በቀድሞ መጠሪያው በጌምድርና ሠሜን ጠቅላይ ግዛት ጎንደር ከተማ ልዩ ሥሙ ፊት ሚካኤል በተባለ ሠፈር መስከረም 12 ቀን 1954 ዓ.ም ተወለደች። በኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት አጭር ልብ ወለድ ደራሲ የዝና ወርቁ። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን በሥራ አስኪያጅነት እያገለገለች ትገኛለች።
ልጅነትና ሥነ ጽሁፍ
የዝና የሥነ ጽሁፍ ፍቅር ያደረባት ገና በልጅነቷ እንደሆነ ትናገራለች። ለዚህ ካበቋት የተለያዩ ምክንያቶች መካከል የመጀመሪያው የእናቷ ተረት አዋቂነት እንደነበረም ታስታውሳለች። “በጊዜ የሚተኛ ፍቅር የሌለበት ቤተሠብ ነው” ይሏት የነበሩት እናቷ ማታ ማታ ለእርሷና ለታናሿ ተረት ያወሩላቸው ነበር። በዘመኑ ለንባብ ይሰጥ የነበረውም ክብር ለሥነ ጽሁፍ ፍቅሯ ሥር መስደድ አንዱ ምክንያት ነበር።
እንደነ ፍቅር እስከ መቃብርና አርአያን የመሳሰሉ መጽሐፍትን ያነበበቻቸው ገና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ነበር። ከዚህም ሌላ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለች የሁለት ዓመት ታላቋ የነበረችው ፈለግ ወርቁ የመጀመሪያውን ድርሰቷን እንድትጽፍ ምክንያት እንደሆነቻት ታስታውሳለች።
የትምህርት ዘግጅት
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን፣ በመቀጠልም በአልፋ ዩኒቨርሲቲ በአስተዳደር የትምህርት መስክ በድጋሚ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ወስዳለች። ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንደገና ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሳ በኢትዮጵያ ፎክሎርና ሥነ ጽሁፍ በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቃለች። በአገር ውስጥና በእንግሊዝ አገርም አጫጭር ሥልጠናዎችን ለመውሰድ በቅታለች።
በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ከጀማሪ እስከ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነት እስከ ሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊነት ድረስ አገልግላለች። “…መንግሥት በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ብሄራዊ መግባባት ለማስፈን የሚቻለው የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች በገዢው ፓርቲ አባላት ሲመሩ ነው” የሚል መመሪያ በማውጣቱ ‹‹ሥነ ጽሁፍን በነጻ አዕምሮ ለመሥራት የፓርቲ አባል አለመሆን ይመረጣል›› በሚለው አቋሟ ፀንታ፣ በቡድን አስባባሪነት በገቢ ጉዳዮች ዙሪያ የሚዘጋጁ የኅትመት ሥራዎችንና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ውጤቶችን በማስተባበር አገልግላለች።
በዚህ ጊዜ ውስጥም፣ በግብርና ቀረጥ ዙሪያ በሚዘጋጀው “ገቢ ለልማት” መጽሔት በዋና አዘጋጅነት፣ በ“ሕይወት ወግ” የሴቶች መጽሔት ዋና አዘጋጅነት፣ በሥጋ ደዌ ላይ የሚያተኩር በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚሰናዳው “እውነታ” (the truth) የተሰኘ መጽሔት ዋና አዘጋጅነት እንዲሁም “በገቢ ለልማት” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት ሠርታለች።
ከመደበኛ ሥራዋና ከድርሰት ተግባሯ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢነት፣ በዜማ ብእር ኢትዮጵያ የሴቶች ሥነ ጽሁፍ ማህበር በፕሬዚዳንትነት እንዲሁም በልማት ማህበሮች ሰብሳቢነት ማህበረሰቡን አገልግላለች።
የመጀመሪያዎቹ አጫጭር ልብ ወለዶቿ የታተሙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያለች ባለቤቷ ከነበረው ከጀማል ሱለይማን ጋር በ1978 ዓ.ም በጋራ ባሳተሙት “የተሸጠው ሴጣንና ሌሎች አጫጭር ልብ ወለዶች” በተባለው መድብል ነው። በዚህ መጽሐፍ የታተሙ አጫጭር ልብ ወለድ ድርሰቶቿ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ልብ ወለድ ድርሰት ፈር ቀዳጅ ከሆኑት ጋር ያስተሳሰሯት ሲሆን፤ በሴቶች የሥነ ጽሁፍ ታሪክ የመጀመሪያዋ ዘመናዊ የአጭር ልብ ወለድ ደራሲ አድርጓታል።
ሌሎች የአጫጭር ልብ ወለዶቿ ስብስብ ለሁለተኛ ጊዜ ከጀማል ጋር፣ “ያልተመቻት ችግኝ” በተባለ መድብል ውስጥ ተካትተው በ1982 ዓ.ም የታተሙት ናቸው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተካተቱት ሥራዎቿ “የመመረቂያው ልብስ” የሚለው ድርሰቷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ክፍል ተመርጦ በጀርመን ኤምባሲ የባህል ዘርፍ ወጪ በእንግሊዝኛ እንዲተረጎም ተደርጓል።
ሌሎች በወድድር የተመረጡ አጫጭር ልብ ወለዶቿና እውነተኛ ትረካዎቿ ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ባሣተማቸው “ክንፋም ሕልሞች”፣ “አዙሪት” እና “ዛሬን ከተጉበት ነገን ያነጉበት” በሚል መድብል ውስጥ ሌሎች ደራሲያን ሥራዎች ጋር ታትመውላታል። እንዲሁም በዜማ ብዕር ቁጥር 1፣ የአጫጭር ልብ ወለዶች መድብል እና በዜማ ብዕር ቁጥር 2፣ የግጥሞች መድብል ውስጥ ሥራዎቿ ተካትተው ታትመዋል።
የዝና፣ በ“የተሸጠው ሰይጣን” መድብል ውስጥ “ሠናይት”፣ በ“ያልተመቻት ችግኝ” መድብል ውስጥ “የቅርብ ሩቅ” በተሰኙ መካከለኛ ልብ ወለድ ሥራዎቿ፣ ረጅም ልብ ወለድ የመጻፍ ችሎታ እንዳላት ፍንጭ ካሳየች በኋላ በ2002 ዓ.ም “የደራሲዋ ፋይል” የተሰኘ ረጅም ልብ ወለድ መጽሐፏን ለንባብ አበቃች።
የየዝና ብዕር የማህበረሰቡን ገበና በማሳየትና በመሄስ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ሕጻናትንም በመልካም ሥነ ምግባር ኮትኩቶ ለማሳደግና አዕምሯቸውን በዕውቀት ለማነጽ የተጋ ነው። የአፍንጮ በር ወፎች፣ ይቅርታ፣ ሰሮን ደንሼ ሳሮን …የተሰኙ ሥራዎቿም ይህንኑ ያረጋግጣል።
የዝና በማህበረሰቡ አንገብጋቢ ጉዳዮችና በሕይወት ጉዞ ሥኬት ላይ ያነጣጠሩ መካሪና አስተማሪ የሆኑ ለትውልድ ቢተላለፉ ይጠቅማሉ ያለቻቸውን፣ አቅመ ቢስ አሸባሪ፣ ዘመን ተሸጋሪ፣ የኢትዮጵያ የግብር ታሪክ…የተሰኙ ሥራዎችን አበርክታለች። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን በሥራ አስኪያጅነት እያገለገለች ትገኛለች። በባላገሩ ቴሌቪዥን በዜና አንባቢነትም ትሠራለች።
የእረፍት ቀናት ውሎ
በባህሪዋ ማህበራዊ ሕይወትን አጥብቃ እንደምትወድ የምትናገረው ደራሲዋ፤ ከሰው ጋር ባላት ማህበራዊ ግንኙነት መልካም ነገሮች አዕምሮዋ ውስጥ እንደሚገዝፉ ትጠቅሳለች። በዚህም ደስተኛና ተጠቃሚ ናት። ልክ እንደ ማህበራዊ ግንኙነቱ የእረፍት ጊዜዋን ከልጅ ልጆቿ ጋር እንደምታሳልፍና ለሕጻናት ልዩ ፍቅር እንዳላትም ትገልጻለች።
የዝና በምሽትና በትራንስፖርት ጉዞ ወቅትም እረፍቷን ለንባብና ለሥነ ጽሁፍ ሥራዎቿ ትጠቀምበታለች። በተለይም የጀማሪ ደራሲያንን ረቂቅ ማንበብና አስተያየት ለመስጠትም ይህን ጊዜ እንደምትጠቀምበት ነው የምትናገረው። በማህበራዊ ሚዲያ ከጓደኞቿ ጋር መረጃ መለዋወጥና ሥሜቶችን መጋራትም የእረፍት ውሎዋ አንዱ አካል ነው።
የሥነ ጽሁፍ ሥራዎቿን እንደ ግጥም፣ አጫጭር ልብ ወለዶች የመሳሰሉትን የምታከናውነውም ከመደበኛ ሥራዋ ውጭ ባለው የእረፍት ጊዜዋ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ችግኝ መትከልና እንክብካቤ ማድረግን ታዘወትራለች።
አንዳንድ ጊዜ ከአዲስ አበባ ከተማ የመውጣት ዕድሉን ስታገኝ በተለይ የዘመድ አዝማድና ጎረቤት ሕጻናት የተሰጥኦ ማሣያ ሁነቶችን በማዘጋጀት ሕጻናት በለጋ ዕድሜያቸው ተሰጥኦዋቸውን እንዲያዳብሩ የማድረግ ልምድ አላት። ይህ ሥራዋ ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ ብቻ ተወስኖ የቀረ ሣይሆን በመኖሪያ ሠፈሯም በተለይ የማይተዋወቁ ሕጻናት በመሰል ሁነቶች እንዲተዋወቁና የማንበብ ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ በማድረግ አካባቢያቸውንና አገራቸውን እንዲወዱ እንዲሁም በጎ እሴቶቻቸው ላይ ያላቸውን ተሞክሮ እንዲለዋወጡ በእረፍት ጊዜዋ ታግዛቸዋለች።
መልዕክት
ደራሲ የዝና፤ “ሰዎችን የበለጠ ማወቅ የሚቻለው አብሮ በመኖር ነው። አብሮ በመኖር ጉድለትን ብቻ ሣይሆን የጉድለቱንም ምክንያቶች ማወቅ ይቻላል። ውጤታማ ሥራ መሥራት የሚቻለውም የችግሮችን መንስዔ ማወቅ ሲቻል ነው። በተለይ ደራሲያን ማህበረሰቡን ቀርበው ማወቅ ይኖርባቸዋል። ሲጻፍም ጥበብ አገርንና ህብረተሰብን ልትገነባ በምትችል መልኩ መሆን አለበት። በተለይ አሁን ባለንበት አገራዊ ሁኔታ አንጻር ብዙ ነገራችን ወድሟል፣ ጠፍቷል ባንልም አደጋ ላይ ነው ያለው። እዚህ ላይ በትኩረት በመሥራት በጎ እሰቶቻችንን ማጠናከር ይገባል።” ስትል ትመክራለች።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013