነው። በማዕድን ቁፋሮ ዘርፍ ሌላኛው ከባድ ችግር በዘርፉ የተሰማሩ ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች በየዓመቱ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ነው። ባህላዊ የማእድን ቁፋሮ አደጋዎች የተከበበ ከመሆኑም ባሻገር ዘመናዊ የማእድን ቁፋሮም የተለያዩ ተግዳሮቶች እያስተናገደ ይገኛል።
አርቱፊሻል ኢንተለጀንስን እና መሽን ለርንኒግን በመጠቀም ግን የዘርፉን ችግሮችን መፍታት እየተቻለ ነው። የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን በመዘርጋት የሥራ ከባቢ ሁኔታዎች ግምገማን፣ የማሽኖች አቋም ፍተሻ እና የጥገና ትንበያ በመከወን ሰዎችን ከጉዳት፤ ዘርፉንም ከኪሳራ መታደግ እየተቻለ መሆኑን ወርልድ ካውንትስ ድረገጽ ሰሞኑን አስነብቧል።
ማዕድን በመፈለግ ሂደት በአንድ የማሽን ቁፋሮ 200 ሜ.ባ የሚደርስ ዳታ እንደሚገኝ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ቁፋሮው ብዛት ሲኖረው የጊጋ ባይት መጠን ያላቸው ዳታዎች መኖራቸው እሙን ነው። ይህን ግዙፍ ዳታ በሰው አቅም መተንተን እና የተሻለውን ቁፋሮ መምረጥ እጅግ አዳጋች መሆኑን የአናሊቲክ ኢንሳይት ዘገባ ያመላክታል።
ሆኖም ማሽን ለርኒግን በመጠቀም እና በመተንተን ይህን ግዙፍ ዳታ በቀላሉ አገልግሎት ላይ እንዲውል ማድረግ አንዱ አማራጭ ነው። የተሻለ ውጤትም ተገኝቶበታል። የማዕድን ዘርፍን ለመለወጥና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመሻገር የተለያዩ ኩባንያዎች የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ባለቤትነቱ የብሪታንያ እና የአውስትራሊያ የሆነው ሪዮ ቲንቶ የተሰኘው የማዕድን ቁፋሮ ኩባንያ ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ብሎም የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ ሲሰራ የቆየ ነው። እ.አ.አ ከ2008 ጀምሮ ራስ ገዝ የሆነ ማዕድን አጓጓዥ የጭነት መኪና መጠቀም መጀመሩን የአናሊቲክ ኢንሳይት ዘገባ አመላክቷል።
ሪዮ ትንቶ በዚህ ብቻ አላበቃም ሪዮ ቲንቶ እና ሌሎች የማዕድን ኩባንያዎች በማዕድን ቁፋሮ ዘርፍ አራተኛውን የኢንዳስትሪ አብዮት (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ዝግጅት ላይ ናቸው። የሪዮ ቲንቶ ሥራዎች 16 ማዕድናት ቁፋሮዎችን፣ አንድ ሺህ 500 ኪሎ ሜትር የባቡር ሀዲድ፣ ሶስት ወደቦችን እና ሌሎችን ያካተተ ሲሆን መሳሪያዎቻቸውን ለመቆጣጠር እንዲረዳ በእውነተኛ ጊዜ መረጃን ከሚሰበስቡ እና ከሚያስተላልፉ ተንቀሳቃሽ መሳሪያዎች እና ዳሳሾች ሁሉ በየደቂቃው 2 ነጥብ 4 ቴራባይት መረጃዎችን ይሰበስባል።
የሪዮ ቲንቶ የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳም ዎልሽ በጋርትነር ዳታ እና አናሌቲክስ ጉባኤ ላይ ሲናገሩ ኩባንያው እነዚህን በርካታ ማዕድናት በአካላዊ ሥፍራ በማይገኙ ኦፕሬተሮች ቁጥጥር በሚደረግ የተቀናጀ ማቀነባበሪያ እና ሎጂስቲክስ ሥርዓት ውስጥ እንዴት በተሳካ ሁኔታ እንዳዋሃደ አስረድተዋል።
እንደ አናሊቲክ ኢንሳይት ዘገባ፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የማሽን መማር የማዕድን ኩባንያዎች የማዕድን ቁፋሮዎችን ለማንኛውም የማዕድን ማውጣት እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ ለሚሰሩ ለማንኛውም የማዕድን አሠራር ሊረዳ ይችላል። ምንም እንኳን ይህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የማሽን ቴክኖሎጂ በጣም አዲስ ቢሆንም የማሽን ትምህርት መተግበሪያ፣ በርካታ የማዕድን ኩባንያዎች በተስፋው ተደስተዋል። ጎልድ እስፖት ዲስኮቨሪስ ኢንኪ የተሰኘው የካናውን የማዕድን ቁፋሮ ኩባንያ ማሽን ትምህርትን በመጠቀም የወርቅ ፍለጋን ሳይንሳዊ የማድረግ ዓላማ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በተመሳሳይ ጎልድኮርኮር እና አይቢኤም ዋትሰን በካናዳ ውስጥ ለወርቅ የተሻሉ የቁፋሮ ቦታዎችን ለማግኘት የሚገኘውን ሁሉንም የጂኦሎጂ መረጃ ለመመርመር ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለመጠቀም ጥረት እያደረገ ነው። እነዚህ ጥረቶች የማሽን ትምህርትን በመጠቀም የማዕድን ማውጫ ቦታዎችን ማግኘት ሲጀምሩ የማዕድን ኢንዱስትሪውን የበለጠ ትርፋማ ለማድረግ ይረዳል።
ራስ-ገዝ ማሽኖቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚኖርባቸው አከራካሪ ባይሆንም፤ የጭነት ማሽኖቹ በዝግታ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ስለ እግረኞች ደህንነት አያስጨንቅም። ይህም ሌላኛው ጉልህ ስኬት ነው። በዚህ ዓመት የኩባንያው ረዥም የራስ-ገዝ የባቡር ስርዓት ኦንላይን የሚሄድ ሲሆን የወደፊቱን የማዕድን ዘርፍ ለማልማት ቀጣዩ እርምጃ ነው ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ከ244 መኪኖች ጋር የራስ ገዝ ባቡሩ ለአምስት ዓመታት ያህል በልማት ላይ የነበረ ሲሆን፣ አንዳንድ ሶፍትዌሮች እና የግንኙነት ችግሮች ሙሉ በሙሉ ከተፈታ በኋላ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ይጀምራል።
በተጨማሪም ሪዮ ቲንቶ ራስ ገዝ ጫኞቹን እና የቁፋሮ ስርዓቶችን ለበርካታ ዓመታት ተጠቅሟል። እንደ ሌሎች የራስ ገዝ መተግበሪያዎች በተለያዩ ዘርፎች ለምርታማነት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል። የሪዮ ቲንቶ ፈጠራም በ10 በመቶ ምርታማነትን እንዳሻሻለ ማረጋገጥ መቻሉንም ነው ዘገባው የጠቆመው።
በአብዛኞቹ የማዕድን ሥራዎች ውስጥ የማዕድን ቁፋሮ የሚሠሩባቸውን ጠቃሚ ቁሳቁሶች ለማግኘት እጅግ በጣም ብዙ አላስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማስወገድን ይጠይቃል። ማዕድኖችን ለመድረስ በርካታ የማይጠቅሙ ዓለቶችን እና ቆሻሻዎችን መለየት ከባድ እና አድካሚ ሥራ ነው። ከዚህ ቀደም በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉትም እነዚህን አላስፈላጊ ቁሳቁሶችን እና ዓለቶችን በማስወገድ ስራ ላይ ነው።
አንዳንድ ኩባንያዎች አንድ ኩባንያ በፈለገው መስፈርት ላይ በመመርኮዝ ማዕድናትን ለመለየት የሚያስችላቸውን ዘመናዊ የማጣሪያ ማሽኖች መጠቀም ጀምረዋል። ይህ ሥራ ነዳጅ እና ኢነርጂ ለመቆጠብ ያስችላል። ይህም በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም ሲያወጡ የነበረውን አላስፈላጊ ወጪ የሚቀንስ ነው።
ማዕድኖች እስከ ወደብ የማቅረብ ስራ ስኬታማ ለማድረግ ሪዮ ቲንቶ በተያዘው የፈረንጆች በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ማዕድን እስከ ወደብ ማድረስ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ ነው። ኩባንያው እየገመገመ ያለው ከ100 በላይ ፈጠራዎች ያሉ ሲሆን፤ ዲጂታል ቲዊንግ ተብሎ የሚጠራ አንድ ተነሳሽነት (ኢንሼቲቪ)፣ በመጀመሪያ በናሳ የተፈጠረው የተለያዩ ነገሮችን ማጓጓዣ ቴክኖሎጂ አሁን በማዕድን ዘርፍም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።
ይህ ቴክኖሎጂ ከቦታው በእውነተኛ ጊዜ መረጃ የሚመግብ ቨርቹዋል ሞዴልን በመፍጠር ሁኔታዎች በፍጥነት መገምገም የሚችሉ ሲሆኑ፤ ኦፕሬሽኖች እና ምርቶች ማሳደግ የሚያስችል ነው ። ይህን ውሳኔዎች በቅጅ ስርዓት ውስጥ ከመተግበሩ በፊት የመፈተሽ ችሎታ ወደ ተሻለ ውጤት የሚያሳድግ ነው።
ለበይነመረብ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና የማዕድን ማውጫ መሳሪያዎች ብልሽቶች ከመከሰታቸው በፊት ክትትል እና እድሳት እንዲደረግላቸው ማድረግ እየተቻለ ነው። የመከላከያ ጥገናን ወደ ትንበያ ጥገና የሚቀይር እርምጃ ለመውሰድ በማሽኖች ላይ የሙቀት መጠንን፣ ፍጥነትንና ንዝረትን መከታተል የሚቻልበት ዘመን ላይ እንገኛለን። በእውነተኛ ጊዜ መረጃዎችን እና ትንታኔዎችን በመገምገም የማዕድን ሥራዎች ለተሳተፉ ሁሉ ደህና ሊሆኑ ይችላሉ ።
የዚህ አዲስ ቴክኖሎጂ እየተለመደ መምጣት የማዕድን ሠራተኞቹን እንደገና ማሰልጠንን ይጠይቃል፤ እናም ሪዮ ቲንቶ ክፍተቱን ለመሙላት ከአውስትራሊያ መንግሥት እና ከሙያ ሥልጠና አቅራቢ ጋር በመተባበር እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ። በጥቅሉ ነባር እና አዳዲስ ሰራተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በሮቦቲክስ ሥራዎችን ለማስተናገድ በጋራ ሁለት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያወጣሉ።
እንደ አናሊቲክ ኢንሳይት ዘገባ፤ ውጤታማነትን እና ምርታማነትን ማሻሻል ለትርፍ ወሳኝ በሆነው በማዕድን ማውጫ ውስጥ ባሉ ምርቶች ውስጥ አነስተኛ የምርት፣ የፍጥነት እና ቅልጥፍና መሻሻል በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ውጤት የማስመዝገብ አቅም አለው። የማዕድን ኩባንያዎች እርስ በእርሳቸው የተቆራኙ ምርቶችን የሚያመርቱ ከመሆናቸውም ባሻገር ከሌሎች ዘርፎች ጋርም የተቆራኙ እንደመሆናቸው በዘርፉ የሚመዘገበው ስኬት የሚያስገኘው ፋይዳም ዘርፍ ዘለል ነው።
የማዕድን ዘርፍ ጥሬ ዕቃዎችን ለሁሉም ኢኮኖሚው በሁሉም በኩል ስለሚያቀርብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በማዕድን ዘርፍ ውስጥ የሚከሰቱ በጎም ሆነ መጥፎ ነገር በሁሉም ኢንዱስትሪዎች ላይ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም አለው። የማዕድን ዘርፍ መሻሻል ሌሎች ዘርፎችን ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። የማዕድን ዘርፍ አለመለወጥ በተመሳሳይ ሌሎች ዘርፎችን በአሉታዊ መንገድ ተፅዕኖ ያሳድራል። በመሆኑም በማእድን ዘርፍ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተመዘገበ ያለው ስኬት ፋይዳው የትየለሌ ነው።
የኢትዮጵያ መልካዓ ምድር የማዕድን ፍለጋና ቁፋሮ እጅግ አስቸጋሪ ካደረጉት ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑ አያጠራጥርም። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘትና መጠቀም ያለባትን ያህል ተጠቃሚ ሆናለች ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት ሰው ሰራሽ አስተውሎት በማዕድን ፍለጋ፣ ቁፋሮ እና ማጓጓዝ ስራዎችን ለማከናወን ሰው ሰራሽ አስተውሎት በስራ ላይ እንዲውል በማድረግ የማዕድን ውጤቶች ለኢትዮጵያም የማዕድን ዘርፍም ሆነ ለሁለንተናዊ ለውጥ እንዲውሉ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ደግሞ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ከፈጠራ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ብዙ ሊሰራ ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013