ልጆች እንዴት ናችሁ? ፈተና ተጠናቆ የክረምት የእረፍት ጊዜ ተጀምሯል አይደል? በዚህ የእረፍት ጊዜ መፅሃፍትን ማንበብ የጠቅላላ እውቀት ባለቤት ከማድረጉም በላይ የቋንቋ ሀብታም፤ ሀሳባችሁን በደንብ መግለፅ የምትችሉ ልጆች ያደርጋችኋል። ከምታነቡት ነገር ውስጥም ሊተላለፍ የተፈለገውን መልዕክት በመረዳት ለቀሪ የሕይወት ጊዜያችሁ የሚጠቅም ነገር መሠነቅ ይኖርባችኋል። ለዛሬ የኢትዮዽያ ተረቶች በሚል ከተዘጋጀው መፅሃፍ ላይ በጋሼ ወርቁ ወልደማርያም የተፃፈውን በዚህ መልኩ አዘጋጅቼ አቅርቤያለሁ። ምልካም ንባብ።
አንድ ሰው አንዲት በጣም ቆንጆ ወፍ በመዳፉ ውስጥ ይዞ ጨምቆ ሊገድላት ሲል ከመሞቷ በፊት አንድ ወይም ሁለት ቃላት ትናገር ዘንድ እንዲፈቅድላት ጠየቀችው።
እንዲህም አለች “እባክህ አትግደለኝ። ሦስት ጠቃሚ ምክሮችን እሰጥሃለሁ። የመጀመሪያው ምክር፤ በእጅህ ያለውን ነገር አትልቀቅ። ሁለተኛው ምክር፤ ስለሆነው ነገር ሁሉ አትቆጭ።” ካለችው በኋላ ዝም አለች።
ሦስተኛውንም ምክር ትነግረው ዘንድ ሲጠይቃት “ሦስተኛው ምክር ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ በጣም ጠቃሚ ስለሆነ ካለቀከኝ አልነግርህም።” አለችው።
በዚህ ጊዜ ሰውየው ሦስተኛውን ምክር ለመስማት በጣም ጓጉቶ ስለነበረ ወፏን ሲለቃት ከአንድ ዛፍ ላይ በርራ ወጥታ “ምንድን ነበር ያልኩህ? ታስታውሣለህ?” ብላ ጠየቀችው። እርሱም “በእጅህ ያለውን ነገር አትልቀቅ ነው ያልሺኝ።” አላት።
“ሁለተኛውስ?”
“ስላለፈው ነገር ሁሉ አትቆጭ።”
“አዎ። ነገር ግን የነገርኩህን ነገር አልተቀበልክም። ባትለቀኝ ኖሮ ከሆዴ ውስጥ ለልጅ ልጆችህ የሚሆን ወርቅ ታገኝ ነበር። ይኸው ነው።” አለችው።
ሰውየው “ሦስተኛውስ ታዲያ?” አላት።
እሷም “ሦስተኛው የሁለተኛው ምክር ድጋሚ ነው። ስላጣኸው ነገር አትቆጭ። ይኸው ነው። ደህና ሁን። ምክሬንም ባለመቀበልህ በድህነት ትኖራለህ።” አለችው።
ልጆች ምክር ለልጆች ጠቃሚ ነገር ነው። የሰውን ምክር በአግባቡ ሠምታችሁ ወደ ሕይወታችሁ ቀይሩ እሺ። መልካም ዕረፍት።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013