ልጆች እንዴት ናችሁ ሠላም ነው? በበርካታ ትምህርት ቤቶች ፈተና እየተጠናቀቀ መሆኑን ሠምቻለሁ። በክረምት የእረፍት ጊዜ ምን ልትሰሩ አስባችኋል? እኔ መፅሀፍትን እንድታነቡ እመክራችኋለሁ። ለማንበብ ምቹ በሚሆን መልክ የተዘጋጀ ከመላው ሀገራችን የተውጣጡ ታሪኮች ከተሠነዱበት ውስጥ ለዛሬ በጋሸ እያሱ ኦሪጎ የተተረከውን እንዲህ አዘጋጅቻለሁ። መልካም ንባብ።
በአንድ ወንዝ ውስጥ ካለ ደሴት ላይ የምትኖር ጦጣ ነበረች።በደሴቱም ላይ አንድ በጣም ጣፋጭ ፍሬዎችን የሚያፈራ ዛፍ ስለነበረ ጦጣዋ ፍሬዎቹን እየተመገበች በደስታ ትኖር ነበር።ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን በወንዙ ውስጥ ይኖር የነበረ አዞ ጦጣዋ አንድ ፍሬ እንድትወረውርለት ጠየቃት።ጦጣዋም ፍሬውን ወርውራለት ከበላው በኋላ ፍሬው ጣፋጭ እንደሆነ ነገራት።“ሌላ ፍሬ ድገሚኝ” ሲላት ጦጣዋ አሁንም አንድ ፍሬ ወርውራለት ሁለተኛውን ፍሬ ለሚስቱ ይዞላት ሄደ።
የአዞውም ሚስት “ይህንን ከየት አገኘህ?” ብላ ስትጠይቀው “አንዲት ጦጣ ሰጥታኝ አንዱን ከበላሁት
በኋላ ይኸኛውን ለአንቺ ይዤልሽ መጣሁ።” አላት።
እርሷም “ጦጣውን ማየት ስለምፈልግ በል አብረን እንሂድ።” ብላው ባልና ሚስቱ አዞዎች ተያይዘው ወደ ጦጣዋ ዘንድ ሄደው “እባክሽ ሁለት ፍሬዎች ስጭን።” አሏት።ጦጣዋም እሺ ብላ ፍሬዎቹን ከወረወረችላቸው በኋላ የአዞው ሚስት “አንቺስ ለምን ወደ እኛ ቤት አትመጭም? ጥሩ ምሣም እንጋብዝሻለን።” አለቻት።
ጦጣዋም “አይ እኔ ዛፍ ላይ መውጣት፣ መውረድ እንጂ ወንዝ ውስጥ መግባት አልችልም።” አለቻት።
አዞዋም “ችግር የለም።እኛ ተሸክመን እንወስድሻለንና ምንም አትሆኝም።” ብላት ጦጣዋን ተሸክመው ወደ ቤታቸው ይዘዋት ሄዱ።
ሦስቱም ተቀምጠው ሣለ ባልና ሚስቱ በለሆሳስ መነጋገር ጀመሩ።ከዚያም ባልየው “አሁን ምሣ እንበላለን።” ብሎ ሲናገር ጦጣዋም “እሺ እኔም ከእናንተ ጋር ምሣ እበላለሁ።” አለች።
ከዚያም አዞው “መጀመሪያ ምሣ አብረሽን ትበያለሽ። ከዚያም እራት አንቺን እንበላሻለን።” አላት።
በዚህ ጊዜ ጦጣዋ በድንጋጤ “ለምንድነው የምትበሉኝ? ያጠፋሁት ነገር አለ? እንዲያውም ፍሬዎች ነው የሰጠኋችሁ።” ስትላቸው ባልየውም “አንቺን የምንበላሽ ልብሽ የእውቀት ምንጭ ስለሆነ ነው።እንዳንቺ ብልህ መሆን ስለምንፈልግ ልብሽን ብቻ በልተን የቀረውን አካልሽን እንጥለዋለን፤ ምክንያቱም ወንዙ ውስጥ በቂ ሥጋ አለ።” አላት።
ጦጣዋም “እንግዲያው ይሁና! እውቀትን ከፈለጋችሁ በሐሳባችሁ እስማማለሁ።ነገር ግን አሁን ልቤን አልያዝኩትም።ዛፉ ላይ ነውና የማስቀምጠው አብረን እንሂድና ልስጣችሁ።” አለቻቸው።
እነርሱም “እዚያ ስለማስቀመጥሽ ርግጠኛ ነሽ?” ሲሏት “አዎ! እርግጠኛ ነኝ።” አለቻቸው።
እናም ተያይዘው ወደ ደሴቷ ሲሄዱ ጦጣዋ ዘላ ዛፉ ላይ ከወጣች በኋላ ትስቅባቸው ጀመር።
ቀጥሎም “ጦጣ ያለ ልብ መኖር ትችላለች ብላችሁ የምታስቡ ምንኛ ጅሎች ናችሁ! ልቤ ከእኔ ተለይቶ እንዴት ዛፍ ላይ ሊሆን ይችላል? በሉ አሁን ኑ፣ ዛፉ ላይ ውጡና ልቤን ውሰዱት።” እያለች መሣቋን ቀጠለች።
ልጆች ምንም ዓይነት ችግር ቢገጥማችሁ በብልሃት ማለፍን ከዚህ ተረት እንማራለን። ብልሆች ሁኑ እሺ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013