ወይዘሮ ሣራ ዘመኑ ሠናይ በጋዜጣችን ለወላጆች ምክር የሚያካፍሉ እናት ናቸው። የህክምና ባለሞያ ሲሆኑ፤ ልጆቻቸውን አሣድገው ለቁምነገር አብቅተዋል። ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገር ሲሆን፤ ለወገኖቼ የተወሰነ ነገር ከልምዴ በማካፈል ብለው በማህበራዊ ድረ-ገፆች መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ። ለዛሬም ካካፈሉን ውስጥ አንዱን እነሆ ብለናል።
እኛ ወላጆች በቃላት አጠቃቀማችን ልጆቻችንን በራሣቸው የሚተማመኑ ማድረግ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ቃል ሃይል አለው፤ በተለይ በልጆች ላይ። ከልጆቻችን ጋር ባለን ግንኙነት በምንጠቀማቸው ቃላት ልጆቻችንን በጥሩ ምግባር መገንባትና ማነጽ እንችላለን። በመጥፎ ቃላቶች ደግሞ ልንጎዳቸው እንችላለን። ከዚህ መሠረታዊ ሐሳብ ተነስተን ልጆቻችንን እንዴት በቃሎቻችን ምርጫ ልናበረታታቸውና ልናንፃቸው እንደምንችል ከዚህ በታች በዕድሜ ከፋፍለን በአንዳንድ ምሣሌዎች እንመልከት።
ከ1 እስከ 5 ዓመት ዕድሜ ያሉትን ልጆቻችን አንድ ልናበረታታበት የምንችልበት መንገድ የሆነ ነገር ሲሰሩ በጥቅሉ ጎበዝ በማለት ፋንታ በዝርዝር በምን ምክንያት እንደተመሠገኑ በማሥረዳት ነው። ለምሣሌ በሚገጣጠሙ መጫዋቻዎች የሆነ ነገር የፈጠረን ልጅ በደፈናው ጎበዝ ብቻ ከማለት፣ አንተ እኮ አዲስ ሐሳብ ማመንጨት ትችላለህ፣ የፈጠራ ችሎታ አለህ፣ ብለን ብናስረዳው ይህንን ገንቢ ሐሳብ በውስጡ ቀረጽን ማለት ነው።
ከ4 እስከ 7 ዓመት ያሉትን ልጆቻችን ደግሞ ይህ ዕድሜያቸው እኩያ ጓደኛ የሚይዙበትና አብሮ የመጫወት ልምድ የሚያዳብሩበት የዕድሜ ከልል ነው። በዚህ ዕድሜ ላይ ያለች አንድ ልጃችንን ከጓደኛዋ ጋር የራስዋን መጫወቻ አጋርታ መጫወቷን ስንመለከት በጥቅሉ አንቺ ጎበዝ ነሽ፣መጫወቻሽን አጋርተሽ ትጫወቻለሽ በማለት ፋንታ አንቺ እኮ መጫወቻሽን ያጋራሽው ደግ ስለሆንሽ ነው፣ በዚህም በጣም ኮራሁብሽ ብለን ብንገልጽላት በውስጧ እኔ እኮ ደግ ነኝ የሚለው ገንቢ ሐሳብ ይቀረፃል ማለት ነው።
በሌላ ምሣሌ ደግሞ ጥሩ ምርጫ ስታደርግ ካየናት አንቺ ጥሩ ምርጫ በማድረግሽ በጣም አድንቄሻለሁ ብለን ብንነግራት እኔ ጥሩ ምርጫ ማድረግ እችላለሁ የሚለው ሐሳብ ይቀረፅባታል ማለት ነው።
ከ8 እስከ 14 ዓመት ያሉትን ልጆቻችን ደግሞ ይህ ዕድሜያቸው ሐሳባቸው ተሰሚነት እንዲያገኝ የሚፈልጉበት ዕድሜ ነው። በተለይ ደግሞ በወላጆቻቸው። ስለዚህ በዚህ ዕድሜ ላይ ያሉትን ልጆቻችንን ሐሳባቸውን እንዲያካፍሉን እያበረታታን እነሱን በደንብ ማዳመጥ ያስፈልጋል። ከዚያም ሐሳባቸው ጥሩ እንደሆነ መንገር፣ በሐሳባቸውም እኛም እንደምንስማማ መግለጽ ይገባናል።
የማንስማማበትንም ሐሳብ ካመጡ በመወያየትና ለጥያቄያዎቻቸው አጥጋቢ መልስ በመስጠት በሐሳብ እንድንስማማ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን ስናደርግ በውስጣቸው የብቁነት ሥሜት ይቀረፃል። ሲያድጉም ሐሳባቸውን ለመግለጽ አያፍሩም።
ከ15 ዓመት በላይ ያሉት ልጆቻችን ደግሞ ይህ ዕድሜያቸው እንደምንወዳቸው ማወቅ ይፈልጋሉ። ለዚህም ልጃችንን በደፈናው እወድሻለሁ ከማለት ለምሣሌ እኔ እኮ ልጄ ስለሆንሽ በጣም ደስተኛ ነኝ፣ በአንቺ እኮ በጣም ነው የምኮራው፣ ወዘተ…እያልን ፍቅራችንን ብንገልጽላት እኔ እኮ እወደዳለሁ የሚለው ሥሜት ይቀረጽፅባታል።
በአጠቃላይ ለልጆቻችን ምሉዕ ዕድገት የቃላት አጠቃቀማችንን በጥንቃቄ መምረጥ ያስፈልጋል። በልጅነት የሠራነው ሥራ ብቁ ትውልድ ሥናፈራ መልሶ ይከፍለናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013