ክሊኒካል ሣይኮሎጅስት መአዛ መንክር ካላቸው እውቀት ለወላጆች ያሉትን እያካፈሉን ይገኛሉ። ለዛሬም ካካፈሉን ሐሳብ ላይ ስለወላጅነት እንዲህ ብለዋል። ወላጅነት ማለት በወላጅ እና ልጅ መካከል ባለ ግንኙነት ውስጥ አንድ ልጅን የሆነ ግብ ላይ ለማድረስ የምንሰራው ያልተቋረጠ ሥራ ነው።
ወላጅነት የማያቆም የሕይወት ዘመን ኃላፊነት ነው። ወላጅነት ወላጆች ለልጆቻቸው ፍላጎታቸውን፣ አመለካከታቸውን፣ እሴቶቻቸውን፣ እምነታቸውንና ፍቅራቸውን የሚያካፍሉበት ትስስር ነው። ወላጅነት በልምድ የሚገኝ ብቻ ሣይሆን ከዘመኑ ጋር ራስን በእውቀት እና ከሌሎች ወላጆች ጋር ልምድ ልውውጥ በማድረግ ማዳበር ይፈልጋል። በተጨማሪም ወላጅነት ከፍተኛ ትዕግሥት እና ፅናትን ይጠይቃል።
ወላጆች ልጆቻቸውን የሚቀርፁበት መንገድ እና ለባህሪያቸው የሚሰጡት ምላሽ አሁን / በጊዜው በሚያሳዩት ባህሪም ሆነ ለወደፊት በሚኖራቸው ስብዕና ላይ ተፅዕኖ አለው። ወላጅነት በጣም ከባድ ኃላፊነት ነው። መልካም ወላጅነት የልጆችን አካላዊ፣ ባህሪያዊ፣ ስሜታዊ፣ መንፈሣዊ እና አዕምሯዊ ዕድገትን በተመጣጠነ ሁኔታ ትኩረት በመስጠት ራሳቸውን በአግባቡ የሚመሩ፣ ለሌሎች እንደራሳቸው የሚያስቡ እና በአገራቸው ዕድገት ላይ በጎ ተፅዕኖ የሚያሣርፉ ልጆችን ማብቃት ሲችሉ ነው።
ለዛሬ በሕይወታችን በጣም አስፈላጊ የሆነውን የስሜት ዕድገትን ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ማዳበር እንዲችሉ ወላጆች ማድረግ ስለሚገባቸው ድጋፍ እንመለከታለን። አንድ ሰው ስኬታማ ሕይወት ለመምራት ከሚያስፈልጉት ክህሎቶች አንዱ የጠንካራ ስሜት ባለቤት መሆን ነው። ታዲያ ልጆች የጠንካራ ስሜት ባለቤት እንዲሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው የቀለም ትምህርት ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉ ሁሉ ለልጆቻቸው ሥሜት ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።
የሥሜት ብስለት መገለጫዎች
• የራስን የውስጥ ሥሜት መረዳት
• ሥሜትን መቆጣጠር
• የሌሎችን ሥሜት መረዳት መቻል እና ከዚህም የተነሣ ጥሩ ማህበራዊ ግንኙነት መኖር።
ወላጆች የልጆችን ሥሜት መቅረፅ ስናስብ ተገቢ የሆኑትን እና ተገቢ ያልሆኑትን ሥሜቶች (ንዴት፣ ፍርሃት፣ ሐዘን፣ ቅናት፣ መጥላት፣ መቆጣት የመሳሰሉትን) መለየት።
ልጆች ተገቢ ያልሆነ ሥሜት ሲያሳዩ እንዴት እንርዳቸው?
1.የሚያሳዩትን ሥሜት አቅሎ አለማየት።
2.ልጅ ያልተገባ ሥሜት ሲያሳይ በመደራደር እና በማታለል አለማስተካከል።
3.ልጅ ሥሜቱን በማልቀስም ሆነ በሌላ መንገድ እንዳይገልፅ አለመከልከል።
ነገር ግን ልጆች ያልተገባ ሥሜት ሲያሳዩ ክስ ተቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሥሜቱን በምክንያታዊነት እንዲገልፅ ሠፋ ያለ ጊዜ ወስደው ሥሜቱን እንዲረዳ አማራጭ መንገዶችን ያስተምሩት። በመጨረሻም በልጆች የሥሜት ብቃት ዕድገት ላይ በልጅ እና ወላጅ መካከል ያለ ጥብቅ ግንኙነት ወሣኝ እና ሚናውም ከፍተኛ መሆኑን ተረድተው በጊዜ ይጠቀሙበት ይላሉ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013